መዝገበ ቃላቱ ፍየልን ከምድረ በዳ ፍየል የተለየ የቤት እንስሳ፣ ከብት ብሎ ይፈታዋል፡፡ ፍየል ከምሳሌያዊ ንግግርም አትጠፋም፡፡ ‹‹ፍየል ከመድረሷ ቅጠል መበጠሷ›› አንዱ ነው፡፡ ‹‹ሜ ባልኩ ፍየል ከፈልኩ፣ የፍየል ዓይን ወደ ቅጠል፤ የነብር ዓይን ወደ ፍየል›› ሌሎቹ ናቸው፡፡ አፈኛ፣ ለፍላፊ፣ ቀባጣሪ ሰው ሲያጋጥም ‹‹ፍየላፍ›› ሲባል ይሰማል፡፡
ከፍየል ዘር የሚመደበው ሚዳቋን በአንዳንድ መጻሕፍት ‹‹የበረሃ ፍየል›› ይባላል፡፡ በመጽሐፈ ምሳሌ (የ1980 ዓ.ም. ትርጉም) ሚስትን ‹‹እንደ ተወደደች ዋላ እንደተዋበችም የበረሃ ፍየል›› አድርጎ ይገልጻታል፡፡
በመጠበቂያ ግንብ እንደተጻፈው፣ በይሁዳ በረሃ የሚኖረውና አነስተኛ ቁጥር ያለው የፍየል መንጋ አዘውትሮ ወደ ዓይንጋዲ ምንጭ ይመጣል። ዓይንጋዲ በዚህ ጠፍ በሆነ ምድር የሚገኝ ብቸኛ አስተማማኝ የውኃ ምንጭ እንደመሆኑ መጠን፣ ለብዙ መቶ ዘመናት ለእነዚህ የበረሃ ፍየሎች አመቺ የውኃ መጠጫ ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል። እንዲያውም ዓይንጋዲ የሚለው ስም ምናልባት “የግልገል ፏፏቴ” ማለትም ሊሆን ስለሚችል ይህ ትንንሾቹ የበረሃ ፍየሎች አዘውትረው በዚህ ቦታ ይገኙ እንደነበረ የሚያሳይ ማስረጃ ነው።
ዛሬም ቢሆን በዓይንጋዲ እንስቷ ዋሊያ ወይም የበረሃ ፍየል ግርማ ሞገስ ተላብሳና ረጋ ብላ ተባዕቱን ፍየል በመከተል ወደ ውኃ ምንጭ ዓለታማውን ገደል ስትወርድ ማየት ይቻላል። በዚህ ጊዜ እንስቷ ዋሊያና ታማኝ ሚስት ያላቸውን ተመሳሳይነት ታስተውል ይሆናል። ረጋ ያለው ተፈጥሮዋና ውብ የሆነው አካሏ የእንስትነት ባሕርይዋን አጉልቶ ያሳያል። “የተዋበ” የሚለው ቃል የበረሃ ፍየል ያላትን ግርማ ሞገስና ድንቅ ውበት ለመግለጽ የገባ ይመስላል።
(ሔኖክ መደብር)