Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየጉለሌ ዕፅዋት ማዕከል ኃላፊዎች በ7.7 ሚሊዮን ብር ሙስና ተጠርጥረው ክስ ተመሠረተባቸው

የጉለሌ ዕፅዋት ማዕከል ኃላፊዎች በ7.7 ሚሊዮን ብር ሙስና ተጠርጥረው ክስ ተመሠረተባቸው

ቀን:

  • በሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ሥራ የተቀጠሩም በክሱ ተካተዋል

የጉለሌ ዕፅዋት ማዕከል ዋና ሥራ አስኪያጅና ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅን ጨምሮ፣ በተለያየ ኃላፊነቶች ላይ ከነበሩ 12 የማዕከሉ ሠራተኞችና ከኮንስትራክሽን ተቋማት በድምሩ 17 ግለሰቦች፣ በመንግሥት ላይ ከ7.7 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት በማድረስ ተጠርጥረው ማክሰኞ ጥር 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 18ኛ ወንጀል ችሎት ያቀረበው ክስ እንደሚያስረዳው ተከሳሾቹ ሙስና ፈጽመዋል ተብለው ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የዋሉትና ክስ የተመሠረተባቸው፣ ለጉለሌ ዕፅዋት ማዕከል ከተከለለው ቦታ ላይ 32 ሔክታር የሚሆነውን ቦታ አፅድቶና አስተካክሎ ለማሠራት፣ ማዕከሉ የካቲት 27 ቀን 2007 ዓ.ም. በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ካወጣው ጨረታ ጋር በተያያዘ መሆኑን ክሱ ያስረዳል፡፡

ተከሳሾቹ የዕፅዋት ማዕከሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ተክሌ ወልደገሪማ፣ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ መስፍን ኃይሉ፣ የሒሳብ ክፍል ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ገብረፃድቅ፣ የማዕከሉ መሐንዲሶች አቶ ፍጹም ደጀኔ፣ አቶ ደረጃ ጉደታና አቶ ግርማ ቡሽራ፣ የተቋሙ ፎርማኖች አቶ አቡበከር ኑሪና አቶ ዮሴፍ ፀጋዬ፣ የወጣውን ጨረታ ማሸነፉ የተገለጸው ሰለሞን ላቀው ጠቅላላ የሥራ ተቋራጭ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ላቀውና ሌሎች ስድስት ተጠርጣሪዎች ናቸው፡፡

በተለይ የማዕከሉ ኃላፊዎች በተቋሙ የነበራቸውን ቆይታና ትውውቅ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ከኮንትራክተሩ ጋር በጥቅም በመመሳጠርና ለራሳቸው ጥቅም ለማግኘት በማሰብ በፈጸሙት ድርጊት፣ በመንግሥት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አስረድቷል፡፡

ማዕከሉ በ32 ሔክታር ላይ ያሉ ዛፎችን በመቁረጥና ጉቶዎቹን በመንቀል መሬቱን ለማስተካከል በዶዘርና በኤክስካቫተር መጠቀም አንዱ መሥፈርት እንደነበር በክሱ ተጠቁሟል፡፡ በመሆኑም ሰለሞን ላቀው ጠቅላላ ሥራ ተቋራጭ የወጣውን መሥፈርት በማሟላት ጨረታውን ማሸነፉንም አክሏል፡፡ ነገር ግን ተቋራጩ በገባው ውል መሠረት ሠርቶ ማስረከብ የሚገባው 32 ሔክታር ሆኖ ሳለ፣ 21.3 ሔክታር ብቻ ሠርቷል፡፡ ተከሳሾቹ የተሠራውን ያወቁ ቢሆንም 30.6 ሔክታር እንደሠራ በማስመሰል፣ በተዘጋጀው የክፍያ ሰነድ ላይ በማስፈረምና በማስፀደቅ 856,750 ብር ያላግባብ እንዲከፈል ማድረጋቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡

ማዕከሉ በጨረታ መለያ ኮድ ሎት-2 ከደቡብ በር እስከ ሰሜን በር፣ እንዲሁም በጨረታ መለያ ኮድ ሎት-3 ከሚሊኒየም ሠፈር እስከ አቡነ ሀብተማርያም (ጉለሌ) መንገድ ድረስ የኮብልስቶን ንጣፍ መንገድ ለማሠራት ጥር 28 ቀን 2007 ዓ.ም. ጨረታ ማውጣቱን የሚያብራራው የዓቃቤ ሕግ ክስ፣ አቶ ወርቅነህ መኮንን የተባሉት ተከሳሽ ማዕከሉ ባወጣው የጨረታ መሥፈርት መሠረት ማለትም ቁመቱና ስፋቱ አሥር ሣንቲ ሜትር በአሥር ሣንቲ ሜትር ለመሥራት አሸንፈው ውል መፈራረማቸውን ያስረዳል፡፡

በጨረታ መለያ ቁጥር-2 እና በጨረታ መለያ ቁጥር-3 ምን ያህል ሜትር ካሬ የኮብልስቶን ንጣፍ በምን ያህል ርዝመትና ስፋት እንደሚሠራ ተዘርዝሮ ውል ተፈጽሞ እያለ፣ ተከሳሾቹ ከኮንትራክተሩ ጋር በጥቅም በመመሳጠር ያልተሠራውን ሥራ እንደተሠራ በማስመሰል፣ 3,332,917 ብር ያላግባብ ክፍያ እንዲፈጸም ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ በዝርዝር አስረድቷል፡፡

ሌላው ጉለሌ ዕፅዋት ማዕከል ጥር 18 ቀን 2008 ዓ.ም. በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ባወጣው ከደቡብ በር መግቢያ ወደ ምዕራብ በር የሚወስደውን መንገድ የአጥር ሥራ ጨረታ ወይዘሪት ማሚታ ወረደ የተባሉት ተከሳሽ፣ ጨረታውን አሸንፈው ውል መፈጸማቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡ በወጣው መሥፈርት መሠረት አጥሩን በ28,275,222 ብር ለማሠራት ማዕከሉ ጨረታውን ያወጣ ቢሆንም፣ ተከሳሾቹ በሚገዛው የአጥር ሽቦ ዋጋ ላይ ‹‹አርቲሜቲክ ኢረር›› እያሉ በጨረታው ላይ በተቀመጠው የዋጋ መጠን ላይ ተጨማሪ 3,576,000 ብር በመደመር ለጨረታ የቀረበውን ገንዘብ 34,572,851 ብር ማድረሳቸውን ዓቃቤ ሕግ በዝርዝር አስረድቷል፡፡ ተከሳሾቹ 3,576,000 ብር ያላግባብ ክፍያ እንዲፈጸም ማድረጋቸውንም አስፍሯል፡፡

ተከሳሾቹ የጉለሌ ዕፅዋት ማዕከል ኃላፊና የተለያዩ የሥራ መደቦች ኃላፊዎች የጨረታ ኮሚቴ አባል ሆነው ሲሠሩ፣ ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመጠቀም በመንግሥት ላይ በድምሩ የ7,765,667 ብር ጉዳት በማድረሳቸው በከባድ የሙስና ወንጀል ክስ መሥርቶባቸዋል፡፡

አቶ አቡበከር ኑሪ፣ አቶ ዮሴፍ ፀጋዬና አቶ ፉፋ ለጂሳ የተባሉ ተከሳሾች ደግሞ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ፣ ነሐሴ 16 ቀን 2008 ዓ.ም. በአዲስ ዘመን የወጣ የሥራ ማስታወቂያ ላይ ተወዳድረው መቀጠራቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡ የሥራ ማስታወቂያው የአራት ዓመት ልምድና የደረጃ 10+3 ዲፕሎማ የሚጠይቅ ሆኖ ሳለ፣ ተከሳሾቹ ከተለያዩ ድርጅቶች የተጻፈ የሥራ ልምድ በማስመሰል ሐሰተኛ ማስረጃ በማቅረብ መቀጠራቸውን በክሱ ተገልጿል፡፡ በመሆኑም ተከሳሾቹ ሐሰተኛ የሥራ ልምድ፣ የመንግሥታዊና የሕዝባዊ ድርጅቶችን ማኅተምና ቲተር አዘጋጅተው በሐሰተኛ ሰነድ በመገልገላቸው፣ በፈጸሙት ሐሰተኛ ሰነድ መገልገል የሙስና ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸዋል፡፡

ተከሳሾቹ የተመሠረተባቸው ክስ ዋስትና እንደማያስከለክላቸው በመግለጽ የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅላቸው በማመልከታቸው፣ ፍርድ ቤቱ በዋስትና ጉዳይ ላይ ብይን ለመስጠት ለየካቲት 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...