Thursday, July 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ከወጡ የማይወርዱ ዋጋዎች

የአገራችን የግብይት ሥርዓት ቅጥ አልባ ስለመሆኑ በርካታ መረጃዎችን መደርደር ይቻላል፡፡ ሩቅ ሳንሄድ ሸማቾች የሚገጥመን የቀን ተቀን ችግር መመልከቱ በቂ ነው፡፡ በግልጽ ከሚታዩ ብልሹ የንግድ አሠራሮች ባሻገር ከሸማቾች ዕውቀት ውጭ የሆኑ ሥውር ውንብድናዎችን እንፈትሽ ካልን ብዙ ጉድ እናገኛለን፡፡ በአብዛኛው ሸማች ዘንድ አይታወቁ እንጂ ከግብይት ሥርዓቱ ውስጥ በርካታ ችግሮች ስለመኖራቸው የአገሪቱን ኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን የሚለኩ አካላት ግን በአኃዝ ጭምር አስደግፈው ሊነግሩን ይችላሉ፡፡

ከሁለት ሳምንት በፊት በዚሁ በሪፖርተር ጋዜጣ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ከአገሪቱ የግብይት ሥርዓት ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን በተመለከተ የጠቃቀሷቸው ነጥቦች ያለውን ችግር አጉልተው ያሳዩ ናቸው፡፡ በርካታ ነጋዴዎችንም እንድንታዘባቸው አስችሎናል፡፡

በገዥው እንደተጠቀሰው ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ውስጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለዕለታዊ ፍጆታ ከሚውሉ ዕቃዎች ጀምሮ እስከ ትላልቅ መሣሪያዎች፣ የግንባታ ግብዓቶችና ከፍተኛ ማሽነሪዎች ላይ ሳይቀር የገበያ ዋጋቸው ወርዶ ታይቷል፡፡ በትንሹ እስከ 30 በመቶ የሚደርስ የዋጋ ቅናሽ የታየባቸው በርካታ ምርቶች አገር ውስጥ ገብተዋል፡፡ ለየትኛውም አገልግሎት የሚውሉ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ባልተጠበቀ ሁኔታ ዋጋቸው ቀንሶ የቆየው ለተከታታይ ዓመታት ነበር፡፡  እነዚህን ምርቶች በገፍ በማስገባት ለሚታወቁ አገሮች አጋጣሚው ሲሳይ ሆኖላቸው ነበር፡፡ ከባንኩ ገዥ እንደተረዳነው አጋጣሚው መልካም ዕድል ነው፡፡ የዚያኑ ያህል ጉዳትም ነበረው፡፡ የዓለም ሸቀጣ ሸቀጥ ምርት ዋጋ መውረድ አገሪቱ ለገቢ ንግድ ታወጣ የነበረውን ወጪ ቀንሶላታል፡፡

ከነዳጅ ግዥ ብቻ በአንድ ዓመት ውስጥ ከ600 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማትረፍ ተችሏል፡፡ በሌሎች ምርቶችም ላይ የበለጠ ቅናሽ ታይቷል፡፡ ለሦስት ዓመታት የታየው ይህ ለውጥ ለአገራችን ሸማቾች ምን ፋይዳ ነበረው? ካልን ምላሹ ፀጉር የሚያስነጭ ሊሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም በዓለም አቀፍ ደረጃ ዋጋው የቀነሰ ምርት አገር ውስጥ ሲገባ መቀነስ ስለሚጠበቅበት ነው፡፡ በዓለም የገበያ ዋጋ ላይ ሸቀጦች ከ30 እስከ 50 በመቶ ቢቀንሱም፣ ምርቶች ወደ ኢትዮጵያ ገበያ ሲደርሱ የሚሸጡበት ዋጋ ግን አስተዛዛቢ ነበር፡፡ የብሔራዊ ባንኩ ገዥ ገለጻም ይህንኑ የሚያሳይ ነው፡፡ በልክ ማትረፍ ነውር የሚመስላቸው ስግብግብ ነጋዴዎች፣ የዓለም ገበያ ያመጣውን ዕድል ለሸማቹ ነፍገው የእጥፍ እጥፍ ስንጥቅ ትርፍ በመያዝ ሲቸበችቡ ታይተዋል፡፡

ዓለም አቀፍ ዋጋን መሠረት አድርጎ በቅናሹ ልክ በአገር ውስጥ ገበያ መሸጥ ሲጠበቅባቸው፣ ምናልባትም ከቀደመው የመሸጫ ዋጋቸው በላይ መቸብቸባቸው እየታወቀ ‹‹አደብ ግዙ›› አለመባላቸው ግራ ያጋባል፡፡

በዓለም ገበያ የነዳጅ ዋጋ ቁልቁል ሲወርድ በነዳጅ መቸርቸሪያ ማደያዎች ዘንድ የዋጋ ቅናሽ ይጠበቅ ነበር፡፡ መንግሥት ጥቂት ቅናሽ አድርጓል፡፡ የቅናሹ መጠን ግን ከዓለም የነዳጅ ዋጋ መውረድ ጋር ሲመሳከር በቂ ቅናሽ ነው ወይ? የሚለው ይቆየንና ቢያንስ ስለቀነሰ እኔም ቀንሻለሁ ማለቱን እንደ መልካም ምላሽ እንቁጠርለት፡፡

ወትሮም በትክክለኛው መንገድ የትርፍ ህዳጉን አስቀምጦ የመገበያየት ልምድ በሌለበትና ስንጥቅ ትርፍ በተለመደበት አገር ውስጥ፣ ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት የታዩት ለውጦች ግን ሸማችን ተጠቃሚ ማድረግ ይገባቸው ነበር፡፡

የቱንም ያህል ዋጋ ቢቀንስላቸው ተወደደ፣ ጨመረ በማለት ሸማቹን በጠራራ ፀሐይ የሚያሞኙትን፣ በስመ ነፃ ገበያ ሰበብ የሚቆልሉትን መንግሥት  ማስቆም አለመቻሉም ሊያነጋግር ይገባዋል፡፡ ቢያንስ 30 በመቶ ሊቀንሱ ይገባቸው የነበሩ ምርቶች 50 በመቶ ጨምረው እየተሸጡ ከሆነ፣ እነዚህን ወገኖች ታረሙ፣ ሥርዓት ያዙ ማለቱ ለምን ከበደው? በዚህ ዓይነት አሠራር፣ ‹‹የሚጨምር እንጂ የሚቀንስ ነገር የለም፤›› በሚለው ጊዜ አመጣሽ አነጋገር እንዲታጠር፣ የወጣ የማይወርድበት ሥርዓት ውስጥ እንዲሰነግ የተገደደ ሸማች ምን ያህል ሲበዘበዝ እንደቆየና አሁንም እየተበዘበዘ እንደቀጠለ ለማሳየት ከዚህ የበለጠ አጋጣሚ የለም፡፡ የግብይት ባህላችን ዓለም አቀፍ ገበያን ያገናዘበ ትክክለኛውን የንግድ አሠራር ያልተከለ ስለመሆኑ ከዚህ በላይ መረጃ ማቅረብ አይቻልም፡፡

አሁንም የሚታይ ወደፊትም ሊኖር የሚችል ከመሆኑ አንፃር እንዲህ ባሉ አጋጣሚዎች ሸማቹ ጥቅሙ እንዳይጎዳ መረጃ የሚያገኝበት አሠራር ቢዘረጋ ብዙ ነገሮችን ለማቃለል ይረዳል፡፡ የሸማቾች ማኅበራት በመንግሥት እንደተደለደሉት ዘይትና ስኳር ቸርቻሪ ከመሆን አልፈው፣ የሸማችን ጤና፣ አካባቢ፣ ባህልና መሰል መብቶች የሚጎዱ ምርቶች እንዳይመረቱ፣ ገበያ ላይ እንዳይሉ ከዋሉም አንገዛም ብለው የማመጽ ተግባራዊ መብትና ኃይል ይጎናጸፉ፡፡

የዓለም ዋጋ ሲቀንስ እዚህም እንዲቀንስ ኅብረተሰቡ መረጃ እንዲኖረው የማድረግ  ኃላፊነት ያለባቸው መንግሥታዊ ተቋማት ሊያስቡበት ይገባል፡፡ በአገራችን በተለይ ከአገሪቱ የገቢ ንግድ ሸቀጦች ውስጥ አብዛኛውን ድርሻ የሚወስዱት ለዕለት ፍጆታ  የሚውሉ ሸቀጦች የዋጋ መረጃዎችን አደራጅተው ለሸማቹ ለማድረስ የሚያስችል በመረጃ የተደገፈ ግብይት ለማካሄድ ስለምን አይቻል ይሆን?

የገበያ መረጃዎች ነዳጅና የውጭ ምንዛሪ ወይም የቡና ዋጋ ብቻ አይደሉም፡፡ ሸማቾችን ለመታደግ ከተፈለገ ብዙ ሸማቾች የሚጠቀሙባቸው ሸቀጣ ሸቀጥ ምርቶች ዋጋም በግልጽ በየዕለቱ የሚደርስበት መንገድ መኖር አለበት፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን የአገር ውስጥ ምርቶች መሸጫ ዋጋን በመሰብሰብ እናገራለሁ ማለቱ አባይረሳም፡፡ እርግጥ ነው በተወሰነ ደረጃ ይተገበራል፡፡ ዋናው ነገር ግን መንግሥት የዓለም ዋጋን መቀነሱን ካረጋገጠ ይህንኑ  በማሳወቅ ነጋዴዎችን መገሰጽ አይኖርበትም ትላላችሁ?

ይህም ቢባል ግን የዓለም ገበያ ዋጋ መውረድ ኢትዮጵያን አይጎዳም ማለት ዘበት ይሆናል፡፡ አገሪቱ ሸቀጦች የሚሸጡበት ዋጋ በዓለም ገበያ መቀዛቀዝ ምክንያት ሲቀንስ አገር ውስጥ የሚያሳድረውን ጫና እያየን ነው፡፡ አገሪቱ የምትልከው የምርት መጠን ጭማሪ ቢያሳይም፣ በዋጋው መውደቅ ምክንያት ማግኘት የሚገባንን ጥቅም ማጣታችን ግልጽ ነው፡፡ 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት