Friday, June 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልትኩረት የሚሻው ዝዋይ ሐይቅና ቅርሶቹ

ትኩረት የሚሻው ዝዋይ ሐይቅና ቅርሶቹ

ቀን:

የዘንድሮ የሁለት ሺሕ ዘጠኝ ዓመት አንድ መቶ ሃምሳ ቀናት ተገባደው ስድስተኛው ወር ተይዟል፡፡ የካቲት ወርም ብቷል፡፡ የተሰናበተው ወርኃ ጥር ከሌሎች ወራት ለየት የሚያደርገው በተለይም ከገበሬው ጋር ተያይዞ የዕረፍትና የፈንጠዝያ ጊዜ መሆኑ ነው፡፡ ክረምቱን (ከሰኔ 26 – መስከረም 25) በእርሻ አሳልፎ፣ በመፀው (ከመስከረም 26 – መስከረም 25) ውስጥ በሚገኘው የመኸር ጊዜ ፍሬውን ይሰበስብበታል፡፡ በጋውን (ታኅሣሥ 26 – መጋቢት 25) ሲያያዘው ጥርና ጥምቀት፣ ጥርና ሠርግ ተያይዘው ሲደርሱለት ዘና ይልበታል፡፡ ብሂልን ከባህል እያዛመደ በዓላቱን ያከብርበታል፡፡

በኢትዮጵያ ክርስቲያናዊ ትውፊት ወርኃ ጥር ዘመነ አስተርዕዮ (የመገለጥ ዘመን) መሰኘቱ ከክርስቶስ ኢየሱስ በዓለ ጥምቀት እስከ ቃና ዘገሊላ፣ በአስተርዕዮ ዘመን እስከሚውለው ቅድስት ማርያም በዓል ድረስ ይዘልቃል፡፡

ወርኃ ጥር በተለይ በማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች የካበተ ልዩ ልዩ በዓላትን የያዘ በመሆኑ የብዙዎቹን ቀልብ እንደያዘ ከዘመን ወደ ዘመን እየተላለፈ የመጣ ነው፡፡ ዘንድሮ ከነበረው አከባበር መሳ ለመሳ የጥምቀትን በዓል (ኤጲፋንያ) በማይዳሰስ ቅርስነት በዓለም ደረጃ ወካይ ቅርስ ሆኖ እንዲዘመገብ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩ ይፋ ተደርጓል፡፡

- Advertisement -

ፍሬ ጉዳዩን የሚያስተባበረው የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣንና ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራቸውን ጀምረዋል፡፡ ለማስመረጫ ሰነዱ ግብአት እንዲሆን በጎንደርና በአዲስ አበባ፣ በአክሱምና በላሊበላ በሚገኙ የጥምቀት ባሕሮች ስነዳው እንደሚከናወን ተገልጿል፡፡

ይሁን እንጂ ከሁለቱ ተቋማት ያልተጠቀሰው በአገሪቱ በዓለ ጥምቀቱ ከሚከበርባቸው ሥፍራዎች ለየት ያለ ገጽታ ያለው በዝዋይ ሐይቅ ከሚገኙ ገዳማት መካከል የሐይቅ ላይ ጉዞ መኖሩ ነው፡፡ ታቦተ ሕጉ እንደሌሎች በመሬት ላይ ሳይሆን በጀልባ መጓዙ ዓይነተኛ መለያው ነው፡፡ በዐሥረኛው ምታመት በነበረው ስደት ሳቢያ ከአክሱም የወጣችው ታቦተ ጽዮን ተቀምጣበት የነበረው ዝዋይ ሐይቅ የበርካታ ጥንታውያን የግእዝ ብራናዎችና ንዋየ ቅድሳት መኖሪያ ነው፡፡   

ዝዋይ ሐይቅ ሲገለጽ

ከአዲስ አበባ ደቡብ 160 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው፣ ከኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ ሐይቆች አንዱ የሆነው ዝዋይ ሐይቅ በውስጡ አምስት ደሴቶች አሉ፡፡ በደሴቶቹ ልክ ያሉት አምስት አብያተ ክርስቲያናት፣ የገሊላ ካህናተ ሰማይ፣ የደብረ ሲና ድንግል ማርያም፣ የጠዴቻ አብርሃም፣ የፉንዱሮ አርባዕቱ እንስሳ፣ የደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ገዳም ሲሆኑ፣ የሚገኙትም በምሥራቅ ሸዋና በአርሲ አህጉረ ስብከት ሥር ነው፡፡

ዮዲት ‹‹ጉዲት›› በዐሥረኛው ምታመት በ970 ዓ.ም. ግድም በነገሠችበት ወቅት የአክሱም ካህናትና ምእመናን ታቦተ ጽዮን ጨምሮ የተለያዩ ንዋያተ ቅድሳትን ብራናዎችን ይዘው የተጓዙት ወደ ዝዋይ ሐይቅ ነበር፡፡ ባንዳንድ ድርሳናት እንደተመለከተው ታቦተ ጽዮን ለአራት አሠርታት ያህል ቆይቶ ቢመለስም አጅበው ከመጡት መካከል በዚያው ቀርተዋል፡፡ ባሁኑ ጊዜ ዛይ ብሔረሰብ በመባል የሚታወቁት እነሱው ናቸው፡፡ ዛይኛ ከግእዝ፣ ትግርኛና ጉራጊኛ ጋር የሚመሳሰል የኢትዮ ሴማዊ ልሳናት ቤተሰብ መሆኑም ይጠቀሳል፡፡

ደሴቶቹ በዘመነ አክሱምም ሆነ ከዘመነ ዛጉዌ (ከ11ኛው እስከ 13ኛው ምታመት) ቀጥሎም በነበሩት ተከታታይ ዘመናት ወደ ዝዋይ የተሰደዱ አበው ሊቃውንትና ካህናት ይዘዋቸው የሄዱና በዚያውም ያዘጋጇቸው ልዩ ልዩ መጻሕፍት ማዕከል ሆነው አገልግለዋል፡፡

‹‹የቤተክርስቲያን መረጃዎች›› ላይ እንደተመለከተው፣ በአፄ ዓምደ ጽዮን ዘመነ መንግሥት (1307-1336) ብዙ አባቶች ወደ ዝዋይ ደሴቶች ተግዘው ነበር፡፡ ገድለ አቡነ ፊልጶስ ‹‹ባሕረ ዞይ›› በሚለው ደሴቱ ውስጥ፣ በንጉሡ ከተጋዙት መካከል አባ አኖሬዎስ፣ አባ በጸሎተ ሚካኤልና አባ አሮን ይገኙበታል፡፡

በዝዋይ ለዘመናት በየአብያተ ክርስቲያናቱና ገዳማቱ ተሸሽገው የተቀመጡ ጥንታውያን የብራና መጻሕፍት ለግእዝ ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ መዳበር ያበረከቱት አስተዋጽኦ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡

የጅማ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር መምህሩ አቶ ቡሩክ ወልደሚካኤል ባደረጉት ጥናት እንዳወሱት፣ በ10ኛው ምታመት የዮዲት እና በ16ኛው ምታመት አህመድ ኢብን ኢብራሂም የከፈቱትን ወረራ ተከትሎ፣ ታቦተ ጽዮንን ጨምሮ አያሌ መጻሕፍትና ታቦታት በዝዋይ ደሴቶች ውስጥ ቢሸሸጉም የእነኚህ ቅርሶች ዓይነትና መጠን ለማወቅ ግን መረጃዎች የተሟሉ አይደለም፡፡

ምንም እንኳ ትክክለኛውን ቁጥር የሚያረጋግጡ መረጃዎችን ለማግኘት አዳጋች ቢሆንም ከዝዋይ ሐይቅ በቅርብ ርቀት በየብስ ላይ የሚገኙ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት በተለይም ከአዳማ አንስቶ እስከ ሻሸመኔ ከጎልጃ (አርሲ) አንስቶ እስከ መቂ ከተማ ዙሪያ የሚገኙ ብዙዎቹ አብያተ ክርስቲያናት ታቦቶቻቸው ከዝዋይ ሐይቅ ወጥተው እንደተተከሉ ይታመናል፡፡

ከመጻሕፍቱ በማንኪያ

በአቶ ቡሩክ ማብራሪያ፣ እንደ ታቦታቱ ሁሉ ዕድሜ ጠገብ የሆኑ ብርቅዬና ውድ የግእዝ ብራና መጻሕፍት መገኛቸውን በዝዋይ ሐይቅ አብያተ ክርስቲያናትና ገዳም ያደርጋሉ፡፡ 

ዳግማዊ ምኒልክ መናገሻ ከተማቸውን በመጀመሪያ እንጦጦ ላይ እንዲመሠርቱ ምክንያት የሆናቸውም ከዝዋይ ሐይቅ አብያተ ክርስቲያናት ባገኙት የአፄ ልብነ ድንግል ክብረ ነገሥት መጽሐፍ ውስጥ ያነበቡት ‹‹የሸዋው ንጉሥ መቀመጫ እንጦጦ ላይ ይሆናል›› የሚል ትንቢታዊ መረጃ ነበር፡፡

ከሐይቁ አብያተ ክርስቲያናት ከተገኙት ውድ የብራና ላይ የጽሑፍ ቅርሶች መካከል ንግሥት እሌኒና አፄ ልብነ ድንግል ለፖርቱጋል ነገሥታት የጻፏቸው ሁለቱ የግእዝ ደብዳቤዎች ይገኙባቸዋል፡፡

ንግሥት እሌኒ ለፖርቱጋሉ ንጉሥ ዶም ማኑኤል በ1501 ዓ.ም. የጻፉት ደብዳቤ የተላከው በፖርቱጋል አምባሳደር በማቴዎስ አማካይነት ሲሆን፣ የአፄ ልብነ ድንግል ደብዳቤ ደግሞ በ1527 ዓ.ም. ለፖርቱጋል ንጉሥ ዶም ዮሐንስ ሦስተኛ የተላከውም በሌላው የፖርቱጋል አምባሳደር ጆን ቤርሙዴዝ አማካይነት ነበር፡፡

የሁለቱም ደብዳቤዎች ይዘት እያየለ መጥቶ ለሉዓላዊነታቸው ስጋት የጋረጠባቸውን የአሕመድ ኢብን ኢብራሂም ኃይል ለመመከት የወታደራዊ ድጋፍ ጥያቄ ነው፡፡

የኢትዮጵያ የጥንትና የመካከለኛው ዘመን ታሪክ ፕሮፌሰር የነበሩት ዶ/ር ሥርግው ሐብለ ሥላሴ፣ እኒህን ሁለት የግእዝ ደብዳቤዎች በሚያዝያ 1956 ዓ.ም. በሮም ተካሂዶ በነበረው አራተኛው የኢትዮጵያ ጥናትና ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ አቅርበዋቸዋል፡፡ ዶ/ር ሥርግው በማስታወሻቸው እንዳሰፈሩት፣ የግእዝ ደብዳቤዎቹን ያገኙት ከርእሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም ጽዮን ቤተ ክርስቲያን ቄሰ ገበዝ ከአባ ተክለሃይማኖት ወልደ ኪዳን ሲሆን ቄሰ ገበዙም ደብዳቤዎቹን ያወጡት ከዝዋይ ሐይቅ ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ገዳም በማስፈቀድ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡

በአፄ ዳዊት (1382-1412) ዘመነ መንግሥት የተጻፈው ገድለ ቅዱሳን፣ በሐይቁ ከሚገኙ የብራና መጻሕፍት አንጻር እጅግ ግዙፍ ሲሆን፣ 63.5 ሴንቲ ሜትር ርዝመትና 45.7 ሴንቲ ሜትር ስፋት እንዳለው ተመልክቷል፡፡ ባሁን ዘመን ያሉት በርካታ መጻሕፍት የንጉሠ ነገሥቱን አፄ ዳዊት ስም መያዛቸው በዘመናቸው ብዙ መጻሕፍት ለገዳሙ ሳይሰጡ እንደማይቀሩ ይገመታል፡፡

ገድለ ቅዱሳን በውስጡ የአሥራ ዘጠኝ ቅዱሳን አባቶችን ገድል የሚያዘክር ሲሆን፣ የታሪክ ትንተና አቀራረቡም የእያንዳንዳቸውን ቅዱሳን አባቶች ሥዕል በማስደገፍ ነው፡፡ በመጽሐፉ ዙሪያ ምርምር ያደረጉት ዶ/ር ሥርግውና ዶ/ር ሄንዝ መጽሐፉ የኢትዮጵያ የመካከለኛው ዘመንን ሥነ ጽሑፍና ሥነ ሥዕል ዕድገት ለማጥናት ወሳኝ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

በ1958 ዓ.ም. የእንግሊዟ ንግሥት ኤልሳቤጥ ኢትዮጵያን ለመጎብኘት በመጡበት ወቅት መጽሐፉ ወደ አዲስ አበባ ተወስዶ ንግሥቲቱ እንዲጎበኙት ሲደረግ፣ በ1972 ዓ.ም. ደግሞ ናይጄሪያ ሌጎስ ላይ በተካሄደው የአፍሪካ ሥነ ጥበብ ፌስቲቫል ላይ መጽሐፉ ኢትዮጵያን ወክሎ በመቅረብ ኢትዮጵያ የወርቅ ዋንጫ ተሸላሚ እንድትሆን አድርጓታል፡፡ በ1977 ዓ.ም. በተመሳሳይ የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ሥልጣን የያዘበትን አሥረኛ ዓመት የአብዮት በዓል በሚያከብርበት ወቅት፣ መጽሐፉ ዳግም ከዝዋይ እንዲመጣ ተደርጎ በአዲስ አበባ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ለሕዝብ ዕይታ ቀርቧል፡፡

ብርቅዬ ከሚባሉ የብራና መጻሕፍት ተርታ የሚሰለፈው ገድለ ካሌብ የሚያትተው፣ የአክሱም ንጉሥ የነበሩት አፄ ካሌብ በየመን በአይሁዳውያን ጭቆና ሲሰቃዩ የነበሩ ክርስቲያኖችን ነጻ ለማውጣት ቀይ ባሕርን አቋርጠው ያደረጉትን ዘመቻና ያስመዘገቡትን ድል ነው፡፡

ለዘመናት ከዓለም ላይ ጠፍቶ የነበረው የመጽሐፈ ሔኖክ የግእዙ ትርጉም የተገኘው በዚሁ በዝዋይ ሐይቅ የደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ገዳም ነው፡፡ በዚህ ረገድ በተለይ በገድለ ካሌብና በመጽሐፈ ሔኖክ ላይ የሚስተዋለው የአክሱማውያን የአጻጻፍ ስልት ምናልባትም መጻሕፍቱ ከታቦተ ጽዮን ጋር ወደ ዝዋይ ሐይቅ ሳይመጡ እንዳልቀረ ያመላክታል ይላሉ አጥኚው፡፡

ቅርሶቹን ለመንከባከብ የተደረጉ ጥረቶችና ችግሮች

በዝዋይ ሐይቅ ደሴቶች የሚገኙት ቅርሶቹ ለዘመናት የሳር ክዳን ጣሪያ በተገጠመላቸው ጎጆ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ በመቆየታቸው፣ የብራና መጻሕፍቱ ገጾቻቸው በዝናብ ምክንያት መበላሸታቸው፣ በአቧራም መደብዘዛቸው፣ ከአያያዝ ጉድለትም መገነጣጠላቸው ይወሳል፡፡

በየዘመኑ ቅርሶቹን ለመንከባከብ ጥረት የተደረገ ቢሆንም፣ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ ካልዕ የበላይ ኃላፊ በነበሩበት ከ1949 ዓ.ም. ጀምሮ ጥረት የብራና መጻሕፍቱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም በሚገኙ ባለሙያዎች እንዲደጎሱ መደረጉን አጥኚው አስታውሰዋል፡፡

ብዙዎቹ ብራናዎች የሚገኙበት ደብረ ጽዮን ደሴት፣ ቀድሞ የነበረውን የጎጆ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን በአዲስ መልክ በቆርቆሮ ጣሪያ በማሠራትም ቅርሶቹ በተሻለ አደረጃጀት በአዲሱ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መቀመጣቸውም ይገለጻሉ፡፡

ከብፁዕ አቡነ ሉቃስ በኋላ በበላይነት የመሩት ብፁዕ አቡነ ናትናኤል፣ የዝዋይ ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ገዳም ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑን በአዲስ መልክ ሙዚየም እንዲኖረው አድርገው በማሳነጽና ለደኅንነትና ለጎብኚዎችም አመቺ እንዲሆን፣ የብረት ሳጥኖችን በማሠራት ሁሉም ቅርሶች በየመደባቸው በማስቀመጥ በቅርሶቹ ጥበቃ ላይ እመርታ ለውጥ አሳይተዋል፡፡

አቶ ቡሩክ የደሴቶቹ ችግሮች ናቸው ብለው የዘረዘሯቸው ብቁ የሆኑ አስጎብኚዎች ያለመኖር፣ ጎብኚዎች መከተል የሚገባቸው ሕጎች በግልጽ ያለመቀመጣቸው፣ ለጎብኚዎች የተቆረጠ የአገልግሎት ዋጋ አለመኖሩና ቅርሶቹን የማስተዋወቁ ሥራ በሰፊው አለመሠራቱ ናቸው፡፡

መፍትሔ ብለው ያስቀመጡት  ደግሞ፣ ከተቻለ በቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ዘርፍ ባለሙያዎችን በመቅጠር ቅርሶቹን የመንከባከብና የማስጎብኘት ሥራውን መምራት፣ ካልተቻለ ግን አሁን ቅርሶቹን በመጠበቅና በማስጎብኘት ላይ የተመደቡት የሃይማኖት አባቶች በቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ እንዲሁም ማስጎብኘት ሥራ ላይ ተከታታይ ሥልጠና በመስጠት የክህሎት ማሳደግ ሥራዎች ሊሠሩ ይገባል ብለዋል፡፡

ቅርሶቹን የማስተዋወቅ ሥራ በሰፊው ከመሠራቱ ጎን ለጎን ከዝዋይ (ባቱ) መሀል ከተማ ወደ ሐይቁ የሚወስደው መንገድ ደረጃውን የጠበቀ አድርጎ መሥራት ምዕመናንም ሆኑ ቱሪስቶች ሳይንገላቱ መድረስ ያስችላቸዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...