የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሰባት የሙስሊም አገሮች ዜጎች ላይ የጣሉትን አሜሪካ የመግባት ጊዜያዊ ገደብ የአገሪቱ ፍርድ ቤት ውድቅ ማድረጉን ተከትሎ፣ ትራምፕ የአገሪቱን ሕግ ተርጓሚ አካል አጣጥለዋል፡፡ በአሜሪካ ታሪክ መሪዎች ፍርድ ቤቶችን ሲያጣጥሉ ተሰምቶ የማይታወቅ ቢሆንም፣ ያሻቸውን የሚናገሩት ትራምፕ ‹‹አሜሪካ ላይ ለሚመጣ ጦስ ፍርድ ቤቶች ተጠያቂ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡
የአሜሪካ ፍርድ ቤት ዳኛ ጀምስ ሮባርት የትራምፕ የጉዞ ማዕቀብ በመላ አገሪቱ ተግባራዊ እንዳይደረግ ከወሰኑ በኋላ ዕግድ የተጣለባቸው የሱዳን፣ የሶማሊያ፣ የኢራቅ፣ የየመን፣ የሊቢያ፣ የኢራንና የሶሪያ ዜጎች ወደ አሜሪካ የገቡ ቢሆንም፣ በድንበርና በኤርፖርቶች አካባቢ የተፈጠረው መደናገር አሁንም አልጠራም፡፡
የዳኛ ሮባርትን ውሳኔ ተከትሎ ያለወትሯቸው አፋጣኝ ምላሽ ያልሰጡት ትራምፕ፣ ዘግይተውም ቢሆን ‹‹አገራችንን ከባድ አደጋ ውስጥ የጣለውን ዳኛ ውሳኔ ማመን ያቅተኛል፡፡ አንድ ነገር ከተፈጠረ እሱንና የአገሪቱን የፍትሕ ሥርዓት ኮንኑ፡፡ ሰዎች እየገቡ ነው፡፡ መጥፎ!›› ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ማስፈራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የዳኛ ሮባርት ትዕዛዝ ‹‹ሞኞች የሚያደርጉት ነው፤›› ያሉት ትራምፕ፣ ‹‹ዳኛ መሳይ›› ሲሉም ዘልፈዋቸዋል፡፡ እሳቸው ይህንን ይበሉ እንጂ የፍትሕ ሥርዓቱ አልተበገረም፡፡
ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ፍርድ ቤት ያገደውን የትራምፕ የጉዞ ማዕቀብ መልሶ ተግባራዊ ለማድረግ የትራምፕ አስተዳደር ለአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያቀረበው አቤቱታ በወቅቱ ተቀባይነት ባያገኝም፣ አሁን ግን አግኝቷል፡፡ የጉዞ ማዕቀቡን የተቃወሙ ግዛቶችና የትራምፕ አስተዳደርም በጉዞ ማዕቀቡ አስፈላጊነትና አላስፈላጊነት ላይ መከራከሪያቸውን እንዲያቀርቡ ተጠይቀዋል፡፡
ከጉዞ ገደቡ ደጋፊዎችና ተቀናቃኞች ወገን መከራከሪያ ነጥቡ ቀርቦ በአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ እስኪያገኝ ድረስም፣ አሜሪካ እንዳይገቡ ገደብ የተጣለባቸው አገሮች ዜጎች ሕጋዊ ቪዛ ይዘው አሜሪካ መግባት ይችላሉ፡፡
ትራምፕ በተከታታይ ባደረጉት የትዊተር መልዕክት ግን፣ ‹‹የአገር ውስጥ ደኅንነት ክፍሉ አሜሪካ በሚገቡ ሰዎች ላይ ጥብቅ ፍተሻ እንዲያደርግ አዝዣለሁ፣ ፍርድ ቤቶች ሥራችንን እያደናቀፉብን ነው፤›› ብለዋል፡፡
ወደ አሜሪካ በድንበር በኩል የሚገቡ ሰዎች በድንበር ጠባቂና በጉምሩክ ፖሊሶች እንዲመረመሩ፣ በአሜሪካ ያሉት ደግሞ በአሜሪካ በቋሚነት መሥራት የሚያስችላቸው የመኖሪያ ፈቃድ መያዝ እንዳለባቸው፣ ከዚህ ቀደም የገቡ ስደተኞችም ሆኑ በተለያዩ የሥራ አጋጣሚዎች የጥቂት ጊዜያት ቪዛ አግኝተው አሜሪካ የቀሩና ሕጋዊ መኖሪያ የሌላቸው ዜጎችን የሚመለከተውን የትራምፕ ትዕዛዝ የዋሽንግተንና የሚኒሶታ ግዛቶች ተቃውመውታል፡፡
ዕገዳው ሕገ መንግሥታዊ አይደለም ያሉት ግዛቶቹ፣ ማንኛውም ሰው ወደ አሜሪካ ለመግባት የሚያስችል ሰነድ ካለው ያለምንም ውጣ ውረድ ሊገባ ይችላልም ብለዋል፡፡ ‹‹በሙስሊሞች ላይ ያነጣጠረና የሃይማኖት ነፃነት የሚጋፋ፤›› ሲሉም የትራምፕን ውሳኔ ኮንነውታል፡፡
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ከግዛቶቹና ከዋይት ሐውስ የሚቀርቡ መከራከሪያዎችን እንደሚያይ የገለጸ ሲሆን፣ ከወዲሁ ደግሞ የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰነዘሩ ነው፡፡ የደኅንነት ጉዳይን መወሰን ለፕሬዚዳንት የተሰጠ ሥልጣን ቢሆንም፣ ዳኛው ሮባርት የፕሬዚዳንት ትራምፕን ሥልጣን በመጋፋት ውሳኔ አሳልፈዋል፣ አሜሪካ ማን መግባትና መኖር እንደሚችል መወሰን የሚችለው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ብቻ ነው የሚሉ አስተያየቶችም ተሰምተዋል፡፡
ዳኛው ካስተላለፉት ውሳኔ ጎን ለጎንም ትራምፕ በዳኛውና በአገሪቱ ፍትሕ ሥርዓት ላይ የሰነዘሩት ዘለፋ ተተችቷል፡፡ ዴሞክራቶቹም ሆኑ ሪፐብሊካኖች ትራምፕ በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ የሰነዘሩትን ትችት ሲያወግዙ ዴሞክራቱ ሴናተር ፓትሪክ ሊይ፣ ‹‹ሚስተር ትራምፕ ሕገ መንግሥታዊ ቀውስ ለመፍጠር የፈለገ ይመስላል፤›› ሲሉ የሪፐብሊካን ሴኔት መሪ ሚች ማክኮኔል በበኩላቸው፣ ‹‹ዳኞችን በግለሰብ ደረጃ መውቀስን ማስወገድ ጥሩ ነው፤›› ብለዋል፡፡
እ.ኤ.አ. ከ2004 በፕሬዚዳንት ጆርጅ ዎከር ቡሽ ዘመን ጀምሮ በፌዴራል ፍርድ ቤት ያገለገሉት ሚስተር ሮባርት ያሳለፉት ውሳኔ፣ የትራምፕ አስተዳደር ለአሜሪካ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ባቀረበው ይግባኝ እስኪቀለበስ ድረስ ሕጋዊ ቪዛ ይዘው አሜሪካ ለሚገቡ የሰባቱ አገሮች ዜጎች መልካም ዜና ሆኗል፡፡ ከእነዚህ አገሮችም ቪዛ የያዙና በትራምፕ ውሳኔ ሳቢያ ባሉበት የቆዩ አሜሪካ መግባት ጀምረዋል፡፡
ትራምፕ ዳኛንና የዳኛ ውሳኔን ሲያንቋሽሹ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም፡፡ በምርጫ ቅስቀሳው ወቅት ከሜክሲኳዊ ቤተሰቦቻቸው በኢንዲያና የተወለዱትና በአሜሪካ ዲስትሪክት ዳኛ የነበሩት ጎንዛሎ ከርል በትራምፕ ዩኒቨርሲቲ ላይ ያሳለፉትን ውሳኔ አስታውሰው፣ ‹‹የሜክሲኮ ዝርያ ስላለው ነው፡፡ በአሜሪካና በሜክሲኮ ድንበር ግንብ እንገነባለን፤›› ብለውም ነበር፡፡
ከጥር 20 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ በትራምፕ ትዕዛዝ የኢራን፣ የኢራቅ፣ የሊቢያ፣ የሶማሊያ፣ የሱዳን፣ የሶሪያና የየመን ዜጎች ቪዛ ቢኖራቸውም ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ መከልከላቸው፣ በኋላም በፍርድ ቤት ትዕዛዝ የትራምፕ ገደብ ለጊዜው መታገዱ አሜሪካን ለውስጥም ለውጭም ፖለቲካዊ ትችት ዳርጓታል፡፡ የትራምፕ ውሳኔ በአገር ውስጥ አሜሪካ ይበልጥ ለጥቃት እንድትዳረግ፣ ከአገር ውጭ ደግሞ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶቿ እንዲሻክሩ ያደርጋልም ተብሏል፡፡
ትራምፕ ውሳኔውን በሰባቱ አገሮች ዜጎች ላይ ያሳለፉት፣ አሜሪካን ከሽብር ጥቃት ለመከላከልና የአገሪቱን ደኅንነት ለማስጠበቅ ነው ማለታቸው ይታወሳል፡፡ ደጋፊዎቻቸውም ከነዚህ አገሮች የሚመጡ ሰዎች ለአሜሪካ ሥጋት ናቸው በማለት አስተያየት ሲሰጡ ተሰምተዋል፡፡ ሆኖም አሜሪካ ውስጥ በደረሱ የሽብር ጥቃቶች፣ የታገዱትን አገሮች ዜግነት የያዙ ሰዎች ተሳታፊ ሆነው አያውቁም፡፡ በአሜሪካ የትራምፕን ውሳኔ በማጣጣል ተቃውሞ የወጡ አሜሪካውያንም፣ ውሳኔውን አንቀበልም ለማለት አንዱ ምክንያታቸው ንፁኃን ስደተኞች በትራምፕ ግዴለሽ ውሳኔ ተጎድተዋል የሚል ነው፡፡
የኢራን መንፈሳዊ መሪ አያቶላህ አሊ ካሚኒ ደግሞ፣ ‹‹ትራምፕ እውነተኛዋን አሜሪካ የገለጡ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡
በአሜሪካ የሚገኙት አፕል፣ ጉግልና ማይክሮሶፍትን ጨምሮ 100 የሚጠጉ ትላልቅ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችም ትራምፕ በስደተኞች ላይ ያሳለፉትን ዕግድ በመቃወም፣ ‹‹የአሜሪካን የንግድ ምኅዳር ይጎዳል፤›› በማለት በሕግ ሊጠይቁ መሆኑ ተሰምቷል፡፡
ትራምፕ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ለመሆን የምረጡኝ ዘመቻ ከጀመሩ ጊዜ አንስቶ ውዝግብ የሚያስነሱ ሐሳቦችን ሲሰነዝሩ፣ ፕሬዚዳንት ከሆኑ በኋላም አንዳንዶች አወዛጋቢና የማያሠራ የሚሏቸውን ውሳኔ ሲያሳልፉ ተስተውለዋል፡፡
በአሜሪካ ነፃና ፍትሐዊ ውሳኔ ይሰጣል የሚባለውን የፍትሕ ሥርዓት ከመኮነን አንስቶ ሙስሊም ከሚበዙባቸው አገሮች ስደተኞች ወደ አሜሪካ መግባት የለባቸውም ሲሉም ተደምጠዋል፡፡
አስተያየት ሰጪዎችም ትራምፕ የአገሪቱን ሕገ መንግሥት ጥሰዋል፣ የደኅንነት ኤጀንሲዎችን አንቋሸዋል ይሏቸዋል፡፡ ሚዲያው በትራምፕ ላይ የሚያቀርበውን ትችትም ሆነ ቅሬታ ‹‹ሚዲያዎች ታማኞች አይደሉም፤›› በማለት በተደጋጋሚ ሲናገሩ ተሰምተዋል፡፡ የትራምፕን ውሳኔና አካሄድ ያስተዋሉ የፖለቲካ ተንታኞችም በዴሞክራሲያዊነቷ የምትታወቀውን አሜሪካ ወደ ግዞት ዓለም የሚያሸጋግሩ መሪ ሲሉ ትራምፕን ገልጸዋቸዋል፡፡ አሜሪካን ዴሞክራሲያዊ ከሚያስብሉ ሥርዓቶች አንዱ ፍርድ ቤቶች ፕሬዚዳንቱን ጨምሮ ጎምቱ ባለሥልጣናትን ተጠያቂ ማድረጋቸው፣ ነፃና ፍትሐዊ መሆናቸው ይገኝበታል፡፡ ራሳቸው ትራምፕ የፍትሕ ሥርዓቱንና ዳኞችን ቢዘልፉም፣ ዞሮ ዞሮ ይግባኝ ያሉት ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ነው፡፡