በኢትዮጵያ ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክ ዘመን (1909-1922) ከነበሩት የአዲስ አበባ ፖሊስ ጣቢያዎቹ የአንዱ ጥብቅ ደጃፍ
(ሔኖክ መደብር)
******************
በአውቶቡስ በር ተይዞ ወደ ፖሊስ ጣቢያ የተወሰደው ሌባ
ኮሎምቢያ ቦጎታ ውስጥ የሆነ ነው፡፡ ቪላ ሔርሞሳ በተሰኘ መንገድ ላይ ይጓዝ የነበረ አንድ የሕዝብ አውቶቡስ ሾፌር አንድን ተሳፋሪ በበሩ ቀርጥፎ ይዞ መንገዱን ይቀጥላል፡፡ ውጭ ያሉ መንገደኞች እየተሯሯጡ በሩን ፈልቅቀው በመክፈት በበሩ የተያዘውን ሰው ለማስለቀቅ እየሞከሩ ይጯጯሀሉ፡፡ ውስጥ ያሉ ተሳፋሪዎችም እንዲሁ ይጮሀሉ፡፡ ሰውዬው አውቶብስ ውስጥ የነበረ ሲሆን ከሌላ ተሳፋሪ ስልክ ሰርቆ ለመውረድ ሲሞክር ነበርና ሾፌሩ በበር ዘግቶ የያዘው ተሳፋሪዎቹ ይጮሁ የነበረው የሾፌሩን እርምጃ በመደገፍ እንጂ ለሰውዬው በመጨነቅ አልነበረም፡፡ ሾፌሩ ሌባውን እንደዚያ አድርጎ በቀጥታ ወደ ፖሊስ ጣቢያ የወሰደ ሲሆን ፖሊስም የሾፌሩን ተግባር ደግፎታል፡፡ ሞባይል ስልክ የተሰረቀችው ተሳፋሪ ግን ክስ መመሥረት አለመፈለጓን ሜትሮ ዘግቧል፡፡
******************
ሐውልት የተሠራለት የዓለም ታዋቂ ድመት
ቶምቢሊ የተሠኘው በኢስታምቡል እንዲሁም በዓለም ድመት ወዳጆች ዘንድ ታዋቂ የሆነው ድመት ምናልባትም ሐውልት የተሠራለት ብቸኛው ድመት ሳይሆን እንደማይቀር ከወራት በፊት የወጣው የዘ ኢንዲፔንደንት ዘገባ አመልክቶ ነበር፡፡ ድመቱ ዚቨርቢይ የተባለውን የኢስታንቡል አካባቢዎች ያዘወትር የነበረ ሲሆን አቀማመጡም እንቅስቃሴውም ግርማ ሞገስ ያለው ስለነበር የብዙዎችን ትኩረት የሳበ ነበር፡፡ ከአንድ ወር ሕመም በኋላ ለሞተው ድመት በግርማ ሞገሱ ይንጎማለል በነበረበት ቦታ ሐውልት ይሠራለት ዘንድ 17,000 ፊርማ ተሰባስቦ በመጨረሻ የካዲኮይ ግዛት አስተዳደር ሐውልቱ እንዲሠራ ወስኗል፡፡
*********************
የሩሲያው ጋዜጣ ሚስቶች በድብደባ ብልዝ ሊኮሩ ይገባል አለ
የሩሲያ ታዋቂ ጋዜጣ የሆነው ኮሞሶዋልሳከያ ፕራቫዳ ጋዜጣ ሚስቶች በድብደባ ምክንያት አካላቸው ላይ የሚፈጠርን ብልዝ ሊኮሩበት ይገባል የሚል አስተያየት ማተሙን ዘ ኢንድፔንደንት ዘግቧል፡፡ ይህ ሕትመት የወጣው ፕሬዚዳንት ፑቲን ወንጀለኞችን የሚቀጣው ሕግ እንዲላላ ፊርማቸውን ማኖራቸውን ተከትሎ ነው፡፡ የአስተያየቱ ጸሐፊ ‹‹ባል ሚስትን ከደበደበ ይወዳታል ማለት ነው›› ይላል፡፡ እንደ አወዛጋቢው የሥነልቦና ባለሙያ ስቶሺ ካንዛዋ ዓነቶች ደግሞ ሚስቶቻቸውን የሚደበድቡት ወንዶች ወንድ የመውለድ ዕድላቸው ከፍተኛ እንደሆነ በድፍረት ለመተንተን ይሞክራሉ፡፡
*******************
ፍሬ ልቡና
በግሪክ የታሪክ (800 ዓ.ዓለም – 200 ዓ.ልደት) መዛግብትም ቢሆን ኢትዮጵያ በግንባር ቀደምትነት ከተቀመጡት አገሮች አንዷ ናት፡፡ ሆሜር ‹‹ኤልያድ›› በተሰኘው መጽሐፉ (800 ዓ.ዓ.) ጁፒተርና ዚየስ የተባሉት አማልክት ከኢትዮጵያውያንና ከሰማያዊ ሰዎች ጋር በፌሽታ ማሳለፋቸውን አስፍሯል፡፡ ሆሜር ከዚህም በተጨማሪ ፓሴይዶን የተባለው የምድር መንቀጥቀጥ አምላክ በኢትዮጵያ ውስጥ ታላቅነቱን በሚመለከት በተዘጋጀው በዓል ተካፋይ ሆኖ እንደቆየ አስፍሯል፡፡
ሆሜር ኢትዮጵያ ትሮይንና ዓረቢያን ትገዛ እንደነበረ አስመልክቶ ባሰፈረው ጽሑፉ ‹‹ቲቶነስ የተባለው የላኦመዶን ልጅ በእጅጉ ቆንጆ ወጣት እንደነበረና ኢዮስ የተባለችው ወጣት እንዳየችው በፍቅሩ ሥር እንደተንበረከከች፣ በዚህም ምክንያት ወደ ውቅያኖስ ከሚፈስ ወንዝ አጠገብ ባሠራችው ቤተ መንግሥቷ እንደወሰደችው፣ ከሱም መምኖና ኢማቲዮን የተባሉ ሁለት ወንዶች ልጆችን እንደወለዱ፣ ኢማቶን የዓረቢያ ንጉሥ ሲሆን ኢማቲዮን ደግሞ የጦር ኃይሉን ይዞ ወደ ትሮይ እንደዘመተና ከግሪኮች ጋር ሲዋጋም እንደሞተ ይገልጻል፡፡
ሔሮዶቱስ የተባለው ዕውቅ ግሪካዊ ጸሐፊም (490 – 425 ዓ.ዓ.) አሞኒያን (ሲዋ ኦየሲስ) የተባሉት የግብፅና በኢትዮጵያ በጋራ ሲገዙ የነበሩ ሲሆን ይኸው የዓለም የታሪክ አባት እየተባለ የሚጠራ ሰው ስለኢትዮጵያና ስለመልክዓ ምድራዊ አቀማመጧ አዘውትሮ ያነሳ ነበር፡፡ ለምሳሌ ‹‹ከደሴቱ ባሻገር አንድ ትልቅ ሐይቅ ይገኛል፡፡ በዚህም ሐይቅ ዳርቻ ዘላኖች ይኖራሉ፡፡ ሐይቁን ተሻግረው ሲሄዱም የዓባይን ምንጭ ያገኛሉ፡፡ በዚህ ወንዝ ለአርባ ቀናት በጀልባ ከተጓዙ በኋላ መርዌ የተባለችውን የኢትዮጵያ መናገሻ ከተማ ያገኛሉ፡፡ በዚህም አካባቢ ወርቅ በአያሌው ያገኛሉ፣ የትልልቅ ዝሆኖች ብዛት ቁጥር ያዳግታል፡፡ በደንም የተሸፈነ ነው፤›› በማለት ገልጿል፡፡
ሔሮዶተስ በእሱ ዘመን ስለነበሩት ኢትዮጵያውያን ሲገልጽ ወንዶቹ ረጃጅሞች፣ ውቦች፣ ከየትኛው አገር የበለጠ ዕድሜ የሚኖሩ ናቸው፡፡ ልብሳቸውም የነብርና የአንበሳ ቆዳ እንደነበር፣ ከዘንባባ፣ ተምር ዛፍ የተሠራ ከአራት ክንድ ያላነሰ ቁመት ያለው ደጋንና አጭር ሆኖ ጫፉ የብረት ሳይሆን የሾለ ድንጋይ የተሰካበት ቀስት እንደሚይዙ፣ የጦራቸው ጫፍም የሰስ (የሚዳቋ) ሹል ቀንድ የተሰካበት እንደነበረ፣ ወደ ጦርነት ሲሄዱም አካላቸውን በቀለም ያዥጎረጉሩ እንደነበር ያብራራል፡፡
ዚየስና ዲዮነሱስ የተባሉ አማልክት ያመልኩ እንደነበር የሚገልጸው ሔሮዶተስ ኢትዮጵያውያን ሲሞቱ እንደ ግብጾች ሁሉ አስከሬኑን በማድረቅ፣ ከደረቀ በኋላም ጀሶ በማጀል፣ ከዚያም በሕይወት ያለ አስመስሎ ቀለም በመቀባትና በተቦረቦረ ክቡር ድንጋይ ውስጥ በመክተትና እንደምሰሶ በመክተት ያስቀምጡት ነበር፡፡ በዚህም አስከሬኑ ስለማይሸትም በቅርብ ቤተሰብ ቤት ለአንድ ዓመት ያህል ይቀመጣል፡፡ በዚህ ጊዜም የመጀመሪያውን ሰብል፣ ፍሬ፣ በመስዋዕት መልክ ያቀርቡለታል፡፡ ከአንድ ዓመት በኋላም ከቤት ያወጡና ከከተማ አጠገብ ይተክሉታል፡፡
በኢትዮጵያውያንና በግብጾች መካከል ተመሳሳይ ባህል እንደነበር የሚገልጸው ሔሮዶተስ፣ ከሁሉም ነገዶች ኢትዮጵያውያን፣ ግብጻውያንና ኮለቺያውያን ብቻ ይገርዙ እንደነበርና ፊንቃውያንና ሶሪያውያንም የመግረዝን ባህል የተማሩት ከእነሱ መሆኑን እንደሚገልጹ ያብራራል፡፡
ከሔሮዶተስ ሌላ ዲዮዶረስ (60 ዓ.ዓ.) የተባለው የታሪክ ጸሐፊ የግብጽ ባህልና ሥልጣኔ ኢትዮጵያ እንደነበረች ያወሳል፡፡ ዘመናዊ የአርኪዮሎጂ ቁፋሮም ኢትዮጵያውያን እስከ ህንድ ድረስ ግዛታቸውን አስፋፍተው እንደነበር ያስገነዝባል፡፡ ይህ የታሪክ ጸሐፊ ኢትዮጵያውያን የመጀመሪያዎቹ ሰዎች መሆናቸውን የሚያረጋግጠው ከሌላ የመጡ ሳይሆኑ በአካባቢያቸው ነዋሪ በመሆናቸው እንደሆነ ያብራራል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ግብጾች ወደ ሌላ ቦታ በመዝመት የቅኝ ግዛት ያስፋፉት በኢትዮጵያውያን አሰማሪነት እንደሆነና ይህንንም ትዕዛዝ የሰጠው የአማልክት ሁሉ አምላክ የሆነው ኢትዮጵያዊው ኦሲረስ ነው፡፡
ኦሲረስ የተባለው አምላክ ወንዝን በክረምት ወራት በሚሞላበት ጊዜ አካባቢውን እንዳያጥለቀልቀው የወንዝ ዳርቻዎች ከፍ እንዲሉ የሚያደርግ፣ የሚፈስ ሲኖርም ማጥና ረግረጋማ አድርጎ የሚያቆይ አምላክ ነበር፡፡ የአማልክት ሁሉ አምላክ የሆነው ኦሲረስ፣ ከቀይ ባሕር ዳርቻ ጀምሮ እስከ ህንድ በመጓዝ ከተሞች እንዲቆረቆሩ አድርጓል፡፡
ሲኩለስ የተባለው የታሪክ ጸሐፊም እንደ ሔሮዶተስ ሁሉ ኢትዮጵያውያን ጥቁሮችና ሰፊ ግዛት የነበራቸው መሆኑን አስፍሯል፡፡ በዚህ ታሪክ ዘጋቢ መግለጫ መሠረት የኢትዮጵያ ግዛት ከምሥራቅ አፍሪካ ጀምሮ እስከ ዓረብ ባሕረ ሰላጤ ድረስ የተዘረጋ ነበር፡፡ ይሁንና በሲቹለስ ዘመን የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ከመርዌ ወርቅ ወደሚታፈስባት ምሥራቅ ተዛወረ፡፡ ይህም የአክሱም ዘመን በተቋቋመበት ጊዜ መሆኑ ነው፡፡
ስትራቦ (ከ63 ዓ.ዓ. – 24 ዓ.ል.) ደግሞ ባለው የሮማውያን ታሪክም በሰፊው የተወሳች ሲሆን በተለይም ገላውዲዮስ ፕቶለሚ (90-168) በአሌክሳንድሪያ ይኖሩ የነበሩ ሮማውያን ሕዝቡን ኢትዮጵያ ብለው ይጠሩት እንደነበር አስፍሯል፡፡ ይህም ጸሐፊ ኢትዮጵያውያን ተብለው የሚታወቁት ሕዝቦች ጥቁሮች፣ ጸጉራቸው ወፍራምና የተጠማለለ እንደነበር ያብራራል፡፡
የባይዛንታይን (700 ዓ.ል.) ጸሐፊዎች ደግሞ ኢትዮጵያ በመሬት ላይ አስቀድማ የተፈጠረች አገር እንደሆነችና እምነትና ሕግንም የመሠረተች እንደሆነች ይገልጻሉ፡፡
ይህም ሁሉ በአጭሩ ሲገለጽ በዘመናዊ የምድረ ከርስ ቁፋሮ የተገኙ እነሉሲን እንድናስብና በኢኮኖሚ፣ በወታደራዊ ኃይል የዳበረች፣ በተለይም በባህር ድንበሮቿ ከፍተኛ የባህር ትራንስፖርት ቴክኖሎጂ ተስፋፍቶ የነበረ መሆኑን ያስገነዝባል፡፡ የባህር ድንበሯም ኩሳዊው አፋር/አዳል እንደሆነ አያጠያይቅም፡፡
- ‹‹አፋር በታሪክ ዓምድ›› (2009)