Friday, September 22, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የአገሪቱ ጎዳናዎች የሞት ማምረቻ ሆነው እንዳይቀጥሉ መንግሥት ኃላፊነቱን ይወጣ!

ከጊዜ ወደ ጊዜ አስከፊነቱ እየጨመረ የመጣውን የተሽከርካሪ አደጋ መግታት ያልተቻለው ለምን ይሆን? በማለት ገራገር ጥያቄ ማንሳት ወቅቱ አይደለም፡፡ ይልቁንም ብዙ የተባለበት ይህ አስከፊ አደጋ መሠረታዊ ችግሮቹ እየታወቁ በቸልተኝነት ምክንያት የዜጎቻችን ውድ ሕይወት በከንቱ ሲያልፍ፣ ለአካላዊና ለሥነ ልቦናዊ ቀውስ የሚዳርግ የአካል ጉዳት ሲደርስና ከፍተኛ መጠን ያለው የደሃ አገር ንብረት ሲወድም በስፋትና በተከታታይ እየታየ ነው፡፡ ማንኛውም ተግባር በሕግና በሥርዓት መመራት አለበት፡፡ እጅግ በጣም አስከፊ የሆነው የተሽከርካሪ አደጋ ቀንሶ የሰው ልጆች ሕይወት እንዳይቀጠፍ፣ ውጤታማና ተዓማኒነት ያለው የትራፊክ መቆጣጠሪያ ደንብ መኖር አለበት፡፡ ሰሞኑን የትራፊክ መቆጣጠሪያ ደንብ ፀድቋል፡፡ የትራፊክ አደጋዎችን ለመቀነስ ያስችላል የተባለው ይህ ደንብ መፅደቁ መልካም ሆኖ፣ በአግባቡ ተግባራዊ መደረግ ካልቻለ ግን ፋይዳ አይኖረውም፡፡ በመጀመሪያ ጥፋት በገንዘብ ቅጣት የሚጀምረው አዲሱ ማሻሻያ የተደረገበት ደንብ፣ እስከ መንጃ ፈቃድ ነጠቃ ድረስ ይዘልቃል ተብሏል፡፡ ጥሩ ነው፡፡ ችግሮቹን በደንብ አበጥሮ ማየት ግን ተገቢ ነው፡፡

ለትራፊክ አደጋ አስተዋጽኦ ያላቸው ተብለው ከተጠቀሱ ዋና ዋና ችግሮች መካከል አልኮል ጠጥቶ ማሽከርከር፣ መብራት ጥሶ ጉዳት ማድረስና የመሳሰሉት ተጠቃሽ ሆነዋል፡፡ ነገር ግን በጎዳና ላይ ከሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ለማስተዋል እንደሚቻለው የሞገደኛ አሽከርካሪዎች መብዛት፣ ብቃት የሌላቸው አሽከርካሪዎች መበራከት፣ በተለያዩ ዕፆችና ሱሶች የተለከፉ አሽከርካሪዎች መበራከት፣ የእግረኞች በአግባቡ በጎዳና ላይ አለመንቀሳቀስ፣ የሕግ አስከባሪዎች ቁጥጥር መላላት፣ መዘናጋትና በመደለያ መታለል፣ የመንገድ መሠረተ ልማቶች አለመሟላት፣ የትራፊክ መብራትና ምልክቶች በበቂ መጠን አለመገኘት፣ ራዳርን የመሳሰሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀም አለመቻል፣ ወዘተ የአደጋ መንስዔዎች ናቸው፡፡ መንግሥት ለእነዚህ መሠረታዊ ችግሮች የሚያሳየው ቸልተኝነት ከመብዛቱ የተነሳ የትራፊክ አደጋ የዘመናችን አሰቃቂ ክስተት ሆኗል፡፡

የአገሪቱ የተሽከርካሪ አደጋ ከመቼውም ጊዜ በላይ የዜጎችን ሕይወት እየቀጠፈ ነው፡፡ ሁነኛ መፍትሔ በአስቸኳይ ተፈልጎ ለመግታት ካልተቻለ አደጋው እየተባባሰ ይቀጥላል፡፡ ችግሮቹ ያለምንም መሸፋፈን ነጥረው ወጥተው መታየት አለባቸው፡፡ የችግሮቹን መጠን ደረጃ በደረጃ ስንቃኝ ከመንግሥት በኩል ያሉትን የማስፈጸም ብቃት ማነስ በተመለከተ የምናገኘው አለ፡፡ በተለይ ይህ ጉዳይ በቀጥታ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት አቅማቸውን አሳድገውና ተቀናጅተው ወደ ሥራ መግባት ሲገባቸው፣ የሞትና የውድመት መርዶ ከመንገር የዘለለ መፍትሔ ማመንጨት አልቻሉም፡፡ አቅማቸውን አስተባብረው ቆፍጣና ዕርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ተግባር ላይ ከማተኮር ይልቅ፣ እዚህና እዚያ የተበጣጠሱ ሲምፖዚየሞች እያዘጋጁ ኅብረተሰቡን ግራ ያጋቡታል፡፡ ውስጣቸውን ፈትሸው የጎደላቸውን አሟልተው በተሻለ ብቃት ላይ መገኘት ሲገባቸው፣ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚወከሉባቸው በጥናት ላይ የተመሠረቱ ግንዛቤዎችን መፍጠር ሲኖርባቸውና ለመፍትሔ የሚበጁ ግብዓቶችን ከምሁራንና ከባለሙያዎች ማግኘት ሲችሉ የሰው ሕይወት በከንቱ እየተቀጠፈ ነው፡፡

እስኪ የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ሥርዓቱን እንመልከት፡፡ በአገሪቱ ለተለያዩ ፕሮጀክቶች፣ ለንግድ ሥራዎችና ለግል አገልግሎት ብዛት ያላቸው ተሽከርካሪዎች ባለፉት አሥር ዓመታት አገር ውስጥ ገብተዋል፡፡ በዚህ የተነሳ በርካታ አሽከርካሪዎች በመፈለጋቸው የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ሥርዓቱ ተለውጧል፡፡ አንድ ሰው በአንድ ጊዜ ከባድ ተሽከርካሪ ለማሽከርከር የሚያስፈልገውን የመንጃ ፈቃድ ማግኘት ይችላል፡፡ ከታች ወደ ላይ ጊዜውንና ጥራቱን ጠብቆ ማደግ የነበረበት አሽከርካሪ ያለምንም ልምድ ከባድ ተሽከርካሪ ይይዛል፡፡ ያውም በለጋ የወጣትነት ዕድሜ፡፡ ሥልጠናውም ሆነ ምዘናው በጥራት ላይ ያልተመሠረተ በመሆኑ በብዛት ለሚደርሱ አደጋዎች ምክንያት ሆኗል፡፡ ከታች ጀምሮ እስከ መጨረሻው እርከን ድረስ የሥልጠናና የምዘና ሥርዓቱ ካልተፈተሸና ዕርምጃ ካልተወሰደ በስተቀር፣ እጁን በሚገባ ያላፍታታ አሽከርካሪ ሕዝብ መጨረሱን ይቀጥላል፡፡ የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ሥርዓቱ ከሙስና የፀዳ ባለመሆኑ በሚገባ ያልሠለጠኑ አሽከርካሪዎች ቀንና ሌሊት ሕዝብ እየፈጁ ነው፡፡ የደሃ አገር ንብረት እያወደሙ ነው፡፡ ይህ በሥራ ላይ ያለ የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ሥርዓት በአስቸኳይ ታርሞ መፍትሔ ካልተፈለገለት አደጋው ተባብሶ ይቀጥላል፡፡ የመንግሥትንም ቸልተኝነት ያሳብቃል፡፡

ሌላው ችግር የቁጥጥር መላላት ነው፡፡ የተሽከርካሪ አደጋን ለመቆጣጠር የሚረዳ ደንብ ቢወጣም ቁጥጥሩ ጠንካራ ካልሆነ ፋይዳ ቢስ ነው፡፡ ደንብ ለማስከበር ከሚሰማሩ ባለሙያዎች ጀምሮ እስከ ተቋማቱ ድረስ ያለው ዝርክርክነትና የግዴለሽነት ብልሹ አሠራሮች በብዛት ይታያሉ፡፡ በቂ የትራፊክ መብራቶች፣ የመንገድ ላይ ምልክቶች፣ በቴክኖሎጂ የተደገፉ የመቆጣጠሪያ ሥልቶች፣ ተከታታይነትና ወጥነት ያለው ሕግ የማስከበር እንቅስቃሴ፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለበት አሠራር፣ ወዘተ የሉም፡፡ ተቋማቱ በሠለጠነ የሰው ኃይል፣ በበቂ ተሽከርካሪዎች፣ በራዳር፣ ዘመኑ ባፈራቸው ቴክኖሎጂዎችና በበቂ በጀት ስለማይደገፉ አደጋው እየከፋ ነው፡፡ የቁጥጥር መላላቱ ከሥነ ምግባር ችግሮችና ከሙሰኝነት ጋር የተቆራኘ በመሆኑ ለአገር መከራ እየሆነ ነው፡፡ በምሽት ከመጠን በላይ አልኮል ተግተው የሚነዱ አሽከርካሪዎችና ደንታ ቢሶች በሚፈጥሩት ችግር የስንቶች ሕይወት እንደ ዋዛ የትም ቀርቷል፡፡ ሕግ አስከባሪዎች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት ባለመቻላቸው ምክንያት ብቻ ሕፃናት ያላሳዳጊ፣ አረጋውያን ደግሞ ያለጧሪና ቀባሪ ለጎዳና ኑሮ ተዳርገዋል፡፡ መንግሥት ምን እያደረገ ነው?

ቸልተኝነት የሚባለው አሳዛኝ የሆነ ድርጊት ደግሞ አደጋውን እያባባሰው ነው፡፡ የመንገድ ጥገና፣ የመንገድ ማቋረጫና የምልክት ቅቦች በምሽት ሲከናወኑ በአግባቡ የአቅጣጫ መጠቆሚያና ምልክቶች ሳይደረጉ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚመጡ ተሽከርካሪዎች ለአደጋ ተዳርገዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ክቡር የሆነ የሰው ሕይወት አልፏል፡፡ ለዚህ ዓይነቱ አሳዛኝ ክስተት መጠየቅ ያለበት አካል ዝም እየተባለ ሌሎች ግን ሰለባ ይሆናሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ መንጃ ፈቃዶች ከሚመለከተው አካል እየወጡ በገንዘብ ሲቸበቸቡ ሃይ የሚል የለም፡፡ በየሥርቻው ሐሰተኛ መንጃ ፈቃዶች እየተፈበረኩ በየቦታው ሲሠራጩ ለምን ብሎ የሚጠይቅ የለም፡፡ ሕግ አስከባሪው ክፍል በቁርጠኝነት ቢነሳ እኮ እንኳን ይህንን ዓይነቱን ተራ ድርጊት አይደለም ለማመን የሚቸግሩ ተግባራትን ማከናወን ይችላል፡፡ በአገሪቱ አውራ ጎዳናዎችም ሆነ በከተሞች ውስጥ ጠንካራ ቁጥጥር የማድረግ ፍላጎት ቢኖርና ከመጠን ያለፈ ራስ ወዳድነት ቢቀር ስንትና ስንት ተዓምር መሥራት ይቻል ነበር፡፡ ይህ ባለመሆኑ ግን አደጋው ከቁጥጥር ውጪ ሆኖ የአገር ሰቆቃ ሆኗል፡፡ ካሁን በኋላ የአገሪቱ ጎዳናዎች ከአደጋ ነፃ ይሁኑ፡፡ አደጋ በፍጥነት ይገታ፡፡ ግልጽነት፣ ተጠያቂነትና ኃላፊነት በተግባር ይረጋገጡ፡፡ ሕግ ይከበር፡፡ ለዚህ ደግሞ የሚመለከታቸው አካላት በፍጥነት ኃላፊነታቸውን ይወጡ፡፡ አዝጋሚ የሆነው የመንግሥት አሠራር ፍጥነት ይኑረው፡፡ የአገሪቱ ጎዳናዎች የሞት ማምረቻ ሆነው እንዳይቀጥሉ መንግሥት ኃላፊነቱን ይወጣ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...

በሰጥቶ መቀበል መርህ መደራደርና ሰላም ማስፈን ለምን ያቅታል?

በያሲን ባህሩ አገር ግንባታ የትውልድን ትልቅና ታሪካዊ ኃላፊነት የሚጠይቅ ተግባር...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲወገድ ነው!

ወጣቶቻችን የክረምቱን ወቅት በእረፍት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በበጎ ፈቃድ ሰብዓዊ አገልግሎትና በልዩ ልዩ ክንውኖች አሳልፈው ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞ መስከረም...

ዘመኑን የሚመጥን ሐሳብና ተግባር ላይ ይተኮር!

ኢትዮጵያ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ሁለት ታላላቅ ክስተቶች ተስተናግደውባት ነበር፡፡ አንደኛው የታላቁ ህዳሴ ግድብ አራተኛ የውኃ ሙሌት ሲሆን፣ ሁለተኛው ኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባ ከተማ ያስጀመረው...

ለሕዝብና ለአገር ክብር የማይመጥኑ ድርጊቶች ገለል ይደረጉ!

የአዲሱ ዓመት ጉዞ በቀናት ዕርምጃ ሲጀመር የሕዝብና የአገር ጉዳይን በየቀኑ ማስታወስ ግድ ይላል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ ዴሞክራሲ፣ ልማትና ዕድገት ያስፈልጋሉ ከሚባሉ ግብዓቶች...