Monday, September 25, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናፓርላማው ከ19 ቢሊዮን ብር በላይ የውጭ ብድር አፀደቀ

ፓርላማው ከ19 ቢሊዮን ብር በላይ የውጭ ብድር አፀደቀ

ቀን:

ፓርላማው ለአንድ ወር የእረፍት ጊዜ ከመበተኑ በፊት ባካሄደው ጉባዔ፣ ከ19 ቢሊዮን ብር በላይ የሚሆን የውጭ ብድር ለተለያዩ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ አፀደቀ፡፡

የአጠቃላይ ብድሮቹ ድምር 860 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን፣ በወቅታዊ የውጭ ምንዛሪ ተመን ከ19.3 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ ብድሮች ናቸው፡፡ ከብድሮቹ መካከል ለገናሌ ዳዋ ሦስት የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያና ማሠራጫ ጣቢያ ግንባታ ማስፈጸሚያ ከቻይና ኤግዚም ባንክ የተገኘው 249.32 ሚሊዮን ዶላር ይገኝበታል፡፡ ከዚሁ ብድር ውስጥ 53.8 ሚሊዮን ዶላር የሚውለው ለኃይል ማመንጫ ሲሆን፣ 195.4 ሚሊዮን ዶላሩ ደግሞ ለኃይል ማስተላለፊያ ግንባታ እንደሚውል የብድር ስምምነቱ ማብራሪያ ያስረዳል፡፡  

ሌላው ብድር ከዚሁ ከቻይና ኤግዚም ባንክ የተገኘውና ለገርቢ የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክት የሚውል 242 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ ይኼ ብድር የአዲስ አበባ የመጠጥ ውኃ ፍላጎትን 80 በመቶ ያሟላል ለተባለው የገርቢ የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክት እንደሚውል የብድር ስምምነቱ ያስረዳል፡፡

የገርቢ የውኃ አቅርቦት ፕሮጀክት በአማካይ በየቀኑ 76,000 ሜትር ኪዩብ ውኃ ማቅረብ እንደሚችልና በከተማዋ የአምስት ክፍላተ ከተሞችን ችግር የሚያቃልል እንደሚሆን ይገመታል፡፡ የተገኘው ብድር ሙሉ በሙሉ የፕሮጀክቱን ወጪ እንደሚሸፍን ስምምነቱ ያስረዳል፡፡

ሌላው ከዚሁ የቻይና ኤግዚም ባንክ የተገኘው 120 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን፣ ለቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ተርሚናል ቁጥር አንድ፣ የቪአይፒ ተርሚናልና ተዛማጅ ሥራዎች ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ በተጨማሪ ብድርነት የቀረበ ነው፡፡

በዓለም አቀፍ ግብርና ልማት ፈንድ ለአራት ክልሎች በአርሶ አደሮች ለሚገነቡ የመስኖ ፕሮጀክቶች የሚውል 102 ሚሊዮን ዶላር፣ ለመቀሌ ዳሎልና ለሰመራ አፍዴራ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ ከአፍሪካ ልማት ባንክ የተገኘው 104.6 ሚሊዮን ዶላር ብድር ይገኝበታል፡፡

በሌላ በኩል ለረዥም ዓመታት የተጓተቱትን የጅማ-ጭዳና ሶዶ-ሳውላ የመንገድ ፕሮጀክቶችን ለማስፈጸም ከአፍሪካ ልማት ባንክ የተገኘው 30 ሚሊዮን ዶላር ብድር፣ እንዲሁም ለሐሙሲት-እስቴ መንገድ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ ከነዳጅ አምራችና ላኪ አገሮች ፈንድ ለዓለም አቀፍ ልማት የተገኘ 20 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡

ፓርላማው ሁሉንም ብድሮች በመጀመርያ ንባብ ማክሰኞ ጥር 30 ቀን ባካሄደው የ2009 ዓ.ም. ግማሽ መንፈቅ ማጠናቀቂያ ውሎው አፅድቋል፡፡ በዚህ መሠረትም ፓርላማው ለአንድ ወር የእረፍት ጊዜ ተበትኗል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...