Saturday, November 26, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ያልተቋጨው የአሉባልታና የእውነታ ፍልሚያ በጋምቤላ

  በጽጌ ሕይወት መብራቱ

  በጋምቤላ እየተካሄደ ያለውን የእርሻ ልማት እንቅስቃሴ ገና ከጅምሩ ከአገር ቤት እስከ ዓለም ዙሪያ የሚገኙ የራሳቸው የሆነ ዓላማ ያነገቡ አካላት ‹‹ከመሬት ወረራ›› ጋር በማያያዝ መነጋገሪያ አድርገውት እንደነበር ይታወሳል፡፡ በተለይም ከትግረኛ ተናጋሪዎች ጋር በማቆራኘት ያካሄዱት የስም ማጠልሸት ዘመቻ በሒደት ባዶ ጩኸት መሆኑ እስኪረጋገጥ ድረስ ትኩረት የሳበ አጀንዳ ሆኖ ነበር፡፡

  ፍፃሜያቸው በማይታወቅ እጅግ በጣም ብዙ ችግሮችና ከባድ ውጣ ውረዶች ሁለመናው የተተበተበው አሰልቺው የጋምቤላ እርሻ ልማት ከመሬት ወረራው ዘመቻ በመቀጠል፣ ከባንኮች ገንዘብ ዘረፉ ጋር በማያያዝ አነጋጋሪነቱ ቀጥሎ ይገኛል፡፡ በተለይም ይህ ጉዳይ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ትኩረት ከማግኘቱም ባለፈ ብዙ ወገኖች አሉባልታውንና እውነታውን መለየት እስኪያቅታቸው ድረስ ሲደናገሩበት እያየን ነው፡፡ በጉዳዩ ላይ ምንም እውቀትና ግንዛቤ ሳይኖራቸው በየተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ውጤቶች ላይ የባጥ የቆጡን ሲዘላብዱም ታዝበናል፡፡

  ከሁሉም በጣም የሚገርመውና የሚያሳስበው ደግሞ የተሳሳተ መረጃ መሠረት በማድረግ ወይም የቀረበላቸውን ግማሽ ብስል ግማሽ ጥሬ የሆነ እርስ በርሱ የሚጋጭ የጥናት ሪፖርት እንዳለ በመቀበል እየደረሱበት ያለው ድምዳሜ አሳሳቢ መሆኑ ነው፡፡ ምክንያቱም ከዚህ በመነሳት ከፍተኛ የአገራችን የሥራ ኃላፊዎች እየሰጡዋቸው ያሉ መግለጫዎችና እየተላለፉ ያሉት ውሳኔዎች ህልቆ መሳፍርት በሌለው የችግር ማዕበል እየተናጠ ያለውን የጋምቤላ እርሻ ልማት ውድቀቱን የሚያፋጥኑ በመሆናቸው ነው፡፡ እኔም ከጉዳዩ ባለቤቶች አንዱ ነኝና መጥፎ ዜና ከመሰማቱና ዘግናኝ ውድቀት ከማጋጠሙ በፊት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት አሉባልታውን ከእውነታው ለያይተው እንዲገነዘቡት በማድረግ የዜግነት ኃላፊነቴን ለመወጣት በማሰብ ነው ይህን ጽሑፍ የማቀርበው፡፡

  ከጋምቤላ ፈተናዎች በጥቂቱ

  የጋምቤላ የግብርና ኢንቨስትመንት ከ2001 ዓ.ም. ጀምሮ የልማት እንቅስቃሴውን ከዜሮ በታች ብቻ ሳይሆን፣ ከብዙ ዜሮዎችም በታች በጣም ወርዶ ነው አሀዱ ብሎ የተነሳው፡፡ መንግሥታዊ አሠራሩ በአስቂኝ ሁነቶች የተሞላ፣ የመሠረተ ልማት ውጤቶች ሽታቸው እንኳን የሚናፍቅ፣ በሰላም ወጥቶ መግባት እንደ ተዓምር የሚቆጠርበት፣ የሕግ የበላይነት የመይታሰብበት፣ መብትን መጠየቅ እንደ ድፍረት የሚቆጠርበት፣ በአጠቃላይ ሲታይ ሁሉም ነገር ግራ የሚገባበት ነበር ጋምቤላ፡፡ በእርግጥ አሁንም ቢሆን መጠነኛ መሻሻሎች መኖራቸውን ብናደንቅም ተዝቀው የማያልቁ አያሌ ችግሮች እንዳሉ መዘንጋት የለበትም፡፡ ወደ እርሻ ልማቱ ስንገባ ደግሞ ሌሎች አዕላፍ ችግሮች ጥርሳቸውን አግጥጠው ዓይናቸውን ጨፍነው ይጠብቃሉ፡፡ የመሬት ፅዳት (ምንጠራ) ሥራው አድካሚነትና የሚበላው ገንዘብ ብዛት ደምን የሚጠጣ ነው፡፡ የአየር ንብረቱ መጨበጫ የለውም፡፡ የሰው ኃይል እጥረቱ፣ በየመንገዱ የሚጠብቅና ገንዘብን እስከ ሕይወት የሚበላ ሥፍር ቁጥር የሌለው ዘራፊ፣ ጎሳውና ቋንቋው ብዛቱ፣ ይኼን ሁሉ ችግርና ፈተና እየታየ ጋምቤላ ወደ ሥራ ለመግባት ሲወሰን ግን ከደፋርነትና ከቆራጥነት ባሻገር፣ ወደፊት ለውጥ መምጣቱ የማይቀር ሒደት መሆኑን ተስፋ ማድረግና የአካባቢውን ነባር ተወላጆች የሚያደርጉት እንክብካቤና ለልማቱ ያላቸውን መልካም አመለካከት በማስተዋል ነው፡፡ ያም ሆነ ይህ ጋምቤላ የእንግዶችን ሕይወትም፣ ገንዘብም እየበላች የመሬት ወረራ አሉባልታ አጀንዳ እንደሆነች በልማት ጎዳና እያዘገመች እስከ 2005 ዓ.ም. ቆይታለች፡፡ ከዚህ ጊዜ በኋላ ደግሞ በተለይ ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች የኢትዮጵያ ልማት ባንክና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የብድር አገልግሎት ማቅረብ በመጀመራቸው፣ ጋምቤላ በመሬት ፈላጊ ዜጎች መጥለቅለቅ ጀመረች፡፡ በደላላ ፈቃድ የደም ዝውውሯ ያለሙስና መንቀሳቀስ እስኪያቅተው ድረስ የብዙ ቴአትሮች መታያ መድረክ ሆነች ጋምቤላ፡፡ ብዙ ተዋንያንም መድረኩን ለመቆጣጠር ባደረጉት መሻኮት የአሉባልታ መነኻሪያነቷ ባሰበት፡፡ ሒደቶች ሳያቋርጡ ፈጠኑ፡፡

  በአሉባልታ ዘመቻ የተለከፈው ኤጀንሲ

  የማያቋርጥ ክትትል፣ ድጋፍና ግምገማ በማካሄድ የግብርና ኢንቨስትመንት ውጤታማነትን ማረጋገጥ ዓላማው ሆኖ በፌዴራል የግብርናና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ሥር የተቋቋመው የግብርና ኢንቨስትመንት አስተዳደር ኤጀንሲና የክልሉ ኢንቨስትመንት ቢሮ በየአቅጣጫቸው መሬት የማደሉን ሥራ ተያያዙት፡፡ ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ ዘርፉን መደገፍና መከታተሉ ቀርቶ የፌዴራሉ ኤጀንሲ የአሉባልታ ፊታውራሪ መሆን የጀመረው ይላሉ ሁኔታውን የሚከታተሉ ሰዎች፡፡ ሌሎች ታክቷቸው የተውትን የመሬት ወረራ አጀንዳ በማንሳት እስከገንዘብ ዘረፋ በማሻገር ከአንድ ብሔር ተወላጆች ጋር በማስተሳሰር ረዥም ጉዞ ተጉዟል፡፡ በሚያገኛቸው አጋጣሚዎች ሁሉ የክልሉን ኢንቨስተሮች በመፈረጅ ልማቱን አጣጥሏል፣ አጥላልቷል፡፡ ጥቃቅን ችግሮችን እያጋነነ ባንኮች ብድር መስጠታቸውን እንዲያቆሙ ደብዳቤ በመጻፍ ወትውቷል፡፡  የጋምቤላ ክልል አመራሮች ባለሀብቶቹን በመጥፎ ዓይን እንዲያዩዋቸውና እንዲያውም የመሬት ኪራይን ዋጋ ከአቅማቸው በላይ በማድረግ፣ አስጨናቂ አገዛዝን በማስፈን አክስረውና አበሳጭተው ከክልሉ ሊያባርሯቸው እንደሚገባ የማሳመን መርዛማ ተግባር እንደፈጸመ ይነገራል፡፡ በአጠቃላይ በአገራችን በግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ለተመዘገበው ዝቅተኛ ውጤት ግንባር ቀደም ተጠያቂ ነው የተባለው ይኼ ኤጀንሲ፣ ወደ እንደዚህ ዓይነት ተግባር የገባው የጋምቤላን መሬት በራሱ ሥር አድርጎ ኪራይ ለመሰብሰብ በነበረው ከፍተኛ ፍላጎት ምክንያት ብቻ ሳይሆን ሌላ ማሳካት የሚፈልገው የተደበቀ ዓላማ ስላለው ሊሆን እንደሚችል፣ የጋምቤላ ኢንቨስተሮች ኅብረት ሥራ ማኅበር አመራር አባላት እምነት ነው፡፡ ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ ለዚህ አባባል ማስረገጫ ከሚሆኑት የኤጀንሲው ተግባራት አንዱ በጋምቤላ የተካሄደውን ጥናት የመራውና ያስተባበረው ሌላ አካል ሆኖ እያለ፣ የጥናት ቡድኑ ውጤት በሚመለከተው ሕጋዊ አካል አቅራቢነት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይትና ግምገማ ተካሂዶበት ይፋ ከማድረጉ አስቀድሞ፣ የኤጀንሲው መሪዎች በማይመለከታቸው ጉዳይ ገብተው ለአገር ውስጥና ለውጭ መገናኛ ብዙኃን የተጣደፈ መግለጫ መስጠታቸው ነው፡፡ በተለይም የጥናቱ ግኝት የተባሉ ግን መሠረተ ቢስ የሆኑትን አፍራሽ ሐሳቦችን አጉልቶ ለማሳየት ያደረጉትን ጥረት ላስተዋለው፣ ለጋምቤላ ልማትና ለልማቱ ተሳታፊዎች ያላቸውን ጥላቻ ቁልጭ አድርጎ ያሳብቅባቸዋል፡፡

  ታኅሳስ 15 ቀን 2009 ዓ.ም. በግዮን ሆቴል በተካሄደው አገር አቀፍ የግብርና ኢንቨስትመንት ንቅናቄና ከታኅሳስ 22 እስከ 23 ቀን 2009 ዓ.ም. ጋምቤላ ላይ በተካሄደው የክልሉ የግብርና ኢንቨስትመንት ንቅናቄ መድረክ ላይ የጥናቱን ውጤት ገለጻ ባደረጉት የኤጀንሲው ዳይሬክተር ላይ፣ በአገራችን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ፊት የጋምቤላ ኢንቨስተሮች ያሳዩት ተቃውሞና ኃይለ ቃላት የተሞላበት ነቀፋ በመካከላቸው ያለው ግንኙነት ምን ያህል የተበላሸ ለመሆኑ ማሳያ ነው፡፡

  በጋምቤላ ባለሀብቶች እንደ አርዮስ እየተወገዘ ያለው ይኼ ተቋም የተሰጠውን ኃላፊነት መወጣት ያልቻለና ለወደፊትም ሊወጣ የማይችል መሆኑ ታምኖበት እንዲፈርስ በመንግሥት መወሰኑ አስደሳች የነበረውን ያህል፣ በሌላ አደረጃጀት የኤጀንሲው አባላት እንደገና ከጋምቤላ የግብርና ኢንቨስትመንት ሥራ ጋር እንዲገናኙ የመደረጉ ዜና ሲሰማም ሌላ ሐዘንና ግርምታን ፈጥሯል፡፡ ይህም ለክልሉ የእርሻ ልማት ሌላ ተግዳሮትና የንትርክ ዘመን በጋምቤላ መቋጫ ካልተበጀለት ውጤት መጠበቅ ከንቱ ነው፡፡ የተደበቁ ሀቆች በጊዜ ተቆፍረው እንዲወጡ ማድረግ አማራጭ የለውም፡፡

  ወርቅ ላበደረ ጠጠር

  ጋምቤላ የግብርና ኢንቨስትመንት የነበረበትን ወለል ለሚያውቅ በአሁኑ ወቅት የደረሰበትን ደረጃ አስተውሎ ከማድነቅና ተዓምራዊ መሆኑን ከመመስከር ሊያግደው የሚችል ኃይል የለም፡፡ ይኼ መመፃደቅ ወይም ማጋነን አይደለም፣ ‹‹ዓይን አይቶ ልብ ይፈርዳልና››፡፡ ዓይኑንና ህሊናውን አውቆ ላልሸፈነ መሬቷ እውነትን በቋንቋዋ ትነግረዋለችና፡፡ ተዓምራዊው የእርሻ ልማት የራሱ የሆኑ ጉድለቶች ቢኖሩበትም ሀቁ ግን በታቀደና በተቀነባበረ የቅብብሎሽ ዘዴ እየተነዛበት ካለው በቅናትና በጥላቻ ከተመረዘ ሰይጣናዊ ዘመቻ ውጤት ጋር ሲነፃፀር ልዩነቱ የሰማይና የምድር ያህል ይራራቃል፡፡

  ባለሀብቶች የፌዴራልና የክልሉ መንግሥት በተደጋጋሚ ያቀርቡት የነበረውን የልማት ጥሪ በመቀበል ወደ ክልሉ የገቡት እጅግ በተንጠባጠበ ሁኔታ መሆኑን እስከ 2005 ዓ.ም. ያሉ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ የመንግሥት የልማት ፖሊሲን መገንዘብ የቀረቡ ማበረታቻዎችን ማስላት ከጊዜ ጋር አብሮ የመሄድ ችሎታ እንዳሉ ሆነው፣ ለዚያውም ደግሞ በጋምቤላ በገሃድ የሚታዩ ከእግር ጥፍር እስከ ራስ ፀጉር የበዙ ችግሮችን እየተጋፈጥኩ ጉልበቴን፣ እውቀቴንና ጥረቴን እሰዋለሁ ብሎ መወሰንና ቁርጠኝነትና ጥረቴን እሰዋለሁ ብሎ መወሰን መቻል ቁርጠኝነትና ጭካኔን ይጠይቃል፡፡ ዛሬ በየከተማው ማኪያቶና ቢራ እየተጎነጩ ሎሚ መስሎ ማስቲካና ብስኩት እየቸረቸሩ ሚሊዮን ብሮች እንደሚታፈሱ እየታወቀ አሁንም ለዚያውም በጋምቤላ፣ ለዚያውም ከብዙ ዓመታት በኋላ ሊገኝም ላይገኝም የሚችል መልካም ውጤት በማሰብ ወደ እርሻ ሥራ ለመግባት መድፈር ለውስን ሰዎች ብቻ የተቸረ ብቃት ነው፡፡ ነገር ግን ከዚህም በላይ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የሰው ዘር ጠረን አልፎበት በማያውቅ ጫካ ተበትነው ከተፈጥሮና ከሰው ሠራሽ ችግሮች ጋር ግንባር ከግንባር እየተፋለሙ አፈር መስሎ መኖራቸው ሳያንስ፣ በጥይትና በአራዊት ሕይወታቸውን ያጡ ጀግኖችን ቤታቸው ይቁጠራቸው፡፡ እንግዲህ በዚህ መራራ ትግል ውጤት ነው ጋምቤላ አሁን ካለችበት የመነጋገሪያነት ምዕራፍ የበቃችው፡፡ ከላይ ከጠቀስናቸው የጋምቤላ ልማት ፈር ቀዳጅ ዜጎች ጥረት ቀጥሎ ከ2005 ዓ.ም. ጀምሮ አንፀባራቂ ውጤት ያመጡት ደግሞ፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክና የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ናቸው፡፡ ንግድ ባንክ በተወሰኑ እርሻዎች ላይ መሳተፉን፣ በተለይም በውጭ አገር ተበዳሪዎቹ ገንዘቡ እንደተዘረፈ ከመስማት ውጪ እውቀቱ ስለሌለኝ ከዚህ በላይ የምለው የለኝም፡፡

  በአልሚዎችና በአጥፊዎች የተከበበ ተቋም

  ከተመሠረተ አንድ መቶ ዓመቱን የዘለለውና በአገራችን በተመዘገቡ የተለያዩ የልማት ውጤቶች ላይ የማይደበዝዝ አሻራውን ያሳረፈው የልማት ባንካችን፣ የጋምቤላ የግብርና ኢንቨስትመንት በሦስት ዓመት ትንሽ ዕድሜ ላስመዘገበው ከፍተኛ ዕድገት ቀጥተኛ ባለቤት ነው፡፡ ብዙ መቶ ሚሊዮን ብሮችን በማበደር ሙሉ በሙሉ ባይሆንም ወሳኝ በሆነ መልኩ የደንበኞቹን ችግር በመፍታት ልማቱ እንዲቀላጠፍ አድርጓል፡፡ ለብዙ ሺሕ ዜጎች ሥራ ዕድል እንዲፈጠር አስችሏል፡፡ ጋምቤላ ሁለንተናዊ የዕድገት ጎዳናን እንድንጀምር ረድቷል፡፡ ሀቀኛ ባለሙያዎቹ ደከመን ሰለቸን ሳይሉ ዜግነታዊ ግዴታቸውን ሲወጡ አይተናል፡፡ በተግባር የምናውቀው ዜጎች ለልማት ባንካችን ያለንን አድናቆትና ምሥጋና መደበቅ አንችልም፡፡ በጣም የሚገርመው ግን ይህን የመሰለ ወርቃማ ታሪክ እየሠራ ያለው ባንክ ከውስጥም ከውጭም የሚዥጎደጎድበት የአሉባልታ ውርጅብኝ በራስ የመተማመን ብቃቱን ሰልቦት ይመስላል፣ የራሱን ተግባርና ውጤት የመግለጽ የማሳመን እንጥፍጣፊ አቅም አጥቶ መታየቱ ነው፡፡ መሥፈርቱን ከአሟሉ ተበዳሪዎች ጋር በተናጠል ስምምነት እየፈጸመ የሚያበድር መሆኑ እየታወቀ፣ ለትግራይ ተወላጆች ብቻ ብድር እንደሚሰጥና ገንዘብንም ሆነ ብሎ ለዘረፋ እንዳመቻቸ ተደርጎ የስም ማጥፋት ዘመቻ ሲካሄድበት ይህን የማስተባበልና እውነቱን ለማስረዳት ተግባር የፈጸመ አይመስልም፡፡

  በእርግጥም ከእርሻ ሥራ ጋር የሚስማማ በጥልቀት የተጠና የብድር አለቃቀቅ ሥርዓት ወጥነት ባለው መልኩ ለማስፈን ያደረገው ጥረት በተፈለገው  ፍጥነት አለመሄዱ እውነት ነው፡፡ ይህም ቢሆን ጋምቤላ ላይ እየተካሄደ ያለው ልማት በባህርይው ከሌሎች አካባቢዎች በእጅጉ የተለየ ከመሆኑ፣ እንዲሁም የተንቀሳቀሰበት የጊዜ ሥሌት አጭር የሚባል ከመሆኑ አንፃር ወጥ የሆነ አሠራር ለመዘርጋት እንደሚከብድ ግንዛቤ መውሰድ ይገባል፡፡ ይህን እውነት ለማስጨበጥ የተደረገ  ጥረት አናሳ መሆን ነው ያስመዘገበው መልካም ውጤቱ አሉባልታውን ማክሸፍ እንዳይቻል ያደረገው፡፡ የባንኩን መልካም ስም የሚፃረር ብልሹ ተግባር የሚፈጽሙ ኃላፊነት የጎዳላቸው ባለሙያዎች የተሰገሰጉበት መሆኑ ሌላው ፈተና ሆኖበታል፡፡ በመንግሥትና በሕዝብ ለተሰጣቸው አደራ ደንታ የሌላቸው የተወሰኑ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሠራተኞች የሕገወጥ ጥቅም ተጋሪዎቻቸው ከሆኑ የተወሰኑ ጥገኛ ኢንቨስተሮች ጋር በመመሳጠር የሚፈጽሙት የተበላሸ ተግባር መኖሩ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ከዚህ በመነሳትም የባንኩ ደንበኞች ‹‹የቤት ልጆችና የእንጀራ ልጆች›› በማለት እርስ በእርሳቸው እየተሰያየሙ በአሽሙር እየተወጋጉ ይታዩ የነበረው ያለ ምክንያት ሊሆን አይችልም፡፡ የባንኩ የቤት ልጆች የሚባሉት የሚያቀርቡት የብድርም ሆነ ማንኛውንም ጥያቄ በሚገርም  ፍጥነት ይፀድቅላቸዋል፡፡ በተግባር ራሳቸውን መግለጽ ላይ ደሃዎች ሆነው ሳለ ቃላቶቻቸው ታማኝና ከማር የሚጣፍጥላቸው ናቸው፡፡ ከእነሱ በታች መሆኑን አምኖ ለማይቀበልና ለአልንበርክክ ባዮች ደግሞ አደናቃፊዎች ናቸው፡፡ ማንኛውም ጎዶሎአቸው ወደ ውጤት ይቀየርላቸዋል፡፡ አንደኛው ፕሮጀክታቸው አፈጻጸሙ በጣም ዝቅተኛ መሆኑ እየታወቀ በሌሎች በተለያዩ ፕሮጀክቶች ስም ወፋፍራም ተጨማሪ ብድሮች የሚፈቀድላቸው ቅምጥል ደንበኞች ናቸው፡፡ በእርግጥ አንዳንዶቹ በሒደት ወደ ትክክለኛው ውጤት መጥተዋል፡፡

  የአበሰኞቹ የእንጀራ ልጆች ግን በተቃራኒው ነው፡፡ ውጤታማ ሥራቸው ዓይነ ግቡ አይደለም፡፡ እንኳን ቃላታቸው ማንነታቸው ራሱ ቀፋፊ ነው፡፡ የሚጉላሉበት ሰበብ ብዙ ነው፡፡ አቤት ቢሉ ሰሚ አያገኙም፡፡ ምክንያቱም ባንኩ አመራሮች የሚያምኑት የፈላጭ ቆራጭ ባለሙያዎቻቸውን ሪፖርት ነውና፡፡ የእንጀራ ልጆች ፈተና በዚህ ብቻ አያበቃም፡፡ ፍትሐዊ አሠራር በመጠየቃቸውና መብታቸውን በገንዘብ ለመግዛት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ‹‹ሽጉጥ ግንባር ላይ እየደገኑ ያስፈርማሉ፣ ይዝታሉ፣ ይሳደባሉ፣ ጋንግስተሮች ናቸው፣ . . . ››  እየተባለ የሐሰት ክስ ይመሠረትባቸዋል፡፡ ‹‹እንዳያማ ጥራው እንዳይበላ ግፋው›› ቀመር ከኢትዮጵያ ሕዝብ ካዝና የተበደሩትን ገንዘብ ለትክክለኛው ዓላማ ከመጠቀምም ባለፈ፣ ያጋጠማቸውን ጉድለት ከራሳቸው ኪስ በመሙላት ልማታቸውን ውጤታማ እያደረጉ መሆናቸው ግን የጋምቤላ መሬት ትመሰክርላቸዋለች፡፡ የኢትዮጵያ ልማት ባንክና ሀቀኛ የባንኩን ሠራተኞች የተቀደሰ ዓላማና ጥረት እጀ ሰባራ የሚያደርጉ የባንኩ ምግባረ ቢሶች ተግባራቸው ድንበር የለውም፡፡ ማፈርና መሸማቀቅ ሲገባቸው እንደገና ዞረው ባለቤቶቹ ራሳቸው እንዳልሆኑ ዘንዳ የባንኩ ገንዘብ በትግራይ ተወላጆች እየተዘረፈ መሆኑን የሚቀባጥሩት ፊታውራሪዎቹ እነሱ ሆነው ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ በ2007 ዓ.ም. መጀመሪያ ላይ የተፈጸመው ሥነ ምግባር የጎደለው ፍፃሜ ሁነኛ ማሳያ ነው፡፡

  በወቅቱ ከጅማ የባንኩ ቅርንጫፍ ተበዳሪ የሆኑ ደንበኞችና ጥያቄያቸው ገና በሒደት ላይ የሚገኙ ተጠባባቂዎች ስም ዝርዝር ከተበደሩትና ተጠባባቂዎቹ ከጠየቁት የገንዘብ መጠን ጋር ተያይዞ፣ ‹‹በትግራይ ተወላጆች የተዘረፈ ገንዘብ›› የሚል ርዕስ የተሰጠው ሰነድ ከዚያው ከጅማ ልማት ባንክ ወጥቶ በኢሳት ቴሌቪዥን ለዓለም ሕዝብ ሲሰራጭ አይተናል፡፡ እስከ ዛሬው ድረስ ለሚፈልጉት ዓላማ እየተጠቀሙበት ይገኛሉ፡፡ ሁሉም ተበዳሪዎች ከተለያዩ የአገራችን ብሔር ብሔረሰቦች የተወጣጡ መሆናቸው ሰነዱ ላይ ያለው ዝርዝር በግልጽ እያሳየ፣ ትግራዋይነት በግድ እንዲጫንባቸው የተፈለገበትን ሚስጥር እንዳጋለጠባቸው እንኳን የሚገነዘቡ ዓይነት አይደሉም፡፡ በወቅቱ ስም ዝርዝራቸው የተካተተው ተበዳሪዎች ሁለቱ ‹‹እኩብ›› እና ‹‹ኡጁሉ›› የሚባሉ የጋምቤላ አኞዋኮች እንኳን ሳይቀሩ የጋምቤላን መሬት የወረሩና የልማት ባንክ የዘረፉ ተብለው የትግራዋይነት ታርጋ ተለጥፎባቸው የተመለከቱ ሁሉ ግርምታቸውን በትዝብት ሳቅ ገልጸዋል፡፡ የባንካቸውን ሚስጥር የመጠበቅ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ያልቻሉ ደካሞች እንዲህ ዓይነት ተራ ስህተትን እንኳን ማስተዋል የሚችል ህሊና እንዲኖራቸው አይጠበቅም፡፡

  የተድፈነፈነ ድግስ

  ከመሬት ወረራ እስከ ባንክ ገንዘብ ዘረፋ የተቀጣጠለው ፕሮፓጋንዳ ምን ያህል ረዥም ርቀት በጥንካሬ እንደተጓዘ ያስመሰከረበት ክስተት የታየው ደግሞ፣ በጋምቤላ የብሔር ብሔረሰቦች በዓል በተከበረበት ወቅት ነው፡፡ ይህ የጋምቤላን መልካም ገጽታ ለማሳየት የሚቻልበት ወቅት ነው፡፡ በጋምቤላ የኢንዱስትሪ ልማት፣ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ….የሚታወቁት በዲስኩር ብቻ ነው፡፡ እያቆጠቆጠ ያለው የኮንስትራክሽን ዘርፍም የግብርናውን ጅምር እንቅስቃሴ ተከትሎ ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ብቅ ያለ ለውጥ ነው፡፡ እናም ብቸኛ የጋምቤላ ዋስትና የሆነው የእርሻ ልማት ያለበትን ደረጃ ለእንግዶቿ ከማሳየት ውጪ ሌላ አማራጭ አልነበረም፡፡ ስለዚህ የክልሉ መንግሥትና የኢንቨስተሮች ማኅበር የጋራ ዕቅድ በማዘጋጀት የውይይት መድረክ፣ የመስክ ጉብኝት፣ የተለያዩ ትርዒቶች፣ የእርሻ ውጤቶች፣ ኤግዚቢሽንና ዘጋቢ ፊልሞች ማቅረብ በዕቅዳቸው አካተዋል፡፡ የፕሮፓጋንዳ ሰለባ ከመሆኑ አንፃር የአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ለመገምገም የራሳቸው ዝግጅት አድርገው እንደሚመጡ በእርግጠኝነት ይታመናልና ወቅቱን መጠቀምም ግድ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዓሉንና ጋምቤላን በተመለከተ ባሰሙት ንግግር ላይ የእርሻ ልማቱን የሚጠቅስ አንድም ቃል ሳይደመጥ ንግግሩ ተቋጨ፡፡ ይባስ ብሎ እስከ በዓሉ ፍፃሜ ድረስ ይህንን አነጋጋሪ ጉዳይ የሚመለከት እንኳን ተግባር የቃል ሽታው እንኳን ናፈቀ፡፡ በዚህ ክስተት ብዙዎች ግራ ተጋቡ፡፡ እንዲያውም የፌዴራል መንግሥቱ ባለሥልጣናት ጥርግርግ ብለው አዲስ አበባ ገቡና ሁሉንም ኩም አደረጉት፡፡ ሁሉንም ግራ ተጋባና ጠያቂ ብቻ እንጂ መልስ ሰጪ ታጣ፡፡

  መልስ የሚሰጠው ይመስል ሁሉም ወደ ኢቢሲ መስኮት ማፍጠጡን ተያያዘው፡፡ በዓሉን በተመለከተ የሚተላለፉ ዜናዎችና ፕሮግራሞች ላይ የጋምቤላን እርሻ እንቅስቃሴ የሚመለከቱ ምልክቶች በስህተት እንኳን ሊታዩ አልቻሉም፡፡ በኢንቨስተሮች ማኅበር ተዘጋጅቶ ስታዲየም በር ላይ የተሰቀለው ’ሬክላም’ እንኳን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሪቫን ሲቆርጡ አብሮ መታየት እንዳይችል ተደርጓል፡፡ ከዚህ በኋላ ነው ነገሮች ሁሉ ሆን ተብሎ እንደተደረጉ ማመን የተቻለው፡፡ እንዲያውም ከአንዳንድ የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር የመገናኘት ዕድል የገጠማቸው ሰዎች ማብራሪያ ለማግኘት ያደረጉት ሙከራ፣ ከኪራይ ሰብሳቢዎችና ከጋንግስተሮች ጋር እንኳን መወያየት ይቅርና አብሮ መታየትም አስፈላጊ እንዳልሆነ የሚያስረዳ መልስ እንዳስገኘላቸው መግለጽ ጀመሩ፡፡ ከዚህ በኋላ ነው በበርካታ ባለሀብቶች አዕምሮ ላይ የመጠላትና የመገፋት ስሜት ማደሩ በግልጽ መታየት የጀመረው፡፡ ጣጣዋ የማያልቀው ጋምቤላና ፈተናቸው የማያልቀው ባለሀብቶቿ ግን አንገታቸው እየደፉም፣ እያቃኑም የአብሮነት ጉዞውን ከመቀጠል አልተገቱም፡፡

  በዚህ ክስተት ዙሪያ በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ቢኖሩም ለመድረክ እንዳይበቃ የታፈነውን ችግር ተሸክሞ ከመጓዝ ውጪ ሌላ አማራጭ አልነበረም፡፡ እንዲያውም ይህ ከፍተኛ መነጋገሪያ የሆነው ጉዳይ የመወያያና የግምገማ መድረኮች ተዘጋጅተው ሁሉም ነገር ይፋ ሊደረግ የሚገባበት ጊዜ ቀደም ማለት ነበረበት እንጂ፣ ችላ መባል አልነበረበትም፡፡ እንደዚህ መሽቶም ግን አልተቻለም፡፡  ስለዚህ ሁሉም ነገር እንደተድፈነፈነ የሚሆነውን ከመጠበቅ ውጪ ሌላ አማራጭ አልነበረም፡፡

  ያልታሰበው ዱብ ዕዳ

  መሪዎቻችን ከጋምቤላ ወደ አዲስ አባባ ተመልሰው ብዙም ሳይቆዩ ባንኮች ለግብርና ኢንቨስትመንት የሚሰጡትን ብድር በአስቸኳይ እንዲያቆሙ መመርያ መሰጠቱ ተገለጸ፡፡ ይህ እንደሚሆን ቀድመው የማወቅ ዕድል ያላቸው የቤት ልጆች የመንግሥትን ውሳኔ ሰምተው እንዳልሰሙ በመምሰል ይሁን በመቅደም የሚፈልጉትን በፍጥነት እንደተሻሙ ጭምጭምታ ተሰማ፡፡ በየጫካው ተበትነው ከቀን እስከ ሌሊት በልማት ተጠምደው ለሚኖሩት ዜጎች ግን ዜናው አስደንጋጭ መርዶ ነበር፡፡ ምክንያቱም ለባንኮች ያስገቡት የብድር መዋጮ በየእርከኑ ሊለቀቅላቸው የነበረ ገንዘብ ሁሉ ተቆልፎበታልና፡፡ በዚህ ሰበብ በተለይም የብድር ገንዘባቸው ሙሉ ለሙሉ ያልተለቀቀላቸው ፕሮጀክቶች እንቅስቃሴ በየነበረበት እንዲቆም ይገደዳልና፡፡ በዚህ ምክንያም ምንጠራ የጨረሰ ማረስ አልቻለም፡፡ ያረሰም ለመዝራት አልቻለም፡፡ ግንባታዎችም በነበሩበት ቆሙ፡፡ እስከዚህ ወቅት ድረስም የታየ ለውጥ የለም፡፡ ብዙ ሀብት ፈሶበት የታረሰ፣ የተመነጠረ መሬት ሁሉ እንደገና ወደ ኋላ ተመልሶ ወደ ጫካነት እየተቀየረ ይገኛል፡፡ ይህ ደግሞ በልማቱ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ምን ያህል  እንደሆነ ለመገመት አያዳግትም፡፡ እንዲያውም አንዳንዶቹ ወደ ሥራ ለመግባት እየተዘጋጁ ባለበት ወቅት የመንግሥትን ውሳኔ ሲሰሙ የሆነው እስኪሆን ድረስ በማለት የወሰዱትን ገንዘብ ወደ ሥራ ሳያገቡ ይዘውት እንደተቀመጡ ይነገራል፡፡ በዚህ ምክንያት በልማቱ ላይ የሚያርፈው ተፅዕኖ ምን  ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡

  የዘገየው ውሳኔ

  ከባንኮች ዕገዳ ቀጥሎ የሚመጣው የመንግሥት ውሳኔ ከባንኮች በብድር የተወሰደው ገንዘብ ለታለመለት ዓላማ መዋሉን ወይም አለመዋሉን ለማረጋገጥ እንዲችል ማስጠናት ነው፡፡ ይህን ተልዕኮ የያዘ ኮሚቴም ተዋቅሮ ሥራውን ለመጀመር ጋምቤላ እንደደረሰ ነው ተቃውሞ የገጠመው፡፡ የመጀመሪያው በፌዴራል እርሻና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር የግብርና ኢንቨስትመንት አስተዳደር ኤጀንሲ በዚህ ኮሚቴ ውስጥ መካተቱ ነው፡፡ ይህ ኤጀንሲ ከዚህ በፊት አደረጋቸው በተባሉት ተገቢ ያልሆኑ አሠራሮችና እስከ ብሔር የዘለቁ የስም ማጥፋት ቅስቀሳዎች ምክንያት፣ ከጋምቤላ የእርሻ ባለሀብቶች ጋር እጅግ በጣም የከረረ ቅራኔ ውስጥ የገባ ስለሆነ ነው፡፡ እናም ይህ ጥላቻን መሠረት ያደረገ አፍራሽ አቋም የያዘ አካል ጥናቱ በተገቢው መንገድ እንዳይካሄድ ተፅዕኖ ይፈጥራል ከሚል ሥጋት የመነጨ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የጉዳዩ ባለቤቶች የሆኑትን ባለሀብቶች በተወካዮቻቸው አማካይነት የጥናት ኮሚቴው አካል እንዲሆኑ ይደረግ በሚል መነሻ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ተቀባይነት ሊያገኙ አልቻሉም፡፡ ገና ከጅምሩ እንቅፋት ያጋጠመው ኮሚቴ በሁለት ዙር ጥናት ያለውን አጠናቆ በሰኔ ወር 2008 ዓ.ም. ሄደ፡፡ በመሠረቱ የአገር ሀብት እየተዘረፈ ነው እየተባለ ከአገር ቤት እስከ ዓለም ዳርቻ በሰፊው አቤቱታ የሚቀርብበትን ይህን ጉዳይ በስማበለው ሳይሆን ጥናት በማካሄድ ተጨባጩን እውነታ ለማግኘት መንግሥት የወሰደው ዕርምጃ ተገቢ ነው፡፡ ከአሉባልታው ተቀባይነትና ስፋት አንፃር ነው ግን ዕርምጃው ቀደም ቢልና በተለይ የተጀመሩ እርሻዎች የማይቋረጡበት መንገድ ተቀይሶ ቢሆን መልካም ይሆን ነበር፡፡ ሳይንሳዊ ጥናት ማካሄድ ሳይንሳዊ መፍትሔ ለማስቀመጥ እንደሚበጀው ሁሉ፣ መነሻው ትክክለኛ ያልሆነ አካሄድም መድረሻው ትክክለኛ ሊሆን እንደማይችል ዕሙን ነው፡፡ ሁሉም ነገር በሰዓቱና በጊዜው ሲሆን ያምራል፡፡

  ጅምላ ፍረጃ

  በባንኮች በግብርና ኢንቨስትመንት ለተሠማሩ ባለሀብቶች የተሰጠው ብድርና ከቀረጥ ነፃ የገቡ ዕቃዎች ለተባለው ዓላማ ስለመዋሉ በማረጋገጥና ውጤታማነቱን በማጣራት በጥናት ሪፖርት ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ማቅረብ የሚል ዓላማውን ከመግቢያው ቀጥሎ በማስቀመጥ፣ ከግቦች እስከ የመረጃ ትንተና ዘዴው ማብራሪያ የሰጠውና በጋምቤላ ብሔራዊ ክልል መንግሥት በግብርና ኢንቨስትመንት ለተሠማሩ ባለሀብቶች የባንክ ብድር አጠቃቀም የጥናት ሪፖርት የሚል ርዕስ የተሰጠው ይህ የጥናት ውጤት፣ በባለድርሻ አካላት በጉጉት እየተጠበቀ ነው የ2009 ዓ.ም. ታኅሳስ ወር የባተው፡፡ ውስጥ ለውስጥ ሹክሹክታዎች መሠራጨት ሲጀምሩ መንግሥት የሪፖርቱን ውጤት ይፋ የሚያደርግበት ወቅት እንደደረሰ ታመነ፡፡ ይኼ በሆነ መንገድ በሚመለከተው አካል ለባለድርሻ አካላት ቀርቦ ውይይትና ግምገማ ይቀርብበታል ተብሎ የሚጠበቀው የዚህ ጥናት ውጤት ከሬድዮ ፋና እስከ ኢሳት ቴሌቪዥን፣ ከፎርቹንና ከሪፖርተር ጋዜጦች እስከ ቪኦኤ ባሉ የመገናኛ ብዙኃን ሥርጭቱ ይፋ የሆነው በድንገት ነበር፡፡ አሉ የተባሉ ችግሮች ማጣፈጫ እየተጨመረላቸው ጋምቤላ ላይ በእርሻ ልማት ስም የአገር ሀብት መዘረፉ አሉባልታ ሳይሆን እውነት መሆኑን የሚያበስሩትን ገለጻዎች የጋምቤላን ባለሀብቶች ክብርና ሞራል አከራካሪ የጎዱ ነበር፡፡ በጋምቤላ እርሻ እያለማሁ ነው ብሎ መናገር እስኪያሸማቅቅ ድረስ፡፡

  ለተለያዩ ሚዲያዎች መግለጫውን ከፈጠራ ጋር እያሳመሩ የሚሰጡት ግለሰቦች በጥናቱ እንዳይሳተፉ ተቃውሞ ቀርቦባቸው የነበሩ ኤጀንሲ መሪዎች ‹‹አንበሳ ገዳይ›› ከሚመስል ኩራት ጋር አሁን አገኘናቸው ዓይነት የብቃለ ስሜት እያንፀባረቁ ሲያራግቡት ለመታዘብ ችለናል፡፡ የጥናት ቡድኑ የተመራው በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የግብርናና የኢንዱስትሪ ፖሊሲና ዕቅድ አፈጻጸም ክትትል ሚኒስትር ዴኤታ በነበሩ ግለሰብ ስለነበርም ስለጥናቱ ውጤት መግለጫ መስጠት የነበረባቸው እሳቸው መሆን ሲገባቸው፣ ጠላት ተብሎ ለተፈረጀው አካል ተላልፎ የተሰጠበት ሚስጥር ምንድን ነው? የሚል ጥያቄና ሀሜት በሰፊው ተስተጋብቷል፡፡ ኃይለኛ ቁጭትም ፈጥሯል፡፡ ምክንያቱም በተለይም የብድር አጠቃቀምን በተመለከተ የሚባለው ሁሉ ከእውነትነት የራቀ ብቻ ሳይሆን፣ በዚህ አገር መንግሥት የሚባል ተቋም መኖሩ እንኳን አጠራጣሪ እንዲመስል የሚያደርግ ነበርና፡፡ ያም ሆነ ይህ በሁኔታው የተበሳጩት የጋምቤላ ኢንቨስተሮች ኅብረት ሥራ ማኅበር አመራር አባላትም እውነታው ሌላ መሆኑን የሚያስረዱ ማስረጃዎችን አየጠቀሱ ለመሞገት ጥረት ማድረጉን ተያይዘውታል፡፡ የዚህ ውጤትም ኅብረተሰቡም የተለያዩ ጥያቄዎችን እንዲያነሳና እውነቱም ገና መሆኑን ወደ መቀበል እንዲደርስ ገፍቶታል፡፡

  እዚህ ላይ ማስተዋል ያለብን በእርሻ ልማት ስም የሚያጭበረብር የለም ብሎ ለመከራከር የሚደፍር የለም፡፡ የመሬት ብድር ለመውሰድ በሚል ሒሳብ ብቻ መሬት የወሰዱ የለም ተብሎ አይታሰብም፡፡ ፕሮጀክታቸውን በመበደል ገንዘቡን ለሌላ ተግባር ያዋሉ አይኖርም ብሎ የሚከራከር የለም፡፡ በጠቅላላውም ገንዘብ ወስደው ሥራ ያልጀመሩም ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ሌላም ችግር ያለባቸው እንደሚኖሩ አያጠራጥርም፡፡ እነዚህንም ለይቶ ማቅረብ ለምን አልተቻም ነው ዋናው ጥያቄ ምርትና ገለባው ለምን አልተለየም ነው ዋናው ጥያቄ፡፡ በጥናቱ ውስጥ ያለው ግኝት ሁሉ ትክክል አይደለም የሚል አይኖርም፡፡ በጣም በርካታ እውነታዎችን የያዘ ጥናት ነው፡፡ በተለይም ከመንግሥት የሥራ አፈጻጸም፣ ከፍትሕና ከድጋፍ ከመልካም አስተዳደር ችግር ጋር አያይዞ ያቀረበው ግኝት ቢያንስ እንጂ አልበዛም፡፡ ነገር ግን በተጨባጭ መሬት ላይ ያሉትን ኢንቨስተሮችን የሚመለከቱ መሠረታዊ ሀቆች አዛብቶ ማቅረብ አልነበረበትም፡፡ እርስ በርሱ የሚጣረስ መሆን አልነበረበትም፡፡ እነዚህ ደግሞ ማንም ተራ ግለሰብ እንኳን ሊፈጽማቸው የማይችሉ ተራ ስህተቶች ተብለው ሊታለፉ የማይችሉ ናቸው፡፡ እናም ሆን ተብሎ የተደረገ ነው እንድንል አስገድዶናል፡፡ ለምሳሌም የተወሰኑትን እንመልከት፡፡  

  1. የጋምቤላ ኢንቨስተሮችን በብድር የደገፉት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ልማት ባንክ ናቸው፡፡ ሁለቱም የየራሳቸው የሆነ አሠራርና ዓላማ ያላቸው ስለሆኑ የተበዳሪዎችን ምንነት አውቆ ከማበደር እስከ ብድር አመላለስ ያለውን ክትትል ቅደም ተከተሉን ጠብቆ የሄደውንና ያልሄደውን ለይቶ ያስቀመጠ መሆን ነበረበት፡፡ የተሰጠውን ብድር ከታለመለት ዓላማ ውጪ ያዋሉትና ያላዋሉት የየትኛው ባንክ ተበዳሪዎች መሆናቸውን ለይቶ ማስቀመጥ ነበረበት፡፡ ሌላው ቀርቶ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ዋናው መሥሪያ ቤትና የጅማ ቅርንጫፍ የሥራ ውጤት ተለያይቶ መቀመጥ ነበረበት፡፡
  2. ከሁሉም ባንኮች ብድር ከወሰዱት ተገልጋዮች ውስጥ የውጭ አገር ዜጎችም ይገኙበታል፡፡ ከሦስት በመቶ የማይበልጥ መጠን ያላቸው እነዚህ የውጭ ባለሀብቶች በጋምቤላ ከተሰጠው የባንክ ብድር 50 በመቶ የሚሆን ለእነሱ የተሰጠ ነው ማለት ይቻላል፡፡ እንዲያውም ሁለት የአገር ውስጥ ዜጎች እንደተበደሩ የሚነገርላቸው ስምንት መቶ ሚሊዮን ብር ሲጨመርበት ከስድስት ወይም ከሰባት ለማይበልጡ ተበዳሪዎች ወደ 77 በመቶ የሚሆነውን እንደወሰዱት ያሳያል፡፡ እስከ 192 የሚደርስ ቁጥር ያላቸው የአገር ውስጥ ተበዳሪዎች የወሰዱት ገንዘብ ምን ያህል እንደሆነ ማስላቱ ቀላል ነው፡፡ የ192  የአገር ውስጥ ተበዳሪዎች የመሬታቸው መጠን ባይኖረኝም፣ ከላይ ከተጠቀሰው መጠን 23 በመቶ በገንዘብ ደረጃ ግን ያነሰውን ገንዘብ የተበደሩ መሆኑን ነው መረጃዎች የሚያሳዩት፡፡ እናም እነዚህን እጅግ የሰፋ ልዩነት ያላቸውን ክፍሎች ጨፍልቆ ውጤት መስጠት እያዩ ማየት አለመፈለግን እንጂ ያስተላለፈው ሌላ መልዕክት የለም፡፡ ከእነዚህ የባህር ማዶ ተበዳሪዎች መካከል ከአንዱ በስተቀር ሌሎቹ በሥራ ላይ የሉም፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ የልማት ባንክ ይሁን የንግድ ባንክ መሆኑን ባናውቅም በብድር የወሰዱትን ገንዘብ ወደ ዶላር እየቀየሩ ይዘውት እንደሄዱ ሹክሹክታ አለ፡፡ ይኼ እውነት ከሆነ ማስረጃ አልተገኘም እንዳይባል እንጂ፣ ምዝበራው ግን በአገራችን ባለሥልጣናትና በአገራችን ባንኮች ፊት መሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ ታዲያ ይኼን ለያይቶ መፈተሽ ያልተቻለው ካለመፈለግ ወይስ ከእውቀት ማነስ ይሆን? ሁሉንም በልማት ባንኩና በአገር ውስጥ ምስኪን ደንበኞች ላይ ኃጢያት ለማብዛት ከሆነም ውጤቱ ለልማታችን መቼ ይጠቅማል?
  3. ለመሬት ልማት ለአገር ውስጥም ለውጪዎችም ከተለቀቀው ገንዘብ ውስጥ 83 በመቶ ለተገቢው ዓላማ መዋሉን በጥናቱ ሰነድ ገጽ ሰባት ላይ ተጽፏል፡፡ የባንኮች ብድር የሚለቀቀው ገንዘብ ለመሬት ልማት ለተሽከርካሪዎች መግዣ፣ ለግንባታ፣ ለሥራ ማስኬጃ፣ . . . በሚሉ ዘርፎች ተመድቦ ነው፡፡ ከባንኮች ለኢንቨስተሮች የተሰጠ ብድር ለታለመለት ዓላማ መዋልና አለመዋሉን የማጥናት ዓላማ ይዤ ተነስቻለሁ ያለው ቡድን፣ ከመሬት ልማት ውጪ ያለውን ገንዘብ አዋዋል በፐርሰንት ሳያስቀምጥልን አልፏል፡፡ በግልባጩ ግን ለእነዚህ ሦስት ዘርፎች የወጣውን ወጪ በአንድ ዓመት የምርት ሽያጭ ለተገኘው ገንዘብ በማካፈል ለታለመለት ዓላማ የዋለው ገንዘብ 18 በመቶ ብቻ መሆኑን አስቀምጧል፡፡ ስለዚህ 85 በመቶ ገንዘብ ለታለመለት ዓላማ አልዋለም ማለት ነው፡፡ ይህ በጣም የሚገርም ስሌት ከሀቁ እጅግ በጣም የራቀ መሆኑን ግን እዚያው ላይ ሰነዱ ያጋልጣል፡፡ ይህም ማለት የውጭ ባለሀብቶችን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ሳይት ላይ ያልተገኙ 59 ተሽከርካሪዎች እንዳልተገዙ ታስቦ ዋጋቸው ወደ ባከነ ገንዘብ ተደምሮ እንኳን፣ ከባንክ ከተወሰደው ብድር ጠቅላላ ውስጥ 79 በመቶ ለታለመለት ዓላማ መዋሉን ያሳያል፡፡ 59 ተሽከርካሪዎች ዋጋቸው ተሰልቶ ቢቀነስና የውጭ ተበዳሪዎና የአገር ውስጥ ተበዳሪዎች ጉዳይ ተለይቶ ሲታይ ደግሞ 94 በመቶ ገንዘብ ለታለመለት ዓላማ መዋሉን ነው ሁኔታው የሚያሳየው፡፡ ይኼንን እውነታ በመካድ ስም ማጥፋት ለምን እንደተፈለገ አሁንም ጥያቄያችን ይቀጥላል፡፡ በጣም የሚገርመው 85 በመቶ የባንክ ብድር ለታለመለት ዓላማ አልዋለም እያለ ሲመራን የዋለው የጥናት ሪፖርት ሰነድ፣ እንደገና ተገልብጦ በማጠቃለያው ገጽ 19 አንቀጽ 2 ላይ ‹‹ምንም እንኳን የተሰጠው ብድር በአብዛኛው ለታለመለት ዓላማ ቢውልም የተወሰኑት ባለሀብቶች ብድሩን ከታለመለት ዓላማ ውጪ እንደተጠቀሙበት ያሳያል›› በማለት ራሱን በራሱ ይቃረናል፡፡ በእኔ በኩል ገርሞኝ ገርሞኝ አላልቅ ብሎኛል፡፡
  4. የጥናቱ ዓላማ በመንግሥት የተቀመጠለትን ተልዕኮ እንዲሳካ ቢፈልግ ኖሮ፣ በሔክታር 43 ብር ተሰልቶ የተሰጣቸው የቤት ልጆችና በሔክታር 19 ብር የተሰጣቸው የእንጀራ ልጆች ያሳዩት የልማት ውጤት መለየት ነበረበት፡፡ የመደራረብ ችግር ያለባቸው 27 ይዞታዎች ብቻ መሆናቸውን ቀደም ብሎ ያረጋገጠ አካል፣ እንደገና ተገልብጦ 380 ብሎ የሌለ ችግር እንዳለ አድርጎ ማቅረብ አይገባውም ነበር፡፡ ለእርሻ ሥራ ከቀረጥ ነፃ የሚፈቀደው በምን ዓይነትና ስንት ተሽከርካሪዎች መግባት እንዳባቸው በሕግ የተቀመጠ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን በመኪና አስመጪ ፈቃድ የተለያየ ከቀረጥ ነፃ ለተፈቀደላቸው ግለሰቦች የተሸጡ ተሽከርካሪዎችና ከእርሻ ጋር ግንኙነት የሌላቸው ማሽነሪዎች ሁሉ በመደማመር 78 መኪናዎች ከቀረጥ ነፃ በአንድ ግለሰብ ወደ ጋምቤላ እንደገቡ አድርጎ፣ ሕዝቡንና መንግሥትን ማሳሳት አይገባም ነበር፡፡ ወደ ዓድዋ የተወሰደን ዓርማታ ብረት ወደ ጋምቤላ ወስዶ መለጠፍ ምን ዓይነት ድንቁርና ያመነጨው ክፋት እንደሆነ የማይገነዘብ ማነው? እንዲህ ዓይነት ወንጀል ሲፈጸም ለመሆኑ አገሪቱ መንግሥት አልነበራትም ወይ? ይህን የሚመልስ ይመልሰው፡፡

  ማጠቃለያ

  ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት ይህ በጥናት ስም የተካሄደ ሪፖርት ለባለድርሻ አካላት ቀርቦ ሳይታይ በጓሮ በር ለመገናኛ ብዙኃን በመሠራጨቱ ብዙ ጉዳት አድርሷል፡፡ ይህ እንዴት እንደሚታደስ ፈጣሪ ይወቀው፡፡ በጣም የሚገርመው ደግሞ በተለይም ሬድዮ ፋና ጉዳዩን በተመለከተ ሚዛናዊ ዘገባ ከማቅረብ ይልቅ አንድ ወገንን ብቻ መሠረት ያደረገ ዘገባ ማቅረቡን እስካሁንም ድረስ መቀጠሉ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ በግዮን ሆቴልና በጋምቤላ በተካሄዱ የንቅናቄ መድረኮች ለባለድርሻ  አካላት ቀርቦ በተደረገው ግምገማ፣ መንግሥትና ተበዳሪዎችን ሊያግባባ አልቻለም፡፡ በተለይ ጋምቤላ ላይ ለሁለት ቀናት የቆየ ውይይት ቢደረግም ከንትርክ በቀር የተገኘ ትርፍ አለመኖሩ በግልጽ ታይቷል፡፡ ለሁሉም የየራሱን ዋጋ በትክክል ከማስቀመጥ ይልቅ ሁሉንም በጅምላ የጨፈለቀ በመሆኑ፣ መሠረታዊ የሆነውን ዓላማውን የዘነጋና ትክክለኛ መፍትሔ እንዳይገኝ እንቅፋት የሚፈጥር ስለሆነ መንግሥት እንዲገነዘበው ለማድረግ ጥረት ተደርጓል፡፡

  ይሁን እንጂ መንግሥት የጥናቱን ውጤት ተብዬ እንደ ትክክለኛ የተቀበለው ይመስላል፡፡ የአገራችን ከፍተኛ መሪዎች በአንዳንድ መድረኮች የሚሰጧቸውን መግለጫዎች ለዚህ ምሥክር ናቸው፡፡  በጋምቤላ እርሻ ልማት ስም በተወሰደ ብድር የተሠሩ ፎቆች እንዳሉ በተጭበረበረ መንገድ ከቀረጥ ነፃ የገቡ ተሽከርካሪዎች እንዳሉ ወዘተ. . . እነዚህም በቁጥጥር ሥር ውለው ወደ ሕግ እንደሚቀርቡ እየተነገረን ነው፡፡ ይህ በተግባር እንዲገለጥና ሌቦች ዋጋቸውን እንዲያገኙ ሁላችንም እንፈልጋለን፡፡ ውጤቱን ከዛሬ ነገ እንሰማለን በማለት በጉጉት በመጠባበቅ ላይ ነን፡፡ ለነገሩ ፎቅ ሊያሠራ የሚችል ገንዘብ የተሰጣቸው እነማን እንደሆኑ የሰጣቸው አካልም በሚገባ ያውቃል፡፡ ‹‹ከአንጀት ካለቀሱ እንባ መች ይገድና›› በዚህም አለ በዚያ ተለባብሶ የሚቀር ሊሆን አይገባም፣ ሊቀርም አይችልም፡፡ በተጨባጭ ሁኔታውን በሚገባ ሳይጨብጡ የሚሰጥ ውሳኔ ስህተትን በስህተት በማደስ ስህተትን ከማበራከት ውጪ ሌላ ውጤት አይኖረውም፡፡ የመንግሥትን ፖሊሲና ሥርዓት በመተማመን ሕይወታቸውንና ጥሪታቸውን በየጫካው ውስጥ ለመስዋዕትነት ያቀረቡ ዜጎች በማንኛውም መመዘኛ መጠቃትና መበደል አይኖርባቸውም፡፡ ለልማት ተብሎ ከደሃ እናት አገራችን ካዝና በብድር የወጣው ገንዘብም ወደ ካዝናው መመለስ ይኖርበታል፡፡ ለዘመናት ከልማት ተገልሎ የኖረው የጋምቤላ ክልልም የተጀመረው የልማት ብርሃን ተመልሶ ሊጨልምበት አይገባም፡፡ የአንዱ አካል መውደቅ የሌላውም መውደቅ ስለመሆኑ፣ ማንኛውም የሚመለከተው ሁሉ ትክክለኛውን እውነታ አሸናፊ እንዲሆን ድጋፍ ማድረጉን እንዲቀጥል እያሳሰብኩ፣ እኔም ሕዝብና መንግሥት ሊያውቁት ይገባል ብዬ ያቀረብኩትን ጽሑፍ በዚሁ ቋጨሁ፡፡   

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፣ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected].  ማግኘት ይቻላል፡፡ 

  spot_imgspot_img
  - Advertisment -

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  Related Articles