Wednesday, September 27, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የአገር ጤንነት ማረጋገጫው የሕግ የበላይነት ነው!

የሕግ የበላይነት በተግባር በተረጋገጠበት አገር የዜጎች መብቶችና ነፃነቶች ጥያቄ አይነሳባቸውም፡፡ ሁሉም ዜጎች በሕግ ፊት እኩል ሲሆኑና የፍትሕ ሥርዓቱም በነፃነት ሥራውን ሲያከናውን ቅሬታዎች ወይም ግጭቶች አይኖሩም፡፡ አገር በሕግ የበላይነት ሥር ስትተዳደር ጤናማ ትሆናለች፡፡ አልፎ አልፎ አስቸጋሪ ክስተቶች ቢያጋጥሙ እንኳ፣ የሕግ የበላይነት ካለ መፍትሔው ቅርብ ነው፡፡ ግለሰቦች ከሕግ በላይ ሲሆኑ፣ በሕግ የተደነገጉ መብቶች ሲጣሱ፣ ጉልበተኞች ያላግባብ ሲያብጡ፣ ሥልጣን ያላቸው በሥልጣናቸው ሲባልጉ፣ ከሕግ ተቃራኒ የሆኑ ሕገወጥ ድርጊቶች ሲስፋፉና ሕዝብ በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ተስፋ ሲቆርጥ የአገር ጤና ማጣት ማሳያ ነው፡፡ የሕግ የበላይነት መኖር አምባገነንነትን ያስወግዳል፡፡ ለሰላም፣ ለብልፅግና፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና ለአገር ዘለቄታዊ ህልውና በጣም ጠቃሚ ነው፡፡

በዓለም ላይ በሰላምና በብልፅግና የሚኖሩ አገሮች የሚመኩት በሕግ የበላይነት ነው፡፡ በቅርቡ የአሜሪካ ፕሬዚዳንትነትን ሥልጣን የተቆናጠጡት ዶናልድ ትራምፕ ከሰባት የሙስሊም አገሮች የሚመጡ ቪዛ የያዙ ሰዎችን ለዘጠና ቀናት ላለመቀበል ማገዳቸው አይዘነጋም፡፡ አቤቱታ የቀረበላቸው የፌዴራል ዳኛ ሕጉን አገናዝበው የፕሬዚዳንቱን ዕገዳ ውድቅ በማድረጋቸው፣ የአሜሪካን ቪዛ የያዙ በርካታ ሰዎች ከተጠቀሱት አገሮች አሜሪካ መግባት ችለዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ በዳኛው ውሳኔ ባለመስማማታቸው ጉዳዩ ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተመርቶ ክርክር ሊካሄድበት ቀጠሮ ተይዟል፡፡ በደል የደረሰባቸው ፍትሕ እንዲያገኙ ለፍርድ ቤት አቤቱታ ቀረበ፡፡ ጉዳዩን የመረመሩት ዳኛ ያለምንም ተፅዕኖ በሕጉ መሠረት ውሳኔ ሰጡ፡፡ በውሳኔው ያልተደሰቱት ፕሬዚዳንት ደግሞ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ አሉ፡፡ ይህ ምሳሌ በሕግ ጥላ ሥር ሆኖ ፍትሕ የማግኘትን መሻት ከማሳየትም በላይ፣ በሕግ የበላይነት ሥር የመተዳደርን ጠቀሜታ ያስገነዝባል፡፡ የአገር ጤንነትን ያመላክታል፡፡

የሕግ የበላይነት ከዘፈቀደ ውሳኔና ከማናለብኝነት አገርንና ሕዝብን የሚያላቅቅ ፈውስ መድኃኒት ነው፡፡ በአገራችን በተለያዩ መንግሥታት ውስጥ በየደረጃው ሥልጣን የተቆናጠጡ ሰዎች በሆነ አጋጣሚ ሲታሰሩ፣ ሲከሰሱና ፍትሕ ደጃፍ ቀርበው ሲከራከሩ የፍትሕ ጉዳይን አንገብጋቢነት ሲመሰክሩ በአደባባይ ተሰምተዋል፡፡ ሥልጣን ላይ እያሉ ትዝ ያላላቸው ፍትሕ እስር ቤት ውስጥ ሆነው ብዙ ዘምረውለታል፡፡ የረባ የፍትሕ ሥርዓት መገንባት ባለመቻላቸው ምክንያት ሲቆረቆሩም ተሰምቷል፡፡ የሚያሳዝነው ግን ሁሉ በእጃቸው ሁሉ በደጃቸው በነበረ ጊዜ አይደለም፡፡ በሁሉም መንግሥታት ጊዜ ሕገ መንግሥቶች ቢኖሩምና የዜጎች ነፃነት በቀለማት ደምቀው ቢጻፉም፣ በተግባር ሥራ ላይ መዋል እያቃታቸው ዜጎችን ደም እንባ አስለቅሰዋል፡፡ ከወረቀት ጌጥነት ያላለፉ የሚያምሩ የመብት አንቀጾች እየተዳጡ ስንቶች በእስር ያለኃጢያታቸው ማቀዋል፡፡ እየማቀቁ ያሉም አሉ፡፡ ይህ የአገርን ጤና አያሳይም፡፡ ይልቁንም የአገርን ፅኑ ሕመም ነው የሚያሳብቀው፡፡

በሠለጠኑ አገሮች አገሪቱን ከሚመራው ፕሬዚዳንት ወይም ጠቅላይ ሚኒስትር ጀምሮ ሁሉም የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የፓርላማ አባላት፣ የፍርድ ቤት ዳኞች፣ ወዘተ ከምንም ነገር በላይ የሚያከብሩት የሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነውን ሕገ መንግሥት ነው፡፡ ሁሉም በቃለ መሃላቸው የሚያፀኑት የሕግ የበላይነት ከምንም ነገር በላይ መብለጡን ነው፡፡ በዚህም መሠረት ሕግ አውጭው፣ አስፈጻሚውና ተርጓሚው እየተናበቡ ሥራቸውን በአግባቡ ሲያከናውኑና የእርስ በርስ ቁጥጥር ሥርዓቱን ተግባራዊ ሲያደርጉ ሣር ቅጠሉ ሳይቀር ለሕግ ያደገድጋል፡፡ ሕዝብም በአገሩ መንግሥታዊ ሥርዓትም ሆነ በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ያለው አመኔታ ይጨምራል፡፡ ሁሉም በሕግ ፊት እኩል መሆኑ ይረጋገጣል፡፡ ይህ በሌለበት ግን በሕግ መተማመን አይቻልም፡፡ ይህ ደግሞ የአገር ሕመምን ያባብሳል፡፡

በአገራችን በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታ ከፈጠሩ ችግሮች አንዱ የፍትሕ ሥርዓቱ ተጠቃሽ ነው፡፡ ዓቃቤ ሕግ መከሰስ ያለበትን አይከስም፡፡ መከሰስ የሌለበትን ግን ፍርድ ቤት ገትሮ መከራ ያሳየዋል፡፡ ያላግባብ ተከሰው ፍርድ ቤት የሚመላለሱ ያሉትን ያህል፣ ክሳቸው ተቋርጦ በነፃ የሚሰናበቱ ስንቶች በብዛት ታይተዋል፡፡ ‘አንድ ንፁህ ሰው ያላግባብ ከሚታሰር ይልቅ አንድ ሺሕ ወንጀለኞች ቢለቀቁ ይሻላል’ የሚለው የሕግ መርህ እየተጣሰ በርካታ በደሎች የደረሱባቸው አሉ፡፡ በጉልበተኞች ንብረታቸውን የተቀሙ፣ ሰብዓዊ ክብራቸው የተደፈረ፣ በተከበሩበት አገር የተዋረዱ፣ ያለጥፋታቸው የመከራ ገፈት እንዲቀምሱ የተደረጉ፣ ወዘተ በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ከጥርጣሬ አልፎ ጥላቻ ቢፈጠርባቸው ምን ይገርማል? ተቃውሞና ብጥብጥ ቢፈጥሩ ምን ያስደንቃል? ለስደት ቢነሳሱ ለምን ተብሎ ይጠየቃል? በሌሎች አገሮች የፍትሕ ሥርዓት ቢቀኑ እንዴት ይደንቃል? በአሜሪካው ዳኛ የነፃነት ውሳኔ ልባቸው ተነክቶ ቢተክዙ ለምን መደመምን ይፈጥራል? ብዙ ማለት ይቻላል፡፡

የሕዝብን ብሶት ከሚቀሰቅሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ የሆነው የሕግ የበላይነት ጉዳይ ትልቅ አፅንኦት ይሻል፡፡ ሁሉም ሰው በሕግ ፊት እኩል መሆን አለበት፡፡ ሥልጣንም ይኑረው አይኑረው በሕግ ሊዳኝ ይገባዋል፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱ ከማናቸውም የአስፈጻሚው አካል ተፅዕኖዎች ነፃ መሆን አለበት፡፡ በገለልተኝነትና በነፃነት ሥራውን ማከናወን ይገባዋል፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ ከመንግሥት በተጨማሪ ባለሀብቶችና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች እጃቸውን መሰብሰብ አለባቸው፡፡ ዳኞች ሕጉና ህሊናቸው በመራቸው ብቻ እንዲሠሩ ነፃነት ይኑራቸው፡፡ ከማናቸውም ዓይነት የፖለቲካም ሆነ የኢኮኖሚ ተፅዕኖ ተላቀው ለሕግ የበላይነት መከበር እንዲሠሩ ዓውዱ መመቻቸት አለበት፡፡ በፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ የሚሳተፉ ባለድርሻ አካላትም በዚሁ መሠረት ሥራቸውን ያከናውኑ፡፡ በፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ ጣልቃ መግባትና የሕግ የበላይነትን መዳፈር ነውር ይሁን፡፡ ይህ ኩሩና ታሪካዊ ሕዝብ በሌሎች አገሮች ነፃነት ከሚቀና ይልቅ የራሱን ነፃነት ያጣጥም፡፡ አገር ጤና የምትሆነው በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡ በሕግ የበላይነት ብቻ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...

ማን በማን ላይ ተስፋ ይኑረው?

በአንድነት ኃይሉ ችግሮቻችንን ለይተን ካወቅን መፍትሔውንና ተስፋ የምናደርግበትን ማወቅ እንችላለን፡፡...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የመላው ሕዝባችን የአብሮነት ፀጋዎች ይከበሩ!

ሕዝበ ሙስሊሙና ሕዝበ ክርስቲያኑ የመውሊድ፣ የደመራና የመስቀል በዓላትን እያከበሩ ነው፡፡ በኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ እኩልና ጉልህ ድርሻ ያላቸው ኢትዮጵያውያን፣ በዓላቱን እንደ እምነታቸው ሕግጋት...

በአገር ጉዳይ የሚያስቆጩ ነገሮች እየበዙ ነው!

በአሁኑም ሆነ በመጪው ትውልድ ዕጣ ፈንታ ላይ እየደረሱ ያሉ ጥፋቶች በፍጥነት ካልታረሙ፣ የአገር ህልውና እጅግ አደገኛ ቅርቃር ውስጥ ይገባና መውጫው ከሚታሰበው በላይ ከባድ መሆኑ...

የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲወገድ ነው!

ወጣቶቻችን የክረምቱን ወቅት በእረፍት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በበጎ ፈቃድ ሰብዓዊ አገልግሎትና በልዩ ልዩ ክንውኖች አሳልፈው ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞ መስከረም...