Monday, September 25, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የመንግሥትና የግል ኢንቨስትመንት አጋርነትን የሚቆጣጠር ኤጀንሲ ሊቋቋም ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

– ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚሆን ይጠበቃል

የመንግሥትና የግል ኢንቨስትመንት አጋርነትን የሚመራና የሚቆጣጠር  ኤጀንሲ ለማቋቋም፣ የሕግ ማዕቀፍ በመዘጋጀት ላይ መሆኑን የሪፖርተር ምንጮች ገለጹ፡፡

እንደ ምንጮች ገለጻ፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ትዕዛዝ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴርና ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተውጣጡ የባለሙያዎች ቡድን የሕግ ማዕቀፉን የማርቀቅ ሒደት ላይ ይገኛሉ፡፡

የመንግሥት ፍላጎት ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሆን ኤጀንሲ እንዲቋቋም፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ደግሞ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶቻቸውን ለዚህ ተቋም እያፀደቁ የሚንቀሳቀሱበትን ሥርዓት መፍጠር ላይ ያነጣጠረ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ኤጀንሲውን ለማቋቋም የሚያስፈልገው ሀብትና ከፍተኛ የሠለጠነ የሰው ኃይል ፍላጎት ተግዳሮት ከሆነ፣ የሕግ ማዕቀፍ ብቻ ተሰናድቶ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ውስጥ ራሱን የቻለ ዲፓርትመንት መፍጠር አማራጭ ሊሆን እንደሚችልም ምንጮች አክለዋል፡፡

የሕግ ማዕቀፉ ዋና ዓላማ በአገሪቱ የሚፈቀዱ የአጋርነት ዓይነቶችን የመለየት፣ የመንግሥትና የግል ኩባንያዎችን የተናጠል ግዴታና ኃላፊነት የማስቀመጥ፣ የክልሎችና የፌዴራል ተቋማት ሚና፣ እንዲሁም የውዝግብ አፈታት ሥልቶችንና የመሳሰሉ መሠረታዊ ነጥቦችን የሚያካትት እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡

የዚህ የሕግ ማዕቀፍና ተቋማዊ አደረጃጀት መፈጠር የውጭ የግል ባለሀብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን በእርግጠኝነት እንዲያፈሱ መተማመኛ እንደሚሰጣቸው፣ መንግሥትም በአሁኑ ወቅት ከገጠመው የልማት ፕሮጀክቶች የበጀት እጥረት መውጫ መንገድ የሚያስገኝለት መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

በመንግሥት በኩል በአሁኑ ወቅት በመንግሥትና በግል አጋርነት እንዲለሙ ከሚፈለጉ የኢኮኖሚ ዘርፎች መካከል የኃይል ማመንጫ፣ የባቡር መሠረተ ልማት፣ የስኳር ፕሮጀክቶችና የማዳበሪያ ፕሮጀክቶች ይገኙበታል፡፡

በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ጌታቸው በትሩ፣ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን የታቀዱ የባቡር መስመሮችን ለማስጀመር የዚህ የሕግ ማዕቀፍ መፅደቅና ወደ ሥራ መግባት እንደሚጠይቅ ገልጸዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ በግልና በመንግሥት አጋርነት ሊያከናውን ካቀዳቸው ፕሮጀክቶች መካከል የሞጆ-ሐዋሳ-ሞያሌ የባቡር መስመርና የአዲስ አበባ-በደሌ-ሱዳን ፕሮጀክቶች ዋነኞቹ ናቸው፡፡

‹‹በተለይ የሞጆ-ሐዋሳ-ሞያሌ ፕሮጀክት የአዋጭነት ጥናቱ የተጠናቀቀ በመሆኑ የግል ባለሀብቶችን ቀልብ የሚስብ መስመር ነው፤››  ሲሉ ዶ/ር ጌታቸው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በበኩሉ በመንግሥትና በግል አጋርነት ከሦስት ሺሕ ሜጋ ዋት በላይ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት ጨረታ አውጥቷል፡፡ ይሁን እንጂ የግል ባለሀብቶች የሕግ ማዕቀፍ መውጣትን እየጠበቁ ነው፡፡  

የመንግሥትና የግል የኢንቨስትመንት አጋርነት በአሁኑ ወቅት በ134 አገሮች ተቀባይነት ያገኘ የኢኮኖሚ ሞዴል መሆኑን የተመድ የልማት ፕሮግራም ጥናት ያመለክታል፡፡

እ.ኤ.አ. ከ2007 እስከ 2011 ድረስ በየዓመቱ 79 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት በዚህ የኢኮኖሚ ሞዴል ተግባር ላይ መዋሉን መረጃው ይጠቁማል፡፡      

 

 

 

                              

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች