Thursday, February 29, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሁለት የእንግሊዝ ኩባንያዎች የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ለመገንባት 850 ሚሊዮን ዶላር አዘጋጅተናል አሉ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ግሎቤሌክና ኮንቲንጀንት ቴክኖሎጂ የተባሉ ሁለት የእንግሊዝ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ በመገንባት፣ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በሽያጭ ለማቅረብ ከመንግሥት ጋር እየተነጋገሩ መሆናቸውን አስታወቁ፡፡ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ ላይ በሚገኘው የገናሌ ዳዋ ወንዝ ላይ 250 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚያስችል ፕሮጀክት ለማካሄድ፣ 850 ሚሊዮን ዶላር ማዘጋጀታቸውን የኩባንያዎቹ ኃላፊዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የኩባንያዎቹ ኃላፊዎች የተካተቱበት የልዑካን ቡድን አዲስ አበባ በመግባት ሰኞ ጥር 29 ቀን 2009 ዓ.ም. በብሔራዊ ቤተ መንግሥት ከፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ጋር መወያየቱን፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ያላቸውን ፍላጎት ማሳየታቸውንም ገልጸዋል፡፡

ገናሌ ዳዋ ስድስት በሚል ስያሜ የፕሮጀክት ግንባታውን በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደሚያጠናቅቁ የተነገረላቸው ሁለቱ ኩባንያዎች፣ ከፍተኛ ጥራት ያለው ዘመናዊ የኃይል ማመንጫ እንገነባለን ብለዋል፡፡ ያላቸውን ልምድ ተጠቅመው በአገሪቱ ውስጥ እስካሁን ከተገነቡ ማመንጫዎች ሁሉ ለየት እንደሚያደርጉና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እንደሚጠቀሙ ኃላፊዎቹ አክለዋል፡፡

ሁለቱ ኩባንያዎች ለፕሮጀክቱ ፍላጎት ከማሳየት በላይ አስፈላጊውን ፋይናንስ ቢያቀርቡም፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ግን ሌሎች ተጫራች ድርጅቶችንም እየተመለከተ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ነገር ግን የግሎቤሌክ ኩባንያ የምሥራቅ አፍሪካ ኃላፊ ክርስቲያን ራይት ኩባንያቸው በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ሰፊ ልምድ ያለው በመሆኑ፣ በኢትዮጵያ ተቀባይነት ሊያገኝ እንደሚችል እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡ ለዚህም ከፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱና ከሌሎች የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር በነበሯቸው ውይይቶች መልካም አቀባበል እንደተደረገላቸውም አስረድተዋል፡፡

የግሎቤሌክም ሆነ የኮንቲንጀንት ቴክኖሎጂ ኃላፊዎች እስከ ሚያዝያ 2009 ዓ.ም. ድረስ ባሉት ጊዜያት ወደ ግንባታ ለመግባት ዝግጅት ማድረጋቸውንም ገልጸዋል፡፡

በጣምራ ፍላጎታቸውን ያሳዩት እነዚህ ኩባንያዎች ወደ አገሪቱ የኃይል ኢንቨስትመንት ሲመጡ፣ ሁለተኛው ግዙፍ የምዕራባውያን ኢንቨስትመንት ይሆናሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡ ለጊዜው ሳንካ እንደገጠመው ቢነገርም ቀደም ብሎ ወደ ኢንቨስትመንት የመጣው የአውሮፓ ኩባንያ የአይስላንዱ ሬክያቪክ ሲሆን፣ ኮርቤቲ የተባለውን የእንፋሎት ኃይል ማመንጫ በመገንባት፣ በአራት ቢሊዮን ዶላር 1,000 ሜጋ ዋት ያመነጫል መባሉ አይዘነጋም፡፡

ሁለቱ የእንግሊዝ ኩባንያዎች ለገናሌ ዳዋሌ ስድስት ፕሮጀክት መደብነው ካሉት አጠቃላይ ፋይናንስ ውስጥ 400 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋው ለመስኖ ግንባታ እንደሚውል ከኃላፊዎቹ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ የመስኖ ልማቱም ሁለት ክፍሎች ሲኖሩት የወይመልና የታችኛው ገናሌ መስኖ ግድብ በመባል ይጠራሉ ብለዋል፡፡ የወይመል መስኖ ግድብ ከአዲስ አበባ 450 ኪሎ ሜትር ኦሮሚያ ክልል በባሌ ዞን ውስጥ ሲገነባ፣ የታችኛው ገናሌ መስኖ ግድብ ከአዲስ አበባ 960 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሶማሌ ክልል ሊበን ዞን ዶሎ አዶ ወረዳ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡ የመስኖ ልማቱ 26,000 ሔክታር መሬት እንደሚያለማም የኩባንያዎቹ የቅድመ አዋጭነት ጥናት ያሳያል፡፡

በተያያዘም እነዚሁ የእንግሊዝ ኩባንያዎች የመተሐራ የፀሐይ ኃይል ማመንጫን ፕሮጀክት ጨረታ ለመሳተፍ ሰነዱን መግዛታቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡ ፕሮጀክቱም 120 ሜጋ ዋት ኃይል እንደሚያመነጭ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያወጣው የጨረታ ሰነድ ያመለክታል፡፡

በአገሪቱ የኃይል ዘርፍ ግንባታና አገልግሎት የቻይና፣ የህንድና የቱርክ ኩባንያዎች ተመሳሳይ ፍላጎት ማሳየታቸው ይታወቃል፡፡ ነገር ግን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በመንግሥትና በግል ዘርፍ አጋርነት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት አልተካሄደም ነበር፡፡ መንግሥት በቅርቡ ይህንን ዘርፍ ለግል ባለሀብቶች ክፍት ለማድረግ መዘጋጀቱን በማስታወቁ የበርካቶችን ትኩረት ስቧል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ አዲስ የሕግ ማዕቀፍ መንግሥት እንደሚያወጣ ይጠበቃል፡፡ የሕግ ማዕቀፉም የግል ዘርፉ እንዲሳተፍ ከማድረግ ባሻገር የኃይል ሽያጭ ተመንም የሚደነግጉ ሕጎችን ያካትታል ተብሏል፡፡ ነገር ግን በርካታ ኩባንያዎች በድርድር ዘርፉን ለመቀላቀል ፍላጎት ቢኖራቸውም፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ሥራ አመራር ቦርድ በዘርፉ ለመሰማራት የሚፈልጉ ኩባንያዎች በጨረታ ብቻ እንዲስተናገዱ ወስኗል፡፡ በዚህ መሠረት እነዚህ የእንግሊዝ በኩባንያዎች የሚኖራቸው ተቀባይነት እስካሁን ማረጋገጫ አለማግኘቱ ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች