Saturday, July 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናአወዛጋቢ ሆኖ የቆየውን የሊዝ አዋጅ ለማሻሻል ረቂቅ ተዘጋጀ

አወዛጋቢ ሆኖ የቆየውን የሊዝ አዋጅ ለማሻሻል ረቂቅ ተዘጋጀ

ቀን:

በትልልቅ ከተሞች ሥር ሰዶ የቆየውን የመሬት አስተዳደር ችግር ለመፍታት፣ ኅዳር 2004 ዓ.ም. የፀደቀው የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ የሚደነግገው አዋጅ ቁጥር 721 በድጋሚ እንዲሻሻል ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ፡፡

ከጥንስሱ ጀምሮ አወዛጋቢ የነበረው የሊዝ አዋጅ የማያሠሩ አንቀጾች እንደነበሩትና ከወዲሁ መስተካከል እንዳለበት የመሬት ሥሪት ባለሙያዎች አስተያየት ሲሰጡ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮና የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የሊዝ አዋጁ ሊሻሻል እንደሚገባው አስተያየት ከሰጡት ውስጥ ይገኛሉ፡፡

መንግሥት ዘግይቶም ቢሆን አምስት ዓመታት ያስቆጠረውን የሊዝ አዋጅ አፈጻጸም የሚገመግም ኮሚቴ አቋቁሞ አዋጁንና አፈጻጸሙን ኦዲት አስደርጓል፡፡ በርካታ የመሬት ሥሪት ባለሙያዎች አዋጁ አስፈላጊ ቢሆንም፣ አንዳንድ አንቀጾች ገዳቢ መሆናቸውን በመተንተን ተከራክረው እንደነበር አይዘነጋም፡፡

በከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር አስተባባሪነት በተካሄደው ኦዲት የሊዝ አዋጁ ሊሻሻል እንደሚገባው ሪፖርት ቀርቧል፡፡ የቀረበውን ሪፖርት መንግሥት የተቀበለው በመሆኑ፣ አዋጁን ለማሻሻል ሚኒስቴሩ አዲስ ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቷል፡፡

የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር ሰሞኑን ከሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ጋር በሊዝ አዋጁ ማሻሻያ ሐሳቦች ላይ መክሯል፡፡ ሚኒስቴሩ ከሁለቱ የከተማ አስተዳደሮችና ከክልሎች በመጡ አመራሮችና ባለሙያዎች በሊዝ አዋጅ ችግሮችና በሚሻሻሉ አንቀጾች ላይ ውይይት አድርጎ መግባባት ላይ መድረሱን ገልጿል፡፡

የሚኒስቴሩ የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት እንደሚጠቁመው፣ በሊዝ  አዋጅ አፈጻጸሙ የሚስተዋለውን ችግር ለመፍታት ከክልሎችና ከከተማ አስተዳደሮች አመራርና ባለሙያዎች ጋር በሊዝ አዋጅ የኦዲት ግኝት ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡

‹‹የሊዝ አዋጅ ባሉት ክፍተቶች፣ መሻሻልና መስተካከል በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት ተደርጎ የጋራ መስማማት ላይ ተደርሷል፤›› በማለት የገለጸው የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርቱ፣ ‹‹መሻሻል ባለባቸው ጉዳዮች ላይ ስምምነት ላይ በመደረሱ የሊዝ አዋጁን ለማሻሻል ረቂቅ ማሻሻያ አዋጅ ተዘጋጅቷል፤›› በማለት በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡

መረጃዎች እንደጠቆሙት የሊዝ አዋጅ ድንጋጌዎች አፈጻጸም በዝርዝር በኦዲት ሲፈተሹ በርካታ የአፈጻጸም ክፍተቶች ተስተውለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ አንፃር አዋጁ ያልመለሳቸው ጉዳዮች ጎልተው ወጥተዋል፡፡

ይሻሻሉ ተብለው ከሚጠበቁት መካከል ልዩ አገራዊ ፋይዳ ላላቸው ፕሮጀክቶች መሬት የሚቀርብበት መንገድ፣ የግል ይዞታና የመንግሥት ቤት በአንድ ግቢ ውስጥ መኖራቸው የፈጠረው ችግርና የማስፋፊያ መሬት ጥያቄዎች መስተናገድ አለመቻላቸው ይገኙበታል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ሥሪት ባለሙያዎች የሊዝ አዋጁ፣  ለማስፈጸም ከወጡ መመርያዎችና ደንቦች ጋር የሚቃረን በመሆኑ የትልልቅ ፕሮጀክቶችን የመሬት ጥያቄ ለማስተናገድ እንደተቸገሩ ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡ የፀረ ሙስና ኮሚሽንም ሕግጋቱ መጣጣም እንዳለባቸው ለመንግሥት ሐሳብ አቅርቧል፡፡

የሊዝ አዋጁ አገራዊ ፋይዳ ያላቸው ፕሮጀክቶች መስተንግዶ መመርያ ቁጥር 15/2005፣ የከተማ መሬት ሊዝ ደንብ 2004 ዓ.ም. እና የሊዝ አዋጅ 721/2004 ዓ.ም. እንደሚቃረን የሚከራከሩ አሉ፡፡

የፀረ ሙስና ኮሚሽን የሕግጋቶቹን ተቃርኖ በሚመለከት በ2005 ዓ.ም. ባወጣው ሪፖርት እንደገለጸው፣ የመመርያው አንዳንድ አንቀንጾች በአፈጻጸም ወቅት አሻሚ ትርጉም እንዳይሰጣቸው ከሊዝ አዋጅ ጋር ተዛማጅ የሆኑ አንቀጾችን በማጣቀስ፣ ለትርጉም የሚዳርጉ የመመርያው አንቀጾች በሊዝ አዋጅ ውስጥ ካሉ ድንጋጌዎች መሠረታዊ ዓላማ ጋር መጣጣም አለባቸው፡፡

አዋጁን እንዴት እንደሚያስፈጽም የተቸገረው የአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ባንክና ማስተላለፍ ጽሕፈት ቤት በየካቲት 2006 ዓ.ም. መመርያ እንዲሰጠው ጠይቆ ነበር፡፡

ጽሕፈት ቤቱ በወቅቱ እንደገለጸው፣ በርካታ የውጭና የአገር ውስጥ ግዙፍ ኩባንያዎች ማኅበራዊ አገልግሎቶች ለሆኑት ለሆቴል፣ ለሆስፒታል፣ ለሞልና ለግዙፍ ሪል ስቴት ግንባታዎች የሚውሉ ቦዎች እንዲሰጣቸው ለከንቲባ ጽሕፈት ቤትና ለመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

የከንቲባ ጽሕፈት ቤትና ቢሮውም የመሬት ባንክና ማስተላለፍ ጽሕፈት ቤት የውሳኔ ሐሳብ እንዲያቀርብ ይጠይቃሉ፡፡ ጽሕፈት ቤቱ እንደገለጸው፣ የባለሀብቶቹ ጥያቄ በልዩ አገራዊ ፋይዳ ባላቸው ፕሮጀክቶች ይስተናገዱ ቢባል እንኳ በሊዝ አዋጅ አንቀጽ 2 እና በአገራዊ ፋይዳ መመርያ ቁጥር 15/2005 ላይ በግልጽ እንዳሰፈረው፣ ‹‹ልዩ አገራዊ ፋይዳ ያላቸው ፕሮጀክቶች ለኢትዮጵያ ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ከፍተኛ ለውጥ የሚያመጡ የልማት ፕሮጀክቶች ወይም የትብብር መስኮች፣ አገሪቱ ከሌሎች አገሮች ጋር ለሚኖራት የተሻለ ግንኙነት መሠረት እንዲጥሉ የታቀዱና የተወሰኑ ፕሮጀክቶች ናቸው፤›› የሚል በመሆኑና ከሊዝ አዋጁ ጋር የሚጋጭ ስለሆነ ለአልሚዎች የቦታ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት መቸገሩን ገልጿል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የሊዝ አዋጁን ተከትሎ የወጣው የሊዝ አፈጻጸም መመርያ ቁጥር 11/2004 አነቀጽ 32 ንዑስ አንቀጽ 2 በግልጽ እንደተደነገገው ከላይ የተጠቀሱት የአገልግሎት ዘርፎች የሚስተናዱት በልዩ ጨረታ እንደሆነ፣ በሊዝ አፈጻጸም መመርያው መሠረት በከንቲባው አማካይነት ለካቢኔ ለሚመሩ ልዩ አገራዊ ፋይዳ ላላቸው ፕሮጀክቶች የሚውሉ ቦታዎች የሚስተናገዱበት መመርያ ቁጥር 15/2005  ቢወጣም፣ መመርያው ከሊዝ አዋጁ ጋር ይጣረሳል ሲል ይተነትናል፡፡

በእነዚህ መሠረታዊ ምክንያቶች አዲስ አበባ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ለማስተናገድ አልቻለችም፡፡ ይህ ችግር በክልል ከተሞች የተለያየ ትርጉም እየተጠሰው አድሎአዊ አሠራር እንዲሰፍን ማድረጉ ተመልክቷል፡፡

ሌላው ችግር በተለይ በከተሞች ውስጥ የቀበሌ ቤት ከግል ይዞታዎች ጋር ተደባልቀው የሚገኙበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡ በዚህ ክስተት ምክንያት ባለይዞታዎች፣ የግላቸውን ይዞታ መሸጥና መለወጥ እንዳይችሉ ያደርጋቸዋል፡፡ በዚህ ሒደት በርካታ ቅሬታዎች እየቀረቡ ሲሆን፣ የሊዝ አዋጁ ይህንን ቅሬታ ለመመለስ አንቀጾችን ባለማካተቱ በማሻሻያው ላይ ይካተታል ተብሏል፡፡

ሌላኛው ችግር የማስፋፊያ ቦታዎች አቅርቦት ነው፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት አንድ ፕሮጀክት ለመስፋፋት ቢፈልግ በአቅራቢያው የሚገኝ ቦታ በድርድር ማግኘት ይቻላል፡፡ ነገር ግን በሊዝ አዋጁ መሬት በጨረታና በምደባ ብቻ የሚቀርብ በመሆኑ፣ ለማስፋፊያ ፕሮጀክት ቦታ ማግኘት አለመቻሉ ከፍተኛ ችግር መፍጠሩ ተጠቁሟል፡፡ ይህ የማስፋፊያ ቦታ አቅርቦት ችግርም ከሚሻሻሉት መካከል እንደሆነ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...