Monday, March 4, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹አሁን የፖለቲካ ምኅዳሩን በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለውጥ ለማምጣት ለሚታገሉ የፖለቲካ ኃይሎች የመክፈቻ ጊዜ ነው››

ዶ/ር አሰፋ ፍስሃ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ተባባሪ ፕሮፌሰርና የፌዴራል ጥናት ማዕከል ሊቀመንበር

ዶ/ር አሰፋ ፍስሃ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ተባባሪ ፕሮፌሰርና የፌዴራል ጥናት ማዕከል ሊቀመንበር ናቸው፡፡ ሕገ መንግሥትና ተነፃፃሪ ፌዴራሊዝም ጥናት ላይ ኤክስፐርት የሆኑት ዶ/ር አሰፋ፣ በተለይ በተነፃፃሪ ፌዴራሊዝም መስክ ተቀዳሚ ከሚባሉ ምሁራን መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በርካታ የጥናትና የምርምር ሥራዎቻቸውን በአገር ውስጥና አውሮፓ ውስጥ በሚገኙ ዕውቅና ተቀባይነት ያላቸው ጆርናሎች ላይ አሳትመዋል፡፡ ዶ/ር አሰፋ ባለፉት 15 ዓመታት በዚሁ ዘርፍ በማስተማርና በምርምር አሳልፈዋል፡፡ ሰለሞን ጎሹ ተመራማሪና የፌዴራሊዝም ኤክስፐርቱን ዶ/ር አሰፋን በአገሪቱ የፌዴራሊዝም ሥርዓት ወቅታዊ ሁኔታ ላይ አነጋጋሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የፌዴራል መንግሥት መዋቅር በመላው ዓለም በተለይ ደግሞ በኢትዮጵያ እንዲስፋፋ ያደረገው ተጨባጭ ሁኔታ ምንድነው?

ዶ/ር አሰፋ፡- የኔሽን ስቴት (አንድ ብሔር፣ አንድ መንግሥት) ጽንሰ ሐሳብና ማነቆዎቹ ፌዴራሊዝም በመላው ዓለም በተለይም በኢትዮጵያ እንዲመረጥ ትልቅ ሚና ተጫውቷል፡፡ ይህም አንድ አውራ ብሔር የአገሪቱን ተቋማት በመቆጣጠር የራሱን ማንነት እያሳደገ ሌሎች ህዳጣን ወይም አናሳ ብሔሮች እንዲገለሉ ማድረጉ ያመጣቸውን ቅሬታዎች መቅረፍ ያስፈልጋል የሚል እሳቤን ይዞ የሚመጣ ነው፡፡ ከዌስትፋሊያ ጀምሮ የዳበረውና በምዕራቡ ዓለም የሚታወቀው የኔሽን ስቴት ጽንሰ ሐሳብ በዋነኛነት ታሳቢ ያደረገው አንድ ብሔር የሰፈረበት የአገር ግዛት ያስፈልጋል በሚል ነው፡፡ ይህም አገር የዚያን ብሔር ፍላጎት በማንፀባረቁና ያ ብሔር የሚሰፍርበት ግዛትና ከዚያ ብሔር የተውጣጣ መንግሥት መቋቋምን ታሳቢ ያደርጋል፡፡ ይኼ አስተሳሰብ ማኅበረሰቡንና ፖለቲካን ለመተንተንና ለመረዳት ግለሰብን በመሥፈርትነት ከሚጠቀመው የሊበራል ሞዴል ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ይህ ሞዴል ደግሞ በበርካታ ያደጉ ምዕራባውያን አገሮች ለዘመናት የተተገበረና የቅኝ ግዛት ዘመን ከተደመደመ በኋላ ወደ አፍሪካ የተቀዳ ነው፡፡ እርግጥ ነው ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት አልተያዘችም፡፡ ነገር ግን ረዥም የፖለቲካ ታሪክ ባላት ኢትዮጵያ በዘመናዊ የአገሪቱ ታሪክ የነበረው አስተዳደር የተማከለ፣ አሃዳዊ፣ ክርስቲያንና አማርኛ ተናጋሪ በመሆኑ ኔሽን ስቴት ነበር፡፡ ይህ ለኢትዮጵያ ማኅበረሰብ የሚፈለገውን ውጤት አላስገኘም፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በኢትዮጵያ ደረጃ የኔሽን ስቴት ግንባታው ሒደት በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ አልነበረም፡፡ በሒደቱ በቋንቋ፣ በባህልና በታሪክ የተሳሰረ አንድ አውራ ብሔር የሆነ ርዕዮተ ዓለም በመከተል ሌሎች አናሳ ብሔረሰቦችን በመጨፍለቅ የአገር ግንባታ ሒደቱን ሲመራ ነበር፡፡ በዚህ ሒደት የተገለሉ ቡድኖች ደስተኛ አልነበሩም፡፡

በተለያየ ጊዜያት ብቅ ያሉ የተለያዩ ርዕዮተ ዓለሞች ማርክሲዝም፣ ሊበራሊዝም፣ ሞዴርናይዜሽንና ግሎባላይዜሽንን ጨምሮ የተነበዩት አንድ ኔሽን ስቴት ሊበራልና ዴሞክራሲያዊ እስከሆነ ድረስ እንዲሁም ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ልማት እስካመጣ ድረስ አናሳ ብሔሮች ወደ አውራው ባህል፣ ልማድና ቋንቋ መቀላቀላቸውና መጥፋታቸው እንደማይቀር ነበር፡፡ ይኼ በተለይ በ1960ዎቹ የሚጠበቅ ነበር፡፡ ይሁንና በተግባር የታየው ተጨባጭ ሁኔታ ይህን አላረጋገጠም፡፡ ነገር ግን የኔሽን ስቴት አስተሳሰብ አሁንም ገዥ ሐሳብ ነው፡፡ አሁን ደግሞ አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ይህን አስተሳሰብ በግልጽ ለማስፋፋት እየጣሩ ነው፡፡ አሜሪካን ከዓለም አቀፍ ተቋማትና ከሁለትዮሽ ስምምነቶች ለማውጣት እየጣሩ ይገኛሉ፡፡ የኔሽን ስቴት ርዕዮተ ዓለም ትክክለኛ ስለመሆኑ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ቀላል ግምት የማይሰጣቸው የኅብረተሰብ ክፍሎችን ከፖለቲካ ሒደቱና ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸው ያገላል፡፡ ማንነታቸውም ሁለተኛ ደረጃ እንዲሰጣቸው ያደርጋል፡፡ ስለዚህ እነዚህ የተገለሉ ቡድኖች ኔሽን ስቴቱን ለማፍረስ ይጥራሉ፡፡ ስኮትላንድ በዩናይትድ ኪንግደም፣ ኪዩቤክ በካናዳና ካታሎኒያ በስፔን ለማድረግ የሚሞክሩት ይኼንን ነው፡፡ ከዚሁ ዓውድ አንፃር ከታየ የኢትዮጵያ የነፃነት እንቅስቃሴዎች ተመሳሳይ ምድብ ውስጥ የሚወድቁ ናቸው፡፡ ኔሽን ስቴት አግላይና የዴሞክራሲ ዕጦት የነበረበት ነው፡፡ እርግጥ ብዝኃነትን እንደ ውድቀት የሚያዩና ለአናሳ ብሔሮች ጉዳዩ ከአመጋገብና አለባበስ ባህል ያልዘለለ ነው ብለው የሚከራከሩ አሉ፡፡ ይሁንና ጠንካራ የባህል ተሟጋቾች የሆኑ እንደ ዊል ኪሚልካና ቻርለስ ቴይለር ዓይነት ምሁራን ኅብረ ብሔራዊ የአስተዳደር ሥርዓት በአንድ አገር ከአንድ በላይ ማንነቶች እንዳሉ ዕውቅና በመስጠት የተገለሉ ቡድኖች፣ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያኙ እንደሚያደርግ ይሞግታሉ፡፡ አንቶኒ ስሚዝ የተባሉ ኅብረ ብሔራዊ የአስተዳደር ሥርዓት ላይ በርካታ ምርምሮችን የሠሩ ምሁር ዘመኑ የብሔር ማንነት ያንሰራራበት እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ይህ ማለት የተለያዩ ርዕዮተ ዓለሞች ግምት እንዳልሠራ የሚያሳይ ነው፡፡

አሁን ሊበራል መንግሥት ራሱ የቡድን ፍላጎትን ገሸሽ ማድረግ አይችልም፡፡ የተከፋፈሉ ማኅበረሰቦች ያሉባቸው አገሮች ውስጥ ማኅበረሰቦች ራሳቸውን በመደብ፣ በፆታ ወይም በሲቪል ማኅበራት አደራጅተው ሊንቀሳቀሱ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ማንነት ወሳኙ የንቅናቄ መሣሪያ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል፡፡ አሁን በሊበራሉ ዓለም ራሱ አዲስ አመለካከት ብቅ ያለ ሲሆን፣ የቡድንና የግለሰብ መብቶች ጎን ለጎን ያሉና ሊከበሩ የሚችሉ ናቸው በሚል ያስገነዝባል፡፡ በአጠቃላይ ግን ሁለት ዓይነት የፌዴራል ሥርዓቶች አሉ፡፡ አሜሪካ፣ ጀርመንና ኦስትሪያ የሚከተሉት አካባቢያዊ ፌዴሬሽን አለ፡፡ የዚህ ዓይነት የፌዴራል ሥርዓት ዋነኛ ዓላማ ሥልጣን ከአንድ ማዕከል ወደ ተለያዩ ማዕከሎች እንዲሠራጭ ማድረግ ነው፡፡ ክልሎች አካባቢያዊ አስተዳደሮችን መሠረት አድርገው እንዲዋቀሩ ይደረጋል፡፡ ‘ኔሽን ስቴት ፌዴሬሽኖች’ በመባልም ይታወቃሉ፡፡ ምክንያቱም በፌዴራል ደረጃ አብላጫ ድምፅ የሚኖረው ብሔር በክልልም ደረጃ ተመሳሳይ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ በሌለ በኩል እንደ ኢትዮጵያና ህንድ ያሉ ፌዴሬሽኖች ዓላማ ሥልጣንን ከማሠራጨት በተጨማሪ የብሔሮችን ጥያቄ መመለስን ታሳቢ አድርገው የተዋቀሩ ናቸው፡፡ የብዝኃነትን ጥያቄ ለመመለስ ፌዴራሊዝምን መከተል ብቸኛው አማራጭ አይደለም፡፡

በኢትዮጵያ የነበረው ችግር ግን ብሔራዊ የነፃነት ንቅናቄዎች ማዕከላዊ መንግሥትን በመቃወም መንቀሳቀሳቸው ነው፡፡ የቡድን ማንነት ፖለቲካዊ ጉልበት አግኝቶ ነበር፡፡ ማንነት በሌሎች የፖለቲካ ንቅናቄ መፍጠሪያ ጉዳዮች ላይ የበላይነት አግኝቶ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ የፌዴራል ፕሮጀክት የተለያዩ የብሔር ቡድኖች ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩና በፌዴራል ተቋማት ፍትሐዊ ውክልና እንዲኖራቸው ቃል ይገባል፡፡ ራስን በራስ ማስተዳደር ፖለቲካዊና የግዛት ነፃነት ማግኘት ማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል የፌዴራል ተቋማት መሬት ላይ ያለውን ብዝኃነት ማንፀባረቅ አለባቸው፡፡ በቡድን ፎቶ ግለሰቦች ቀድመው የራሳቸውን ፎቶ እንደሚያዩት ሁሉ፣ የፌዴራል ተቋማቱ ውስጥ የተለያዩ የብሔር ቡድኖች ቀድመው የሚፈልጉት የቡድናቸውን ተወካይ ነው፡፡ ይህ የተቋማቱን ተቀባይነትም ይጨምራል፡፡ እነዚህ ቡድኖች በብሔራዊ ደረጃ የፖሊሲ አወጣጥ ላይ ተፅዕኖ የመፍጠር ዕድል እንዲያገኙም ያደርጋል፡፡

ሪፖርተር፡- ባለፉት ሁለት ዓመታት አገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች አለመረጋጋት አጋጥሞ ነበር፡፡ ለአንዳንዶች ይኼ የፌዴራል ሥርዓቱ በአግባቡ እየሠራ ላለመሆኑ ማሳያ ማሳያ ነው፡፡ ለሌሎች ግን የፌዴራል ሥርዓቱ ስኬት በቅርብ ከገጠመው መደናቀፍና መንገራገጭ በላይ የሰፋ ነው፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱ ተግዳሮቶችና ተስፋዎች ላይ ከእርስዎ በላይ የተመራመረ የለምና በአሁኑ ወቅት ሥርዓቱ ስላለበት ሁኔታ ያለዎት ምልከታ ምንድነው?

ዶ/ር አሰፋ፡- ይኼ በጣም ሰፊ ርዕሰ ጉዳይ ነው፡፡ በመጀመሪያ አገሪቱ የፌዴራል ሥርዓት እንድትከተል ያደረጋትን ከላይ የገለጽኩትን የፖለቲካ ዓውድ በአግባቡ መረዳት ይኖርብናል፡፡ በበርካታ መሥፈርቶች የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ጥያቄ ከመመለስና የፖለቲካና አስተዳደር አካላትን ከመገንባት አኳያ ብዙ ርቀት መጥተናል፡፡ ከ25 ዓመታት በፊት ዝቅተኛውን አገልግሎት ለመስጠት እንኳን የሚያስችል ተቋማዊ አቅምና የሰው ኃይል አልነበራቸውም፡፡ አሁን ክልሎች ከሰው ኃይል አንፃር በአግባቡ የተደራጁ ናቸው፡፡ በተወሰነ መልኩ የገንዘብ አቅምም አዳብረዋል፡፡ ይሁንና ችግሮችም እንዳሉብን ግልጽ ነው፡፡ ትኩረት ሰጥቼ መግለጽ የምፈልገውም ይህንኑ ነው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ አገሪቱ በ2008 እና በ2009 ዓ.ም. የገጠማት ተግዳሮት የጠቆመን ነገር ቢኖር፣ ፌዴራሊዝሙን እንደ አዲስ የማኅበረሰብ ግንባታ መሣሪያ አድርገን አለመጠቀማችንን ነው፡፡ ስኬታማ ፌዴሬሽኖች አዲስ ማንነት ለመፍጠር ፌዴራሊዝምን በአግባቡ ይጠቀሙበታል፡፡ ከሽግግሩ ጊዜ ጀምሮ እስካሁን የዘለቀው አንዱ አከራካሪ ጉዳይ በኢትዮጵያዊ ማንነትና በብሔር ማንነት መካከል ያለው ግንኙነት ነው፡፡ በእነዚህ ክርክሮች ሁሌም የሚስተዋለው ነገር በሁለቱ መካከል ግልጽ የሆነ ልዩነት እንዳለ መታመኑ ነው፡፡ ይኼ ግን ስህተት ነው፡፡ በፌዴሬሽን የተለያዩ ማንነቶች ይኖራሉ፡፡ የሆነ ቦታ ትወለዳለህ፡፡ የአንድ የሙያ ማኅበር አልያም ሃይማኖታዊ ቡድን አባልም ልትሆን ትችላለህ፡፡ ሁላችንም ኢትዮጵያዊ ነን፡፡ የተለየ የብሔር ማንነትም ይኖረናል፡፡ እነዚህን የተነባበሩ ማንነቶች እንዴት ማስታረቅ እንችላለን? በተገቢ ሁኔታ እየሠሩ ባሉ ፌዴሬሽኖች በተለያየ ደረጃ የተለያዩ ማንነቶች ይኖሩናል፡፡ ነገር ግን እነዚህ ማንነቶች ሁሌም ይጋጫሉ ማለት አይቻልም፡፡ የብሔር ማንነትህን በአካባቢያዊ አስተዳደሮች ልትጠቀምበት ትችላለህ፡፡ ነገር ግን ሁሉንም የሚያቅፈው ኢትዮጵያዊ ማንነትም አለህ፡፡ ኢትዮጵያዊ ማንነት በሌሎች ማንነቶች ላይ ዋጋ በመክፈል የሚገኝ እንደሆነ ወይም የብሔር ማንነት ከሌሎች ሁሉ ማንነቶች በላይ እንደሆነ አድርጎ ማሰብ የተሳሳተ የፌዴራሊዝም አረዳድ ነው፡፡ በእኔ ዕይታ በተለያየ ደረጃ የሚገኘው የፖለቲካ አመራርም ይህን ተገንዝቦ ፌዴራሊዝምን በመጠቀም የተለያዩ ማንነቶች ያላቸው የተለያዩ ህልሞች ለማስታረቅ አልቻለም፡፡

      ሁለተኛ በፖለቲካ ቀውሱም ሆነ ከዚያ በፊት በነበረው ጊዜ ያየነው ሌላው ችግር ራስን በራስ በማስተዳደር ፅንሰ ሐሳብ ላይ የተሳሳተ ዕይታ መኖሩ ነው፡፡ ራስን በራስ ማስተዳደር በክልላዊ ወይም አካባቢያዊ የፖለቲካ ተቋማት መተዳደር ማለት ነው፡፡ የራስን ቋንቋና ባህልን መጠቀምም ይጨምራል፡፡ ነገር ግን በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች ራስን በራስ የማስተዳደር መብትን ጎጥ ለመገንባት ሊጠቀሙበት ሲሞክሩ ይስተዋላል፡፡ ክልላዊ ብሔርተኝነት እያደገ በመጣበት ሁኔታ ይኼ አደገኛ ነገር ነው፡፡ ራስን በራስ ማስተዳደር ለሌላው ማንነት ክብር መስጠትና ማስተናገድም ጭምር ነው፡፡ በተለያዩ ማንነቶች መካከል ንግግርና ግንኙነት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ከቀውሱ በኋላ ወደ ተለያዩ ክልሎችና ራቅ ያሉ ወረዳዎች የመጓዝ ዕድል አግኝቼ ነበር፡፡ የፌዴራል ባንዲራን መያዝ አደገኛ ነገር እንደነበር ሰምቻለሁ፡፡ ልትገደል ትችላለህ ነው ያሉኝ፡፡ ክልላዊ ብሔርተኝነት ፅንፍ ይዞ በተሳሳተ አቅጣጫ በመሄድ የተለየ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎችን ሲያሸብር በማየቴ በጣም ነው የደነገጥኩት፡፡ እርግጥ ከጥቂት ዓመታት በፊት ተመሳሳይ ችግር በጋምቤላና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ተስተውሏል፡፡ ነገር ግን በዚህኛው ቀውስ ችግሩ ጎልቶ በመውጣቱ በርካታ የማኅበረሰቡ ክፍል በጠቅላላ በሥርዓቱ ዕጣ ፈንታ ላይ እንዲጨነቅ እስከማድረግ ደርሷል፡፡ በሽግግሩ ወቅት የወጣ የትምህርት ፖሊሲ አለን፡፡ በፖሊሲው መሠረት አማርኛ የአገሪቱ የሥራ ቋንቋ በመሆኑ ከሦስተኛ ወይም ከአምስተኛ ክፍል ጀምሮ ተማሪዎች እንዲማሩት መደረግ አለበት፡፡ ነገር ግን በአንዳንድ ክልሎች እንዳየሁት የአማርኛ ክፍል ሲጀምር ተማሪዎች ወጥተው ስፖርት እንዲሠሩ፣ እንዲዘፍኑ ወይም እንዲደንሱ ይደረጋል፡፡ ይኼ በአንዳንድ ክልሎች ታስቦበት የሚደረገው የሥራ ቋንቋው እንዳይስፋፋ ነው፡፡ ይኼ ሌላኛው ጎጥ የመገንባት መገለጫ ነው፡፡ ቡድኖች ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር በመደራደር ቋንቋቸው የፌዴራል መንግሥቱ የሥራ ቋንቋም እንዲሆን ማድረግ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ግልጽ የሆነ የፌዴራል ፖሊሲን አለመተግበር የጋራ ትስስሩን ያዳክማል፡፡

      ሦስተኛ የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ግንኙነት ተደጋጋፊ ነው፡፡ አንዳቸው ያለ ሌላቸው አይኖሩም፡፡ አንዱ ክልል ቀውስ ሲኖረው ችግሩ የዚያ ክልል ብቻ ይመስለናል፡፡ ነገር ግን በፌዴሬሽን ውስጥ የአንዱ ክልል ችግር ሌሎች ክልሎችንና የፌዴራል መንግሥቱን መንካቱ የማይቀር ነው፡፡ በቅርቡ ኦሮሚያና አማራ ክልሎች ችግር በገጠማቸው ወቅት መጀመሪያ ማንንም ሳይጠብቁ ምላሽ መስጠት የነበረባቸው ክልሎቹ ራሳቸው ናቸው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ሌሎች ክልሎችና የፌዴራሉ መንግሥት መርዳት አለባቸው፡፡ በኦሮሚያ ክልል ቀውሱ ለ11 ወራት ሲቀጥል የክልሉ መንግሥት ችግሩን ለመቅረፍ ምንም ዓይነት የፖለቲካ መፍትሔ አልሰጠም፡፡ እንደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ያሉ የፌዴራል ተቋማትም ችግሩን ለመቅረፍ ጥረት አላደረጉም፡፡ በአማራ ክልልም ተመሳሳይ ነገር ነው የተፈጸመው፡፡ ስለዚህ በፌዴራል ሥርዓታችን የእነዚህ ተቋማት ተመጋጋቢነት ማየት አልቻልንም፡፡ ተቋማቱ ብቻ ሳይሆን ሕዝቡም ይህ እምነት ያለው አይመስልም፡፡ ተቋማቱ የሚጠበቅባቸውን ሚና በወቅቱ ከመወጣት ይልቅ ገዥው ፓርቲ ምላሽ እስኪሰጥ ይጠብቁ ነበር፡፡ በሒደቱም በርካታ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በርካታ ንብረትም ወድሟል፡፡ ይኼ መሆን አልነበረበትም፡፡ ጣልቃ ገብነት የመጨረሻው አማራጭ መሆን ነበረበት፡፡ ችግሮቹን ለመቅረፍ መቅደም የነበረበት የፖለቲካ መፍትሔ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ከ22 ዓመታት ሕገ መንግሥታዊ ሙከራ በኋላም በፌዴራል ሥርዓቱ ቃልና የሕግ ማዕቀፍ፣ እንዲሁም ተግባራዊነት ያለው ሰፊ ክፍተት ላይ መሠረታዊ ልዩነት ያልታየው ለምንድን ነው?

ዶ/ር አሰፋ፡- ይህን ክፍተት ይበልጥ ዘርዘር አድርጎ መግለጽ ያስፈልጋል፡፡ በአንዳንድ ጉዳዮች ሥርዓቱ የገባውን ቃል በተግባር ፈጽሟል፡፡ ለምሳሌ ሰፋፊ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ተካሂደዋል፡፡ ኢኮኖሚውም በአግባቡ እያደገ ነው፡፡ ነገር ግን በአስተዳደር ረገድ ክፍተቶች በስፋት ይታያሉ፡፡ ከ1993 ዓ.ም. ጀምሮ ልማት ላይ ትኩረት ያደረገ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ይስተዋላል፡፡ በዚህም ምክንያት አሁን በአገሪቱ ሁለት ቁልፍ ፕሮጀክቶች አሉ፡፡ በአንድ በኩል ፌዴራሊዝሙ የኢትዮጵያ ዘመን ጠገብ የፖለቲካ ችግር የሆነውን የሥልጣን መሰብሰብን ለመቅረፍ በመፍትሔነት ተቀምጧል፡፡ በሌላ በኩል ልማት ላይ ያተኮረው ርዕዮተ ዓለም ደግሞ ሌላኛውን የኢትዮጵያ ዘመን ጠገብ ችግር ድኅነትን ለመፍታት በመፍትሔነት ተቀምጧል፡፡ በሌላ በኩል ልማት ላይ ያተኮረው ርዕዮተ ዓለም ደግሞ ሌላኛውን የኢትዮጵያ ዘመን ጠገብ ችግር ድኅነትን ለመፍታት በመፍትሔነት ተቀምጧል፡፡ እነዚህ ሁለት መሠረታዊ ምዕላዶች በራሳቸው ችግር አይደሉም፡፡ ነገር ግን በእነዚህ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ላይ ያሉ ችግሮች ለፖለቲካ ቀውሱ መነሳት ምክንያት እስከመሆን ደርሰዋል፡፡ የመንግሥት የልማት ርዕዮተ ዓለም ግዙፍ ፕሮጀክቶች በማዕከላዊነት እንድታቀዱ አድርጓል፡፡ በዚህም የተነሳ ክልሎችና ማኅበረሰቦች በፕሮጀክቶቹ ዕቅድና አፈጻጸም ላይ ያላቸው ተሳትፎ ላይ ጥያቄዎች ያነሳሉ፡፡ የፕሮጀክቶቹ ማኅበራዊ ጠቀሜታ ላይም ቅሬታዎች አሉ፡፡ በተደጋጋሚ ቀውሶች በተከሰቱባቸው የጋምቤላና የኦሮሚያ ክልሎች ማኅበረሰቡ ስለፕሮጀክቶቹ አስቀድሞ መንግሥት አላማከረንም የሚል ቅሬታ አለው፡፡ አንዳንድ ፕሮጀክቶች ደግሞ ስኬታማ ናቸው ቢባሉ እንኳን የአካባቢውን ማኅበረሰብ ፍላጎትና ጥቅም አስከብረዋል ሊባሉ አይችሉም፡፡ በዚህም ምክንያት የአካባቢው ማኅበረሰብ ቁጣውን ገልጿል፡፡ ይኼ ችግር ከመሬት ጋርም የተቆራኘ ነው፡፡ የሕገ መንግሥቱ መሬትን የተመለከቱ ድንጋጌዎች በራሳቸው ግልጽ አይደሉም፡፡ ይህም የመሬት አስተዳደር በተግባር ይበልጥ የተወሳሰበ እንዲሆን የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

ሕገ መንግሥቱ መሬትና የተፈጥሮ ሀብቶችን የተመለከቱ ሕጎች የማውጣት ሥልጣን የፌዴራል መንግሥቱ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ በፌዴራል ሕግ አማካይነት መሬት የማስተዳደር ሥልጣን የክልሎች እንደሆነም ተደንግጓል፡፡ ነገር ግን በአንቀጽ 40 ላይ መንግሥትና ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የመሬት የጋራ ባለቤቶች እንደሆኑ ተደንግጓል፡፡ ራስን በራስ ማስተዳደር በራሱ ከመሬት ጋር የተገናኘ ነው፡፡ በእኔ ዕይታ መሬት የፌዴራል መንግሥቱና የክልሎች የጋራ ሥልጣን ሥር የሚወድቅ ነው፡፡ የአገሪቱ ችግር ካለው የፓርቲ ሥርዓት ጋርም የተገናኘ ነው፡፡ በአገሪቱ ያለው የአውራ ፓርቲ ሥርዓት ከሃያ ዓመታት በላይ የፌዴራልና የክልል ተቋማትን በበላይነት ተቆጣጥሯል፡፡ ይህ እየሆነ ያለው በዴሞክራሲያዊ ሒደት እስከሆነ ድረስ ችግር የለውም፡፡ የሕዝቡ በጎ ፈቃድ እስካለ ድረስ በምርጫ እያሸነፉ ለበርካታ ጊዜያት ሥልጣን ላይ መቆየት በራሱ ችግር የለውም፡፡ ችግር የሚሆነው ይህ እየሆነ ያለው ያለ ሕዝብ በጎ ፈቃድ ከሆነ ነው፡፡ የአፍሪካንና የሌሎች አገሮችን የፖለቲካ ታሪክን እንዳነበብኩት አንድ ፓርቲ ምርጫን መቶ በመቶ ካሸነፈ በኋላ በ2008 እና በ2009 ዓ.ም. እንደታየው ዓይነት ተቃውሞ ማስተናገዱ እጅግ ያልተለመደ ነወ፡፡ ምርጫውን መቶ በመቶ ካሸነፍክና ለሕዝቡ ጥቅም እየሠራህ ከሆነ በዚህ መጠን በአጭር ጊዜ ውስጥ ተቃውሞ ሊቀርብብህ አይችልም፡፡

መንግሥት በግንቦት ወር 2007 ዓ.ም. ተመረጠ፡፡ መስከረም ወር 2008 ዓ.ም. መንግሥት መሠረተ፡፡ በኦሮሚያ ክልል ተቃውሞና አመፅ የጀመረው በኅዳር ወር 2008 ዓ.ም. ነው፡፡ ይኼ በጣም ያልተለመደ ክስተት ነው፡፡ ይኼ ለምን ሆነ ብለን መጠየቅ አለብን፡፡ የአውራ ፓርቲ ሥርዓታችን ከኢኮኖሚ ዕድገት፣ ከሕዝባዊ ንቅናቄና ከሰላምና ደኅንነት አንፃር ተዓምር ሠርቶ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን በዚህ ሒደት ታማኝ የተቃዋሚ ፓርቲን ገፍተን ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህም ምክንያት ተቃውሞ ያለው የኅብረተሰብ ክፍል ፓርላማና ሚዲያን ጨምሮ በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞውን የሚገልጽበት ዕድል ተነፍጓል፡፡ ይህ ደግሞ በተራው ተቃውሞ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ፅንፈኛ የሆነ የፖለቲካ አቋም ወደሚያራምዱ የውጭ ኃይሎች እንዲያዩ በር ከፍቷል፡፡ ለዚህም ነው አንጋፋ የተቃዋሚ ፖለቲካ አመራሮች በአደባባይ ተቃውሞውን እኛ እየመራነው አይደለም ሲሉ ያልተገረምኩት፡፡ አሁን የፖለቲካ ምኅዳሩን በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለውጥ ለማምጣት ለሚታገሉ የፖለቲካ ኃይሎች የመክፈቻ ጊዜ ነው፡፡ የአውራ ፓርቲ ሥርዓቱ ሌላኛው ተፅዕኖ ገዥው ፓርቲ በጣም ጠንካራና በፌዴራልና በክልል መንግሥታት ፍጹም የበላይነት ያለው በመሆኑ፣ ተቋማት የሚጠበቅባቸውን እንዳይሠሩ ተፅዕኖ መፍጠሩ ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ በሕግ ከተቋቋሙ ተቋማት ገለልተኛ ሆኖ መሥራት ይኖርበታል፡፡

ሪፖርተር፡- እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ኅብረ ብሔራዊ አገሮች የፌዴራል ሥርዓት ለመቀበል ምክንያት ከሚሆኗቸው መነሻዎች አንዱ የግጭት መፍቻ ሥርዓት ይዘረጋል መባሉ ነው፡፡ በአንዳንድ ሥራዎችዎ የፌዴራል ሥርዓቱ ግጭቶችን ለማብረድ ሥራ ላይ ስለመዋሉ ተከራክረዋል፡፡ ነገር ግን ብሔርና ማንነት ተኮር ግጭቶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተባባሱ መምጣታቸውን የሚያሳዩ ሪፖርቶች አሉ፡፡ እነዚህን የሚጋጩ ሐሳቦች እንዴት ይገመግሟቸዋል?

ዶ/ር አሰፋ፡- በእኔ እምነት የብሔር ግጭት ተብለው ሪፖርት የሚደረጉት አብዛኛዎቹ ጉዳዮች የብሔር ግጭቶች አይደሉም፡፡ የስልጤ፣ የቅማንትና የኮንሶ ጉዳዮችን እንደ ልዩ ሁኔታ መውሰድ ይቻላል፡፡ ቋንቋን መሠረት አድርገው የተዋቀሩ ክልሎች አሉን፡፡ በዚህም መሠረት በፌዴራል ደረጃ አናሳ የሆኑ ብሔረሰቦች በክልላቸው አብላጫ ድምፅ የማግኘት ዕድል አላቸው፡፡ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ዕውቅና ያገኙ 76 ብሔረሰቦች አሉ፡፡ ነገር ግን ዘጠኝ ክልሎች ብቻ ነው ያሉን፡፡ ስለዚህ በሁለቱ መካከል ያለመመጣጠን አለ፡፡ ስለዚህ በክልሎችም ውስጥ አናሳ ብሔረሰቦች ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን የእነዚህ አናሳዎች መብት በአግባቡ አይከበርም፡፡ የራሳቸው ክልል ወይም ዞን ወይም ወረዳ ያላቸው በተሻለ መብታቸው ይጠበቃል፡፡ ሆኖም በክልሉ ላይ የበላይነት ያላቸው ልሂቃን የሌሎችን መብት የማክበር አዝማሚያ አይታይባቸውም፡፡ በጥናታችን መሠረት እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ በአራት ጉዳዮች ላይ ማሻሻያ ሊደረግ ይገባል፡፡ አንደኛው ቁጥራቸው አናሳ ቢሆንም አናሳ ብሔረሰቦች በክልሉ ሕግ አውጭ፣ አስፈጻሚና ተርጓሚ አካል ውስጥ ተመጣጣኝ ውክልና እንዲኖራቸው ማድረግ ነው፡፡ ለእነዚህ ማኅበረሰቦች ተመጣጣኝ በጀት መመደብም ያስፈልጋል፡፡ እነዚህን ቡድኖች በአግባቡ በመያዝ አብላጫና አናሳ ድምፅ ባላቸው ወገኖች መካከል ያለውን ውጥረት ማርገብ ይቻላል፡፡ ሁለተኛው ዕርምጃ የራሳቸውን ቋንቋና ባህል እንዲጠቀሙ ማድረግ ነው፡፡ ይኼ ከግዛት ውጭ ያለ ነፃነት የሚባለው ነው፡፡ ኦሮሞዎች በአዲስ አበባ የሚጠይቁት ይህንን ነው፡፡ ሦስተኛው ዕርምጃ እነዚህ ሁኔታዎች ሳይሟሉ ከቀሩ የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ መፍቀድ ነው፡፡ የመጨረሻው ዕርምጃ ደግሞ በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች እንዲተገበሩ ማድረግ ነው፡፡ ብሔር ተኮር የሆኑ ግጭቶች የሉም ባልልም አብዛኛዎቹ ግን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ጉዳዮች ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ከእነዚህ የአናሳዎች መብቶች በተቃራኒ ያሉ የማንነት ጥያቄዎች አፈታት ላይ ተሳታፊ የሆኑ ተቋማትን የእስካሁን አፈጻጸም እንዴት አዩት?

ዶ/ር አሰፋ፡- በተቋማዊ የፖለቲካ ሒደት እንዲፈቱ ጥያቄ የቀረበባቸው የማንነት ጥያቄዎች በሙሉ ረጅም ጊዜ ወስደዋል፡፡ አንዳንዶቹም አሁንም እየታዩ ናቸው፡፡ በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ የማንነት ትርጉም በራሱ ግልጽ መግባባት ያልተፈጠረበት ጉዳይ ነው፡፡ ቡድኖች የተለየ ማንነት ለመያዝ ቋንቋ ብቸኛው መሥፈርት አይደለም፡፡ ከላይ የገለጽኳቸውን የተነባበሩ የማንነት መሠረቶች በመጠቀም ቡድኖች ለአዲስ ማንነት ሊንቀሳቀሱ ይችላሉ፡፡ በተለይ መገለልና አድልኦ ካለ ይኼ ተጠናክሮ ሊመጣ ይችላል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝብን ሲተረጉም ግትር ባልሆነ መንገድ ነው፡፡ ነገር ግን ኤክስፐርቶቹ ሲተረጉሙ ይህን መንፈስ ጠብቀው አይደለም፡፡ ተቋማቱም በአስቸኳይ ምላሽ አይሰጡም፡፡ አንዳንድ ጉዳዮች እስከ አሥር ዓመታት ይወስዳሉ፡፡ ጉዳዩን ለመፍታት ረጅም ጊዜ በወሰድክ ቁጥር የፖለቲካ ልሂቃኑ እንዲንቀሳቀሱና እንዲያደራጁ በሒደትም ፅንፈኛ አቋም እንዲወስዱ ዕድል ትሰጣለህ፡፡ ይህ ደግሞ ወደ ግጭት ሊያመራ ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- ለበርካታ አስተያየት ሰጪዎችና ተንታኞች የወልቃይት ጉዳይ የኢትዮጵያ የፌዴራል ሥርዓት ከዚህ ቀደም ያላየውን አዳዲስ ተግዳሮት ይዞ መጥቷል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአወዛጋቢነቱ አቻ በማይገኝለት በዚህ ጉዳይ ላይ የእርስዎ አቋም ምንድነው?

ዶ/ር አሰፋ፡- ወደ ታሪካዊ ውዝግቡ ጠልቆ መግባት ሳያስፈልግ ከወልቃይት ጉዳይ ጋር የተያያዙ ሁለት ችግሮች አሉ፡፡ አንደኛው የፖለቲካ ንቅናቄ ጉዳይ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የአናሳዎች መብት ነው፡፡ ቀደም ብሎ ሸዋ የሚባል ክፍለ ሀገር ነበር፡፡ አገሪቱ ከነበራት 14 ክፍለ ሀገሮች አንዱ ነበር፡፡ የአገሪቱም ዋና ከተማ ነበር፡፡ አሁን ይህ የለም፡፡ በሸዋ ክፍለ ሀገር ሥር የነበሩት አካባቢዎች አሁን በኦሮሚያ፣ በአማራና በደቡብ ክልሎችና በአዲስ አበባ አስተዳደር ሥር ይገኛሉ፡፡ ሐረርጌ ይባል የነበረው ክፍለ ሀገርም በሥሩ የነበሩት አካባቢዎች አሁን በኦሮሚያ፣ በሶማሌ፣ በሐረር፣ በአፋር ክልሎችና በድሬዳዋ አስተዳደር ሥር ይገኛሉ፡፡ እነዚህን ምሳሌዎች የማነሳው በወልቃይት ጉዳይ የተነሳውን የፖለቲካ ንቅናቄና ችግር ለማሳየት ነው፡፡ በአካባቢው አማርኛ ተናጋሪ ማኅበረሰብ በትክክል ሊኖር ይችላል፡፡ የዚህ ማኅበረሰብ መብት እንደ ማንኛቸውም አናሳዎች መብት ሊከበር ይገባል፡፡ ነገር ግን ይህ ግዛት የተወሰደው ከጎንደር በመሆኑ ለጎንደር ሊመለስ ይገባል የሚለው ክርክር ግን ከሸዋና ከሐረርጌ ምሳሌ ጋር ሲነፃፀር የራሱ ተቃርኖ አለው፡፡ ከታሪክ አንፃር በአንድ ወቅት ወደ ጎንደር ሥር ነበር፣ በሌላ ወቅት ደግሞ በትግራይ ሥር ነበር፡፡ የትኛው ታሪክ የበለጠ ተዓማኒና ጠቃሚ ነው? የሚለው አሁን አስፈላጊ አይመስለኝም፡፡ በአንድ ወቅት ቋንቋን መሠረት አድርገን ክልሎችን ለማደራጀት በሕገ መንግሥታችን ወስነናል፡፡ በአካባቢው አብላጫው ዜጋ ትግሪኛ ተናጋሪ ከነበረ በትግራይ ክልል ሥር የማይሆንበት ምንም ምክንያት አይታየኝም፡፡ ነገር ግን ይህን ነገር እንዳናይ ከመጠን በላይ የተደረገው የፖለቲካ ንቅናቄ የከለከለን ይመስለኛል፡፡ ነገር ግን ይኼ ውዝግብ የነዋሪዎቹ መብት እንዲከበር በምንም መንገድ ሊጋርደን አይገባም፡፡

 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ለኢትዮጵያ የሚበጀው ኮስተር ብሎ የባህር በር ጥያቄውን መግፋት ብቻ ነው›› ብሩክ ኃይሉ (ፕሮፌሰር)፣ አንጋፋ የዲፕሎማሲና የሚዲያ ባለሙያ

ለረጅም ዓመታት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አስተምረዋል፡፡ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በፈረንሣይና በአሜሪካ ተመድበው በዲፕሎማትነት አገልግለዋል፡፡ ዳያስፖራው በ‹‹ኖ ሞር›› ንቅናቄ ሲያደርግ በማስተባበር ተሳትፈዋል፡፡ መንግሥትና ዳያስፖራው ለአንድ...

‹‹የዋጋ ንረቱን ለማርገብ የተተገበረው የገንዘብ ፖሊሲ ውጤታማ ነው ለማለት ያስቸግራል›› አቶ አሰግድ ገብረመድህን፣ የፋይናንስ ባለሙያና አማካሪ

የዓለም ኢኮኖሚ በተለያዩ ተግዳሮቶች እየተፈተነ ነው፡፡ በተለይ የዋጋ ንረት መጠኑ ይለያይ እንጂ፣ የእያንዳንዱን አገር በር አንኳኩቷል፡፡ መንግሥታት ይህንን ችግር ለማርገብ የተለያዩ የፖሊሲ ዕርምጃዎችን እየወሰዱ...

‹‹በአመራሮቻችን የተነሳ የፓርቲያችን ህልውና ጥያቄ ውስጥ ገብቷል›› አቶ አበባው ደሳለው፣ የአብን አባልና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአማራ ከተመሠረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአመዛኙ የተሻለ ሕዝባዊ ድጋፍ ያገኘ፣ ከሦስት ዓመታት በፊት በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ተወዳዳሪ...