እነሆ መንገድ! ከሜክሲኮ ወደ ቄራ ልንጓዝ ነው። ጎዳናው በባለርስቶቹ ዘመን ብዙ ለምዶ ኖሮ እንደተወረሰ ሰፊ እልፍኝ፣ ‹አቤት አቤት አልኩኝ ብቻዬን ቀርቼ. . .› ይባልበት ይዟል። እልፍ ነን። ብቻ ለብቻ ቆመናል። ሐሳቦቻችንና ውጥኖቻችን በሕይወት መድረክ ላይ የተጠላለፉ ደብዛዛ መስመሮች ሆነዋል። ያ ወንድሜ እንደማያውቀኝ፣ ያቺ እህቴ እንዳልተወለደችኝ አቀርቅራ ትጓዛለች። ካልያዙ መያያዝ አይቻልም የተባልን እንመስላለን፡፡ ገንዘብን መነሻ መድረሻችን ያደረግን ይመስል ይኼው እየደረቡ መታረዝ፣ እየበሉ መራብ ሆኗል። በወል አቧድኖ የሚያቧጭቀን የማካበት ወኔ በነጠላ ኑሮ ያብከነክነናል። ተሳፋሪ ይወርዳል ደግሞ ይሳፈራል። ሥር እየሰደደ ያስቆዘመን ቋንቋ የለሽ የባይተዋርነት ስሜት ግን መቋጫ ፌርማታ እንዳጣ ነው። ሳንነጋገር ተግባብተን፣ ይኼንኑ የብቻነት ቅዝምዝም መንገድ ያበጀንለት መስሎን በፋሽን አልባሳት፣ በሞዴል አውቶሞቢሎች፣ በዘመነኛ ደርበ ብዙ የመኖሪያ ቤቶች ብንሸፍነውም አላሸነፍነውም። ምክንያቱም መንገድ አልቆ አያልቅምና፣ ስሜትና ሐሳብ የመንገድ ገባር ናቸውና፣ ሰው ቆሞ ከሄደ እርካታው በዘለዓለም ዕድሜ አትሠፈርም።
እንባና ሳቅ ሰው የመሆን ዕዳ ተፈጥሮአዊ አካል ናቸው። ይኼው እዚያች ታክሲ ጎማ ሥር አንድ ጠኔ ያደባየው ወድቆ እጆቹን መዘርጋት አቅቶት፣ ያው መንገዱን ተሻግሮ አንዱ ሕይወት አልጋ ባልጋ ሆናለት ጭረት የማያውቀው የሚመስል ጎልማሳ ልኳንዳ ቤት በር ላይ ቁረጡ እንቁረጥ ሲል፣ የመሸብን ሳይነጋልን የነጋላቸው የንጋታቸው ብርሃን ዓይን ወግቶ ይገላል። ሕይወት በአድሏዊነት ስትታማ ደግሞ መልሳ የወደቀውን አንስታ፣ ከፍ ከፍ ያለውን ዝቅ አድርጋ ስሟን እያደሰች ግራ ታጋባለች። እንጀራን ተገን አድርጎ የሚያጣድፈን ኑሮ ሞልቶ ሳይሞላ ጎሎ ሳይጎድል ለምንባዝን ምስኪኖች የጎዳናው ጥልቅ ዓላማ ከትርምሱ ጀርባ ለምን? ለማን? እንዴት? ከየት? ወዴት? እያስባለ ጥያቄና ጥያቄ ብቻ የሚደርደር ይመስላል። ባይመስልም ለነገሩ የኑሮ ትርፉ መጠየቅ ብቻ ነው።
ጉዟችን ተጀምሯል። ከሾፌሩ ጀርባ የተቀመጡ ወጣቶች በኢሞ እያወሩ ነው። ‹‹እሺ እባክህ እናንተ በውስኪ እኛ ደግሞ በውኃ እየራስን ነው። ክብሩ ይስፋ እርሱ መድኃኔዓለም ይላል. . .›› በወዲያ በኩል። ‹‹ምናለበት ለብቻቸው ቢያወሩ? ላውድ ላይ አድርገው ሲያደነቁሩን ዝም ትላለህ?›› ይላል መሀል መቀመጫ ላይ ከጎኔ የተቀመጠ ጎልማሳ። ወያላው በፈገግታ ብቻ ጥሎን ሸሸት አለ። ‹‹እኔ የምለው? አሜሪካ እንዴት ነው ዌዘሩ?›› አለ እዚህ ሸገር የቄራ ታክሲ የተሳፈረው። ‹‹አሸወይና ነው። ምን ኑሮማ ያለው አዱገነት አይደለም እንዴ? እኔማ ከእንግዲህ ቆይ ታየኛለህ ያለችኝን ሰባስቤ ሮጬ መምጣት ነው. . .›› ይለዋል። ‹‹እኛ በየት በኩል ሮጠን እንውጣ እንላለን እሱ ሮጬ እመጣለሁ ይላል። አይ አለማወቅ። ከራርመው ሲለዩዋት እንኳን አገር ወፍም ታባባለች እኮ?›› ይላል ጎልማሳው፡፡ ‹‹የሚናገረውን አያውቅምና ይቅር በሉት ብሎ ማለፍ ነው፤›› ባዩዋ ደግሞ ከጀርባ፣ ሦስተኛው ረድፍ ላይ ቢጫ ስካርፍ የጠመጠመች ተሳፋሪ ናት። ‹‹ትራምፕን ያላየ ብዙ ይቀባጥራል. . .›› በማለት ነገሩን አንጠልጥሎ የተወው ደግሞ አንዱ ነው፡፡
ህም ይላል ጎልማሳው ዓይን ዓይኑን እያየ። ‹‹እኔ የምልህ እስኪ ሚስትም ፈልጉልን እንጂ። እኛማ እንዳያያዛችን ማጥመድ የምንችል አልመሰለኝም. . .›› ሲል የአሜሪካው፣ ‹‹ይኼው ዕድሜ ለሚሊኒየማችንና ለዳያስፖራ ተንከባካቢው መንግሥታችን ከየሄዳችሁበት ሰብስቦ አምጥቶ ሲበትናችሁ ለመድናችሁ። እንዳንተ ይኼን ያህል ዘመን አሜሪካ መኖር አይደለም አንድ ሦስት ሚስት አታገባም ነበር?›› አለውና ታሳሳቁ። በዚህ መሀል ኔትወርክ አስቸገራቸውና ጨዋታቸው ተደነቃቀፈ። ‹‹ወይ ትራምፕ ያልሰማው ጉድ. . .›› እያለ የቅድሙ ያንጠለጠለውን መልስ ይተወዋል፡፡
ወያላው ሒሳብ እየሰበሰበ ነው። ሾፌራችን እንደ ሰደድ እሳት ጨዋታ ሲቀጣጠል፣ ‹‹ታክሲ ውስጥ በህቡዕ መደራጀት ክልክል ነው፤›› እያለ ለወያላው የሬዲዮኑን ድምፅ ጨመር ያደርገዋል። የስፖርት ትንታኔ እናደምጣለን። “ሊቨርፑል በመሸነፉ የተሰማን ሐዘን በእውነቱ . . . በእውነቱ ቅስም የሚሰብር ነው. . .” ይላል ጋዜጠኛው። ‹‹ስለራሱ ቅስም አያወራም እንዴ? ለምን የእኛን ይጨምራል?” ይላል ከመጨረሻ ወንበር። “እውነት ግን አርሰናልም አንጀት ይበላል። ሁሌ እኮ ነው ለዋንጫ ደረሰ ሲባል አይሳካለትም፤” ስትል ባለስካርፏ፣ ‹‹የተሳካለት አይተሽ ታውቂያለሽ?›› ብሎ ጎልማሳው አፈጠጠባት። ‹‹በኳስ መፋጠጡን ትታችሁ በአገር አትፋጠጡም? ለምሳሌ እንደ ሩሲያና አሜሪካ. . .” ብሎ አንዱ ከጋቢና ወሬ አስገለበጠ። ከሾፌሩ ጀርባ የተቀመጠች ወይዘሮ፣ “በስንቱ ተፋጠን በስንቱ እንቃጠል” አለችው። ወዲያው ጋቢና የተቀመጠው ወጣት ቀልባችንን ወደ ሜሲና ሮናልዶ ፍጥጫ ወሰደው።
አፍታም አልቆየ ሜሲ ይበልጣል ሮናልዶ ክርክሩ ጦፈ። “ደግሞ ሜሲ ተጨዋች ነው? በስንት ተጋዳይ ሰማዕታት ላብና ደም እኮ ነው እዚህ የደረሰው፤” ሲል አንዱ ሌላው ተቀብሎ፣ “ስለኳስ ተጫዋቹ ሜሲ ነው የሚያወራው ወይስ ሜሲ ደደቢት በረሃ ታግሏል?” ይላል ሌላው። “ሮናልዶንማ የሚያክለው የለም። ምናልባት ራሱ ስለራሱ ችሎታ አዳንቆ ሜሲን እበልጠዋለሁ ማለቱ ቢያስተቸውም. . .” ብሎ ሌላው ንግግሩን ሳይጨርስ ደግሞ ወዲያ ጋቢና ያለው ጣልቃ ገብቶ፣ “እኔ እኮ ሐበሻ ብቻ ይመስለኝ ነበር በእኔ እበልጥ በእኔ እሻል የሚሻኮተው። የእኔ አስተዳደር፣ የእኔ አገር የግንባታ፣ የኢኮኖሚ ልማት፣ ወዘተ ካለፈው ከሚመጣው ይለያል የሚል ሐበሻ ብቻ ይመስለኝ ነበር። ለካ ፈረንጅም ራሱን ያንቆለጳጵሳል?” ብሎ ባለታኬታን ዘውድ ከሚጭነው ያመሳስላል። በተረፈ ተሳፋሪው ‘የሜዳን ለባለሜዳው! የዙፋንን ለባለዙፋኑ’ ቢባል ጆሮ ዳባ ልበስ ባይ ሆኖ ይኼው ዘመናት እየነጎዱ ነው፡፡
ጉዟችን ቀጥሏል። የታክሲያችን ፍጥነት እየጨመረ ሲሄድ ጆሮ የሚያደምጠው፣ ዓይን የሚታዘበው ነገር አብሮ ጨምሯል። ሁለት ሴቶች እየተንሾካሾኩ እየተመካከሩ የደወለላቸውን ደንበኛ ያስለፈልፋሉ። “እኔ የምለው? የካርድ መሸጫው የአባትህ ነው ወይስ የእናትህ? ምናለበት ስልኩን ባትጫወትበት?” ስትል እሱ የሚላትን አንሰማም። “እኛ በቀላሉ አንገኝማ! ልማት ላይ ነንና፤” ጓደኛዋ በይው ያለቻትን ትለዋለች። ስለብቸኝነት አነሳባት መሰል ደግሞ፣ “ሁሉም ብቸኛ በሆነበት አገር የአንተ ብቸኝነት ምኑ ይገርማል? ፓርላማችን ብቸኛ፣ ሕዝቡ ብቸኛ፣ አገራችን በበጎም በክፉም አንደኛና ብቸኛ! ታዲያ ያንተ ብቸኛ መሆን ምኑ ላይ ነው የሚያሳዝነው?. . . እያሾፍኩብህ ከመሰለህ ‘ኔትወርኩን’ ለሠርቶ አዳሪዎች ለቀቅ አድርግላቸው. . .” ትለዋለች። ተሳፋሪው የመድረክ ጭውውት እንደሚያዳምጥ አንዳንዴ ሴቶቹን ዘወር ብሎ እየገላመጠ፣ ዘና እያለ፣ እያዘነ. . . ልቡን ጥሎ ይከታተላቸዋል።
ጥቂት እንደተጓዝን ስልኩ ተዘጋ። “አሁን አንዳንዴ የኔትወርክ መቆራረጥ ባይኖር ምን ይውጠን ነበር? ሥራ ፈት. . .” ብላ ስታናግር የነበረችው ልጅ ተቆናጠረች። ጓደኛዋ፣ “ቆይ ግን እሱን የሚያክል ሰውዬ? በዚህ ዕድሜው ነውር አይደለም? ትንሽ ዕፎይ ብንል ነገር ተረሳና ንሰሐም ያስተዋሽ ያለህ ማለት ጀመረ? እምዬ ኢትዮጵያ ስንት ጉድ በሆዷ እንዳላመቀች? ሆሆ!” ብላ አንባረቀች። “አይገርምሽም? ደግሞ ብቸኝነት አሰቃየኝ ይለኛል ሌላው ኅብረት እንደሚያውቅ ሁሉ። በዛሬ ጊዜ ያውም ‘ኮንዶሚኒየም’ የሚባል ነገር ከመጣ ወዲህ ማን ማንን ጠይቆ? እኔ እና አንቺ እንኳን የተገናኘነው መቼ ነበር?” እየተባባሉ ወደ ግል ጨዋታቸው ዞሩ። የኮንዶሚኒየም ነገር ሲነሳ ምድረ ቆጣቢ እየተጠቃቀሰ ‘ስለቁጠባ ቤቱ ጉዳይ የሰማችሁ እስኪ እንያችሁ?’ መባባል ያዘ። ብሎክ ጠፋ፣ ፈተና ተሰረቀ፣ ስኳሩ እስከ ፋብሪካው ተላሰ በሚባልባት አገር ቤትን እሱ ፈጣሪ ካልሠራው በልማት ሠራዊት መፈክርና በቁጠባ ባህል ብቻ ታየን ባለቤት ስንሆን ይባባል ነበር ተሳፋሪው!
ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። “ኧሁሁሁ!” ብሎ አንዱ ወደ መጨረሻ ወንበር በረጅሙ ተነፈሰ። “ምነው? ታፍነህ ነበር እንዴ?” አሉት አጠገቡ የተቀመጡት። “የለም በነፃ መኖር አምሮኝ ነው!” ብሎ መለሰ። “ሲያምርህ ይቅር እንዳንልህ አንተም እንደ እኛ ብዙ አምሮህ የቀረ ነገር ስለሚኖር ሌላ ዕጦት አንመኝልህም፤” አለችው ቆንጂት። “ደግሞ በነፃ መኖር ያማረው ማን በነፃ ሲኖር አይቶ ነው? እንኳን በሰው በአህያም አልተቻለ፤” ጎልማሳው ገባበት። “አህያ? የምን አህያ?” ጠየቀች ወይዘሮዋ። “አልሰማችሁም ይህቺን ጆክ። ሰውዬው በቃ ኑሮ ከበደውና የእኔ ቢቀር አህያዬን በነፃ ማኖር አለብኝ ብሎ ቆርጦ ተነሳ። ከዚያ ቀስ እያለ የዕለት ምግቧን ሲቀንስ፣ ቀስ እያለ ሲቀንስ. . . ሲቀንስ. . . ሲቀንስ. . . መጨረሻ ላይ አህያው ፍግም። ምን ቢል ጥሩ ነው? ‘ወይኔ በነፃ ላኖራት ትንሽ ሲቀረኝ አህያዬ ሞተች!’ ጉድ እኮ ነው፤” ሲል ተሳፋሪዎች ተሳሳቁ። “እህም! ቀልድ። እንኳን በነፃ በዋጋስ መኖር ተቻለ እንዴ ዘንድሮ?” ብላ ወይዘሮዋ ነገር መብላት ስትጀምር፣ “ዋጋው ዋጋ ስላጣ እኮ ነው እኔም በነፃ መኖር ያማረኝ?” ብሎ ያ ቀልደኛ ወጣት ጣልቃ ገባባት። መጨረሻ ብሎ ወያላው ሲያወርደን የነፃና የዋጋ ነገር ከየልቦናችን ጋር አፋጠጠን። ‘በስንቱ ተፋጠን እንቃጠል?’ ነበር ያለችው ወይዘሮዋ? መልካም ጉዞ!