Sunday, June 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ ማቅረብ ከምትችለው በአሥር በመቶ እያቀረበች መሆኗ በጥናት ተመለከተ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ40 በላይ ለሆኑ ያላደጉ አገሮች የንግድ ዘርፍ ማሳደጊያ ድጋፍ እየሰጠ የሚገኘው የተቀናጀ የንግድ ማሳደጊያ ተቋም፣ ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ከምትችለው የምርት መጠን ውስጥ ከአሥር በመቶ ያነሰውን በማቅረብ ላይ እንደምትገኝ በጥናት አመለከተ፡፡

 በዓለም ንግድ ድርጅት አስተባባሪነት፣ በስድስት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኤጀንሲዎችና በዓለም የፋይናንስ ተቋማት ተባባሪነት የተመሠረተው ይህ ዓለም አቀፍ የንግድ ማሳደጊያና ማበልጸጊያ ተቋም ዋና ዓላማው፣ ያላደጉ አገሮችን አቅም መገንባት ነው፡፡

ተቋሙ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪ የአፍሪካ አገሮችና የመን የታደሙበትን ዓውደ ጥናት በአዲስ አበባ ለሳምንት ያህል ባካሄደበት ወቅት ይፋ ያደረገው ጥናት እንዳመለከተው፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ካለው አቅም በታች ከጠቅላላ አገር ውስጥ ምርት አኳያ ለውጭ ገበያ እያቀረባቸው የሚገኘው የወጪ ንግድ ሸቀጦች ከአሥር በመቶ በታች  ናቸው፡፡

ጥናቱ በንግድ ስትራቴጂ፣ በንግድ ተወዳዳሪነትና በንግድ ፋሲሊቴሽን፣ በአግሮ ኢንዱስትሪ፣ በቆዳና በቆዳ ውጤቶች ኢንዱስትሪዎች፣ እንዲሁም በጨርቃ ጨርቅና በአልባሳት መስክ እንደተካሄደ ተቋሙ ይፋ ያደረገው ሰነድ ይጠቁማል፡፡ አገሪቱ ካላት የጥሬ ዕቃ ሀብት አኳያ በወጪ ንግድ ላይ ያተኮረ ስትራቴጂ መከተሏን በጥሩ ጎኑ አውስቷል፡፡ እሴት የታከለባቸውና ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጡ ምርቶችን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን አዎንታዊነት ያሳየው የተቋሙ ጥናት፣ ምንም እንኳ እ.ኤ.አ. ከ2011 ጀምሮ የዓለም የሸቀጥ ገበያ ዋጋ እየዋዠቀ ቢመጣም፣ የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ዘርፍ እስከ ካቻምና በነበሩት አምስት ዓመታት ውስጥ የ8.2 በመቶ ዓመታዊ ዕድገት እያስመዘገበ እንደነበር አስታውሷል፡፡

ይሁንና ይህ ዕድገት በማኑፋክቸሪንግ መስክ ከሚታየው ለውጥ አኳያ አሁንም ዝቅተኛ ሆኖ መገኘቱ በጥናቱ ተመልክቷል፡፡ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ዕድገት ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አኳያ ያለው ድርሻ 4.5 በመቶ ብቻ በመሆኑ አዝጋሚ አሰኝቶታል፡፡

በዓለም የንግድ ድርጅት ሥር የሚንቀሳቀሰው ተቋም በንግድ ስትራቴጂ መስክ የኢትዮጵያ መንግሥት ተግባራዊ እንድታደርጋቸው በመፍትሔ ሐሳብነት ካቀረባቸው ነጥቦች ውስጥ፣ በከፍተኛው የፖለቲካ አመራር ደረጃ የሚመራ የንግድ ፖሊሲ ማስተባበሪያ ምክር ቤት መመሥረት ይጠቀሳል፡፡ ይህ ምክር ቤት አገሪቱን የንግድ ስትራቴጂና ፖሊሲዎች ከመቅረፅ በተጨማሪ፣ አገሪቱ በደቡባዊና ምሥራቃዊ የአፍሪካ አገሮች የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) በሚመራው የአኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ውስጥ አባል በመሆን እንድትቀላቀል ማድረግ እንደሚጠበቅበትም ተቋሙ ጠይቋል፡፡ ከዚህም በተጓዳኝ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ሒደቱን በማፋጠን፣ የኢንቨስተሮችን አመኔታ ማትረፍና በርካታ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንቶችን መሳብ እንዲቻል ማድረግ እንደሚገባም አሳስቧል፡፡

የተቋሙ የቁጥጥርና የምዘና ዘርፍ አስተባባሪ ጄምስ ኤድዊን ለሪፖርተር እንዳስረዱት፣ የዓለም የንግድ ድርጅትን በአባልነት መቀላቀል የመንግሥት ውሳኔ ነው፡፡ ይሁንና ተቋማቸው መንግሥት በሚፈልጋቸው መስኮች ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ መንግሥት ለዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት የሚያበቃውን እንቅስቃሴ ማድረግ ከጀመረ ዓመታትን ቢያስቆጥርም፣ አሁንም ድረስ ግን ዘገምተኛ አካሄድን እየተከተለ ይገኛል፡፡

በንግድ ዘርፍ ተወዳዳሪነትና ፋሲሊቴሽን መስኮች ንግድና ሎጂስቲክስን ለማስፋፋት የሚካሄደውን መጠነ ሰፊ ኢንቨስትመንት በጥሩ ጎኑ እንደተመለከተው የዓለም ንግድ ድርጅት ጥናት ይጠቁማል፡፡ በንግድ ዘርፍ የአፈጻጸም እንዲሁም በሎጂስቲክስ መመዘኛዎች ኢትዮጵያ በዓለም አገሮች ተርታ ዝቅተኛውን ደረጃ ይዛ ስለምትገኝ፣ ይህንን መለወጥ የመንግሥት ኃላፊነት እንደሆነ አስፍሯል፡፡ ለዚህ ሥራ በመፍትሔነት ከጠቀሳቸው መካከል ብሔራዊ የንግድ ፋሲሊቴሽንና የሎጂስቲክስ ምክር ቤት ማቋቋም ሲሆን፣ ይህ ምክር ቤትም የንግድ ፋሲሊቲ ሪፎርሞችንና በኤጀንሲዎች መካከል የሚኖሩትን ቅንጅቶች የሚከታተል መሆን ይኖርበታል ብሏል፡፡

የሎጂስቲክስ ሥርዓትን የሚመራ ብሔራዊ ስትራቴጂ ለመተግበር መንግሥት እየተንቀሳቀሰ ሲሆን፣ ይህ ስትራቴጂ በርካታ ለውጦችን ለማምጣት መሣሪያ እንደሚሆን የዓለም ንግድ ድርጅት ተቋም ያምናል፡፡

በአገሪቱ ኢንዱስትሪዎች ላይ የሚታየውን የንግድ እንቅስቃሴ በተመለከተም በጥናት እንደታየው፣ አብዛኞቹ የግብርናና የምግብ አምራች ኢንዱስትሪዎች ትልቅ የአቅም ችግር አለባቸው፡፡ ሁለት ሦስተኛው አምራቾች ከአቅም በታች የሚያመርቱ፣ በዚህ ዘርፍ የተሠማሩ ከ98 በመቶ ያላነሱ ባህላዊና አነስተኛ አምራች ገበሬዎች ሲሆኑ ተገቢውን የቴክኖሎጂና የጥራት ደረጃ የማይከተሉ ሆነው ተገኝተዋል፡፡

በቆዳና በቆዳ ውጤቶች መስክ የተሠማሩትም አብዛኞቹ ካላቸው የማምረት አቅም 50 በመቶውን ብቻ የሚጠቀሙ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ ትልቅ ችግር ይታይባቸዋል ከተባሉት የጥሬ ዕቃ ዘርፎች ውስጥ የጥሬ ምርትና የንግድ ሰንሰለት መሆኑም ታይቷል፡፡

በዓመት የ37 በመቶ የኤክስፖርት ዕድገት እያስመዘገበ እንደመጣ የሚነገርለት የጨርቃ ጨርቅና አልበሳት ኢንዱስትሪም ቢሆን፣ በችግሮች የተተበተበ መሆኑ አልቀረም፡፡ በአገሪቱ ያለው የጥጥ ሀብት በተገቢው መንገድ ለፋብሪካዎች መቅረብ የሚችልበት አግባብ አለመታየቱ ሲጠቀስ፣ አገሪቱ ከውጭ በሚገባ በመጠኑም ቀላል ግምት በማይሰጠው ጥጥ ላይ ጥገኛ ሆና እንደምትገኝ የዓለም ንግድ ድርጅት ይፋ አድርጓል፡፡

እንዲህ ያሉ የጥናት ውጤቶችን ላላደጉ አገሮች እያቀረበ የንግድ ዘርፎቻቸውን እንዲያሻሽሉ የሚመክረው የዓለም የንግድ ድርጅት፣ የንግድ ማሳደጊያና ማበልፀጊያ ማዕቀፍ ታዳጊ አገሮች በወጪ ንግድ አቅማቸው እንዲገነባ ከማድረግ ባሻገር፣ የዓለም ንግድ ድርጅትን እንዲቀላቀሉና በዓለም የንግድ ሥርዓት ውስጥ መስተጋብር እንዲፈጥሩ ድጋፍ እያደረገ የሚገኝ ተቋም ነው፡፡

ተቋሙ ላለፉት አምስት ዓመታት በዓለም ላይ ላላደጉ 40 ያህል አገሮች ድጋፎች ሲሰጥ የቆየበትን የመጀመሪያ ምዕራፍ ካቻምና አገባዷል፡፡ የሁለተኛው የአምስት ዓመት ምዕራፍ አምና የተጀመረ ሲሆን፣ ኢትዮጵያም በዚህ ምዕራፍ ተጠቃሚ መሆን እንደጀመረች፣ በያመቱም እስከ 900 ሺሕ ዶላር የሚጠጋ የአቅም ግንባታ ድጋፍ በቀጥታ እያገኘች እንደምትገኝ፣ በንግድ ሚኒስቴር ተጠባባቂ የተቋሙ የኢትዮጵያ አስተባባሪ አቶ ደምለው መኮንን ተናግረዋል፡፡ ከዚህም በተጓዳኝ አዋጭ የሆኑና ድጋፍ ቢሰጣቸው ሊያድጉ የሚችሉ ፕሮጀክቶችን በማፈላለግ እስከ ሦስት ሚሊዮን ዶላር ፈንድ ሊለቀቅላቸው የሚችሉ የንግድ ሥራዎችን ተቋሙ የሚደግፍ በመሆኑ፣ በዚህ ዕድል መጠቀም የሚችሉ ኩባንያዎችን ለመመልመል እንደታሰበም አቶ ደምለው ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች