Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ያልተገላበጠ ማረሩ አይቀርም!

ሰላም! ሰላም! “ኧረ እኔስ ፈራሁ. . .” አለች አሉ ሚስቲቱ። ባል ተሰማዋ። በትንሽ ትልቁ እየተሰማን አንዳንዴ እኮ ባሎች ስንባል እናበዛዋለን። እና “እንዴት! እንዴት! ምን ለማለት ነው እኔ እዚህ ተቀምጨ ፈራሁ ማለት?” ይላል። ጀግንነት የፈታንበት መዝገበ ቃላችን ከተፈጥሮም ከፈጣሪም አራርቆን የለ?! እንዲያው እኮ።  ሚስት ነገሩ ወዴት እንደሄደ ገብቷት (መቼም ሴት ልጅ ብልህ ናት፣ ብልጠት ከሥልጣኔ ጋር አጉል ሰዓት ተገናኝተው አጉል እያደረጉዋት ተቸገረች እንጂ) “እህ ሰው አይፈራም? ይፈራል እኮ!” ብላ ባልን በሙሉ ዓይኗ ሳታየው መለሰችለት። ባል ቱግ ብሎ በአሽሙር፣ “ለነገሩ የሴት ወጉ ነው መፍራት፤” ብሎ ላይ ታች ሲገላመጥ ሚስት ቀበል አድርጋ፣ “ታዲያ ወንድነትስ ከየት የመጣ ይመስልሃል?” አለች አሉ። በአሉ እንጀምረው ብዬ እኮ ነው! አስኮብላይና ኮብላይ ልብ ለልብ ይተዋወቃል ይባላል። እኛን ያስቸገረን ግን ራስን ማወቅ ሳይሆን አይቀርም። እውነቴን እኮ ነው። ደርሶ ግንፍልተኛው አልበዛባችሁም? በበኩሌ ጦር ጠማኝ ባለፍ ባገደምኩበት እየተከተለ እየለከፈኝ ተቸግሬላችኋለሁ በተለይ ፈገግ ብላችሁ ተረጋግታችሁ፣ ወንዶች ደረት ነፍታችሁ፣ ሴቶች ቀጭ ቋ እያላችሁ ስንትጓዙ የተገኛችሁ እንደሆነ አበቃ።

የክፍለ ከተማ ጣጣ፣ የአገር ውስጥ ገቢ እንግልቱ፣ የተበጠበጠ ትዳሩ. . . ብቻ አንዱ ትዝ ብሎት፣ “ምናባታችሁ አቧራ ታቦናላችሁ? ኦባማ ነህ አንተ? ወይስ ኩዊን ኤልዛቤት ነሽ?” እያለ ለዱላ የሚጋበዘውን ፌዴራል ፖሊስም አልቻለውም አሉ። “እንዴት ያለ ነገር ነው ጃል? የሚያማርረን ነገር በዛና ለእያንዳዳችን አንድ አንድ ፕላኔት ሊሰጠን አማረን ይሆን?” ብዬ ከባሻዬ ልጅ ጋር ሳወራ የባሻዬ ልጅ ከት ብሎ ስቆ፣ “ኮንዶሚኒየም ሳይደርሰን ጭራሽ በስማችን አንዳንድ ፕላኔት?” ብሎ አላገጠብኝ። ቆይ ግን እኔ መቼ ይሰጠን አልኩ? ይኼን እኮ ነው የምላችሁ። ክብደት እንጂ መደማመጥ ቀንሰናል። እህ? ሰውዬው “እኔ እያለሁ ፈራሁ ምንድነው?” እንዳለው ሰው እያደር ተፈጥሯዊ የሆነውን ዑደት ሳይቀር በእሱ ዓይን ብቻ ዓይቶ እየተረጎመ መንገዱን ‘ዋን ዌዬ’ ብቻ አድርጎ መድረሻ አጣን። እንዲያው እኮ!

የቀጠሮዬ ሰዓት ደረሰ። ደንበኛዬ ከአውሮፓ የመጣች ጠና ያለች ወይዘሮ ነች። አገሩ ስለተቀያየረባት አንድም ከተማውን እያያዟዟርኩ ላሳያት፣ አንድም እጄ ላይ የነበረ ባለሦስት ፎቅ ዘመናዊ መኖሪያ ቤት መግዛት ስለፈለገች። በቤቱ ጉዳይ ወስና ስለነበር ብዙ አልተንከራተትኩም። በዕድገት ጎዳና ላይ ያለችውን አገራችንን (አዲስ አበባም ያው አገራችን ውስጥ ያለች አገራችን ናት) ማስቃኘቱ ግን አድካሚ ነበር። ወዲህ ስወስዳት ወዲያ ሳመጣት በሲኤምሲ፣ በመገናኛ፣ በቦሌ፣ በሜክሲኮ፣ በሳር ቤት. . . ሳዞራት ዋልኩ። “ውጭ አገር ነው ያለሁት ኢትዮጵያ?” ስትለኝ እኔ ደግሞ ዕድገቱን እያሞካሸች መስሎኝ፣ “ይኼውልሽ እንግዲህ የሚፈርስበት እየፈረሰበት የሆነለት እያለማበት ያደግንበት ሠፈር ጠፍቶናል፤” እያልኩ እለፈልፋለሁ። ለካ ሴትዮዋ ባለፍን ባገደምንበት ሁሉ በእንግሊዝኛ ፊደል ፈረንጅኛ መጠሪያዎችን እያነበበች በሽቃ ነው። “የት ሄዶ ነው ኢትዮጵያዊው ፊደል?” ስትለኝ ነው ነገሩ የገባኝ። (ምን አውቃለሁ ቋንቋችንም እንደ ቡናችን ኤክስፖርት መደረግ ጀምሮ ይሆናላ!)

ነገርን ነገር ያነሳዋል። ለነገረኛም ነገረኛ ያዝለታል። አላዝልን እያለ የተቸገርነው በበሽታች ልክ መድኃኒት ብቻ ነው። “በሽተኛው በዛ መድኃኒት አነሰው፤” ያለው ዘፋኙ ወዶ መሰላችሁ? ‘ማንም የወደደውን ያገባና የዘፈነ የለም’ እንዳትሉኝና እንዳልስቅ። ማንጠግቦሽ ሰሞኑን በገባች በወጣች ቁጥር፣ “ሐዋሳ ላንጋኖ ለሽርሽር ሄጄ ያየሁሽ. . .” እያለች ትሞዝቅላችኋለች። እኔ ደግሞ ‘መልዕክት ይኖረው ይሆን? ሽርሽር አማረኝ እያለችኝ ይሆን?’ እያልኩ መጨነቅ። አሥር ጊዜ የባንክ ደብተሬ ወጪና ገቢ ላይ ማፍጠጥ። ስቀንስ ስደምር የሆቴል፣ የምግብ፣ የትራንስፖርት፣ . . . ሳባዛ ሳካፍል መዋል። ግን ለምንድነው ዘንድሮ ሽርሽር ለመጓዝ ሲታሰብ ገና ድካም የሚተርፈን? የኢኮኖሚው ዕድገት ማሳያ ይሆን እንዴ? ቢጨንቀኝ እኮ ነው የምጠይቃችሁ።

