Tuesday, October 4, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  ሜትር ታክሲዎች በኪሎ ሜትር አሥር ብር ታሪፍ እንዲሠሩ ተወሰነ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

   –  በወጣው ታሪፍ በማይሠሩት ላይ ዕርምጃ ይወሰዳል ተብሏል

   –  የታክሲ ማኅበራት ታሪፉን በግዴታ እንደተቀበሉት ይናገራሉ

  ወደ አገር ውስጥ በመግባት ሥራ ከጀመሩ ከአምስት ወራት በላይ የቆዩት ቢጫዎቹ ሜትር ታክሲዎች፣ ከረቡዕ የካቲት 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ከዚህ ቀደም በወጣላቸው በኪሎ ሜትር አሥር ብር ታሪፍ መሠረት አገልግሎት መስጠት እንዲጀምሩ መወሰኑን መንግሥት አስታወቀ፡፡

  በፌደራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን በወጣው ታሪፍ መሠረት እንዲሠሩ ታክሲዎቹን የመቆጣጠር ኃላፊነት የተሰጠው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ባለሥልጣን፣ ከ1,163 ሜትር ታክሲዎች (የኤርፖርቶቹን አቫንዛ ታክሲዎች ጨምሮ) ውስጥ 750 የሚሆኑት ከየካቲት 1 ቀን ጀምሮ በታሪፍ መሥራት እንደሚጀምሩ ይፋ አድርጓል፡፡ የባለሥልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ምትኩ አስማረ በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፣ ታክሲዎቹ በየቦታው ተዘዋውረው እንዲሠሩ የሚያስገድድ የሶፍትዌርና የመመርያ ዝግጅት ሥራ ሲከናወን መቆየቱን አስረድተዋል፡፡ በዚህ መሠረት ለ26 የሜትር ታክሲ ማኅበራት መመርያው ከመተላለፉም በላይ፣ ከየካቲት 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ በተጓዙበት የኪሎ ሜትር ርቀት ልክ እየለካ በሚያስከፍለው ሶፍትዌር እየታገዙ እንዲሠሩ መወሰኑን ዋና ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡

  ላለፉት አምስት ወራት የሜትር ታክሲዎቹ በኪሎ ሜትር እየለኩ የሚያስከፍሉበት ሶፍትዌር ሲዘጋጅ መቆየቱን የገለጹት አቶ ምትኩ፣ ዝግጅቱ ተጠናቆ በከተማው በየትኛውም አካባቢ ተዘዋውረው እንዲሠሩ የሚችሉበት ሥርዓት ተዘርግቷል ብለዋል፡፡

  ታክሲው ከመንቀሳቀሱ በፊት አሥር ብር መነሻ ሒሳብ ሆኖ ለአንድ ኪሎ ሜትር ተሳፋሪው አሥር ብር እንዲከፍል የሚደረግበት አሠራር በታክሲ ባለንብረቶች ዘንድ ቅሬታ አሳድሮ ነበር፡፡ በርካቶቹ የታሪፉ ዋጋ ማነሱን በመግለጽ መንግሥት እንዲያስተካክል ሲጠይቁ ቆይተዋል፡፡ ከታሪፉ በተጨማሪ ግን መሠረታዊ የሥርዓት ችግር ስላለበት ይህም መታየት ነበረበት ያሉት የ‹‹ዘ ሉሲ ታክሲ›› ባለንብረቶች ማኅበር ኃላፊ አቶ አንተነህ ትሪሎ ናቸው፡፡

  ‹‹በታሪፉ ላይ ቅሬታ ነበረን፡፡ የታሪፍ አሞላሉ ቅሬታ አሳድሮ ነበር፡፡ በተለይ የተሳፋሪው ቆይታ ጊዜ ማለትም በጉዞ ወቅት ወርዶ ጉዳዩን ፈጽሞ የሚመለስ ተሳፋሪ የሚስተናገድበት አሠራር የለውም፡፡ የነዳጅ ታሪፍ ለውጥ ሲኖር፣ በዝናብ፣ እንደ አፍሪካ ኅብረት ያለው ስብሰባ በሚኖርበት ወቅት ለሚፈጠረው የመንገድ መዘጋጋት ምላሽ የሚሰጥ ሥርዓት አልተዘጋጀም፤›› ያሉት አቶ አንተነህ፣ አሠራሩ ከውጭ እንደ መግባቱ መጠን እንዲህ ያሉ ጥያቄዎችን ለማስተናገድ የሚችል መሆን ሲገባው ይህን አላደረገም ብለዋል፡፡

  ከዚህም በላይ ሳይንሳዊ ጥናት ተደርጎበት ተግባራዊ አልተደረገም በማለት የሜትር ታክሲ ሥርዓቱን የተቹት አቶ አንተነህ፣ መንግሥት ግደየለም አገልገሎቱን እየሰጣችሁ መሻሻል ያለበት ነገር ካለ እየታየ ይስተካክላል በማለት ትራንስፖርት ሚኒስቴርና በሥሩ የሚመሩት መሥሪያ ቤቶች አቋም በመያዛቸው ወደ ሥራ ለመግባት ታክሲዎቹ መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ተቀብለናል ማለት ተስማምተናል ማለት አይደለም፤›› ያሉት አቶ አንተነህ፣ ‹‹መንግሥትን አምነን ከእኛ የበለጠ ያውቃል፣ እኛ ያላየነውን አይቶ ይሆናል፤›› በማለት በታሪፉ መሠረት ለመሥራት ስምምነት መደረጉን ገልጸዋል፡፡

  ከቀረጥ ነፃ የገቡት ሜትር ታክሲዎቹ በቀን በአማካይ 120 ኪሎ ሜትር በመሸፈን፣ 75 በመቶው ጉዟቸው ተሳፋሪዎችን በማመላለስ እንደሚሸፈን ታሳቢ ተደርጎ የወጣ ታሪፍ እንደሆነ ተብራርቷል፡፡ ታሪፉ የታክሲ ባለንብረቶች የሚያሰማሯቸውን ሾፌሮች አበልና የታክሲ ማሳደሪያ ጨምሮ ሌሎችም ወጪዎችን ከመሸፈን በተጨማሪ ጥቅም እንደሚያስገኝ ተሰልቶ የወጣ መሆኑን አቶ ምትኩ ገልጸዋል፡፡ የታክሲ ባለንብረቶች ስለሚያቀርቧቸው ቅሬታዎች ተጠይቀው ሲመልሱም፣ ‹‹ታሪፉ ያንሳል ይበዛል ለማለት መሞከርና ውጤቱ መታየት አለበት፤›› በማለት በሒደት እየታየ ማሻሻያ ማድረግ ካስፈለገ እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡

  በአስገዳጅነት ጭምር የሚተገበረው የሜትር ታክሲ አገልግሎት፣ በተገቢው መንገድ ሥራ በማይጀምሩት ላይ የገንዘብ ቅጣትን ጨምሮ የአገልግሎት ሰጭነት ፈቃድን እስከ መንጠቅ የሚደርስ ዕርምጃ እንደሚወስድ ባለሥልጣኑ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡ ለ26ቱም ማኅበራት ደብዳቤ ከመበተን በተጨማሪ ለ750 ያህል ታክሲዎች ሶፍትዌር መገጠሙም ተገልጿል፡፡ የተቀሩት መኪኖች ጋራዥ የሚገኙ፣ የኪሎ ሜትር ቆጣሪያቸው የተበላሹና መስተካከል የሚገባቸው በመሆናቸው እንደዘገዩ አቶ ምትኩ አስረድተዋል፡፡

  በወጣው ታሪፍ መሠረት የሊፋን ሞተርስ ሥሪት የሆኑት ሳሎን (ቢጫ) ታክሲዎች በኪሎ ሜትር አሥር ብር ሲያስከፍሉ፣ አቫንዛ የሚባሉት ቶዮታ ሠራሽ ታክሲዎች 13 ብር ያስከፍላሉ፡፡ ይህ ሒሳብ ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ ምሽቱ አራት ሰዓት ላለው ጊዜ የሚያገልግል ነው፡፡ ከአራት ሰዓት በኋላ ሒሳቡ በግማሽ በመጨመር እንደሚሠራበት አቶ ምትኩ አብራርተዋል፡፡

  ሜትር ታክሲዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ በማድረግ የተፈቀደበት አሠራር ለሰፊው ሕዝብ አገልግሎት በሚሰጡት እንደ ሚኒባስ ላሉት ቢፈቀድ፣ በትራንስፖርት እጥረት ለሚጉላላው ሕዝብ እፎይታ እንደሚያስገኝ ብዙዎች ያምናሉ፡፡ ስለዚህ ጉዳይ በሪፖርተር የተጠየቁት አቶ ምትኩ፣ የሚኒባስ ባለንብረቶች ተደራጅተው አውቶቡስ እንዲያስገቡ ተመሳሳይ ዕድል እንደተሰጣቸው ገልጸዋል፡፡ መንግሥት የሜትር ታክሲዎችን ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ዕድሉን የሰጠው የዲፕሎማሲ መናኸሪያ ለሆነችው አዲስ አበባ ገጽታ በማሰብ፣ እያደገ የመጣውንና በእነዚህ ታክሲዎች ለመጠቀም አቅም ያለውን የኅብረተሰብ ክፍል ለማገልገል እንዲቻል ታስቦ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ከዚህም በላይ ግን በድርድር መደበኛ ባልሆነ አኳኋን ከታሪፍ ውጪ የሚሠሩትን ሳሎን ታክሲዎች ወደ ታሪፍ አሠራር ለማስገባት ጭምር ተፈልጎ ተግባራዊ የሚሆን ሥርዓት እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

  ‹‹የውበት እስረኞች›› የሚል ስያሜ የወጣላቸው የሜትር ታክሲዎች በገቡበት አግባብ በወቅቱ አገልግሎት ሊሰጡ ባለመቻለቻው፣ በመንግሥትና በታክሲዎቹ ባለንብረቶች መካከል በተፈጠረው አለመግባባት ምክንያት በሜትር አገልግሎት ሊሰጡ ባለመቻላቸው፣ ያማሩ ቢሆኑም የተፈለገውን አገልግሎት ባለመስጠታቸው  እንደሆነ በከተማው በስፋት ይነገራል፡፡

  የሳሎን ታክሲዎች ሥምሪት ሥራ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አስተዳደር ወቅት እንደተጀመረ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የታክሲ አገልግሎት ማኅበራቱ በደርግ መንግሥት ወቅት እንዲበተኑ ሲደረግ በርካታ የታክሲ ባለንብረቶች ተወርሰው ነበረ፡፡ በኢሕአዴግ መንግሥት ወቅት የቀደሙት የሥርዓቱ መሥራቾች እንዲፈቀድላቸው በመጠየቅ ተደራጅተው መሥራት እንደጀመሩና በአብዛኛውም በኤርፖርትና በሆቴሎች አካባቢ ሲሠሩ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡ 

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች