Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርሕገወጥ ስደትና የወቅቱ ሥጋት

ሕገወጥ ስደትና የወቅቱ ሥጋት

ቀን:

በዳዊት ከበደ አርዓያ

በዓለም ላይ 15.4 ሚሊዮን የሚሆኑ ስደተኞች እንዳሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን መረጃ ያሳያል፡፡ የሰው ልጆች (ዜጎች) የትውልድ አገርን ጥሎ መሰደድ የነበረ ክስተት ቢሆንም፣ አሁን ባለንበት ዘመን ግን የተለያዩ አገሮች ዜጎች የሚያልቁበት መቅሰፍት እየሆነ ነው፡፡ የተለያዩ ሕገወጥ ተግባራት የሚፈጸምበት የሰው ልጅ ከጦርነትና ድርቅ ባልተናነሰ የሚያልቅበት የዘመናችን አሳዛኝ ክስተት ሆኗል፡፡ ያልበለፀጉ አገሮች አምራችና አገር ተረካቢ ዜጎቻቸውን የሚያጡበት ብቻ ሳይሆን፣ የበለፀጉ አገሮችም ከአቅማቸው በላይ የተጋረጠባቸው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ትኩሳት በመሆኑ ነው፡፡ በተለይም የአውሮፓ ኅብረት አባል አገሮች ይህን አደገኛና የዜጎቻቸውን ህልውና የሚፈታተን ሕገወጥ ተግባር እንደ ዋነኛና ፈጣን ምላሽ የሚጠይቅ አጀንዳቸው አድርገው እየተንቀሳቀሱ ያሉት፡፡

በቅርቡም የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የሆኑት ዶናልድ ትራምፕ እንደ ዋነኛ መወዳደሪያ አጀንዳቸው አድርገው ነው የተንቀሳቀሱት፡፡ ትራምፕ አይደለም በሕገወጥ መንገድ በሕጋዊ መንገድም አገራቸው አሜሪካ ስደተኞችን የምታስተናግደበት ዕድል እንደሌለ አሳውቀዋል፡፡ ቃለ መሐላ ፈጽመው ሥራ ከጀመሩበት ቀን ጀምሮም በሕጋዊ መንገድ ቪዛ አግኝተው ለመጓዝ የተዘጋጁ የተለያዩ አገሮች ስደተኞች ጉዟቸው እንዲቋረጥ ሲደረግ፣ ቀድመው ወደ አሜሪካ የተጓዙትም ከውሮፕላን ማረፊያዎች እንዳይወጡ ተደርገዋል፡፡ የስደተኞች ጉዳይ የአውሮፓ ኅብረት አባል አገሮችን አንድነት አደጋ ላይ የጣለ አደገኛ ክስተት መሆኑን የተናገሩት ፕሬዚዳንት ትራምፕ፣ በተለይም የጀርመን መራሒተ መንግሥት አንገላ መርከል ጀርመን ከአንድ ሚሊዮን በላይ ስደተኞች እንድትቀበል መፍቀዳቸው ‹‹የመቅሰፍት ያህል ስህተት ሠርታለች፤›› ሲሉ ኮንነዋል፡፡

በእርግጥም በአሁኑ ጊዜ የአውሮፓም ሆነ የአሜሪካ ፖለቲከኞች ራስ ምታትና ቅድሚያ የሚሰጠው የመንግሥታት አጀንዳ እየሆነ መምጣቱ እየተገለጸ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ የሕገወጥ ደላሎችና የሰው ንግድ አዘዋዋሪዎች መናኸሪያ የሆነችው ሊቢያም ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫቸው አድርገዋታል፡፡ በተለይም በሕገወጥ ስደተኞች ላይ በዚያች አገር የሚፈጸመው እጅግ በጣም ዘግናኝና ኢሰብዓዊ ተግባር በጊዜው ካልተቀጨ፣ ዓለም ከዚህ በፊት ያላየችው የሰው ልጅ የመቅሰፍት ምድር መሆንዋ እንደማይቀር የተለያዩ የመገናኛ ብዙኃንና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሥጋታቸውን እየገለጹ ነው፡፡

በቅርቡ የስደተኞች ሁኔታ የሚከታተል (North Africa Migration Hub) የተባለ የጥናት ተቋም ሊቢያን መነሻ አድርገው በሕገወጥ መንገድ ጣሊያን የገቡ 341 ስደተኞችን በማነጋገር ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚለው ከሆነ፣ 85 በመቶ በሕገወጥ የስደት ጉዞ ያዩት የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ በየእስር ቤቱ ለወራት ያለምግብና ውኃ መታጎርና መሞት፣ የሴት ልጆች በግላጭ በአደባባይ መደፈር፣ የኩላሊት ንግድ፣ እንዲሁም በዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ አልፈው አውሮፓ ከደረሱ በኋላ ያጋጠማቸው አሳዛኝ ሕይወትን በተመለከተ ምንም ዓይነት ዕውቀትና ግንዛቤ ሳይኖራቸው ነው ለስደት የተነሱት ብሏል፡፡

 እነዚህ ሕገወጥ ስደተኞች በስደት ጉዞው ውስጥ ያሳለፉት አስፈሪና ዘግናኝ ችግርና አደጋም ሆነ አውሮፓ ውስጥ ያለውን ተጨባጭ ኑሮን በተመለከተ ቀደም ሲል ቢያውቁት ኖሮ ስደትን እንደማይመርጡ ተናግረዋል፡፡ በተለይም ከምሥራቅ አፍሪካ ኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ሶማሊያ የሚመጡ ሴቶች ስለስደት ጉዞው ፈተናና አደገኛነት ያላቸው ዕውቀት በጣም አነስተኛ መሆኑን፣ አብዘኛዎቹም በሕገወጥ ደላሎች የተደፈሩ፣ ከዚህም በተጨማሪ አዘዋዋሪዎቹ ስደተኞቹን አሳፍረው ለሚጓዙ አሽርካሪዎች (ሾፌሮች) ሴቶችን እንደ ተጨማሪ ክፍያ ለፆታ ጥቃት አሳልፈው እንደሚሰጡዋቸው ጥናቱ አረጋግጧል፡፡

በቅርቡም በአንድ ማንነቱ ያልታወቀ ጽንፈኛ ቡድን ብዛት ያላቸው የምዕራብና የምሥራቅ አፍሪካ ስደተኞች በሊቢያ በረሃ በጭካኔ በጥይት ተደብድበው መገደላቸውን፣ የተለያዩ መገናኛ ብዙኃንና ማኅበራዊ ድረ ገጾች በምሥል አስደግፈው አሰራጭተውታል፡፡

በዚህ በሰሃራ በረሃና በሜዲትራንያን ባህር የሚደረግ የስደት ጉዞ በጣም አስፈሪና አደገኛ ቢሆንም ግን፣ አሁንም ብዛት ያላቸው ስደተኞች ከሞት ጋር እየተፋጠጡ ወደ አዉሮፓ መጉረፍን አላቆሙም፡፡ ለዚህም ነው የችግሩ ገፋት ቀማሽ የሆነችው ጣሊያን በሊቢያ ትሪፖሊ ዘግታው የቆየችው ኤምባሲዋን በመክፈት ዋና ሥራውም  በሕገወጥ ደላሎች የሚደረገውን የሰው ንግድ መቆጣጠርና ጠንካራ ዕርምጃ እንዲወሰድ ማስተባበር እንደሚሆን፣ የአገሪቱ የአገር ውስጥ ጉዳይ ደኅንነት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ በተጨማሪም የሊቢያን ባህር ኃይል ማሠልጠንና ማጠናከር እንዲሁም በአገራቱ የባህር ክልል ወታደራዊ ቅኝት በማድረግ ሕገወጥ ስደተኞች በባህር ጉዞ ላይ እያሉ ወደ መጡበት የሚያስችል ሰምምነት ከሊቢያው የአንድነት መንግሥት ጋር ተፈራርማለች፡፡

የአውሮፓ መንግሥታት በሕገወጥ ስደት ምን ያህል እንደተማረሩና ከፍተኛ ጫና ውስጥ እንደገቡ በየቀኑ እየተነገረ ነው፡፡ በቅርብ በማልታ የተሰበሰቡት የአውሮፓ ኅብረት አባል አገሮች የአገር ውስጥ ጉዳይ ደኅንነት ሚኒስትሮች፣ ከአውሮፓ ውጪ በሰሜን አፍሪካ የስደተኞች መጠለያ ካምፕ በማቋቋም  በጉዞ ላይ ያሉትን ብቻ ሳይሆን አውሮፓ ውስጥ ገብተው የጥገኝነት ጥያቄያቸው ውድቅ የተደረገባቸውን ሕገወጥ ስደተኞች ለማስወጣት ውሳኔ ላይ ደርሰዋል፡፡

ይኼም የሚያሳየው የአውሮፓ አገሮች ሕገወጥ ስደተኞችን በራሳቸው ግዛት ውስጥ በካምፕ (Refugee Camp) ለዓመታት ማቆየት መፍትሔ እንዳልሆናቸው ነው፡፡ አሁን በተለያዩ የአውሮፓ አገሮች ጥገኝነት ጠይቀው በመጠለያ የሚገኙ የተለያዩ አገሮች ሕገወጥ ስደተኞችን አስወጥተው፣ በሊቢያና በቱኒዚያ በሚያቋቋሙት አዲስ መጠለያ ለማስፈርም ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡ በቀጣይም ወደ መጡበት አገር ለመመለስና ለማቋቋም የሚያስችል የፋይናንስ ድጋፍ በአውሮፓ ኅብረት እንዲሸፈን ወስነዋል፡፡ በተጨማሪም ሕገወጥ ደላሎችንና አዘዋዋሪዎችን ለመግታት እንዲቻል የሊቢያን ባህር ኃይል ለማሠልጠንና ለማጠናከር የ200 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ለማድረግ ወስነዋል፡፡

ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት እንደሚለው ከሆነ በአሁኑ ጊዜ በሕገወጥ መንገድ ወደ በለፀጉት አገሮች የሚደረግ ስደት ገንዘብና ራስን የሕገወጥ ደላሎች ሲሳይ ከማድረግ ዉጪ እርባና የለውም፡፡ የአውሮፓ አገሮች ሊታገሱት ከሚችሉት በላይ ስለሆናቸው፣ ማንኛውም የሕገወጥ ስደት የጥገኝነት ጥያቄ ላለመቀበል ብቻም ሳይሆን ያን ሁሉ መከራና ችግር አልፈው የገቡትንም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለማስወጣትና ለመመለስ ቆርጠው ተነስተዋል፡፡

ዛሬ ሰዎች በፍላጎት ወይም በሕገወጥ መንገድ ተታለው ሳይፈልጉ እንደሚሰደዱ የሚገልጹት በርካታ ድርጅቶች፣ የመሰደዳቸው ምክንያትና ከተሰደዱ በኋላ የሚያጋጥማቸው ያልተጠበቁት ሁኔታ ለአዕምሮ ሕመም ይዳርጋቸዋል፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት አውሮፓ ውስጥ ከገቡት ስደተኞች ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት ድብርት (Dipression) ውስጥ የሚገቡ ሲሆን፣ በተለይም በመጀመርያ ወደ ስደት የተጓዘ ግለሰብ በሄደበት አገር ባሰበው መንገድ መኖር ባለመቻሉና ወደፊት ኃላፊነት ወስዶ የሚያመጣቸው የቤተሰብ አካላት ሕይወትን አስመልክቶ በሚገጥመው መጨናነቅ የአዕምሮ ሕመም ችግር እንደሚፈጠርበት ነው፡፡ ብዙዎቹም የዚህ ችግር ተጠቂ ናቸው፡፡ በተለይም በመካከለኛው ምሥራቅ የዓረብ አገሮች በሕጋዊም ሆነ በሕገወጥ መንገድ ከሚጓዙት 23 በመቶ የሚሆኑት በአሠሪዎቻቸው ይደበደባሉ፡፡ 20 በመቶ የፆታ ጥቃት ስለሚገጥማቸው የአዕምሮ ችግር ውስጥ እንደሚገቡ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡

ከስደት ጋር ተያይዞ የአዕምሮ ጤናን ሊያውኩ የሚችሉ ተብለው ከተቀመጡት መካከል አንድ ሰው ስደትን ሲያስብ እንዴት ልጓዝ? ከደረስኩ በኋላ ማረፊያየስ የት ነው? ምንስ እሠራለሁ? እንዲሁም ሊያጋጥመኝ የሚችል ችግር ምን ይሆን? የሚሉትን ጥያቄዎች ቀድሞ ከመሰደዱ በፊት በአዕምሮው የሚያሳድረው ፍርኃት አንዱና ዋና መነሻ ነው፡፡

ስለአካባቢው ባህል፣ እምነትና የአኗኗር ዘይቤ ከማወቅ ጋር ተዳምሮ ሊያግባባ የሚችል ቋንቋ ያለመኖር፣ ሲጓዙ ታስቦ የነበረ ጥቅማ ጥቅምና ለውጥ ባሰቡት ልክ ያለማግኘትና በመሳሰሉት ስደተኛው ጭንቀቱ ተባብሶ ለከፍተኛ የአዕምሮ ሕመም ይዳረጋል፡፡ በተለይም ከምሥራቅ አፍሪካ  ከኢትዮጵያ፣ ከኤርትራና ከሶማሊያ የሚሰደዱ ሴቶች ዕውቀትን መሠረት ያላደረገ ስደት በማከናወናቸው በሚገጥማቸው ፆታዊ ጥቃት የጉልበት ብዝበዛና ድብደባ፣ በተለይ ተበድረው ከሄዱ ከገቡበት ዕዳ አንፃር፣ እንዲሁም ለቤተሰብ ሊያደርጉት ከሚያስቡትና በአጠቃላይ ሳይሳካላቸው ሲቀር በአዕምሮአቸው ላይ ከፍተኛ ጫናን ያሳድራል፡፡ ባልተገባ ሥራ በሕገወጥ ሥራ ውስጥም ይገባሉ፡፡ ያልቻሉት ደግሞ ወደ አገራቸው ሲመለሱ በቤተሰብ ሊገጥማቸው የሚችለውን ችግር በማሰብ ለአዕምሮ መታወክ እንደሚዳረጉ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በተለይም ኢትዮጵያና ኤርትራን በመሳሰሉ አገሮች ያለው የቤተሰብ ትስስር፣ የማኅበረሰብ ቁርኝትና ማኅበራዊ መስተጋብሩ ከውጭው ጋር ፍፁም የተለየ መሆኑ ችግሩን የከፋ ያደርገዋል፡፡ ጓደኛ፣ ቤተሰብ፣ ጎረቤት ዘመድም ሆነ ማኅበራዊ ጉዳይ በጋራ ለመምራት የሚያስችሉ ሁኔታዎች ያለመኖር ለብቸኝነትና በራስ የመተማመን መንፈስን ከማሳጣቱም በተጨማሪ፣ የአዕምሮ ሕመም ሊያስከትሉ የሚችሉ ሱሶች ውስጥ እንዲዘፈቁ እያደረጋቸው ነው፡፡ ‹‹አገሬ እያለሁ የገንዘብ እጥረት ነበረብኝ፡፡ እዚህ ግን አሁን በራስ የመተማመን ሰብዕናዬን አጥቻለሁ፡፡ ከእንግዲህም ተመልሼ ሙሉ ሰው የምሆን አይመስለኝም፤›› ብሏል አንድ በጀርመን የመጠለያ ካምፕ ውስጥ የሚገኝ ኢትዮጵያዊ ስደተኛ፡፡

‹‹በጉዞዬ ወቅት ስቃይ፣ ድብደባና ችግር እንዲሁም እምቦቀቅላ ሕፃናት ወደ ባህር ሲወረውሩ ያየሁት እስካሁን ድረስ የአዕምሮ እረፍት ነስቶኛል፡፡ እዚህ እንደደረስኩ ያገኘሁትና የጠበቅኩት ለማመን የሚያስቸግር ነው፡፡ የአዕምሮና የልብ ስብራቴን የሚጠግን አንዳችም ነገር አላገኘሁም፤›› ብሏል አንድ በጀርመን የመጠለያ ካምፕ የሚገኝ ኤርትራዊ ወጣት፡፡

ዜጎች በመረጃ ባልተደገፈ መንገድ መጓዝ ሊያመጣ የሚችለውን ከፍተኛ ችግር ተረድተው ሕጋዊ አግባብን እንዲጠቀሙ፣ በአገራቸው ውስጥ ሠርተው መለወጥ የሚችሉበትን  አግባብና ዕድል ለማመቻቸት ማስረዳት፣ በተለይ ያን ሁሉ የበረሃ ስቃይና መከራ ለማለፍ የሚያሳዩት ድፍረትና ቁርጠኝነት በአገራቸው ሠርተው ለመለወጥ ቢያውሉትና ቢተገብሩት ራሳቸውን ጠቅመው አገራቸውን የሚያኮሩ እንደሚሆኑ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ ከአስፈሪው በረሃና የባህር ማዕበል ጋር ግብግብ እንደሚገጥሙ ሁሉ ኑሮን ለማሸነፍና ለመለወጥ ቁርጠኝነቱና ድፍረቱ ለምን እንደሚያጡ አንዳንዴ ግራ የሚያጋባ ጉዳይ ነው፡፡

እዚህ ላይ በሕገወጥ ደላሎች ላይ የሚደረገው ሕጋዊ ዕርምጃ እንዳለ ሆኖ መንግሥት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ በተለይም የመገናኛ ብዙኃን በሕገወጥ የስደት ጉዞ ያለው ችግርና አደገኛ የሕይወት ውጣ ውረድ፣ የሚያስከትለው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ፣ ስደተኞች እንደ ተስፋይቱ ምድር በናፍቆት የሚጓዙባቸው አገሮች ያለውን እውነታና የመንግሥታቱ ፖሊሲ በማስገንዘብና በማሳወቅ ረገድ የተቀናጀና ቀጣይነት ያለው የግንዛቤ ሥራ ማከናወን ያስፈልጋል፡፡ በሕገወጥ ስደትም ሆነ ሕጋዊ  ሆኖ ቢጓዙም ያቀዱትን መሆን ባለመቻል የሚገጥሙ ችግሮች ከስደተኛው በተጨማሪ የቤተሰብ መበታተን፣ የተጧሪዎች ቁጥር መጨመር፣ የቤተሰብ አስተዳዳሪ የሆኑ ልጆች መብዛት፣ የሞት መበራከት፣ የአምራች ኃይል እጥረት፣ የግጭት መብዛት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አለመረጋጋት፣ ከዚህም በተጨማሪ ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ መሆንን እንደሚያመጣ ሁሉም ልብ ሊለው የሚገባ የጋራ ጉዳይ መሆኑን ትኩረት በመስጠት ችግሩን መቀነስ ያስፈልጋል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...