Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዝንቅ‹‹እጅ እነሣለሁ!!››

‹‹እጅ እነሣለሁ!!››

ቀን:

በአፍሪካ ኅብረት 28ኛው የመሪዎች ጉባኤ ላይ ከተገኙት መካከል (በግራ) የደቡብ ሱዳንና የሱዳን ፕሬዚዳንቶች ሳልቫ ኪር እና ኦማር ሀሰን አልበሽር፤ የዚምባቡዌና የግብፅ ፕሬዚዳንቶች ሮበርት ሙጋቤ እና አብዱልፈታህ አልሲሲ እጅ ሲነሣሱ፡፡

ፎቶ በናሆም ተስፋዬ 

*******

የመርዝ ዛፍ

ከወዳጄ ጋራ ተኳርፌ ነበር

ቁጣዬም አበቃ፤ ቁጣዬን ባማክር፡፡

ከጠላቴም ጋራ ነበር ተኳርፌ

ቁጣዬ ጠጠረ፤ ሳልነግረው ቀርቼ፡፡

ውኃም አጠጣሁት በሥጋት በፍርሃት፤

ቀንም ሆነ ሌሊት እንባዬን በማንባት

በፈገግታዎቼም አሞቅኩት ፀሐይ፤

በተለሳለሰ ሽንገላ አስመሳይ፡፡

ዛፊቱም አደገች ቀንና ሌሊት፤

ቁልጭ ያለች በለስ እስቲፈራላት

ያ የኔ ጠላትም ስታበራ አየና፤

ነገሩ ሲገባው የኔ ለመሆኗ፤

ከመካነ ዕጽዋቴ ሾልኮ በመግባት

ግንዷን ያ ጨለማ ሲሸፋፍናት፤

ማግስቱን ማለዳ በደስታ አየሁት

ከዛፏ ሥር ወድቆ፤ የተዘረረውን ያ የኔን ጠላት፡፡

የቅኔው ሰምና ወርቅ

ቅኔው ስለትዕግስት ሆኖ፤ በሰምና ወርቅ የተሸፋፈነ ነው፡፡ ማለትም፣ እኔ (ደራሲው) እባብን ተመስዬ (ሆኖም ህሊና ያለው እባብ)፤ ጠላቴን (የሰው ልጅ፤ አዳምን) በበለስ አጓጓሁትና ለውድቀት አበቃሁት፡፡ ሰሙ እንደዚህ ሲሆን፤ ወርቁ ደግሞ ቁጣዬን በገራሁት ኖሮ ጠላቴም ባልሞተ የሚለው ነው፤ ሁሉም ወዳጅ ሆኖ በሰላም በኖረ፡፡ ይህ ትርጓሜ የኔ ሲሆን፤ የናንተ የተለየ ቢሆን ሕገ ወጥ አያሰኘውም፡፡ የናንተ ትርጉም እንደ በለስ ያጓጓኛል፡፡

  • በዊልያም ብሊክ (1557-1727)፣ ስድ ትርጉም በከበደ ዳግማዊ

*******

ፍሬ ልቡና!

እነ ጃፓን እንዴት አድርገው ነው ለዚህ ታላቅ ልማትና እድገት የበቁት ብለው ነው፣ አንዳንድ የእኛ ሐሳብ አፍላቂዎች ፍተሻቸውን የወጠኑት፡፡ ይህን እኛ ብቻ ሳንሆን ብዙ የቀደሙት አገሮች ሕዝቦች ራሳቸውን ያስጨነቁበት ጥያቄ ነበር፡፡ ‹‹ለምን ወደኋላ ቀረን?!›› የተደጋገመ ጥያቄ፡፡ ‹‹ከ140 ዓመታት በፊት የተጀመረው የአእምሮን ሉዓላዊነትና ብርሃን ፈንጣቂነት፣ እንዲሁም የሰላም አስፈላጊነት ጅምር እንዴት ባለህበት እርገጥ ሆኖ ቀረ?›› አስቸጋሪ፣ ነገር ግን የግድ መልስ የሚሻ ጥያቄ ነው፡፡ ይህንኑ ጥያቄ ከአንድ ምዕት ዓመት በፊት ጀምረው ልክ እንደ እኛ የለውጥና የተሓድሶ ጉዞ እስካሁን ያልተሳካላቸው ሕዝቦች ይጠይቁታል፡፡ ጥያቄው ግን ቀላል መልስ የለውም፡፡ ወደ ጃፓን ተመክሮ ከመዝለቃችን በፊት ግን ልክ እንደ እኛ በቀደምት አያቶቻቸው ገናና ታሪክና ለዓለም ባበረከቱት አስተዋጽኦ የሚኩራሩት ዓረቦች ምሳሌ ላስቀድም መሰለኝ፡፡ ፕሮፌሰር ጀሚል አል ኻሊሊ የተባለ የኢራቅ ዝርያ ያለው የሳይንስ ታሪክ ተመራማሪና በሱሪ ዩኒቨርሲቲ የፊዚክስ ፕሮፌሰር፣ ቀደምት ዓረቦች ለምዕራባውያን እውቀት መዳበር ያደረጉትን አበርክቶ አስመልክቶ ዓረቦች ምን ያህል ለእንግሊዞች ባለውለታ እንደሆኑ በአጽንኦት ተናግሮ ሲያበቃ፣ አንዲት በዕድሜ ጠና ያሉ የንግግሩ አድማጭ ከወንበራቸው ብድግ ብለው ‹‹ዓረቦች፣ እውነትም አንተ አሁን የዘረዘርካቸውን ሁላ በዚያን ዘመን ካበረከቱ፣ ታዲያ አሁን ምን ሆነው ነው በአንድ ቦታ እየረገጡ ወደኋላ የቀሩት?›› የሚል ጥያቄ አቀረቡለት፡፡

‹‹የቀድሞ አያቶቻችን የተባለውን የእውቀት ምርት ማበርከት የቻሉት የማሰብ ነፃነት እስከተከበሩበት ጊዜ ድረስ ነበር፡፡ በኋላ ላይ የበላይነቱን ያሰፈነው ሃይማኖታዊ ጽንፈኛነት በነጻ የማሰብን መንፈስ አንቆ በመግደሉ ምክንያት የማሰብ፣ የመመራመርና አዲስ ሐሳብ የማፍለቁ ተግባር ሞተና የዓረቦቹ የሳይንስ እውቀት አበቃለት፡፡ የሁሉም መልስ በመንፈሳዊ መጻሕፍትና በቅርስ ውርሱ ውስጥ በሚገባ ተቀምጧል ስለተባለ፣ በአዲስ አስተሳሰብ ለመቅረብ የሞከረ ሁሉ ተወግዞ ካፊር (ከሃዲና ኢአማኝ) ተሰኘ፡፡ በኋላ ላይ የዓረቡን ዓለም ያቆረፈደው ድህነትም ተመራማሪዎቻችን በምርምርና አዲስ ሐሳብ ማፍለቅ ላይ እንዳይጠመዱ ቀፍድዶ ያዛቸው፤›› በማለት በረዥሙ አስረዳ ፕሮፌሰሩ፡፡

  • ዩሱፍ ያሲን፣ ‹‹ኢትዮጵያዊነት፤ አሰባሳቢ ማንነት በአንድ አገር ልጅነት›› (2009)  

*******

ገላምጣኛለች ያሏት ድመት ላይ የተኮሱት አዛውንት

ስማቸው ያልተገለጸ የ69 ዓመት አዛውንት አሜሪካ ውስጥ ገላምጣኛለች፣ የማይገባ አስተያየት አይታኛለች ያሏትን ድመት ተኩሰው መግደላቸውን ቴሌግራፍ ዘግቧል፡፡ በፍሎሪዳ አርሞንድ ኗሪ የሆኑት እኚህ አዛውንት፣ በገዛ መኖሪያቸው እንዲያ የገላመጠቻቸው ድመት እጅግ አናድዳቸው እንደነበር ለፖሊስ ገልጸዋል፡፡ ድመቷ የሌላ የ60 ዓመት ጐረቤት አዛውንት መሆኗ ታውቋል፡፡ ድመቷ ላይ የተኮሱት አዛውንት ድርጊቱን በንዴት ተገፋፍተው ያደረጉት እንደሆነ ቢገልጹም፣ እንስሳት ላይ በጭካኔ ጉዳት በማድረስ ክስ ሊቀርብባቸው ይችላል፡፡ ሰውየው ድመቷን ከፊታቸው ገለል ለማድረግ እንጂ ሊጎዷት አስበው አለመተኮሳቸውን ቢናገሩም ከዚህ በፊትም ድመት ላይ እንደተኮሱ አምነዋል፡፡ ይህችኛዋም ድመት በጣም ስትጎዳ የቀድሞዎቹ ድመቶች ግን ማምለጥ ችለዋል፡፡

*******

የፕሬዚዳንቱን ሞት የተነበዩት ኮከብ ቆጣሪ ታስረው በዋስ ተለቀቁ

የሲሪላንካው ፕሬዚዳንት ከጥቂት ቀናት በፊት እንደሚሞቱ ተንብየው የነበሩት የአገሪቱ ታዋቂ ኮከብ ቆጣሪ መታሰራቸውን፣ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ዘግቧል፡፡ የ52 ዓመቱ የቀድሞ የአገሪቱ ባሕር ኃይል አባል የዛሬው ኮከብ ቆጣሪ እንደተነበዩት ፕሬዚዳንቱ በተባለው ዕለት አልሞቱም፡፡ ነገር ግን ትንበያው በማኅበረሰቡ አለመረጋጋትን ፈጥሮ እንደነበር፣ ኮከብ ቆጣሪውም ትንበያቸውን ለስድስት ወራት በተለያዩ ማኅበራዊ ድረ ገጾች ሲጽፉ መቆየታቸውን ፖሊስ አስታውቋል፡፡ ኮከብ ቆጣሪው ከዚህ ቀደምም የቀድሞ የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ራጂቭ ጋንዲ ላይ የግድያ ሙከራ አድርገው እንደነበር ያስታወሰው ፖሊስ፣ ሰውየው ለእስር እንግዳ አይደሉም ብሏል፡፡ ለጊዜው በ13,300 ዶላር ዋስ ከእስር እንዲለቀቁ ሆኗል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...