Saturday, June 10, 2023

ዓላማውን የሳተውንና ጥገኛውን የአፍሪካ ኅብረት የመለወጥ ጅምር

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ተቀማጭነቱ በአዲስ አበባ የሆነው 55 አባል አገሮች የሚሳተፉበት የአፍሪካ ኅብረት በፖለቲካዊና በአስተዳደራዊ አካላት የተዋቀረ ተቋም ቢሆንም፣ በበርካታ አፍሪካውያን ዘንድ እዚህ ግባ የሚባል ተቀባይነት የለውም፡፡ ኅብረቱ ከአፍሪካውያን ጋር ያለው ግንኙነት በጣም የላላና እነሱም የባለቤትነት ስሜት ስለማይሰማቸው፣ ይህ መለያየት ኅብረቱን ለአፍሪካውያን ዋጋ አልባ አድርጎታል፡፡ ምክንያቱም የዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ውስጥ ስለሌለ፡፡ አባል አገሮች በኅብረቱ ጥላ ሥር መሆናቸው ቢነገርም፣ በተለያዩ አኅጉራዊና ክፍለ አኅጉራዊ ጉዳዮች የተከፋፈሉ፣ ለታይታ ያህል አንድ ቢመስሉም ከአንድነታቸው ይልቅ ልዩነታቸው የሰፋ በመሆኑ ኅብረቱ በአፍሪካውያን ዘንድ ቸል ቢባል አይገርምም፡፡ የኅብረቱ አወቃቀር በራሱ ከክፍለ አኅጉራዊ የኢኮኖሚ ማኅብረሰቦችና ከመሳሰሉ ተቋማት ጋር ያልተቀናጀ ከመሆኑም በላይ፣ እያደገ ከመጣው የአፍሪካውያን የኢኮኖሚና የፖለቲካ መብቶች ፍላጎት ጋር ያልተጣጣመ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

በተጨማሪም የአፍሪካ ኅብረት ለሚያከናውናቸው ፕሮግራሞቹና የሰላም ማስከበር ተልዕኮው የውጭ ለጋሾች ጥገኛ መሆኑ ደግሞ ሁኔታውን የከፋ ያደርግበታል፡፡ በዚህም ምክንያት ኅብረቱ ከተጋረጠበት ችግር ውስጥ ወጥቶ ራሱን በአዲስ የለውጥ ምኅዋር ውስጥ ማስገባት የወቅቱ ጥያቄ ሆኗል፡፡ በአፍሪካ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች፣ የሰብዓዊ መብት ረገጣዎች፣ የብዙዎቹ አገሮች ፖለቲካ አሁንም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መሆኑ፣ ከድህነት ለመላቀቅ የሚደረገው እንቅስቃሴ አዝጋሚነት፣ ወዘተ የለውጥ ያለህ የሚሉ ናቸው፡፡ የአፍሪካ ኅብረት የወደፊት ዓላማዎቹ ነፃ የንግድ ቀጣና መፍጠር፣ የጋራ የጉምሩክ ሥርዓት መመሥረት፣ አንድ የጋራ ገበያ ማቋቋም፣ ወጥ የሆነ ማዕከላዊ ባንክና የጋራ መገበያያ ገንዘብ በመፍጠር አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ መገንባት የሚቻለው ደግሞ አሁን ባለው ተቋማዊ ቁመና አለመሆኑ ታምኖበታል፡፡ ይህም የለውጥን አስፈላጊነት የበለጠ አጉልቶታል፡፡

በበርካታ አፍሪካዊያን ዘንድ ያን ያህል ትኩረት የማይሰጠው የአፍሪካ ኅብረት አሁን ለውጥ የሚያስፈልገው ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ብዙዎች በብቃትና በውጤታማነት ድክመት ምክንያት የአኅጉሪቱን ዋነኛ ችግሮች መፍታት ተስኖታል የሚሉት የአፍሪካ ኅብረት፣ ችግሮቹን ከመሠረታቸው ፈትሸው ለጥንካሬ የሚያበቁት የለውጥ ምክረ ሐሳቦች ቀርበውለታል፡፡ ሰሞኑን በአዲስ አበባ የተካሄደው 28ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ በጎንዮሽ የቀረቡት የለውጥ ምክረ ሐሳች፣ እ.ኤ.አ. በሐምሌ ወር 2016 በሩዋንዳ ካጋሊ በተካሄደው የኅብረቱ ጉባዔ በመሪዎች ጥያቄ መሠረት ተሰናድቶ የቀረበ ነው፡፡ በወቅቱ ለሩዋንዳ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ በተሰጠው አደራ መሠረት ኅብረቱን እንደገና ለማደራጀትና ጉድለቶቹን ለመፈተሽ የሚረዱ ምክረ ሐሳቦች ተጠንተው እንዲቀርቡ ተወስኖ ነበር፡፡ ፕሬዚዳንት ካጋሜ ከውሳኔው በኋላ በአፍሪካ ውስጥ ታዋቂ የሆኑ ሰዎች የተሰባሰቡበት ዓቢይ ኮሚቴ በማቋቋም በዘንድሮ የመሪዎች ጉባዔ ለለውጥ የሚረዱ ምክረ ሐሳቦችን ይዘው ቀርበዋል፡፡

‹‹የአፍሪካ ኅብረትን በአስቸኳይ የማጠናከር አስፈላጊነት›› የሚል ርዕስ ያለውን የለውጥ ጥናት ሰነድ ይዘው የቀረቡት ፕሬዚዳንት ካጋሜ፣ ኅብረቱ ጥልቅ የሆነ ተቋማዊ ለውጥ በማድረግ ውጤታማነቱን ማሳደግ ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡ በቅርቡ የኅብረቱን ፕሬዚዳንትነት ለተተኪያቸው ያስረከቡት የቻድ ፕሬዚዳንት ኢድሪስ ዴቢ በመሩት የጎንዮሽ ስብሰባ የአፍሪካ መሪዎች ምክረ ሐሳቦችን መቀበላቸው ተሰምቷል፡፡ የቀረቡት የለውጥ ምክረ ሐሳቦች ኅብረቱ ለወደፊት ህልውናው ሲባል በ700 ገጾች በዝርዝር መቅረባቸው ተሰምቷል፡፡ እንደገና ማደራጀትና ተጨማሪ ኃይል መስጠት፣ የፕሮግራሞቹንና የፕሮጀክቶቹን አፈጻጸም ማጎልበትና ከአፍሪካውያን ጋር በማቆራኘት የራሱን አጀንዳ መቅረፅ የሚችልበት አቅም መፍጠር የሚሉት ናቸው፡፡ በተለይ በፋይናንስ በኩል የሌሎች ጥገኛ ከመሆን ወጥቶ ራሱን ችሎ የሚቆምበት መደላድል እንዲፈጠር አፅንኦት ተሰጥቷል፡፡

የአፍሪካ ኅብረት እጅግ በጣም የሚተችበትና በአፍሪካውያን ጭምር ዋጋ ቢስ ተደርጎ የሚታየው ቅድሚያ ሊሰጣቸው ለሚገቡ ጉዳዮች ትኩረት መንፈጉ ነው፡፡ በሰነዱ ውስጥ የተገለጹት የፖለቲካ፣ የሰላምና የፀጥታ፣ የኢኮኖሚ ትስስር፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ አኅጉሪቱን በሚገባ መወከልና የመሳሰሉት የአፍሪካ ምሁራን የዘወትር መነጋገሪያ ናቸው፡፡ በበጀት ራሱን መቻል አቅቶት የሌሎች ጥገኛ መሆኑ ደግሞ ሌላው የሚነሳ ጉዳይ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከክፍለ አኅጉር ድርጅቶችና ተቋማት ጋር ያለው ግንኙነት የላላ መሆኑና ትብብር አለመኖሩ፣ እንዲሁም በልማት ፕሮግራሞች አፈጻጸም ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ማጣቱ ይጠቀሳሉ፡፡

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀመንበር የነበሩት ኤራስተስ ምዌንቻ ኅብረቱ የራሱን ወጪ መሸፈን  አቅቶት የሌሎች ጥገኛ መሆኑ አንደኛው የለውጥ አጀንዳ ነው ይላሉ፡፡ ብዙዎቹ የአፍሪካ ኅብረት አባል አገሮች ዓመታዊ መዋጮአቸውን ካለመክፈላቸውም በላይ፣ ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጣቸው ስለሚያስቸግሩ ችግሩን ከሥሩ ለመቅረፍ አንድ ዘዴ መነደፉን አውስተዋል፡፡ በዚህም መሠረት እያንዳንዱ አባል አገር 0.2 በመቶ ከአፍሪካ ውጪ በሚመጡ ገቢ ዕቃዎች ላይ ታክስ በመጣል ለኅብረቱ 1.2 ቢሊዮን ዶላር በዓመት ማስገኘት እንደሚቻል ታምኖበታል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ይህንን ዘዴ ተግባራዊ ለማድረግ ኢትዮጵያ፣ ሩዋንዳ፣ ኬንያ፣ ቻድና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ዝግጁ መሆናቸው ተገልጿል፡፡ ምዌንቻ እንደሚሉት ይኼኛው ቀመር ፍትሐዊ እንደሆነ፣ ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር መሠረት የኅብረቱን በጀት 75 በመቶ ያዋጡ የነበሩት አምስት አገሮች ብቻ ናቸው፡፡ በዚህም የተነሳ የበጀት አቅርቦቱ አስተማማኝነት ስለሌለው የአፍሪካ ኅብረት ለበርካታ ፈተናዎች መጋለጡን ምዌንቻ አምነዋል፡፡ በተለይ ደግሞ የራሱን አጀንዳ ቀርፆ ለማራመድና በሶማሊያ ለተሰማራው የአፍሪካ ሰላም አስከባሪ ኃይል አስፈላጊውን ለማድረግ የበጀት ችግር ትልቁ ተግዳሮት ነበር ብለዋል፡፡ በአዲሱ የበጀት አቅርቦት ምክረ ሐሳብ አማካይነት ግን ኅብረቱ መቶ በመቶ ራሱን ሲችል፣ 75 በመቶውን ለልማት ፕሮግራሞች እንዲሁም ቀሪውን 25 በመቶ ደግሞ ለሰላም ማስከበር ተልዕኮ እንደሚያውለው ተጠቁሟል፡፡ በዚህም መሠረት አባል አሮች የአገሮቻቸውን ሕጎች በማስተካከል መዋጮአቸውን በአግባቡ እንደሚጀምሩ ይጠበቃል ተብሏል፡፡

ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ፣ ‹‹ለራሳችን ጉዳይ ራሳችን ለመክፈል ተስማምተናል፡፡ ይህ ውሳኔ ራስን ከጥገኝነት ለማላቀቅ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ ነው፡፡ ለራስ ክብር መስጠትና የራስን አጀንዳ በራስ ማውጣት ማስቻል ነው፤›› ሲሉ ምክረ ሐሳቡ በመሪዎች ጉባዔ ተቀባይነት ማግኘቱን አስታውቀዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ እንደሚሉት የአፍሪካ ኅብረት 97 በመቶ የሚሆኑ ፕሮግራሞቹ በውጭ ለጋሾች ነበር የሚሸፈኑት፡፡ እ.ኤ.አ. ከዲሴምበር 2016 ጀምሮ ግን ከግማሽ በታች የሚሆኑት አባል አገሮች ያለባቸውን ዕዳ በሙሉ ከፍለዋል፡፡ በተለይ ኅብረቱ በገንዘብ ሙሉ በሙሉ ራሱን እንዲችል ባለፈው ሐምሌ በኅብረቱ የመሪዎች ጉባዔ መወሰኑ፣ ተቋማዊ ለውጥ ለማምጣት መነሳሳትን መጫሩን ፕሬዚዳንት ካጋሜ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ይህ አጋጣሚ አይደለም አንዴ ከፋይ መሆን ሲጀመር ሁሉም አባል አገሮች ባለቤትነት ይሰማቸዋል፡፡ ጥቂት ትልቅ የሚባሉ አገሮች ብቻ መዋጮ መክፈል የለባቸውም፡፡ እያንዳንዱ አባል አገር የሚጠበቅበት ትክክለኛ ድርሻ መክፈል አለበት፤›› ብለዋል፡፡ በቀረበው ጥናት መሠረት ከጠቅላላ አባል አገሮች 30 ያህሉ በከፊል ወይም ሙሉ ለሙሉ ዕዳቸውን ያልከፈሉ ናቸው፡፡ ይህም በዕቅድ በሚያዝና በተግባር በሚገኝ በጀት መካከል ሰፊ ክፍተት ፈጥሯል፡፡

የአፍሪካ ኅብረት ሌላው ችግር የክንውኖች ተደራራቢነትና ከሌሎች አጋሮች ጋር ሊኖረው የሚገባው ቅንጅትና ትብብር ውጤታማ አለመሆን ነው፡፡ ለምሳሌ ከአፍሪካ ልማት ባንክ፣ ከአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን፣ እንዲሁም ከአኅጉራዊ የኢኮኖሚ ማኅበረሰቦች ጋር ያለው ግንኙነት ጥልቀት ሊኖረው ይገባል ተብሏል፡፡ በዚህም በተለያዩ መስኮች የሚደረጉ ጥረቶች እንዳይደራረቡና በቅንጅት ከመሥራት እንዳይፋለስ ለማድረግ የለውጥ ሒደት አስፈላጊነት ተመልክቷል፡፡ እዚህ ላይ በኅብረቱና በሌሎች ተቋማት መካከል ጥርት ያለ የሥራ ክፍፍል መኖር እንዳለበት ግን መዘንጋት እንደማይኖርበት የሚያሳስቡ አሉ፡፡ ጊዜና ገንዘብ ቆጣቢ የሆነ ተቋማዊ አደረጃጀት በመፍጠር የአፍሪካዊያንን ፍላጎት የሚያሟላ ኅብረት መሆን እንዳለበት በምክረ ሐሳቡ መዳሰሱን ምዌንቻም አስረድተዋል፡፡ የአፍሪካ መሪዎች ብዙ ጊዜ የሚወቀሱበት የአፍሪካ ኅብረትን ለአፍሪካውያን ፍላጎት በሚያመች መንገድ አላዋቀሩም ተብሎ ነው፡፡ እንደ አኅጉራዊ ተቋምነቱ በአፍሪካዊያን ዘንድ ተዓማኒነት ማጣቱ በራሱ የአሁኑን ለውጥ አስፈላጊነት ያጎለዋል ተብሏል፡፡

ፕሬዚዳንት ካጋሜ የለውጥ ምክረ ሐሳቦችን ሪፖርት ሲያቀርቡ እንዳስረዱት፣ የአፍሪካ ኅብረት ያጋጠመው ፅኑ የሚባል ችግር ውሳኔዎቹን ተግባራዊ ሲያደርግ ቀውስ ውስጥ መዘፈቃቸው ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ኅብረቱ በአፍሪካውያን የማይጠቅም ተቋም ተብሎ ተፈርጇል፡፡ የአፍሪካ ኅብረት በተለያዩ የትኩረት ምልከታዎቹ ምክንያት የተከፋፈለ፣ ከመጠን በላይ በለጋሾች ዕርዳታ ላይ ጥገኛ የሆነ ተቋም ነው ሲሉ ካጋሜ የችግሩን ፅናት አመልክተዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ይህንን ተቋማዊ የለውጥ አጀንዳ እንደ ወትሮው ሁሉ ዝም ብሎ መቀበል ሳይሆን፣ በመሪዎች ጉባዔም ሆነ በአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን አማካይነት ኃላፊነቱን የሚወጣ አካል ተመድቦ በግልጽ ለውጥ መታየት አለበት ሲሉ ፕሬዚዳንት ካጋሜ ማሳሰባቸው ተደምጧል፡፡

የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ወደ አፍሪካ ኅብረት ከተቀየረ 17ኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ የአፍሪካ ኅብረት 55 አባል አገሮችን ይዞ ያነገባቸው ዓላማዎችም ከሞላ ጎደል አራት ናቸው፡፡ እነሱም የአኅጉሪቱን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ትስስር ማፋጠን፣ ዓለም አቀፍ ትብብሮችን በማጠናከር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ሁለንተናዊ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች ሥራ ላይ እንዲውሉ ማገዝ፣ የአኅጉሪቱን ሰላምና ፀጥታ ማረጋገጥ፣ ዴሞክራሲያዊ መርሆችንና ተቋማትን በማስተዋወቅ የአኅጉሪቱን ሕዝቦች ተሳትፎ ያረጋገጠ መልካም አስተዳደር ማስፈን ናቸው፡፡ ምንም እንኳ በአፍሪካ ያለው ሰላምና ፀጥታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለና የኢኮኖሚ መነቃቃት እየታየ ቢሆንም በተለይ የወጣቶች ሥራ አጥነትና ስደት፣ በመንግሥታቱ አስተዳደር ደስተኛ ያለመሆን፣ ዴሞክራሲ በሚፈለገው መጠን አለመጎልበቱና ተስፋ መቁረጥ እንደ ችግር ይወሰዳሉ፡፡ የአፍሪካውያን ድምፅ በሚገባ የማይደመጥበት የአፍሪካ ኅብረት፣ ግልጽ በሆነ አሠራር ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ተግባራት ባዕድ መሆኑና ለጋሾች በሚሰጡት ገንዘብ አጀንዳቸውን ማራመጃ ማድረጋቸው ሌላው ራስ ምታት ነው፡፡

‹‹ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔዎች›› የሚባለውን ኅብረቱ አሁንም ቅድሚያ የሚሰጠው አጀንዳ ቢሆንም፣ በአፍሪካ የውስጥ ጉዳዮች የውጭ እጆች ይታያሉ፡፡ በአገሮቹ መካከልም መጠራጠር እንዲኖርና ለክፍፍል በር ይከፍታሉ ይባላል፡፡ የአፍሪካ ኅብረት ራሱን ባለመቻሉ ምክንያት በተባበረ ድምፅ ሲወከል በብዛት አይታይም፡፡ እንደ ምሳሌም የሚወሳው በእንግሊዝኛና በፈረንሣይኛ ተናጋሪዎች መካከል ያለው ልዩነት፣ ከዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት አባልነት መገለል ላይ ተመሳሳይ ድምፆች አለመስማት፣ የክፍለ አኅጉራዊ የኢኮኖሚ ማኅበረሰቦችና የአፍሪካ ኅብረት አለመናበብ፣ ወዘተ ይጠቀሳሉ፡፡ በእንዲህ ዓይነቱ አጣብቂኝ ውስጥ የዘለቀው የአፍሪካ ኅብረት ከመዋቅራዊ ለውጥ በቀር የሚበጀው እንደሌለ ነው የሚነገረው፡፡

የአፍሪካ ኅብረት የኢኮኖሚ ጉዳዮች ኮሚሽነር አንቶኒ ሞታዬ ማሩፒንግ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ አዲሱን ለውጥ ተግባራዊ ለማድረግ ብዙ አገሮች ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት በተለይ የኅብረቱ መዋጮ የተወነሰ ጊዜ ተሰጥቶታል፡፡ አገሮቹ ለመዋጮው ራሳቸውን ለማዘጋጀት ይህ ዓመት እንዲሰጣቸው፣ ሌሎች ደግሞ ከአዲሱ አሠራር ጋር የሚጣጣም የሕግ ማስተካከያ ማድረግ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል ብለዋል፡፡ በዚህም መሠረት እ.ኤ.አ ከ2017/18 ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን ማረጋገጫ ሰጥተዋል፡፡ ከፕሬዚዳንት ካጋሜ ቢሮ የወጣው አጭር መግለጫም፣ ‹‹ዋናው ግብ ቀልጣፋና ውጤታማ የአፍሪካ ኅብረት እንዲኖርና በዚህም መሠረት በዓለም አቀፍ ደረጃ የአፍሪካውያንን የጋራ ድምፅ ማስተጋባት ነው፤›› ብሏል፡፡ ይህንን  ተስፋ ሰንቋል የተባለ አዲስ ጅምር ለማሳካት ምን ያህል ቁርጠኝነት አለ? የሚለው ራሱን የቻለ ጥያቄ ነው፡፡  

በጣም የሚጠበቀው አዲሱ መዋቅራዊ ለውጥ አበክሮ የሚያሳስበው ኅብረቱ ትኩረቱን በተወሰኑ ነገር ግን ቅድሚያ በሚሰጣቸው ጉዳዮች ላይ ማድረግ ነው፡፡ ኅብረቱ አኅጉሪቱን ወደ ውህደት ከሚያመራው ተቀዳሚ ጉዞው ወጥቶ ሲባንክ መቆየቱና ሁሉም ቦታ ጥልቅ እያለ መደራረቦችን መፍጠሩ ያስተቸዋል፡፡ በአኅጉሪቱ ውስጥ የሚታዩ የሰላምና የፀጥታ መደፍረሶች ታክለውበትና ከቅኝ ግዛት ዘመን የተንከባለሉ ችግሮች ጥርት ያለ ዓላማ ይዞ እንዳይንቀሳቀስ እንቅፋት መሆናቸው ይነገራል፡፡ አሁን ግን በአዲሱ የለውጥ ምክረ ሐሳብ በአፍሪካ ኅብረት ሥር ያሉ ተቋማትን ሚና እንደገና ማደራጀትና ግልጽ የማድረግ አስፈላጊነት ሰፍሯል፡፡ በዚህም አሁን በተጨባጭ የሚታየውን ነባራዊ ሁኔታ መቀየር ዋናው ጉዳይ ሆኗል፡፡ በተጨማሪም የኅብረቱን የፍትሕ አካላትና የፓን አፍሪካ ፓርላማን ኃላፊነትና ሚና ግልጽ የማድረግ ጉዳይም በሰነዱ ውስጥ ተካቷል፡፡ ልዩነት መፍጠር ከቻሉ በሚል፡፡

ሌላው የአፍሪካ ኅብረት ብዛት ያላቸው ስብሰባዎች፣ ደንቦችን ማውጣትና የፖለሲ ቀረፃዎች ጉዳይ ነው፡፡ እነዚህ ሚዛናቸውን መጠበቅ ያልቻሉ ነገር ግን ጠቀሜታ ሊኖራቸው ቢችልም ጉዳታቸው ያመዝናል ነው የሚባለው፡፡ ባለፈው ዓመት ብቻ ከ200 በላይ ፖሊሲዎችንና ስምምነቶችን ለማዘጋጀት ከፍተኛ ወጪ መውጣቱ ይነገራል፡፡ አንድ ፖሊሲ ለመቅረፅ 200 ሺሕ ዶላር ያህል ያስወጣል፡፡ በዓመት አንድ ቢሊዮን ዶላር የወጣባቸው ፖሊሲዎች ተግባራዊ መሆን አለመቻላቸው ደግሞ ሌላው ራስ ምታት ነው፡፡ ይህንንና መሰል ተግዳሮቶችን መልክ ለማስያዝና ኅብረቱ በእርግጥም የአፍሪካውያን እንዲሆን ለውጡ አይቀሬ መሆን እንዳለበት ብዙዎችን አስማምቷል፡፡ ተቋማዊ ለውጡ ተግባራዊ ተደርጎ ኅብረቱ ፕሮጀክቶቹንና ፕሮግራሞቹን ለማሳካት ዝርዝር ፍኖተ ካርታ ቀርቧል፡፡ ከዚህ በኋላ የሚጠበቀው ተግባራዊነቱ ብቻ ነው፡፡ (ለዚህ ዘገባ አሥራት ሥዩም አስተዋጽኦ አበርክቷል)

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -