Friday, May 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአንድ ቢሊዮን ብር ሽያጭ ያቀደው አረቄና አልኮል ፋብሪካ ቮድካ ማምረት ጀምሯል

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአረቄና አልኮል ምርት በፋብሪካ ደረጃ በኢትዮጵያ መመረት ከጀመረ ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ ያስቆጠረ ታሪክ እንዳለው ይነገርለታል፡፡ ምናልባትም በኢትዮጵያ ረዥም ዕድሜ በማስቆጠር በቅብብሎሽ ከ110 ዓመታት በላይ የዘለቀ የኢንዱስትሪ ዘርፍ የአረቄና አልኮል ማምረቻ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡ በዚህ መስክ የመጀመርያው የአልኮል ፋብሪካ እንደሆነ የሚነገርለት የሰበታ አረቄ ፋብሪካ የተመሠረተው በ1889 ዓ.ም. እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት የሰበታ የአረቄ ፋብሪካን ጨምሮ በተለያዩ ጊዜያት የተገነቡትን ሌሎች ሦስት የአረቄና የአልኮል ፋብሪካዎች በባለቤትነት የሚያስተዳድረው ብሔራዊ አረቄና አልኮል ፋብሪካ የተባለው የመንግሥት የልማት ድርጅት ነው፡፡

በ1969 ዓ.ም. አራቱ የአረቄና የአልኮል ፋብሪካዎች በደርግ መንግሥት ተወርሰውና በአንድ ድርጅት ተጠቃለው ብሔራዊ አልኮልና ፋብሪካ በሚል ሥያሜ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሲንቀሳቀሱና በተለይ ሦስቱ ቅርንጫፎች እስካሁን ድረስ በአትራፊነት መዝለቅ እንደቻሉ ይነገርላቸዋል፡፡

ይህ የመንግሥት የልማት ድርጅት ከአራቱ ቅርጫፎቹ በአዲስ አበባ ከተማ መካኒሳ አካባቢ የሚገኘውና በጣልያኖች እንደተገነባ የሚነገርለት ፋብሪካው በተለይ ከፍተኛ ምርት የሚመረትበት መሆኑ ተገልጿል፡፡ ይሁንና በ1930 ዓ.ም. የተመሠረተውና አቃቂ ቅርንጫፍ እየተባለ የሚጠራው ፋብሪካ በእርጅና ሳቢያ ከምርት ውጭ በመሆኑ አሮጌ መሣሪያዎቹ ለታሪክ መዘከሪያነት ተቀምጠዋል፡፡ ሰበታ ከተማ ውስጥ የሚገኘው ፋብሪካ የምርት አቅሙ አነስተኛ ቢሆንም፣ ከ79 ዓመታት በኋላም ቢሆን ምርት በማምረት ላይ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የማምረት አቅሙን ለመጨመር የማስፋፊያ ግንባታ እያካሄደ ሲሆን፣ በትግራይ ክልል ማይጨው ከተማ ውስጥ የሚገኘው ቅርንጫፍም በሥራ ላይ ይገኛል፡፡  

ከሌሎቹ ቅርንጫፎች ይልቅ የተሻለ የሚያመርተው የመካኒሳውን ፋብሪካ አቅሙን ለማሳደግ ለማስፋፊያ ሥራ የወጣበት የኢንቨስትመንት ወጪ የአልኮልና የአረቄ ገበያው የደራ እንደሆነ የሚያመላክት ሆኗል፡፡

እያደገ ከመጣው የምርት ፍላጎት አንፃር በመካኒሳው ፋብሪካ ሲካሄድ የቆየውና የተጠናቀቀው የማስፋፊያ ግንባታ የበለጠ ተወዳዳሪ ያደርገዋል ተብሏል፡፡ ብሔራዊ አረቄና አልኮል ፋብሪካ እስከ 1994 ዓ.ም. ድረስ በአገሪቱ ብቸኛ የአረቄና አልኮል አምራች የነበረ ሲሆን፣ ገበያውን ለብቻው ተቆጣጥሮ ቆይቷል፡፡ ከ1995 ዓ.ም. በኋላ ግን የግል ኩባንያዎች ወደዚህ ዘርፍ እየገቡ ሲመጡ፣ መንግሥታዊውን ድርጅት ተወዳዳሪ ወደሚያደርገው የአቅም ግንባታ ሥራ በማካሄድ ተጨማሪ የማስፋፊያ ሥራዎች ውስጥ ገብቷል፡፡

ቅዳሜ፣ ጥር 27 ቀን 2009 ዓ.ም. በመካኒሳ የሚገኘው ፋብሪካ የማስፋፊያ ግንባታ መገባደዱን በማስመልከት የመንግሥት የልማት ድርጅትን ሚኒስቴር ዶ/ር ግርማ አመንቴ በተገኙበት ወቅት እንደተገለጸው፣ አዲስ ለተተከለው ማምረቻ 193 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎበታል፡፡ በሚቀጥለው ዓመት እንደሚጠናቀቁ የሚጠበቁት ሌሎች ግንባታዎችንም እያካሄደ ነው፡፡ የሰበታው ፋብሪካ የማስፋፊያ ፕሮጀክት ሲታከልበትም የድርጅቱ አጠቃላይ የኢንቨስትመንት ወጪ 450 ሚሊዮን ብር ይደርሳል ተብሏል፡፡

የብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኃይለ ማርያም ግደይ እንደገለጹት፣ አዲስ የተተከለው የመካኒሳው ማምረቻ ብቻውን በቀን 18 ሺሕ ሊትር አረቄና አልኮል የማምረት አቅም አለው፡፡ ከማስፋፊያ ግንባታው በፊት በአሮጌ መሣሪያዎች እየታገዘ በቀን ያመርት የነበረው 5,000 ሊትር ብቻ እንደነበርም ተገልጿል፡፡ በሰበታ የተጀመረው የማስፋፊያ ግንባታ ሲጠናቀቅ ደግሞ በሚቀጥለው ዓመት መጨረሻ ላይ የድርጅቱ ማምረቻዎች በቀን የሚኖራቸው ጥቅል የማምረት አቅም 30 ሺሕ ሊትር ይደርሳል፡፡ 18 ሺሕ ሊትር በመካኒሳ፣ ቀሪው 12 ሺሕ ሊትር አረቄና አልኮል በሰበታ ይመረታል፡፡

ድርጅቱ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ከዕቅዱ በላይ በመሥራት ውጤታማ መሆን ችሏል ተብሏል፡፡ እንደ ድርጅቱ መረጃ ከ2003 እስከ 2007 በነበሩት ዓመታት ውስጥ በአማካይ 123 በመቶ ውጤት እያስመዘገበ ተጉዟል፡፡ በ2008 ዓ.ም. 9.3 ሚሊዮን ሊትር የአልኮል መጠጥ አምርቷል፡፡ 88 ሚሊዮን ብር ለማትረፍ አቅዶ 131 ሚሊዮን ብር እንዳተረፈ ተገልጿል፡፡ የዓምና ጠቅላላ ሽያጩ 460 ሚሊዮን ብር እንደነበር የሚያስረዳው ድርጅቱ፣ የዚህ ዓመት ዕቅዱ 10.5 ሚሊዮን ሊትር የአልኮል መጠጦችና 4.3 ሚሊዮን ሊትር ንፁህ አልኮል ማምረት እንደሆነ ይፋ አድርጓል፡፡ ከዚህ ምርት ሽያጭ 508 ሚሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት እየሠራ እንደሚገኝም አስታውቋል፡፡ ድርጅቱ ከ2003 እስከ 2007 ዓ.ም. ድረስ በአማካይ 38.04 ሚሊዮን ብር በየዓመቱ ትርፍ ለማግኘት ቢያቅድም፣ ክንውኑ ግን 166 በመቶ እያደገ ስለነበር በአማካይ 63.01 ሚሊዮን ብር ማትረፍ ችሎ ነበር፡፡

ባለፈው የዕድትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን መጀመሪያ ላይ ማለትም በ2003 ዓ.ም. 22.5 ሚሊዮን ብር ለማትረፍ አቅዶ በአፈጻጸሙ 36.7 ሚሊዮን ብር ለማትረፍ እንደቻለ ድርጅቱ አስታውሷል፡፡ ይህ የትርፍ መጠን በየዓመቱ እያደገ ሄዶ በተለይ በ2007 ዓ.ም. ከዕቅዱ በላይ 104 ሚሊዮን ብር አትርፎ እንደነበር ጠቅሷል፡፡ በዕቅዱ መሠረት የሚታሰበው ትርፍ 64 ሚሊዮን ብር እንደነበር የድርጅቱ መረጃ ያሳያል፡፡

ከታክስ በፊት የተመዘገበው የ104 ሚሊዮን ብር ገቢ፣ ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ ላስቆጠረው ድርጅትና ከ100 ዓመታት በላይ ለቆየው ታሪኩ መዘከሪያ የሚሆን ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ትርፍ ማግኘት መቻሉ ተገጣጥሞሹን አሳምሮለታል፡፡ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን፣ የትርፍ መጠኑ ይበልጥ እያደገ እንደሚሔድ ተገምቷል፡፡ ድርጅቱ ከ2008 እስክ 2012 ዓ.ም. ላሉት አምስት ዓመታት ያስቀመጠው ዕቅድ እንደሚያሳየው፣ የፋብሪካው የሽያጭ መጠን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚደርስ ነው፡፡ ይህም አሁን ካለው የሽያጭ መጠኑ በእጥፍ የሚጨምር ነው፡፡   

ፋብሪካው የምርት መጠን ከማሳደግ ባለፈ የራሱን G+10 ሕንፃ እና የፍሳሽ ማጣሪያ ማሽን ተከላም እያከናወነ ነው፡፡ አዳዲስ ምርቶችንም ለገበያ እንደሚያበቃ አስታውቋል፡፡ በተለይ ቮድካ ለማምረት የሚያስችለውን ማሽን በመግዛት ተከላውን አጠናቆ የሙከራ ምርት እንደጀመረ አቶ ኃይለ ማርያም ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

‹‹ብሔራዊ ቮድካ›› የሚል መጠሪያ ያለው የቮድካ ምርት በደንበኞች ቅምሻ ተደርጎበት ተቀባይነት ማግኘቱ የገለጹት አቶ ኃይለ ማርያም፣ ገበያ ላይ ያልዋለው ለቮድካው ማሸጊያ ጠርሙስ እስኪዘጋጅለት ነው ብለዋል፡፡ አሁን ፋብሪካው በሚጠቀምበት ጠርሙስ አሽጎ ላለማውጣት ሲባል ለገበያ አልቀረበም ብለዋል፡፡ አዲስ የጠርሙስ ዲዛይን ተመርጦና በህንድ ተመርቶ በቅርቡ ወደ አገር ውስጥ የሚገባ በመሆኑ፣ ብሔራዊ ቮድካ በጥቂት ወራት ውስጥ ለገበያ ይቀርባል ተብሏል፡፡ ፋብሪካው ቮድካውን ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ምርቶቹንም በአዲስ ጠርሙስ አሽጎ እንደሚያቀርብ  ያመለከቱት አቶ ኃይለ ማርያም፣ አሁን ገበያ ላይ ያሉ ጠርሙሶች እንደሚቀየሩ ገልጸዋል፡፡

ብሔራዊ አረቄና አልኮል ፋብሪካ ለ110 ዓመታት በዘለቀው ታሪክ በአርመኖችና በተለያዩ የግል ኩባንያዎች ባለቤትነት ሥር ሲተዳደር ቆይቷል፡፡ በ1969 ዓ.ም. በደርግ መንግሥት አራቱ ፋብሪካዎቹ በመወረሳቸው በአንድ ተጨፍልቀው ሲተዳደሩ ነበር፡፡ ከደርግ በኋላም በኢሕአዴግ መንግሥት ባለቤትነት ሥር የቆየው ይህ ፋብሪካ፣ የተከፈለ ካፒታሉ 12.2 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ከ450 በላይ ሠራተኞች እያስተዳደረ ሲገኝ፣ ጂንን ጨምሮ ከአሥር በላይ የተለያዩ የአረቄ ምርቶች፣ ንፁህ አልኮልና የእሳት አደጋ አልኮል ያመርታል፡፡ ከድርጅቱ የአረቄ ምርቶችም ግማሽ ያህሉ አዲስ አበባ ከተማ እንደሚሸጡ ታውቋል፡፡

  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች