Wednesday, April 17, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሐዋሳና ሰመራ ኤርፖርቶች ተርሚናል ግንባታ ለአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ተሰጠ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት የሐዋሳና የሰመራ ኤርፖርቶች የመንገደኞች ማስተናገጃ ሕንፃዎች ግንባታ ለሁለት አገር በቀል ኮንስትራክሽን ድርጅቶች ሰጠ፡፡

የሐዋሳ ኤርፖርት ተርሚናል ግንባታ ኤፍኢ ኮንስትራክሽን ኩባንያ በ126,534,721 ብር ለማካሄድ ጨረታውን ያሸነፈ ሲሆን፣ የሰመራ ኤርፖርት ተርሚናልን ግንባታ ደግሞ አፍሮ ጽዮን ኮንስትራክሽን ኩባንያ በ149,852,672 ብር አሸንፏል፡፡

የኮንትራት ውሉን የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ቴዎድሮስ ዳዊት ከኤፍኢ ኮንስትራክሽን ባለቤትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፍፁም ታዬ ጋር፣ ዓርብ ጥር 26 ቀን 2009 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤት ተፈራርመዋል፡፡

የሐዋሳ ኤርፖርት ዘመናዊ የመንገደኞች ማስተናገጃ ሕንፃ በአንድ ጊዜ 120 መንገደኞች የማስተናገድ አቅም ይኖረዋል፡፡ የሕንፃውን ንድፍ በረከት ተስፋዬ ኮንሰልቲንግ አርክቴክትስ ኤንድ ኢንጂነርስ ሠርቶ አጠናቋል፡፡ የአውሮፕላን መንደርደሪያና ማረፊያ ሜዳው በዮቴክ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ አራት ወራት ሆኖታል፡፡ የተርሚናሉን ግንባታ ኤፍኢ ኮንስትራክሽን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ውል ገብቷል፡፡

የሰመራ ኤርፖርት የመንገደኞች ማስተናገጃ ሕንፃ በአንድ ጊዜ 120 መንገደኞች የማስተናገድ አቅም ያለው ዘመናዊ ሕንፃ ሲሆን፣ አፍሮ ጽዮን ኮንስትራክሽን በዘጠኝ ወራት ጊዜ ውስጥ ገንብቶ ለማስረከብ ተስማምቷል፡፡ አፍሮ ጽዮን ኮንስትራክሽን የሰመራ ኤርፖርት የአውሮፕላን ማኮብኮቢያና ማረፊያ ግንባታን በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

የሰመራ ኤርፖርት መንገደኞች ማስተናገጃ ሕንፃ ንድፍ የሠራው ኬ2ኤን አርክቴክቶችና ኢንጂነሮች የተሰኘ ኩባንያ ነው፡፡ የሁለቱም ተርሚናሎች ንድፍ የአካባቢዎቹን ሕዝቦች ባህልና አኗኗር የሚያንፀባርቅ ነው፡፡

በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት አቶ ቴዎድሮስ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት በሁሉም ክልሎች ተደራሽ ለማድረግ በርካታ የኤርፖርቶች ግንባታ ፕሮጀክቶች በማካሄድ ላይ እንደሆነ ገልጸው፣ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ያሉትን ኤርፖርቶች ቁጥር ወደ 30 (25 አስፋልትና 5 ኤር ስትሪፕ) ለማሳደግ አቅዶ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ድርጅቱ የሐዋሳ፣ የሰመራ፣ የጂንካ፣ የሮቤ፣ የሽሬ ኤርፖርቶችን በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡

የሐዋሳና የሰመራ መንገደኞች ማስተናገጃ ሕንፃዎች ግንባታ ሁለት ዓመት የሚፈጅ ቢሆንም፣ ከኮንትራክተሮች ጋር በመደራደር በአንድ ዓመትና ባነሰ ጊዜ ገንብቶ ለማጠናቀቅ ከስምምነት ላይ መደረሱን አቶ ዳዊት ተናግረዋል፡፡

የሕንፃዎቹ ግንባታ ቀደም ብሎ መካሄድ የነበረበት ቢሆንም፣ የፋይናንስ ምንጭ ከውጭ ባንኮች የማፈላለግ ሥራ ጊዜ በመውሰዱ በታሰበው ጊዜ ግንባታው ሊካሄድ እንዳልቻለ የገለጹት አቶ ቴዎድሮስ፣ ከውጭ ፋይናንስ ለማግኘት የተደረገው ጥረት ባለመሳካቱ በራስ አቅም ለመጠቀም መወሰኑን አስረድተዋል፡፡ የባከነውን ጊዜም ለማካካስ የግንባታውን ጊዜ ለማሳጠር ከኮንትራክተሮቹ ጋር የተሳካ ድርድር መደረጉን ገልጸዋል፡፡ የግንባታ ጊዜው ማጠር በሕንፃው ጥራት ላይ የሚያስከትለው ተፅዕኖ እንደማይኖር አስረድተዋል፡፡

የአፍሮ ጽዮን ኮንስትራክሽን ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሲሣይ ደስታ ኩባንያቸው በሰመራ የግንባታ ሥራዎችን በማካሄድ ላይ በመሆኑና አስፈላጊዎቹን ማሽነሪዎች በአካባቢው ስላሉት፣ ግንባታውን ለመጀመር ጊዜ እንደማይወስድባቸው ገልጸዋል፡፡ አፍሮ ጽዮን የጂንካ ኤርፖርትን ገንብቶ ለማስረከብ በዝግጅት ላይ ሲሆን፣ የሰመራ ኤርፖርት መንደርደሪያን በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡

ኩባንያው የአፋር ክልል ዋና ከተማ በሆነችው ሰመራ ከተማ ዘመናዊ ስታዲየም በመገንባት ላይ ነው፡፡ በመሆኑም ክሬሸርና ሌሎች የግንባታ ማሽነሪዎች ከመሀል አገር ማጓጓዝ ሳያስፈልገው የመስክ ሥራውን የሥራ ውል በተፈረመ ማግሥት እንደሚጀምር ታውቋል፡፡ ‹‹ስምምነት ላይ ከመድረሳችን አስቀድመን ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልገን የሰው ኃይል፣ የመሣሪያዎች ዓይነትና የግንባታ ግብዓቶችን ለይተን ዝግጅት አድርገናል፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ስላለ የሚያስፈልጉንን ዕቃዎች አስቀድመን እናዛለን፤›› ብለዋል፡፡

የኤፍኢ ኮንስትራክሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፍጹም ታዬ በበኩላቸው ኩባንያቸው ከኤርፖርቶች ድርጅት ጋር ሲሠራ የመጀመሪያው ቢሆንም፣ የተሰጠውን የሕንፃ ግንባታ በተሰጠው የጊዜ ሰሌዳ በሚፈለገው የጥራት ደረጃ አከናውኖ እንደሚያስረክብ ቃል ገብተዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች