Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየነገ ሕይወታችንን በዛሬ መስታወት

የነገ ሕይወታችንን በዛሬ መስታወት

ቀን:

ኢሕአዴግ መራሹ የኢትዮዽያ መንግሥት ሰሞኑን “ብቁና ውጤታማ ፐብሊክ ሰርቪ ለአገራዊ ህዳሴ” በሚል ርዕስ ለአገራዊ ፐብሊክ ሰርቪሱ ጥልቅ ተሃድሶ ያገለግል ዘንድ ባዘጋጀው ባለ ሰላሳ አምስት ገጽ የመወያያ ጽሑፍ ላይ እንደተገለጸው፣ አገራችን በለውጥ ውስጥ እንደምትገኝና ይኼ ለውጥም በከተሞች ብቻ የማይታጠር ይልቁንም ደግሞ በገጠር የጀመረና አርሶ አደሩን መነሻ ያደረገ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ጽሑፉ አገራችን ለበርካታ ምዕተ ዓመታት ከተጓዘችበት የማሽቆልቆል ጉዞ መግታት የተጀመረው ከዛሬ ሃያ አምስት ዓመታት ወዲህ እንደሆነ ያብራራል፡፡ በዚህ የማሽቆልቆል ጉዞ ዋነኛ ሰለባ የነበረው ደግሞ የገጠሩ ማኅበረሰብ በተለይም አርሶ አደሩ እንደነበር ያትታል፡፡

በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ሲነገር እንደምንሰማው አገራችን ከዛሬ ሃያ አምስት ዓመታት በፊት እንቅልፍ ላይ እንደነበረች ነው (ጉዳዩ አከራካሪ ቢሆንም ቅሉ)፡፡

ታላቁ የዓለም የታሪክ ምሁር ፕሮፌሰር አርኖርድ ቶይንቢም በአንድ ወቅት እንደጻፉት፣ አንድ ሰው አዲስ አበባ ውስጥ ሆኖ የአሥራ አምስት ዓመት እንቅልፍ ቢወስደውና ቢነቃ ያለበትን ሥፍራ በምንም ዓይነት ሊረሳ አይችልም፡፡ ሀቀኛይቱንና ያችው እንደተፈጠረች ያለች ኢትዮዽያን ሳትለወጥ ያገኛታል ብለው አስፍረዋል፡፡

ይኼ ሐሳብ ከላይ ያነሳሁትን ጉዳይ የበለጠ ያብራራዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ እኛ ኢትዮዽያዊያን ከዛሬ ሃያ አምስት ዓመታት በፊት እንቅልፍ ላይ ነበርን ወይስ አልነበርንም? የሚለውን ጥያቄ ሊመልስልን የሚችል አባሪ እንደሆነ እገምታለሁ፡፡ የውጭ የታሪክ ባለሙያዎች ሳይቀሩ የአገራችንን የረዥም ጊዜ በእንቅልፍ ማሳለፍና ኋላቀርነት ሲዘግቡና በታሪክ ማኅደራቸው ከትበው ሲያስቀምጡ እንደነበር እንረዳለን፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ አንድ የሚነገር ተረት ነበር፡፡ ክርስቶስና መላዕክት የመካከለኛው ምሥራቅ አውሮፓን ሲጎበኙ ቆይተው ኢትዮጵያ ሲደርሱ፣ “ይች ከሁለት ሺሕ በፊት የነበረችዋ አገር ነች” ብለው እንደተረቱ ይነገራል፡፡ እንግዲህ በአገራችን የተተረተው እስከዚህ ድረስ ነው፡፡ በድሮ ጊዜ ምን ያህል በልማትና በዴሞክራሲ እንዳላደግንና ኋላ ቀር እንደነበርን ያመለክታል፡፡ አንድ ሰው ለብዙ ዓመታት ከአገሩ ቢወጣና ተመልሶ ቢመጣ የሚያገኛት ያችን ድሮ የሚያውቃትን አገር እንደሆነ ለማስረዳት የተተረተ ነው፡፡ የተማረ ዜጋ ባለመኖሩ፣ ለፍትሕና ለዴሞክራሲ መዳበር የሀቀኛ መሪ ወደ ፖለቲካው መድረክ አለመምጣት፣ በየአካባቢው የነበሩ የብሔር ግጭቶችና ለበላይነት ይደረጉ የነበሩ ትግሎች፣ . . . ወዘተ ደግሞ አገሪቷን ለዘመናት በእንቅልፍ ውስጥ እንድታሳልፍ ምክንያቶች እንደሆኑ ባለሙያዎች ሲናገሩ ይደመጣል፡፡

ፕሬዚዳንት ፍራንክሊን ዲላኖ ሩዝቬልት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ዋዜማ የተረከቧት አሜሪካ በኢኮኖሚ መመሰቃቀል፣ በሥራ አጥነት፣ በኑሮ ውድነትና በሌሎች ችግሮች የተተበተበች ነበረች፡፡ ከዚያ ሁሉ ችግር አሜሪካን አውጥቶ፣ ከጀርመን ናዚዝምና ከጃፓን ሚሊታሪስት አምባገነን መንግሥታት ጋር ተዋግቶና ድል አድርጎ፣ አውሮፓን አቋቁሞ (በማርሻል ፕላን አማካይነት) ዛሬ ዓለምን የምትመራ አገር ለመመሥረት መሠረት ጥለው አልፈዋል፡፡

 በ1930ዎቹ አጋማሽ የነበረው የአሜሪካ ውጥረት እጅግ አሳሳቢና ለትንሳዔዋ ትልቅ አመራርን የሚጠይቅ ነበር፡፡ ያን ጊዜ ነበር ሩዝቬልት፣ “ነገ ለመኖር ዛሬ መንቀሳቀስ አለብን፡፡ የተረሳችውንና በእንቅልፍ ውስጥ ረጅም ጊዜ ያሳለፈችውን  አሜሪካ ማስታወስ ይገባናል፤” የሚል የፖለቲካ መርህ ይዘው የተነሱት፡፡ ይኼ የፖለቲካ መርህ ለዛሬው አሜሪካውያን ዕድገትንና ዴሞክራሲን ይዞ መጣ፡፡ የዛሬዎቹ የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶችም ይኼንን የዕድገትና የዴሞክራሲ ሌጋሲ በማስቀጠልና የበለጠ የተሳለጠ በማድረግ የዛሬ ልዕለ ኃያሏን አገር አሜሪካ መገንባት ችለዋል፡፡

የኢሕአዴግ መንግሥት ደግሞ በተቃራኒው ከዛሬ ሃያ አምስት ዓመታት በፊት የተረከብኳት አገር ለብዙ ዓመታት በእንቅልፍ ውስጥ እንዲያውም በማሽቆልቆል ሒደት ላይ የነበረች ናት ሲል ይሞግታል፡፡ ይኼን የማሽቆልቆል ጉዞ ለመግታት ደግሞ  የአሜሪካው ፕሬዚዳንት የነበሩት ፍራንክሊን ዲላኖ ሩዝቬልት እንደወሰዱት ዓይነት ዕርምጃ ከዛሬ ሃያ አምስት ዓመት ጀምሮ በመውሰድ፣ አገሪቷን ከዚህ ቀውስ መታደግ እንደተቻለ ያብራራል፡፡ ከ1983 ዓ.ም. ወዲህ አዲስ የመንግሥት ሥርዓት በመዘርጋትና  ሕገ መንግሥት በማርቀቅ በአገሪቷ ላይ ለውጥ ማስመዝገብ መቻሉን በመግለጽ፡፡

የስኬታማ ልማታዊ መንግሥት መሠረታዊ የብቃት ምንጮችን በመተግበር ማለትም ለኅብረተሰብ ልማት የቆረጠና የሕዝብ አገልጋይ የሆነ ፖለቲካዊ አመራር በመጎናፀፍ፣ በመንግሥት ራዕይና ተልዕኮ እንዲሁም መመርያዎች ላይ የተሟላ ግልጽነት፣ አመኔታና የመፈጸም ተነሳሽነት ያለው ፐብሊክ ሰርቪስ በመገንባትና ልማታዊ ተነሳሽነት ያለው ኅብረተሰብ በመፍጠር የአገራችንን የልማትና የዴሞክራሲ ግንባታ የተሳለጠ ማድረግ እንደተቻለ ያብራራል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ ደግሞ ከአሥራ አምስት ዓመታት በኃላ አገሪቷን በልማትና በዴሞክራሲ ጎዳና ወደ ተሻለ ደረጃ ማሸጋገር እንደተቻለ በተዘጋጀው የመወያያ ጽሑፍ ላይ ተገልጿል፡፡ በአገራችን 54 በመቶ የነበረው ሕዝብ ከድህነት ወለል በታች ይኖር የነበረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ግን ወደ 22 በመቶ ዝቅ ማድረግ ተችሏል፡፡ በገጠርም ሆነ በከተማ ከመቼውም ጊዜ የተሻለ የመሠረተ ልማት አቅርቦት መጥቷል፡፡ ከሃያ አምስት ዓመታት በፊት 45 ዓመት የነበረው የዜጎች አማካይ በሕይወት የመኖር የዕድሜ ጣራ ዛሬ ላይ ከ19 ዓመታት በላይ ጭማሪ አሳይቶ ወደ 64 ዓመታት ከፍ ማድረግ ተችሏል ሲል ያስረዳል፡፡

ኢሕአዴግ ይኼንን ይበል እንጂ በተቃራኒው የልማትና የዴሞክራሲ ግንባታ ሒደቱን የሚፈታተኑና የሚገዳደሩ ጉዳዮች እየገጠሙት እንደሆነም ሳይጠቅስ አላለፈም፡፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተፈጥረው የነበሩ አገራዊ ችግሮችን በመጥቀስ፡፡ ዋነኛ የችግር ምንጮች ናችው ብሎ ከፈረጃቸው ምክንያቶች መካከል ደግሞ በሥልጣን ላይ ባሉ አንዳንድ አመራሮች ሕጋዊ ሥርዓቱ ከሚፈቅደው ውጪ ተጠቃሚ ለመሆን የመፈለግና በተግባርም የመንቀሳቀስ አዝማሚያ በመፈጠሩ የተነሳ እንደሆነ ያምናል፡፡

ኢሕአዴግም ይችን ተረስታና በማሽቆልቆል ሒደት ውስጥ የነበረች አገር ለመታደግ ደፋ ቀና ስል ይኸው ድፍን 25 ዓመታት ሞሉኝ ሲል በየሚዲያው ይናገራል፡፡

ሮናልድ ሬገን እ.ኤ.አ. በ1966  ለካሊፎርኒያ ገዥነት መወዳደር ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ በ1981 የአሜሪካ ፕሬዚዳንት እስከሆኑበት ጊዜ ድረስ በየሥፍራው “ስለተረሳችው አሜሪካ” ሺሕ ንግግሮችን አድርገዋል፡፡ በዚህ ንግግራቸውም ሚሊዮን አሜሪካውያን ልባቸውን ሰጥተዋቸዋል፡፡ የተረሳቸውና ለረጅም ጊዜ በእንቅልፍ ውስጥ ነበረች የምትባለዋን አሜሪካ ህዳሴዋንና ልማቷን እንዲሁም ዕድገቷን ለማምጣት በሮናልድ ሬገን ንግግር አማካይነት ሚሊዮን አሜሪካውዊያን ከጎናቸው ሆነው ተንቀሳቅሰዋል፡፡

ኢሕአዴግ በአሁኑ ወቅት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ይችን የተረሳችና በማሽቆልቆል ሒደት ውስጥ የነበረች አገር ለመታደግ ከጎኔ ቆመዋል ሲል ይሰብካል፡፡ ባደረግኩት የመታደስና የመለወጥ ሒደትም አገሬን በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተፈጥሮ የነበረውን ችግር በቁጥጥሬ ውስጥ አውዬዋለሁ፣ የአገሪቷን ዕድገትም እያፋጠንኩ ነው ሲል ይሞግታል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና የተወሰኑ ግለሰቦች ከመውቀስና ከመወንጀል ባይቆጠቡም፡፡

በአገራችን የታሪክ ሒደት ውስጥ መወቃቀስና መወነጃጀል የተለመደ ነው፡፡ አንዱ መሪ ወደ ሥልጣን ሲመጣ ከእሱ በፊት ያለውን ይወነጅላል፡፡ አፄ ዮሐንስ አፄ ቴዎድሮስን ሲወነጅሉ፣ አፄ ምኒሊክ አፄ ዮሐንስን ሲወነጅሉ፣ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አፄ ሚኒሊክን ሲወነጅሉ፣ ደርግ የንጉሡን ሥርዓት ሲወነጅል፣ ኢሕአዴግ ደግሞ ደርግን ሲወነጅል ይኸው እዚህ ደርሰናል፡፡ መሪዎች የሚገመገሙት በሠሩት የአገር ኃላፊነት የሥራ አፈጻጸም ነው፡፡ የኩባ ፕሬዚዳንት የነበሩት ፊደል ካስትሮ “ታሪክ ነፃ ያወጣኛል (History Absolves Me)” ብለው የተናገሩት በሚሠሩት ሥራ ነገ ሊወነጀሉም ሆነ ሊሞገሱ እንደሚችሉ ቀድመው ያውቁት ስለነበር ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት መሪዎች በዓለም ላይ ተወዳጅነትን አትርፈው ነው የሚያልፉት፡፡

ኢሕአዴግም የታሪክ ተወቃሽ እንዳይሆን አሁን ላይ እየሠራቸው ያሉ ሥራዎች የሕዝብን ውግንና የሚያስገኙና ልማትን የሚያፋጥኑ መሆን አለባቸው፡፡ በመነሻዬ ላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ለኅብረተሰባችን ለውጥ በቁርጠኝነት መሥራት አለበት፡፡ ለአገራችን አርሶ አደር ከወሬ ባለፈ መሠረተ ልማቶችን ልናፋጥን ይገባል፡፡ መንገዶች ቀበሌን ከቀበሌ ለማገናኘት መሠራት አለባቸው፡፡ የሚሠሩ መንገዶች አስፋልት ዳርና ዳር ላሉ የኅብረተሰባችን ክፍሎች ብቻ ሳይሆን እስከ ታች የገጠሩ ክፍል መዝለቅ አለባቸው፡፡ የመብራት አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን አለባቸው፡፡ አስተማማኝና ዘላቂ የምርት ውጤት እንዲመዘገብ የግብርና ባለሙያዎች ከልብ ከአርሶ አደሩ ጐን ሆነው አዳዲስ አሠራሮችንና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን አርሶ አደሩ እንዲጠቀም ማድረግ አለባቸው፡፡ 

በከተማ ደረጃም የሚኖሩ በከፋ ድህነት ውስጥ ያሉ ዜጐች አስፈላጊው የሥራና የሌሎች ዕድሎች ተጠቃሚ መሆን አለባቸው፡፡ ለወጣቱ የሥራ ዕድል መፈጠር አለበት፡፡ እንደ ሌሎች የአሜሪካና የአውሮፓ አገሮች መንግሥት የመሪነት ሚናው የጐላ መሆን አለበት፡፡ በታሪክ ያለፈውን ትውልድ ከመውቀስና ከማሽቆልቆል ጉዞ ገትተን ገና አሁን ወደፊት እየሄድን ነው የሚል አጉል ወቀሳና ውንጀላ በመላቀቅ ጊዜያችንን በአግባቡ በመጠቀም ከድህነታችን ልንወጣ ይገባል፡፡ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይም ብዙ ሥራ ያስፈልጋል፡፡

ዛሬ ላይ ሆነን የነገ መንገዳችንን አሻግረን ማየት አለብን፡፡ የነገ ሕይወታችንን በዛሬ መስታወት በመመልከት ወደ ከፍታው ልንወጣ ይገባል፡፡ 

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...