አቶ ስሜነህ ቃበቶ ይባላሉ፡፡ በዝዋይ ሐይቅ ካሉት አምስት ገዳሞች ደብረ አብርሃ በሚባለው ተወልደው ያደጉ ሲሆን በሐይቁ ላይ ያለውን የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ የአቅማቸውን ለማበርከት ሞክረዋል፡፡ ተሰማርተውበት ከነበረው ንግድ ወደ ጀልባ ሥራ በመዞር ብዙ ጀልባዎችን ሠርተዋል፡፡ አሁንም ጀልባዎችን በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ የእንጨትና የሞተር ጀልባዎች የሚሠሩትን አቶ ስሜነህን በሥራቸው ዙሪያ እንዲሁም ወደፊት ሊሠሩ ስላቀዱት ታምራት ጌታቸው አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- የት ተወለዱ ዕድገትዎስ ምን ይመስላል?
አቶ ስሜነህ፡- የተወለድኩት ከአዲስ አበባ 160 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ዝዋይ ከተማ ዝዋይ ሐይቅ ላይ ሲሆን፣ በሐይቁ ካሉት አምስት ደሴቶች ደብረ አብርሃ (አይሠት) በሚባለው ውስጥ ነው፡፡ ውልደቴም ከዛይ ማኅበረሰብ ሲሆን የቄስ ትምህርት በገዳሙ በመማር፣ ዘመናዊ ትምህርቴን ደግሞ በአካባቢው ከነበረው ስዊድን ሚሽን አዳሪ ትምህርት ቤት ተከታትያለሁ፡፡ የተግባርና የቴክኒክ ትምህርቴን እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያጠናቀቅኩት በዝዋይና በመቂ ከተማ ነው፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን እንዳጠናቀቅኩ ወዲያው ወደ ዓሳ ማጥመድና መንገድ ነበር ሥራዬ፡፡ ገዳሙንም በመልቀቅ በከተማዋ መኖር ጀመርኩ፡፡ በደርግ ዘመነ መንግሥት ከሐይቁ ዓሳ አጥምዶ መሸጥ ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግበት ተግባር ስለነበር ፈቃድ በማውጣት ወደ አዲስ አበባ በመላክ ሥራውን በደንብ መሥራት ቻልኩ፡፡
ሪፖርተር ፡- ጀልባ ለመሥራት ምን አነሳሳዎት ንግዱ አላዋጣዎትም?
አቶ ስሜነህ፡– ሥራው ለእኔ በጣም አዋጭ ነበር፡፡ ምክንያቱም እንደዛሬው ሰዎች አልበዙበትም፡፡ የምንሠራው ጥቂት ሰዎች ነበር፡፡ ጀልባ እንድሠራ ያነሳሳኝ እኔ ያደግኩበት አካባቢ በሐይቅ የተከበቡ ደሴቶች ላይ ነው፡፡ እኔን ጨምሮ እዚህ የሚኖሩ ማኅበረሰቦች ከመሬት የራቁ በመሆኑ ከፍተኛ ትራንስፖርት ችግር በመኖሩ ዕድገታቸው ኋላ ቀር ነበር፡፡ ሕክምና ለማግኘት አስቸጋሪ ስለነበር ሟች ይበዛ ነበር፡፡ በተለይ ደሴቶቹ የተራራቁ በመሆናቸው መረዳዳት እንኳን አስቸጋሪ ነበር፡፡ ሌላው በነዚህ ገዳማት በርካታ ጥንታዊ ቅርሶች ያሉ ሲሆን፣ ነዋሪው ማኅበረሰብ በራሱ ፈቃድ ነው የሚጠብቀው፡፡ ታዲያ ሁሌም ዓሳ ለማጥመድ ወደ ሐይቁ ስመላለስ ችግራቸውን በመመልከት ሐይቁ ላይ ለሚኖረው ኅብረተሰብ ትልቅ ችግር የሆነውን የውኃ ላይ ትራንስፖርት ላይ ብሠራ ነገሮችን እንደማሻሻል በማሰብ ነው የጀመርኩት፡፡
ሪፖርተር ፡- ጀልባ ለመሥራት ዕውቀትና ልምድ የሚጠይቅ ይመስለኛል አደጋ እንኳን ቢደርስ በቦታው ቶሎ ለመድረስ ስለሚያስቸግር እንደዚህ ያሉ ነገሮችን ከግንዛቤ ማስገባት አላስፈለገም?
አቶ ስሜነህ፡- በመጀመሪያ የባህር ላይ ትራንስፖርትን ስቃዩን አውቀዋለሁ፡፡ ነገር ግን ደግሞ የተግባርና የቴክኒክ ተማሪ መሆኔ መነሻ ሆኖኛል፡፡ ከዛም በማንበብ የመርከብና የጀልባዎችን ንድፍ ዲዛይን እመለከት ነበር፡፡ ለአካባቢው እንዲመች በማድረግ የመጀመሪያዋን የእንጨት ጀልባ በ1984 ዓ.ም. ለወንድሜ በመሥራት ሙከራዬ በትክክል ተሳካ፡፡ ለእሱ የሠራሁት የሰው ማጓጓዣ ሲሆን፣ ሌላ የዓሳና የዕቃ መጫኛ ጨምሮ አሠራኝ፡፡ የእሱን እያዩ ለ16 ግለሰቦችና ለ20 ማኅበራት በጠቅላላው 36 የሰው ማጓጓዣ፣ ለዓሳ ማጥመድ፣ እንዲሁም የዕቃ ማጓጓዣ የሚሆኑ የእንጨት ጀልባዎችን በመሥራት ለኅብረተሰቡ አቀረብኩ፡፡ ስለዚህ ያለምንም ተጨማሪ ዕውቀት በመሥራቴ እንደልብ ባይሆንም የደሴቷ ነዋሪዎች መንቀሳቀስ ቻሉ፡፡ የሐይቁ ላይም ትራንስፖርት መሻሻል አሳየ፡፡
ሪፖርተር፡- መሥሪያ የሚሆን ግብዓትስ ከየት ነው የሚያገኙት በዲዛይን ስህተት ይሁን በአጠቃቀም እስካሁን በሠሩዋቸው ጀልባዎች ላይ የደረሰ አደጋ የለም?
አቶ ስሜነህ፡- ከአጠቃቀም ጉድለት የደረሰ አንድ አደጋ አስታውሳለሁ፡፡ በተረፈ አላጋጠመኝም፤ ምክንያቱም ጀልባዎቹ ሲሠሩ ከራሳቸው ክብደት ውጪ እንደየአገልግሎቱ የመጫን አቅማቸው በምን ዓይነት የአየር ፀባይ እንደሚሄዱ ይለጠፍባቸዋል፡፡ ጀልባ አንደኛው ትምህርት እየወሰድኩ ነው የምሠራው፡፡ ሌላው ጊዜያቸውን ጠብቀው ይታደሳሉ በተለይ ውኃው የሚያገኘውን የጀልባ ክፍል የቅርብ ክትትል ይደረግለታል፡፡ ምክንያቱም ወደ ጀልባዋ ውኃ ገባ ማለት አደጋን መጥራት ማለት ነውና፡፡
ሪፖርተር ፡– ከባህላዊ ጀልባዎች የሞተር ጀልባዎች ለባህር ላይ ጉዞ ተመራጭ እንደሆኑ የአካባቢ ተጠቃሚዎች ይገልጻሉ፡፡ ይህንን ፍላጎት ለማሟላት ቶሎ ቶሎ መሥራት ይቻላል?
አቶ ስሜነህ፡- አንድ ጀልባ ሙሉ በሙሉ ሠርቶ ለማጠናቀቅ አንድ ወር ይፈጃል፡፡ እኔ አሁንም የምሠራው በግቢዬ ውስጥ ነው፡፡ የምጠቀምበትም ማሽን መስኮትና በር በምሠራበት ማሽን ነው፡፡ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ የመጣው የቁሳቁስ ዋጋ እንደልብ ሊያሠራኝ አልቻለም፡፡ ካፒታልም ስለሌለኝ በተሰጠኝ ቀብድ ነው ሥራውን የምጀምረው፡፡ ዛሬ የሚሠሩት ጀልባዎች ከ50-60 ሰው የመጫን አቅም ያላቸው፣ ለበርካታ ዓሳ አጥማጆች፣ እንዲሁም ብዙ ዕቃ ሊያጓጉዙ የሚችሉ ናቸው፡፡ እንደ ባለቤቱ ፈቃድ በሚገጠምላቸው ሞተር ፍጥነታቸውም የተለያየ ቢሆንም ከባህላዊዎቹ እጥፍ ይፈጥናሉ፡፡ የአገልግሎት ዘመናቸውም ቢሆን እድሳት እየተደረገላቸው ከአሥር እስከ 15 ዓመት አገልግሎት እየሰጡ ይቆያሉ፡፡ በዝዋይ ሐይቅ ላይ አሁን ከሚታዩት በርካቶቹ በእኔ የተሠሩ ናቸው፡፡
ሪፖርተር ፡- በሐይቁ ላይ ከሚታዩት ጀልባዎች ብዙዎች የአደጋ መከላከያ መንሳፈፊያ ልብስ የላቸውም፤ አደጋ ቢመጣ እንዴት ነው ሊከላከሉ የሚችሉት?
አቶ ስሜነህ፡- እኔ በመሠረቱ በዋናነት የምሠራው ጀልባውን ነው፡፡ በጀልባ ላይ ማዕበል ቢመጣ፣ ውኃ ወደ ውስጥ ገብቶ ጉዳት እንዳያደርስ መከላከያ ይሠራለታል፡፡ ሚዛን እንደጠበቀ በፍጥነት እንዲጓዝ ከአደጋ የጸዳ ጀልባ ማዘጋጀት ነው፡፡ ሁለተኛው ልክ እንደ እንጨት ጀልባዎች ሁሉ የሞተር ጀልባዎችም ላይ ስለጀልባዋ ሙሉ መረጃ የሚሰጥ ጽሑፍ ይለጠፍበታል፡፡ እዚህ ድረስ የእኔ ኃላፊነት ሲሆን፣ ይህን ብዬ ግን አልተውም፡፡ ከሠራሁላቸው በኋላ በተለጠፈው መሠረት እንዲጠቀሙበት እንዲሁም በሚጭኑት ሰው ልክ የአደጋ ማንሳፈፊያ እንዲያዘጋጁ በየጊዜው ውኃ የጀልባው የሚነካው አካል እንዲታደስ እንዲያደርጉ ትምህርት እሰጣለሁ፡፡ ግን ተግባራዊ አያደርጉም፡፡ የ40 ሰው መጫኛ ጀልባ ላይ 60 ሰው የሚጭኑም አሉ፡፡ ይህንን ባለማክበር የደረሰም አደጋ ነበር፡፡
ሪፖርተር፡- መቼ ነው አደጋው የተፈጠረው የደረሰው ጉዳትስ?
አቶ ስሜነህ፡- አደጋው የተከሰተው በ1998 ዓ.ም. ታኅሣሥ ወር ላይ ነበር፡፡ በወቅቱ ጀልባዋ ለዓሳ ማጥመጃና ማጓጓዥ የተሠራች ነበረች፡፡ ባለቤቱ ግን ዓሳውንም፣ ሰውም፣ እንዲሁም በላይዋ ላይ የእንጨት ጀልባ ጭኖ ነበር የሚጓዘው፡፡ ከጀልባዋ አቅም በላይ የተጫነች በመሆኗ ሐይቁ ላይ በተነሳው ትንሽ ማዕበል የሰዎች ሕይወት ሊያልፍ ችሏል፡፡ እንግዲህ መጀመሪያ ላይ የመከላከል ሥራ ነው መሠራት ያለበት፡፡ ይህን ሁሉ አልፎ አደጋው ቢከሰት ደግሞ እንደድሮው ሳይሆን አሁን ጀልባዎች በሐይቁ ላይ በብዛት ስለሚንቀሳቀሱ መተያየት ይችላሉ፡፡ እሱም ካልሆነ ደግሞ ሞባይል በመጠቀም በአካባቢው ያሉ ጀልባዎች ቶሎ ስለሚደርሱ አደጋው ሳይከፋ መድረስ ይቻላል፡፡
ሪፖርተር፡- ይህን ሥራ ሲሠሩ ያገኙት ድጋፍ አለ? ፈቃድስ አግኝተዋል?
አቶ ስሜነህ፡- ይህን ሥራ ከጀመርኩ ከሃያ ዓመት በላይ ሆኖኛል፡፡ 36 ባህላዊ ጀልባዎች፣ ከ30 በላይ ደግሞ የሞተር ጀልባዎችን ሠርቼ ለኅብረተሰቡ አቅርቤያለሁ፡፡ እነዚህን እየሠራው የዕውቅና ጥያቄ እንዲሁም የማምረቻ ፈቃድ፣ ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ጀምሮ እስከታችኛው ድረስ ጥያቄ አቅርቤ እስካሁን መልስ አላገኘሁም፡፡ በተጨማሪም ከየትኛውም የመንግሥት አካል ምንም ነገር አላየሁም፡፡ ሥራዬንም አይቶ አስተያየት የሰጠኝም የለም፡፡ ለወደፊት ይመጣሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- አንዳንዶች የጀልባ ዋጋ እየጨመረብን ነው ይላሉ፤ አንድ ጀልባ በምን ያህል ነው የሚሠሩት?
አቶ ስሜነህ፡- እኔ ይህን ሥራ ስጀምር ማኅበረሰቡ እንዲያገለግል እንጂ ገንዘብ ለማግኛ ብዬ አልነበረም፡፡ ቀስ በቀስ ግን ሥራው መኖሪያዬ እየሆነ ስለመጣ በአነስተኛ ዋጋ እጠይቃለሁ የምሠራው በቤቴ በመሆኑ ከሚሠራበት ዕቃና ትንሽ የጉልበቴን በመጨመር ነው የማስከፍለው፡፡ አሁንም በሐይቁ ላይ ትራንስፖርት ተስፋፍቶ ማየት እንጂ እየነገድኩ አይደለም፡፡ ተወደደ የተባለውም ከዓመት ዓመት እየጨመረ በመጣው የዕቃዎች ውድነት እንጂ ለራሴ ጨምሬ አይደለም፡፡
ሪፖርተር ፡- እስካሁን በሠሩት ኅብረተሰብ ተጠቃሚ ሆኗል ብለው ያስባሉ? ወደፊትስ ምን አስበዋል?
አቶ ስሜነህ፡- እኔ ተሳክቶልኛል ብዬ አስባለሁ፡፡ የሐይቁን የትራንስፖርት ችግር ቢያንስ 60 በመቶ ፈትቻለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡ ማረጋገጫው ምንድነው ቢባል፣ በሐይቁ ላይ የሚገኙ ደሴቶችና ገዳሞችን ለማየት የሚመጡ ቱሪስቶች መጨመር፣ ሌላው በተፈለገ ጊዜ ሲወጣ ትራንስፖርት መኖሩና በኮንትራትም መገኘቱ ነው፡፡ ለወደፊት በልጄ ረዳትነት እንዲሁም በቤቴና በተለመደ ማሽን መሥራት ይከብደኛል፡፡ መረዳዳት ያስፈልገኛል ብዬ አምናለሁ፡፡ እነዚህ እየተስተካከሉ የሚሄዱ ከሆነ ጣራ፣ መስኮት ምቹ መዝናኛ ያላቸው ቅንጡ ጀልባዎችን መሥራት እፈልጋለሁ፡፡ በቅርቡ ግን እሠራዋለሁ ብዬ የማስበው፣ ፈጣን የጀልባ አምቡላንስ ነው፡፡ አሁንም በአካባቢው የሚኖሩ ማኅበረሰቦች የሕክምና አገልግሎት የሚያገኙት ሐይቅ አቋርጠው ነው፡፡ ስለዚህ ሙሉ የሕክምና መስጫ መሣሪያ የተገጠመለት ጀልባ ሆኖ ቢያንስ ሐይቁን እስከሚሻገሩ ሕክምና እያገኙ ይሄዳሉ፡፡ ሐይቁንም በደቂቃዎች ስለሚያቋርጡ ቶሎ ምድር ወዳለው ሕክምና መስጫ ያደርሳሉ ማለት ነው፡፡