Monday, May 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናአረና ፓርቲ አቶ አብርሃ ደስታን ሊቀመንበር አድርጎ መረጠ

አረና ፓርቲ አቶ አብርሃ ደስታን ሊቀመንበር አድርጎ መረጠ

ቀን:

ዓረና ትግራይ ለሉዓላዊነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ በአራተኛ መደበኛ ጉባዔው አቶ  አብርሃ ደስታን ሊቀመንበር አድርጎ መረጠ፡፡

ከጥር 27 እስከ 28 ቀን 2009 ዓ.ም. በመቐለ በሚገኘው ዋና ጽሕፈት ቤቱ አራተኛው ጉባዔውን ያካሄደው ድርጅቱ፣ ያለፉት ሦስት ዓመታት ሥራዎቹን በመገምገም በአገራዊና በክልላዊ አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረጉን ለሪፖርተር ገልጿል፡፡

ፓርቲው ባለፉት ሦስት ዓመታት እንቅስቃሴው ድክመቱንና ጥንካሬውን መገምገሙን የገለጹት የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዓምዶም ገብረ ሥላሴ፣ በተለይ ባለፈው አምስተኛ ጠቅላላ ምርጫ በአባላት ደረሰ ያሉት አፈና በሌሎች ተቃዋሚዎች ላይ የደረሰ መሆኑን፣ ጠቅላይ የሆነው የምርጫ ውጤት ደግሞ ባለፈው ዓመት ለተከሰተው ሁከት መነሻ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ፓርቲው በተመሠረተበት ትግራይ ክልል ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ወጣቶች ሥራ አጥ በመሆናቸው አስቸኳይ መፍትሔ እንዲያገኙ፣ የኢትዮ ኤርትራ ሰላምም ጦርነትም አልባ ሁኔታ ክልሉን በፀጥታና በኢኮኖሚ ረገድ በከፍተኛ ደረጃ እየጎዳ እንዳለና ሰላማዊ ዕልባት እንዲያገኝ ፓርቲው ውሳኔ ማስተላለፉን ገልጸዋል፡፡

በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ፓርቲው ወደ አገራዊ ሊቀየር ነው ተብሎ የተሠራጨው ወሬ ስህተት መሆኑን አቶ ዓምዶም ይናገራሉ፡፡ በአገሪቱ ባለፈው ዓመት በተነሳው ሁከት ላይም ፓርቲው ተወያይቶ ውሳኔ ማስተላለፉን ገልጸው፣ በቅርቡ ሊደረግ የታሰበው ድርድር ከዚህ ቀደም ፓርቲው አባል የሆነበት መድረክ ያቀረባቸው የድርድር ነጥቦች መሠረት አድርጎ እንዲከናወን ጥሪ አቅርበዋል፡፡ እንዲሁም ከወልቃይት ጋር ተያይዞ የተነሳ ውዝግብ እንደተባለው የማንነት ጥያቄ ሳይሆን የአስተዳደር ችግር መሆኑን ፓርቲው የገመገመ መሆኑን፣ በሌሎች የትግራይ ክልል አካባቢዎች ያለው ከፍተኛ የፍትሕና የአስተዳደር ጉድለት መገለጫ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም ደግሞ በሁለቱም ክልሎች (በአማራና በትግራይ) መካከል ያለው የወሰን አለመግባባት ሙሉ ለሙሉ ይፈታ ዘንድ አስተዳደራዊ መፍትሔ እንዲያገኝ ፓርቲው ጠይቋል፡፡ በአሁኑ አከላለል በአማራ ክልል የሚገኙ ትግርኛ ተናጋሪዎች ቀደም ሲል በ2004 ዓ.ም. ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ያቀረቡት በአሥር ሺዎች የሚቆጠር ፊርማ የያዘ ቅሬታም አብሮ እንዲታይ፣ በደል የደረሰባቸው ሰዎችም ጉዳያቸው እንዲታይ የሚል የመፍትሔ ሐሳብ አረና ፓርቲ ማቅረቡ ተገልጿል፡፡

ፓርቲውን ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት በበላይነት የሚመራ አሥራ አንድ አባላትን ያካተተ አዲስ የሥራ አስፈጻሚ አመራር የመረጠ ሲሆን፣ ላለፉት ሦስት ዓመታት በሊቀመንበርነት የመሩት አቶ ብርሃኑ በርኸን በማውረድ በምትካቸው አቶ አብርሃ ደስታን መርጧል፡፡

አቶ አብርሃ ደስታ በመቐለ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር ሲሆኑ፣ በሽብርተኝነት ተጠርጥረው ለሁለት ዓመታት በእስር ማሳለፋቸውና ባለፈው ዓመት መጨረሻ መለቀቃቸው የሚታወስ ነው፡፡

እንዲሁም ፓርቲው አቶ ጎይቶኦም ፀጋይን ምክትል ሊቀመንበር፣ አቶ ዓምዶም ገብረ ሥላሴን ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ፣ አቶ ተክለዝጊ ወልደገብርኤል የድርጅት ጉዳዮች ኃላፊ፣ አቶ ዮሐንስ ካሕሳይን የፋይናንስ ኃላፊ፣ እንዲሁም አቶ ዘነበ ሲሳይ የድርጅቱ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አድርጎ መርጧል፡፡

የቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት የፓርቲው መሥራችና የመጀመሪያው ሊቀመንበር አቶ ገብሩ አሥራት፣ ወ/ት አረጋሽ አዳነ (መሥራች)፣ ዶ/ር ማርቆስ ገሰሰ፣ አቶ ኪዳነ አመነ፣ አቶ ካሕሳይ ዘገየ ከሥራ አስፈጻሚ አባላት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመስቀል አደባባይ የመግቢያ ክፍያ ለምን?

ወጣቶች፣ ሕፃናትና አረጋውያን ሳይቀሩ መንፈሳቸውን የሚያድሱበት እንዲሁም ሐሳባቸውን በነፃነት...

በሕገ መንግሥቱ የተዋቀረው ‹‹የብሔር ፖለቲካ›› እና ‹‹ሥርዓቱ›› ያስከተለው መዘዝና መፍትሔው

(ክፍል አራት) በዓቢዩ ብርሌ (ጌራ) ባለፈው ጽሑፌ (በክፍል ሦስት) አሁን ያለው...

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብና የመንግሥት መሪ ምሥል

በበቀለ ሹሜ በ2015 ዓ.ም. መጋቢት ወር ውስጥ ይመስለኛል በ‹ሸገር ካፌ›...

ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ያደረገው አዋጅ የፍትሐዊነት ጥያቄ አስነሳ

በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ስምንት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ በማድረግ ተቋማዊና...