ኋላ ታዲያ አስቤ አስቤ ሲደክመኝ የባሻዬን ልጅ “ምን አባቴ ባደርግ ይሻለኛል?” ብዬ ማማከር። ምን ይለኛል፣ “ቆይ ትንሽ ታገስ ማንጠግቦሽ ብቻ አይደለችም ሐዋሳ ላንጋኖ እያለች የምትዘፍነው። ሁሉም ነው፤” አለኝ። “እንዴት ሁሉም?” ስለው፣ “ኦባማ ሲመጡ ድፍን አዲስ አበባ ጭር ትላለች እየተባለ ስለሆነ፣ ጭር የመባባል ጉዳያቸውን ፈጽመው እስኪመለሱ መንግሥት ወጪያችንን ሸፍኖልን ወጣ ብለን ተናፍሰን እንምጣ እያልን ነው፤” አለኝ። በቃ ነዳጅ ብናወጣ ነው ብዬ “ታዲያ ምነው እንዲህ ያለውን የምስራች ቀደም አድርገህ ሳትነግረኝ” ስለው “ምን ይታወቃል? ‘የህዳሴው ግድብ ሳይጠናቀቅ በቦናፓርቲዝም ልታጨመላልቁን ነው ወይ?’ የሚል መልስ ከመጣስ ብዬ ነዋ፤” አይለኝ መሰላችሁ? ጉድ እኮ ነው እናንተ! “ፅድቁ ቀርቶብኝ በቅጡ በኮነነኝ” አለች አሉ (ማን ነች ግን እሷ?)። “እኔ እኮ ነዳጅ ያወጣን መስሎኝ ነው። በመንግሥት በጀት ነው ላንጋኖን ያለማችኋት?” እለዋለሁ፣ “ተው እንጂ በማለም መብታችንማ አትምጣ፤” ብሎ ተቆጣኝ። ኧረ እንዴት ነው ነገሩ ይኼ ዓለም እያደር የህልም ዓለም ሆነ እኮ ጎበዝ!

አቤት ቻፓና ነገር ቶሎ ቢገቡልኝ። ይኼኔ  ልማታዊ ባለሀብት ሆኘ ሕንፃ ሠርቼ በእንግሊዝኛ ሰይሜው ነበር። ግን እንኳንም አንዳንዱ ምኞት በነበር የሚቀር ሆነ። ደንበኛዬ ነገሩን ችላ ብላ ማለፍ አቃታት። ጭራሽ ‘ፍሬንች ኪስ’ የሚል ስያሜ ስታይማ ራሷን ስታ እጄ ላይ ወደቀች። እኔ የጠየቅኩት ጥያቄ አንድ ነው።  ‘ከዚህች ሴትዮና ከእኔ ጤነኛው ማን ነው? አጥወልውሏት ራሷን ስታ እስክትወድቅ መያዣ መመለሻ  ያጣው የማንነት ቀውስ ለእኔ ምንም ያልመሰለኝ ምን ሆኜ ነው?’ ብዬ ውሎ አድሮ ባሻዬን ስጠይቃቸው፣ “ዓይን እኮ ራሱን አያይም። ቅርብ ነሃ። ተላምደኸው እየኖርክ ነው። ገና ብዙ ጉድ የሚሠራን ይኼው መላመድ ነው። ጠብቅ ባሻዬ ምን አሉ ትላለህ፤” ብለውኛል። እናም ከመልመድ ለመሸሽ መሰደድ አለብን? ሳይቃጠል በቅጠል እያለ? ለስደትስ የሚገፋፋን ይኼ እንደሆን ተጠንቷል? ወይስ ስደትን በተመለከተ ሕገወጥ ደላሎች ብቻ ናቸው ተጠያቂዎቹ? ‹‹What is Wrong with us?›› ካላልኩ ጆሮም አላገዘኝ መሰል!

እንሰነባበት። አልፎ አልፎ ቢሆንም ምርጫ እንደደረሰለት የፖለቲካ ፓርቲ ዕቁብ ከተበላ የምጣደፈው ነገር አለኝ። ማንጠግቦሽ ይኼን አዝጋሚነት እንዳሻሽል ደጋግማ ብትነግረኝም የምርጫ ሰሞን የመቀስቀስ ዝግመኛ ልምዳቸውን እንዲተው ስንነግራቸው፣ የማይሰሙንን ፖለቲከኞች ይመስል አልሰማኋትም። በረባ ባረባው በጭቅጭቅና በአጉል ጥርጣሬ የጠፋውን ጊዜ የሚክስ ‘ኮሚሽን’ አስገኝቶልኝ ካሚዩኑ ሲሸጥ ስልኬ ጠራ። የጠፋ የሃምሳ ብር ካርዴን አግኝተውልኝ መስሎኝ ሳነሳው ከዓመት በፊት የጎረቤታችን ልጅ የቁጠባ ቤቶች ዕጣ ደርሶት ስለነበር ፌሽታ መደረጉን ሰማሁ። የባሻዬ ልጅ፣ “ዛሬ ቢራ በነፃ የምንራጭበት ቦታ ተገኝቷል፤” ሲለኝ ወደ ሠፈሬ ከነፍኩ። እኔ ስደርስ ዕድለኛው ወጣት ከሥራ ሲመለስ አንድ ሆነ። ቤቱ እስኪገባ እንደ መሲሁ ዘንባባ ተነጠፈለት። በዕልልታው ድምቀት መንደራችን በፌዴራል ፖሊስና እሳት አደጋ ተከበበች። ይኼን ያየ አንድ ተናጋሪ፣ “ይኼኔ የአንዳችን ቤት እሳት ይዞት ቢሆን ነገም አይመጡ፤” አለ። ሌላው ቀበል አድርጎ፣ “ምን ታውቃለህ በቅናት ለሚቃጠሉት ከሆነስ የመጡት?” ይለዋል። የባሻዬ ልጅ “ስማ! ዝም ብለህ አዳምጥ!” ይለኛል። ነገሩ ሌላ መስሏቸው ሠግተው የነበሩ ሰላም አስከባሪዎች ጫጫታው በሌላ ጎኑ ጥሩ ቅስቀሳ መሆኑ ስለገባቸው የደስታው አድማቂ ወደ መሆን ተገልብጠዋል። ‹አትገለባበጡና ዝም ብላችሁ ከንፈር ንከሱ!› ያለው ማን ነበር?

ሥነ ሥርዓቱን ለማደፍረስ የሚያስቡ እኩዮችን ከአፍራሽ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ የሚያስጠነቅቁም አሉ፡፡  ጭብጨባውና ዕልልታው የቀዘቀዘ የመሰላቸው አንዲት ወይዘሮ ደግሞ “አዳሜ በደንብ አታጨበጭቢም? ነግሬያለሁ የዛሬ አምስት ዓመት እንኳን ለቤት ለጭብጨባውም ላትቆሚ ትችያለሽ፤” ይላሉ። “ምንድነው እርስዎ ደግሞ፣ የሚያስፈራሩን? ከዚህ በላይ እጃችን ይቆረጥ?” ሲል የፈራቸው፣ ያመናቸው ደግሞ “እንዴ ሌላው ዙር ዕጣ የሚወጣው የዛሬ አምስት ዓመት  ነው ማለት?” ሲል ግራ ተጋብቶ ግራ ያጋባል። እንዲያው በአጠቃላይ በትንሽ ትልቁ ነገሩን ፖለቲካዊ አንድምታ ሊሰጠው የማይጥር የለም። ግርግሩ በረድ ብሎ እኔና የባሻዬ ልጅ ወደ ዕድለኛው ቤተሰብ ቤት ስንገባ ከየት መጡ ሳንላቸው ባሻዬ ከኋላችን ከች ብለው፣ ‹‹ትሰማላችሁ ሰው የሚለውን? ወይ ዕጣና ቁጠባ! የማያናግረን የለም እኮ፤” ብለውን ወደ ጓደኞቻቸው ተቀላቀሉ። እኛም ተገኘ ብለን ልንጋተው የነበረው ቢራ ገና ሁለተኛውን እንዳጋባን ራሳችን ላይ ወጣ። ‹‹እኛ ነገር ስንበላ ሌላው እየተገለባበጠ ስንት ታሪክ ሠራ?›› የሚል ድምፅ ቢሰማኝም ራስ ምታት ለቀቀብኝ፡፡ ለካ ዓለም እንዲህ ናት!   ያልተገላበጠ ማረሩ አይቀርም እንዲሉ! መልካም ሰንበት!  

 

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት