Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየተሽከርካሪ አደጋ ተጎጂ የአስቸኳይ ሕክምና አተገባበር በታዳጊ ክልሎች ክፍተት እንዳጋጠመው ተጠቆመ

የተሽከርካሪ አደጋ ተጎጂ የአስቸኳይ ሕክምና አተገባበር በታዳጊ ክልሎች ክፍተት እንዳጋጠመው ተጠቆመ

ቀን:

በታዳጊ ክልሎች የሦስተኛ ወገን መድን አዋጅን ተከትሎ የወጣው የተሽከርካሪ አደጋ ተጎጂ የአስቸኳይ ሕክምና አገልግሎት አፈጻጸም መመሪያን በመተግበር ረገድ ክፍተቶች መታየታቸውን የመድን ፈንድ አስተዳደር ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

በጋምቤላ፣ በአፋር፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች ከታዩት ክፍተቶች መካከል፣ በተሽከርካሪ ጉዳት ለደረሰባቸው ተጎጂዎች የአስቸኳይ ሕክምና አገልግሎት ለሰጡ የጤና ተቋማት ክፍያ አለመፈጸም አንዱ መሆኑን የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ይስሀቅ አበራ አመልክተዋል፡፡

ጤና ተቋማቱ ለሰጡት አገልግሎት ደረሰኝ ይዘው ወደ ጤና ቢሮዎች አለመሄዳቸውና ጤና ቢሮዎችም ስለሦስተኛ ወገን መድን ክፍያ ግንዛቤ አለመፍጠራቸው አፈጻጸሙ ላይ መስተጓጐል ፈጥሯል ተብሏል፡፡

የኤጀንሲውን የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም አስመልክተው ዋና ዳይሬክተሩ ያስረዱት፣ የሦስተኛ ወገን መድን ሽፋን የሌላቸው፣ የነበራቸውም ሆነው ያላሳደሱ ተሽከርካሪዎች በተጠቀሱት ክልሎች ልዩ ልዩ ሥፍራዎች ሲሽከረከሩ እየታዩ በሚመለከታቸው አካላት ቁጥጥርና ክትትል አለመደረጉ ሌላው ክፍተት መሆኑን ነው፡፡

በመኪና አደጋ ለሚደርስባቸው አስቸኳይ የሕክምና አገልግሎት የሚውል 6.4 ሚሊዮን ብር ታዳጊዎችን ጨምሮ ለሁሉም ክልሎችና ለሁለት ከተማ አስተዳደሮች የጤና ቢሮዎች በ2007 ዓ.ም. ታኅሣሥ ላይ ኤጀንሲው እንዳከፋፈለ፣ የየድርሻቸውንም ገንዘብ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አማካይነት በየአካውንቶቻቸው ገቢ እንደተደረገላቸው ያስታወሱት ዳይሬክተሩ፣ አምስቱ ክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች በአፈጻጸሙ መመሪያ መሠረት ሲንቀሳቀሱ፣ በተጠቀሱት ታዳጊ ክልሎች ግን ተጎጂዎች በጤና ተቋማት የአስቸኳይ ሕክምና አገልግሎት እያገኙ ቢወጡም ጤና ቢሮዎች በአካውንታቸው ገቢ ከሆነው ገንዘብ ለጤና ተቋማቱ ሲከፍሉ እንደማይታዩና የገባላቸው ገንዘብም እስካሁን እንዳልተንቀሳቀሰ ገልጸዋል፡፡

የኤጀንሲው የኮሙዩኒኬሽን ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክተር አቶ ዘውዱ ወንድም በበኩላቸው፣ ‹‹የተሽከርካሪ አደጋ ሦስተኛ ወገን መድን አዋጅ ከመውጣቱ በፊት የነበረው የካሳ ክፍያ ተጎጂውን ብቻ ታሳቢ ያደረገና ጉዳት አድራሹን ያገለለ ነበር፡፡ አዋጁ ከወጣ ወዲህ ግን ሁለቱንም ወገኖች ተጠቃሚ ያደረገ አካሄድ ሊፈጠር ችሏል፤›› ብለዋል፡፡

በዚህም መሠረት ተጎጂው ተገቢውን ካሳ እንደሚያገኝ፣ አሽከርካሪው ደግሞ እጅግ በተመጠነ የአረቦን ታሪፍ መሠረት የአንድ ዓመት የሦስተኛ ወገን መድን እንደሚገባና በሦስተኛ ወገን ላይ ለሚያደርሰውም ጉዳት የኢንሹራንስ ኩባንያው የጉዳት ካሳ እንደሚከፍልለት አስረድተዋል፡፡

በተጠናቀቀው ግማሽ በጀት ዓመት በተሽከርካሪ አደጋ የንብረት፣ የአካልና የሞት ጉዳት ለደረሰባቸው እንዲሁም በተመላላሽነትና ተኝተው ለታከሙ 4,870 ተጎጂዎችና የተጎጂ ቤተሰቦች በድምሩ 79 ሚሊዮን ብር ካሳ እንደተከፈላቸው ከኤጄንሲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...