Wednesday, February 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህል​የእሳት ተራራ - የጨው ምድር

​የእሳት ተራራ – የጨው ምድር

ቀን:

ከፍታው 613 ሜትር የሆነው የኤርታአሌ እሳተ ገሞራ ይገኝበት የነበረው ሥፍራ ተዳፍኖ በቅርብ ርቀት ሌላ እሳተ ገሞራ የመፈንዳቱ ዜና የተሰማው ከሳምንታት በፊት ነበር፡፡ ዘወትር ያለማቋረጥ ህያው በመሆኑ ዝናው በዓለም የናኘው እሳተ ገሞራው ተዳፍኖ ለምልክት ጭስ ብቻ ሲቀር፣ አዲሱ እሳተ ገሞራ ከአፍ እስከ ገደፍ ሞልቶ መፍሰስ መጀመሩም ተገልጿል፡፡ ከእሳተ ገሞራው በጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቀት በሚገኘው ማኅበረሰብ ላይ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል የሚል ሥጋትም ነበር፡፡ በፍንዳታው ሰሞን በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ የመሬት መንቀጥቀጦች ከአዲሱ እሳተ ገሞራ ጋር ተያያዥነት ይኖራቸው ይሆናል ሲባልም ነበረ፡፡

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና የአፋር ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋዜጠኞችን ወደ አካባቢው የጋበዙት የአዲሱ እሳተ ገሞራ ፍንዳታ ዜና ትኩስ ሳለ ሲሆን፣ ከአዲስ አበባ ሰመራ ከዛም ወደ አፍዴራ በመቀጠልም ወደ ኤርታአሌ የተጓዘው ቡድን ወደ አዲሱ እሳተ ገሞራ ያቀናው አመሻሽ ላይ ነበር፡፡ ወደ ኤርታአሌ በሚወስደው አሸዋማው የመንገዱ ክፍል የመኪና ጎማ ሳይዋጥ ለማለፍ በፍጥነት ማሽከርከር የግድ ነበር፡፡ በአካባቢው ነዋሪዎች መሪነት ወደ ኤርታአሌ የሚጓዙ ሰዎች ዝግጅት የሚያደርጉበት ካምፕ ከደረስን በኋላ ዘጠኝ ኪሎ ሜትር የሚሆን የእግር ጉዞ ይጠብቀናል፡፡  

አስጎብኚዎች ወደ ተዳፈነው ኤርታአሌ የሚወስደውን መንገድ በደንብ ስለሚያውቁት ጎብኚዎችን ወደ ሥፍራው ለማድረስ በተጠንቀቅ ይጠባበቃሉ፡፡ ጎብኚዎች በእግራቸው ሲሄዱ ዕቃቸውን የሚያጓጉዙላቸው ግመሎች ያዘጋጃሉ፡፡ እሳተ ገሞራው የሚገኘው ኢትዮጵያና ኤርትራን የሚያዋስነው ድንበር አካባቢ በመሆኑ የጎብኚዎችን ደኅንነት የሚጠብቁ ልዩ ኃይሎችም አሉ፡፡ ከዚህ ቀደም በአካባቢው የተገደሉና የታገቱ ቱሪስቶች እንደነበሩ ይታወሳል፡፡ የእጅ ባትሪና ተራራውን ስንወጣ የሚገጥመንን ጭስ ለመከላከል የሚረዳ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ተሰጥቶን፣ ዕቃችን በግመል ተጭኖ፣ በመንገድ መሪዎችና በልዩ ኃይል ታጅበን ጉዞ ጀመርን፡፡ 

ወደ አዲሱ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ የሚወስደውን መንገድ እንደ ቀድሞው እሳተ ገሞራ ያልተላመዱት መሪዎቻችን መንገዱን ለማግኘት መቸገራቸው የታወቀው ወደ ሁለት ሰዓት ገደማ በእግር ከተጓዝን በኋላ ነበር፡፡ መንገዱን ለማግኝት የተደረገው ጥረት ተጓዡን ወደ ፊትና ወደ ኋላ ያመላለሰ ነበር፡፡ አሸዋማው መንገድ በአባጣ ጎርባጣ ድንጋይ ሲተካ የተጓዦች አቅምም ይፈተሽ ጀመር፡፡ ቀጥሎ የገጠመን በሹል ድንጋዮች የተሞላ አካባቢ ሰው የቱን ድንጋይ ረግጦ ወደ የቱ እንደሚሄድ ግራ ያጋባል፡፡ ጭራሽ   የእሳተ ገሞራው ፍሳሽ የሆነው ያልደረቀ ላቫ ጋር ደረስን፡፡ ላቫው ስላልደረቀ ሲረገጥ ይፈረከሳል፡፡ በሰዓታት ጉዞ የተዳከሙ ተጓዦች በተፈረከሰው ላቫ ይገቡ፣ ይደናቀፉና ይወድቁም ጀመር፡፡ የአብዛኞቻችን ባትሪ ኃይል መዳከሙ ደግሞ ነገር አከበደ፡፡

መሪዎቹና ልዩ ኃይሉ ወደ እሳተ ገሞራው የሚወስደውን መንገድ ለማግኘትና ምቹ መንገድ ለመምረጥ ከተጓዦች ቀድመው ለደቂቃዎች ይጓዙና ወደ ኋላ ይመለሳሉ፡፡ በዚህ መልኩ ትክክለኛውን መንገድ ለማግኝት መኳተናቸውን ለሰዓታት ቀጠሉ፡፡ ጎን ለጎን የደከሙ ተጓዦችን የማበረታታትና የመደገፍ ሥራም ያከናውናሉ፡፡ በስተመጨረሻ ወደ አዲሱ እሳተ ገሞራ መቃረባችንን የሚያመላክተው የእሳተ ገሞራው ጢስ ታየ፡፡

ከርቀት የተመለከትነው እሳተ ገሞራ ተራራው ጫፍ ድረስ ሞልቷል፡፡ አልፎ አልፎ ወደ ላይ የሚወጣው የእሳት ፍንጣቂም የተመልካችን ቀልብ ይስባል፡፡ የቆምንበት ተራራ ነፋሻ አየርና በቅርብ ርቀት ያለው የሚንቀለቀል እሳት ተቃርኖ ተመልካች የተፈጥሮን ሚስጥር ቆም ብሎ እንዲያጤን ያደርጋል፡፡

እሳተ ገሞራውን ከተመለከትን በኋላ ምግብ፣ መጠጥና ማረፊያ በግመሎች ተጭኖ ስለሚመጣ እዚያው አካባቢ አድረን ንጋት ላይ ወደ ካምፑ የመመለስ ዕቅድ ነበረን፡፡ በምናርፍበት ቦታ ከኛ ቀደም ብለው ወደ እሳተ ገሞራው ካቀኑት የክልሉ ፕሬዚዳንትና ሌሎችም አመራሮች ቡድን ጋር ለመቀላቀል ታስቦ ነበር፡፡ ይህ ሊሆን ስላልቻለ ወደ ካምፑ መመለስ እንዳለብን ተገለጸልን፡፡ የመልሱ ጉዞ እንደ መጀመርያው ፈታኝ ነበር፡፡ በጥቂት ደቂቃዎች ልዩነት አረፍ ከማለት በዘለለ በአንድ ቦታ ብዙ መቆየት አልተቻለም፡፡ እንደ አመጣጣችን ሁሉ እርስ በርስና በልዩ ኃይልም እየተደገፍን ከመመለስ ሌላ አማራጭ አልነበረም፡፡ የማይደረስበት አገር ይመስል ከራቀው ካምፕ የተመለስነው ከአሥር ሰዓታት ጉዞ በኋላ ነበር፡፡ በጉዞው ወድቀው እጃቸውና እግራቸው የቆሰለባቸው ነበሩ፡፡ ያልደረቀው ላቫ ያስከትል ከነበረው ጉዳት አንፃር ብዙዎች ተርፈዋል ማለት ይቻላል፡፡ በዚህ ረገድ ክልሉ ጉዞውን ከማዘጋጀቱ በፊት ስለ አዲሱ እሳተ ገሞራ መንገድ አስቀድሞ ማጥናት ነበረበት፡፡ ቀደም ባሉት ጊዜያት እንደሚደረገው ስለ እሳተ ገሞው የሚያጠና ቡድን አስቀድሞ በሂሊኮፕተር መላክም ይቻል ነበር፡፡ በኃላፊነት ይህንን ያደረገ አካል ባለመኖሩ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ማሰብ ይከብዳል፡፡

የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊዎችና ሌሎችም የአካባቢው ነዋሪዎች እንደገለጹልን ወደ ኤርታአሌ የሚወስደው ትክክለኛ መንገድ ሰባት ኪሎ ሜትር ሲሆን፣ ጉዞው የወሰደብንን ያህል ሰዓታት አይፈጅም፡፡ መሪዎቹ መንገድ ባይጠፋባቸውም ውጣ ውረዱ አይገጥመንም ነበር፡፡ ካምፕ አድረን ንጋት ላይ በርሀይሌ ከተማ እረፍት አድርገን በነጋታው ከእሳት ተራራ ኤርት አሌ ወደ ጨው ምድር ዳሎል አቀናን፡፡ የሰው ዓይን መመልከት እስከሚችልበት ጥግ ድረስ በጨው ግግር የተሸፈነው ምድር በዋናኛነት በአዮዳይዝድ ጨውና የፖታሽየም ምርቱ ይታወቃል፡፡ የአረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቡናማ፣ ሰማያዊና ሌሎችም ኅብረ ቀለማት ውህዱ  እንኳን ደህና መጡ እያለም ይቀበላል፡፡

ከኅብረ ቀለማቱ ውበት በላይ በማዕድን ሀብቱ የሚታወቀው ዳሎል፣ ውስጡ የታመቀው የእሳተ ገሞራ ሙቀት ፍል ውኃ ሆኖ ይወጣል፡፡ እንደ ‹‹ሌላ ፕላኔት›› የሚታየው አካባቢው እስከ አምስት ኪሎ ሜትር ጥልቀት ያለው ጨው ይገኝበታል፡፡ ሙቀቱም እስከ 48 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ የሚደርስበት ወር አለ፡፡ ከዳሎል ጋር በተያያዘ የአፍዴራ የጨው ግግርንም ማንሳት ይቻላል፡፡ እንደ ዳሎል አዮዳይዝድ ባይሆንም ከፍተኛ የጨው ክምችት ይገኝበታል፡፡

የአፋር ክልል በርካታ ተፈጥሯዊ ሀብቶች ቢኖሩትም፣ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ቱሪስቶች ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጧቸውን ዳሎልና ኤርታአሌን ለጋዜጠኞችና ለአካባቢው የአመራር አካላት ከጥር 25 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ለአምስት ቀናት አስጎብኝቷል፡፡

አዲሱ እሳተ ገሞራ

‹‹የሚጨስ ተራራ›› ወይም ‹‹የገሀነም መግቢያ በር›› በሚል ስያሜ የሚታወቀው ኤርታአሌ ከ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ለረዥም ዓመታት የቆየ እሳተ ገሞራ በመሆን ግንባር ቀደምነቱን ይይዛል፡፡ አዲሱ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ በናሳ ኧርዝ ኦብዘርቫቶሪ ሳይት የተለቀቀው ጥር 19 ቀን 2009 ዓ.ም. ሲሆን፣ ከጥር 13 ጀምሮ እንደነበረ ተመልክቷ፡፡ አዲሱ እሳተ ገሞራ ሲፈነዳ ካምፑ አካባቢ ጭስ መታየቱም ተዘግቧል፡፡ ከቀደመው እሳተ ገሞራ ወደ ሰባት ኪሎ ሜትር ገደማ የሚሆን ርቀት ላይ 250 ሜትር ዝቅ ብሎ እንደሚገኝም ተገልጿል፡፡ ዘገባው እንደወጣ ወደ እሳተ ገሞራው መጠጋት እንደማይቻል ተገልጾ ነበር፡፡ በዚህም ሳቢያ የአካባቢው ነዋሪዎችና ሌሎችም ሥጋት ላይ ወድቀው ነበር፡፡ በተለይም የአካባቢው ነዋሪዎች የእሳተ ገሞራው ፍንጣቂና ጭሱ በሰውና እንስሳት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ እንዲሁም ፍንዳታውን ተከትሎ የመሬት መንቀጥቀጥ ሊከሰት እንደሚችል ገምተዋል፡፡

አፍዴራ ሐይቅ አካባቢ ምርምር ለማድረግ ወደ ቦታው አቅንተው ያገኘናቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ምኅዳር ትምህርት ቤት ስትራክቸራል ጂኦሎጂስት ፕሮፌሰር ተስፋዬ ኪዳኔ የእሳተ ገሞራውን መንስኤ ሲገልጹ፣ ‹‹የኤርታአሌ እሳተ ገሞራ የቀይ ባህር ወገብ አካል ሲሆን፣ ሒደቱ ከ30 ሚሊዮን ዓመት ጀምሮ እየተካሄደ ነው፡፡ የዓረብ ፕሌት ከአፍሪካ ፕሌት መለያየት የጀመረው ከ30 ሚሊዮን ዓመታት በፊት ቢሆንም ሙሉ ለሙሉ ስላልተለያየ ተያይዞ ይገኛል፡፡ ሆኖም በየዓመቱ 20 ሚሊ ሊትር ይለያያል፡፡ እሳተ ገሞራውም በመለያየት ሒደቱ የተከሰተ ነው፤›› ይላሉ፡፡

በእሳቸው ገለጻ፣ ከኤርታአሌ ሥር ያለው የላቫ ወይም የማግማ ቋት የእሳት ሐይቅ ሠርቶ ይታይ ነበር፡፡ ይህ ሐይቅ ቦታውን ሲቀይር በቀድሞው ቦታ ጢስ ብቻ ይታያል፡፡ ‹‹ከ2005 ዓ.ም. ጀምሮ በደቡብ አቅጣጫ የሚገኘው እሳተ ገሞራ ንቁ የነበረ ሲሆን፣ አሁን በስተደቡብ ምሥራቅ ሌላ መከፈቱ ልዩ ያደርገዋል፤›› ይላሉ፡፡ እሳተ ገሞራው አንዳንዴ ሞልቶ የሚንተከተክ አንዳንዴም ታች የሚቀር ሲሆን፣ አዲሱን እሳተ ገሞራ በጎበኘንበት ወቅት እስከ ጫፍ ሞልቶ ነበር፡፡ ከእሳተ ገሞራው ጋር በተያያዘ ስላሉ ሥጋቶች የጠየቅናቸው ፕሮፌሰር ተስፋዬ፣ ‹‹ኤርታአሌ በከፍተኛ ጉልበት ስለማይፈነዳ እሳተ ገሞራው በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ያለ አይመስለኝም፤›› ሲሉ መልሰዋል፡፡ እሳተ ገሞራው ሞልቶ ቢፈስም በተራራው አካባቢ የተወሰነ በመሆኑ የአካባቢውን ነዋሪ እንደማያሠጋም ያክላሉ፡፡

አዲሱ እሳተ ገሞራ በፊት ከነበረው ጉድጓድ ዝቅ ማለቱ ከሥር ወዳለው የእሳተ ገሞራ ቋት እየቀረበ መሄዱን እንደሚያመላክት ይገልጻሉ፡፡ እሳተ ገሞራው ፍሳሽ  ክፍተት ባገኘበት ቦታ እንደሚወጣና በፊት የወጣበት ቦታ ያህል የመድረስ ጉልበት እንደሚያንሰውም ያስረዳሉ፡፡ በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች በእሳተ ገሞራው ፍንዳታ ሰሞን የተከሰቱ የመሬት መንቀጥቀጦች ከፍንዳታው ጋር የተያያዙ ናቸው የሚል መላ ምት ተደምጧል፡፡ ፕሮፌሰሩ እንደሚሉት፣ በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች የሚነሳው የመሬት መንቀጥቀጥና የእሳተ ገሞራው ፍንዳታ አይገናኝም፡፡ ‹‹የምሥራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ ሐዋሳ ካለው የመሬት መንቀጥቀጥ ጋር ግንኙነት የለውም፡፡ ሁለቱም የተለያየ ስምጥ ሸለቆዎች ናቸው፤›› ይላሉ፡፡ ከእሳተ ገሞራው አካባቢ የሚነሱት ሰልፈር ዳይኦክሳይድና ካርቦን ዳይኦክሳይድ መርዛማ ቢሆኑም፣ ከኤርታአሌ አካባቢ ወጥተው ከአየር ከተቀላቀሉ በኋላ በአካባቢው ነዋሪ ላይ ጉዳት እንደማያደርሱም ያብራራሉ፡፡

ፕሮፌሰር ተስፋዬ በአሁኑ ወቅት ስለ አፍዴራ ሐይቅ ጥልቀትና ቅርፅ እየተመራመሩ ሲሆን፣ ከእሳተ ገሞራ ሰንሰለቶች ማለትም ከኤርታአሌ፣ ታታሌና አላይታ ጋር ስላለው ግንኙነትም ያጠናሉ፡፡ የኤርታአሌ እሳተ ገሞራ ፍንዳታ እንደተሰማ የሥነ ምኅዳር ትምህርት ቤት በሂሊኮፕተር ተጉዞ ጥናት ለማድረግ በዝግጅት ላይ እንደነበረም ያስረዳሉ፡፡ ከኤርታአሌ ቀጥሎ ስለ ዳሎል ሲገልጹ፣ የዳሎል ሆት ስፕሪንግ (ፍል ውኃ) ይዞ እንደሚወጣ ይናገራሉ፡፡ ቢጫው ቀለም ሰልፈሪክ አሲድ ሲሆን፣ ሰልፈሩ ለኦክስጅን ሲጋለጥ ቡናማው ቀለም ይፈጠራል፡፡ በሁለቱ የተፈጥሮ ሀብቶች ላይ በየጊዜው የሚታየው ተፈጥሯዊ ለውጥ ደግሞ በቱሪስት መስህብነቱ ይታወቃል፡፡

ቱሪዝም በኤርታአሌና ዳሎል

ኤርታአሌና ዳሎል በአፋር ክልል ብቻ ሳይሆን በአገሪቱም ተጠቃሽ የቱሪስት መዳረሻዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ ቱሪዝሙ ምን ያህል አድጓል? የሚል ጥያቄ ማንሳት ያስፈልጋል፡፡ ከአካባቢው ሀብት አንፃር ቱሪስቶችን በመሳብ፣ የአካባቢውን ማኅበረሰብና አገሪቱንም ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ በቂ ሥራ ተሠርቷልን? የሚለውም ተያይዞ ይነሳል፡፡ ለቱሪዝም ፍሰት መጨመር በዋነኛነት የሚያስፈልገው የመሠረተ ልማት ዝርጋታና አካባቢውን የማስተዋወቅ ሥራ ሲሆን፣ በጉብኝታችን ወቅት ሁለቱ ዘርፎች ብዙ እንደሚቀራቸው አስተውለናል፡፡

በመሠረተ ልማት ዝርጋታ ረገድ አብዛኛው አካባቢ መንገድ ቢኖረውም፣ ጠጠር መንገዶችም አሉ፡፡ በቱሪስት መዳረሻ አካባቢዎች ለቱሪስቶች አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ውስንነትም ይስተዋላል፡፡ የአፋር ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ መሐመድ ያዩ እንደሚናገሩት፣ ካለፉት ዓመታት አንፃር የክልሉ የቱሪስት ፍሰትና ገቢውም እየጨመረ መጥቷል፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች ስለ ቱሪዝም ጠቀሜታ በመገንዘብ አገልግሎት ሰጪ ተቋሞች በመክፈት ተሳታፊ ከመሆናቸው ባሻገር የቱሪስት ማረፊያዎች በማዘጋጀትም ጅማሮዎች አሉ፡፡ ቢሆንም ግን ዘርፉ ሙሉ በሙሉ ጎልብቷል ለማት እንደማይቻል ይገልጻሉ፡፡

እንደ ምሳሌ የሚጠቅሱት የአገር ውስጥ ጎብኝዎች ቁጥር አነስተኛ መሆኑን ነው፡፡ የአገር ውስጥ ቱሪዝምን ለማሳደግ በነፃ የሚጎበኝበት ዕድል መፍጠራቸውን አቶ መሐመድ ያስረዳሉ፡፡ በተያያዥም የአካባቢው የቱሪስት መስህቦችን በስፋት የማስተዋወቅ ሥራ በመሥራት ከቱሪዝም የሚገኘውን ገቢ ማሳደግ ይቻላል፡፡ የመሠረተ ልማት አለመሟላት በጎብኚዎች ላይ ተፅዕኖ እንደሚፈጥር ገልጸው፣ እየተሠሩ ያሉ መንገዶች ሲጠናቀቁ ባለሀብቶች በቱሪስት መዳረሻ አካባቢዎች አገልግሎት መስጫዎች ለመሥራት እንደሚነሳሱ ይናገራሉ፡፡

አዲሱ የኤርታአሌ ፍንዳታ የተመራማሪዎችንና ጎብኚዎችን ትኩረት ይስባል የሚል እምነት ያላቸው ኃላፊው፣ እሳተ ገሞራው ከፈነዳበት ጊዜ ጀምሮ ስለ ሁኔታው በማስተዋወቅ ላይ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡ በሚመጣው ዓመት ክስተቱን ለመመልከት ወደ አካባቢው የሚሄዱ ጎብኚዎች ቁጥር እንደሚጨምርም ተስፋ ያደርገጋሉ፡፡ ቱሪስቶች በሥፍራው ከደረሱ በኋላ የቆይታ ጊዜያቸውን ማራዘም ሌላው ጉዳይ ነው፡፡ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ሲሟላ ቱሪስቶች ረዘም ላለ ጊዜ የመቆየት ፍላጎት ይኖራቸዋል፡፡ ‹‹አሁን በክልሉ ቱሪስቶች ከአምስት እስከ ስድስት ቀን ይቆያሉ፡፡ የተመቻቸ ማረፊያ ሊኖር የቆይታ ጊዜ ስለሚራዘም በመሠረተ ልማት ዝርጋታ ብዙ ሥራ ይጠብቀናል፤›› ይላሉ፡፡

የአፋር ክልል አፈ ጉባዔ አቶ መሐመድ ከድር እንደሚናገሩት፣ በአካባቢው ትልቅ ችግር የሆነው መንገድ እንደመሆኑ ችግሩን ለመቅረፍ የመንገድ ቅየሳ የተደረገላቸው ቦታዎች አሉ፡፡ ከነዚህም ወደ ኤርታአሌ የሚወስደው ጠጠር መንገድ ይጠቀሳል፡፡ በእርግጥ እስከ ካምፑ መዳረሻ ያለውን የአሸዋ መንገድና ከካምፑ እስከ ኤርታአሌ የሚገኘውን ተራራማ መንገድ አስፋልት ለማድረግ የአካባቢው ተፈጥሯዊ አቀማመጥ አያመችም፡፡ ከዛ ውጪ ያለውን ጠጠር መንገድ ግን የመሥራት ዕቅድ እንዳለ የተናገሩት አቶ መሐመድ፣ ቱሪስቶች ከባድ ተሞክሮ (አድቬንቸር) ስለሚፈልጉ መንገዱ መሠራት የለበትም የሚለውን አስተያየት አያይዘው ያነሳሉ፡፡

‹‹የመንገዱ ወጣ ገባነትን ቱሪስቶች ይወዱታል፤›› የሚል የመከራከሪያ ነጥብ ያላቸው ቢኖሩም፣ መንገድ መሥራት በሚቻልበት ቦታ ሁሉ መገንባት እንዳለበት አፈ ጉባዔው ይገልጻሉ፡፡ የባህልና ቱሪዝም ኃላፊውም ሐሳባቸውን ተጋርተው፣ ‹‹አገር ለቱሪስት ብቻ ሳይሆን ለዜጋውም ምቹ መሆን አለበት፤›› ይላሉ፡፡

ማኅበረሰብ አቀፍ ቱሪዝም

በቱሪስት መዳረሻ አካባቢዎች ያለውን ማኅበረሰብ ከዘርፉ ተጠቃሚ የማድረግ ነገር ቸል የሚባል አይደለም፡፡ ማኅበረሰቡን በቱሪዝም ማሳተፍ የቱሪስት ሀብቶችን እንዲጠብቁም መንገድ ይከፍታል፡፡ በኤርታአሌ፣ በዳሎልና አፍዴራ ሐይቅ አካባቢ በማኅበር የተደራጁ የአካባቢው ነዋሪዎች ለጎብኚዎች የተለያየ አገልግሎት ሲሰጡ ተመልክተናል፡፡ የቱሪስቶች ማረፊያ በማዘጋጀት፣ አካባቢውን በማስጎብኘት፣ ግመል በማከራየት፣ በፅዳትና በሌሎችም ዘርፎች የተሰማሩ ነዋሪዎች አሉ፡፡

የአፋር ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የኢንቨስትመንትና ፓርኮች ልማት የሥራ ሒደት ባለቤት አቶ አህመድ አብዱልቃድር እንደሚናገሩት፣ ባለሀብቶች በአካባቢው ለቱሪስት ማረፊያ እንዲያዘጋጁ ከማበረታታት በተጨማሪ ነዋሪዎችም ከቱሪዝሙ እንዲጠቀሙ ይደረጋል፡፡ ኤርታአሌ አካባቢ ለቱሪስቶች በ600 ብር ግመል የሚያከራዩና በ250 ብር መንገድ የሚያመላክቱ ነዋሪዎች (አስጎብኚዎች) ገጥመውናል፡፡ አፍዴራ ሐይቅ አካባቢ በድንኳን ለቱሪስቶች ማረፊያ በማዘጋጀት የሚጠቀሙም ይጠቀሳሉ፡፡ በተለያየ ቢዝነስ የተሰማሩት የአካባቢው ነዋሪዎች ከመስከረም እስከ ሚያዝያ ባለው ወቅት ገቢ የሚያገኙ ሲሆን፣ ከሚያዝያ በኋላ ሙቀቱ ከፍተኛ ስለሆነ ጎብኚዎች አይኖሩም፡፡

የቱሪስት መዳረሻ ጥበቃ

አፋር ክልልም ይሁን አገሪቱ ከቱሪዝም የሚያገኙት ገቢ ከቱሪስት መዳረሻ አካባቢዎች ጥበቃ ጋር ቀጥተኛ ተዛማጅነት አላቸው፡፡ ከዓለም ዝቅተኛ ቦታ የሆነው ዳሎል ልዩ ልዩ ማዕድኖች የሚገኙበት እንደመሆኑ የኢንቨስተሮችን ትኩረት እየሳበ ሲሆን፣ ኢንቨስተሮች በማዕድን ቁፋሮ እንዲሰማሩም ይበረታታሉ፡፡ ሆኖም ማዕድኖቹን በማውጣት ሒደት የአካባቢው ተፈጥሯዊ ይዘት ላይ ተፅዕኖ በማድረግ ቱሪዝሙን አይጎዳውምን? የሚል ጥያቄም ይሰነዘራል፡፡

የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ መሐመድ እንደሚናገሩት፣ ፖታሽየም ለማውጣት መሬት በጥልቀት ሲቆፈር፣ ጎብኚዎችን የሚስበው ኅብረ ቀለም ሊጠፋ ይችላል የሚል ሥጋት አለ፡፡ ፖታሽየም ለማውጣት ወደ አካባቢው የገባውን አንድ ድርጅት ላለፉት አምስት ዓመታት ጥናት እያደረገ መሆኑን ገልጸው፣ ‹‹ሌሎችም ድርጅቶች ወደ አካባቢው ሲመጡ ቦታው ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ስለመኖሩ እኛም እያስጠናን ነው፤›› ብለዋል፡፡ ለአጭር ጊዜ ቢዝነስ በሚል የረዥም ዓመት ዕድሜ ያለው ሀብት መጥፋት የለበትም የሚሉት ኃላፊው ለጉዳዩ ትኩረት እንደሚሰጠውም ያክላሉ፡፡

የቱሪስት መዳረሻዎች ጥበቃ እንደ ኤርታአሌና ዳሎል ባሉ ተፈጥሯዊ ሀብቶች ብቻ መወሰን የለበትም፡፡ የአካባቢው ታሪክ፣ ባህልና ቅርስ ጥበቃ ቅድሚያ ሊሰጠውም ይገባል፡፡ በዚህ ረገድ አደጋ ያንዣበባቸው ጥንታዊ የአፋር ቤተ መንግሥቶችን ጉዳይ ማንሳት ይቻላል፡፡ ጥበቃ በማጣት እየፈራረሰ ያለው ታሪካዊ ሀብት የተቆርቋሪ ያለህ ማለት ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ ከቅርስ ጥናትና ጥበቃ ጋር በተያያዘ የውይይት መድረኮች ስለ አካባቢው እሮሮ ከመስማት የዘለለ መፍትሔ ግን አልታየም፡፡

12ኛው የብሔር ብሔረሰቦች በዓል

      የአፋር ክልል የ12ኛው ብሔር ብሔረሰቦች በዓል አዘጋጅ እንደመሆኑ በዓሉን አስታኮ ብዙ ጎብኝዎች ይመጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ኃላፊው ይናገራሉ፡፡ ‹‹ዓመቱን የጉብኝት በማድረግ ወደ ክልሉ የሚመጡ ሰዎች ክልሉን የበለጠ ያስተዋውቃሉ ተብሎ ይጠበቃል፤›› ይላሉ፡፡ በክልሉ ፕሬዚዳንት በሚመራ ዓብይ ኮሚቴ ለበዓሉ ዝግጅት እንደጀመሩ ያክላሉ፡፡ በክልሉ ዋና ከተማ ሰመራ ብቻ ሳይሆን በአዋሽ፣ አሳይታና ሌሎችም ከተሞች የሆቴሎች ግንባታ መጀመሩን ኃላፊው ይገልጻሉ፡፡ የስቴዲየም፣ የአስፋልትና የሆቴል ግንባታ በተያዘላቸው ጊዜ እንደሚጠናቀቁም ያምናሉ፡፡ በእርግጥ የሁሉም ግንባታ በአንድ ዓመት ባይጠናቀቅም አብዛኛው  እንደሚያልቅ ተስፋቸውን ገልጸዋል፡፡

ከበዓሉ ጋር በተያያዘ ክልሉን ለቱሪስቶች ከማስተዋወቅ በተጨማሪ ኢንቨሰትመንት ይስፋፋል የሚል ተስፋም አለ፡፡ በአካባቢው ኢንቨስት የሚያደርጉ ባለሀብቶች ከውጪ የሚያስገቧቸውን ቁሳቁሶች ከቀረጥ ነፃ የማድረግና ሌሎችም ማበረታቻዎች ቢሰጡም፣ በሚፈለገው መጠን ለውጥ መጥቷል ለማለት አያስደፍርም፡፡ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም ማስፋፋትና ፓርኮች ሥራ ሒደት ባለቤት አቶ አህመድ አብዱልቃድር እንደሚገልጹት፣ በአካባቢው ኢንቨስት ለማድረግ ቃል የሚገቡ ባለሀብቶች ቢኖሩም በክልሉ በኩል ተከታትሎ ከግብ የማድረስ ክፍተት አለ፡፡ ከማበረታቻ ባሻገር የባለሀብቶችን እንቅስቃሴ መከታተል ተገቢ መሆኑንም ይናገራሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ጥቁር የመልበስ ውዝግብና የእምነት ነፃነት በኢትዮጵያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ኅዳር ወር ላይ በፓርላማ...

የኢንሹራንስ ዘርፉን የሚቆጠጠር ገለልተኛ ተቋም ለመመሥረት እንቅስቃሴ ተጀመረ

ከ70 በላይ አዳዲስ የፋይናንስ ተቋማት ዘርፉን ሊቀላቀሉ ነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ...

እስቲ አንገፋፋ!

እነሆ መንገድ። ጊዜና ሥፍራ ተጋግዘው በውስንነት ይዘውናል። መፍጠን ያቃተው...