[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚስታቸው ጋር እያወሩ ነው]
- ምነው ተከዝሽ?
- ብዙ ነገር ያሳስበኛል፡፡
- ምን ያሳስብሻል?
- የወደፊት ሕይወታችን፡፡
- የወደፊት ሕይወታችን ምን ሆነ?
- መቼ ይገባሃል አንተ?
- ማለት?
- ቤት እንኳን መቼ አለን?
- ይኼኛው ቤትስ?
- አይ አንተ?
- ምነው?
- ቤቱ እኮ የመንግሥት ነው፡፡
- ቢሆንስ እየኖርንበት አይደለ እንዴ?
- ዕድሜ ልክህን ሥልጣን ላይ የምትቆይ ይመስልሃል?
- የሰማሽው ነገር አለ እንዴ?
- ምን?
- ከሥልጣን ልነሳ ነው እንዴ?
- ኧረ የሰይጣን ጆሮ ይደፈን፡፡
- ታዲያ ምንድን ነው የምታወሪው?
- ስለወደፊቱ ዕጣ ፈንታ ከአሁኑ ማሰብ አለብህ፡፡
- እና ምን ይደረግ እያልሽ ነው?
- ከአንድ ሰው ጋር ሳወራ ነበር፡፡
- እሺ፡፡
- እነዚህ የ40/60 ቤቶች በጣም አሪፍ ናቸው አሉ፡፡
- እሱማ እኔም ሰምቻለሁ፡፡
- ታዲያ እነሱ ቤቶች እንዴት ናቸው?
- ምን እያልሽ ነው?
- የምለውማ ገብቶሃል፡፡
- ሴትዮ ጤነኛ ነሽ ግን?
- በሚገባ እንጂ፡፡
- እነሱ እኮ የሕዝብ ናቸው፡፡
- አይ አንተ?
- ስሚ ሕዝብ ቆጥቦ እኮ ነው የተሠሩት፡፡
- ቢሆንም እኔ ወሬ ሰምቻለሁ፡፡
- የምን ወሬ?
- የተዘጋጁት ለማን እንደሆነ፡፡
- ለማን ነው?
- ለባለሥልጣናት!
[ክቡር ሚኒስትሩ አንድ ወዳጃቸው ሚኒስትር ጋ ደወሉ]
- ሄሎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንዴት ነህ ወዳጄ?
- ሰላም ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ቢዚ እንደሆንክ አውቃለሁ፣ አንድ ነገር ልጠይቅህ ነበር፡፡
- ምን ክቡር ሚኒስትር?
- እነዚህ 40/60 ቤቶች እንዴት ናቸው?
- ያው በጥሩ ሁኔታ እየተሠሩ ነው፡፡
- እሱማ አውቃለሁ ግን…
- ግን ምን ክቡር ሚኒስትር?
- ቤቶቹን እንዴት ማግኘት ይቻላል?
- ተመዝግበዋል እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
- ኧረ በፍጹም፡፡
- እና ቤቶቹን ወደዷቸው?
- በጣም ነው የወደድኳቸው፡፡
- ዋናው እንኳን እርስዎ ወደዷቸው፡፡
- ማግኘት እችላለሁ እንዴ?
- እንዴታ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- የተሠሩት ለሕዝቡ መስሎኝ?
- የተሠሩትማ…
- እ…
- ለእኛው ነው!
[የክቡር ሚኒስትሩ የቅርብ ዘመድ ደወለላቸው]
- ሄሎ ጋሼ፡፡
- እሺ እንዴት ነህ?
- ኧረ ችግር ውስጥ ነኝ ጋሼ፡፡
- የምን ችግር ደግሞ?
- ትንሽ ከመንግሥት ጋር እየተጋጨሁ ነው፡፡
- ተቃዋሚ ሆንኩ እንዳትለኝ?
- እንደሱ አይደለም ጋሼ፡፡
- ታዲያ ምን ተፈጠረ?
- በታክስ ጉዳይ ነው፡፡
- ታክስ አትከፍልም እንዴ?
- ኧረ እኔ እከፍላለሁ፡፡
- በታክስ እኔ ቀልድ እንደማላውቅ ታውቃለህ?
- አውቃለሁ ጋሼ፡፡
- ታዲያ ምንድን ነው?
- አንድ ከገጠር ያመጣሁት ዘመዳችን ነበር፡፡
- እሺ ምን ሆነ?
- ለእሱ የከፈትኩለት ሱቅ ነበር፡፡
- እሺ፡፡
- እኔ ሳላውቅ ለካ ለዓመታት ታክስ ከፍሎ አያውቅም፡፡
- ታዲያ አንተ ምን አገባህ?
- ሱቁ በእኔ ስም ነው ያለው፡፡
- ወይ ጣጣ፡፡
- አሁን ዓቃቤ ሕግ ነገሩን እያከረረው ነው፡፡
- እና ምን አድርግ ነው የምትለኝ?
- አንተ ሚኒስትር አይደለህ እንዴ ጋሼ?
- ታዲያ ብሆንስ?
- ክሱን አስቋርጠው፡፡
- እስቲ ለማንኛውም የዳኛውን ስምና ቁጥር ቴክስት አድርግልኝ፡፡
- እሺ ጋሼ፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ዳኛው ጋ ደወሉ]
- ሄሎ፡፡
- እንዴት ነህ ክቡር ዳኛ?
- ማን ልበል?
- ክቡር ሚኒስትር ነኝ፡፡
- እንዴት ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
- ሰላም ነኝ፡፡
- ምን ልርዳዎት?
- አንድ ዘመዴ አንተ ጋ ኬዝ ነበረው፡፡
- የምን ኬዝ?
- ትናንትና በታክስ ጉዳይ ፍርድ ቤት የነበረው ኬዝ፡፡
- እ… አወቅኩት ሰውዬውን፡፡
- ስለእሱ ጉዳይ ለማውራት ነበር፡፡
- ያውሩኛ ምን ችግር አለው?
- በስልክ ጥሩ ስላልሆነ በአካል ተገናኝተን ብናወራስ?
- ክቡር ሚኒስትር ሥራ ስለሚበዛብኝ ከቻሉ የሚፈልጉትን በስልክ ይንገሩኝ፡፡
- ሰውዬው ጥፋተኛ አይደለም፡፡
- እሱማ በፍርድ ቤት የሚታይ ጉዳይ ነው፡፡
- አይገባህም እንዴ አንተ?
- ስልኩን ልዘጋው ነው ክቡር ሚኒስትር?
- በጣም ተናንቀናል ማለት ነው፡፡
- ምን አሉኝ?
- የምነግርህን አትሰማም እንዴ?
- ክቡር ሚኒስትር ፍርድ ቤቱ በትዕዛዝ አይደለም የሚሠራው፡፡
- እና በምንድን ነው የሚሠራው?
- እንዴት እንደሚሠራ ለማወቅ ሕገ መንግሥቱን ቢያነቡት ጥሩ ነው፡፡
- እና ትዕዛዙን አትቀበልም?
- ለመሆኑ ሰሞኑን ሚዲያ ተከታትለዋል?
- በምን ጉዳይ ላይ?
- አሜሪካ ስለተፈጸመው ጉዳይ፡፡
- ምን ተፈጸመ?
- ፕሬዚዳንቱ አንድ ትዕዛዝ አውጥተው ነበር፡፡
- እሺ፡፡
- ከዛ በኋላ ግን የፕሬዚዳንቱን ትዕዛዝ ፍርድ ቤት ሻረው፡፡
- ምን እያልከኝ ነው?
- ልልዎት የፈለኩትማ ፍርድ ቤትን ማንም አያዘውም ነው፡፡
- ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ አሉ፡፡
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- አሜሪካ ሌላ…
- እ…
- ኢትዮጵያ ሌላ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከአማካሪያቸው ጋር እያወሩ ነው]
- ስማ ይኼ ትራምፕ የሚባለውን ሰውዬ እየተከታተልከው ነው?
- በሚገባ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ያወጣውን መመርያ ሰምተሃል አይደል?
- ትራቭል ባኑን ነው?
- ታዲያስ?
- እሱ እኮ እኛን አይመለከትም፡፡
- እንዴት አይመለከትም?
- ለሰባት አገሮች ነው እኮ የወጣው፡፡
- እኔ እሱን አይደለም የምልህ፡፡
- ታዲያ ምን እያሉኝ ነው?
- እዛ ያሉ ኢትዮጵያውያንን ጠራርጎ ሊልካቸው ነው፡፡
- ማለት?
- በቃ ይኼ ዶክመንት የሌለው ሁሉ መጠረዙ አይቀርም፡፡
- ኧረ እንደዛ የሚባል ነገር የለም፡፡
- ሰውዬው ሕገወጥ ስደተኛን አባርራለሁ ብሏል፡፡
- ቢሆንም due process የሚባል ነገር አለ፡፡
- ምንድን ነው እሱ?
- አሜሪካ ምድር የረገጠ ሰው ዝም ብሎ አይባረርም፡፡
- እንዴት አይባረርም?
- ኬዙ በፍርድ ቤት ተይዞ እስከ አሥር ዓመት ሊቆይ ይችላል፡፡
- ሰውዬው ለምን እንደተመረጠ ታውቃለህ?
- ለምንድን ነው?
- የማስፈጸም ብቃቱ ፈጣን በመሆኑ ነው፡፡
- ምን እያሉ ነው ታዲያ?
- አዲስ ስትራቴጂ ነው የሚጠቀመው፡፡
- ምን ዓይነት ስትራቴጂ?
- Fast due process የሚሉት፡፡
- ስለ due process አላውቅም ብለውኝ አልነበር እንዴ?
- የምትለውን ልስማ ብዬ ነው እንጂ በደንብ ነው ጠንቅቄ የማውቀው፡፡
- እኔ ግን አሁን ስለሚሉት ነገር ሰምቼም አላውቅም፡፡
- አታነብማ ችግሩ እሱ ነው፡፡
- ብለው ነው ክቡር ሚኒስትር?
- ለማንኛውም አሁን መዘጋጀት አለብን፡፡
- ለምኑ ነው የምንዘጋጀው?
- አሁን የመንግሥትን ልማት ሲያንቋሽሹ የነበሩ ጠላቶቻችን መምጫቸው ቀርቧል፡፡
- እ…
- በቃ በየጊዜው ባለሥልጣናትን ሲያዋርዱ የነበሩ ጉዳቸው ነው፡፡
- አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
- ስማ ያ ሰውዬ ጠርዞ ሲልካቸው እዚህ በሚገባ እንቀበላቸዋለን፡፡
- ሰሞኑን ግን መንግሥት መግለጫ አውጥቷል፡፡
- ምን የሚል?
- እዛ ያሉ ኢትዮጵያውያን መንግሥትን የሚቃወሙት ለግሪን ካርድ ስለሆነ ወደ አገራቸው ተመልሰው በልማት ላይ መሳተፍ ይችላሉ ብሏል፡፡
- እሱማ የሚሰማሩት ልማት ላይ ነው፡፡
- ታዲያ እርስዎ ምን እያሉ ነው?
- ጥያቄው የሚያለሙት ምንድን ነው የሚለው ነው?
- ምንድን ነው የሚያለሙት ታዲያ?
- ቂሊንጦን!