Wednesday, October 4, 2023

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከቀነ ገደቡ አስቀድሞ እንደማይነሳ መንግሥት አስታወቀ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

– ቁጥጥር ሥር ውለው የነበሩት በሙሉ ሥልጠና ወስደው ተለቀዋል

– አሜሪካ ሰነድ አልባ ኢትዮጵያዊያንን የምታባርር ከሆነ መንግሥት እጄን ዘርግቼ እቀበላለሁ አለ

    የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የዜጎችን ሰላማዊ ሕይወት እንዳስጠበቀና ከቀኑ ገደቡ አስቀድሞ ለማንሳት ሐሳብ እንደሌለ አስታወቀ፡፡

ዓርብ ጥር 26 ቀን 2009 ዓ.ም. አመሻሽ ላይ ለአገር ውስጥ ጋዜጠኞች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ዶ/ር ነገሪ በአንዳንድ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ቀደም ሲል በአገሪቱ የተወሰኑ ክልሎች ተከስቶ በነበረው ተቃውሞ ሳቢያ  የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አራት ወራት እንደሞሉት፣ የሕዝቡ ሰላምና ደኅንነት ወደነበረበት እንዲመለስና በሕዝቡ የተነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ የተያዘው ግብ ከሞላ ጎደል ለማሳካት እንደረዳ ተናግረዋል፡፡

እንደ አስፈላጊነቱ ከተያዘለት ቀነ ገደብም ሊራዘም እንደሚችል በአዋጁ ውስጥ የተደነገገ ሲሆን፣ በቅርብ ጊዜ ምናልባትም ከቀኑ ገደብ በፊት መንግሥት አስፈላጊ ሆኖ ካገኘው ሊያነሳው እንደሚችል ፍንጭ ሰጥቶ እንደነበር አይዘነጋም፡፡

ሆኖም ዶ/ር ነገሪ እንደሚሉት ከሞላ ጎደል አዋጁ ዓላማውን ያሳካ ቢሆንም፣ በአንዳንድ አካባቢዎች በሰላማዊ ዜጎች ላይ ቦምብ የሚያፈነዱና ሁከት የሚያነሳሱ ጽሑፎች የሚበትኑ ሰዎች እየተስተዋሉ በመሆናቸው ከቀኑ ገደብ በፊት አዋጁን ለማንሳት ሐሳብ የለም፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀ ጊዜ ጀምሮ ኮማንድ ፖስቱ የአገሪቱን ሰላምና የሕዝቡን ደኅንነት ለማስጠበቅ የተሳካ ሥራ መሥራቱን የገለጹት ዶ/ር ነገሪ፣ በቅርቡ የተለቀቁት 11,350 ሰዎችን ጨምሮ በተቃውሞው ተሳትፎ የነበራቸውና በሕግ ቁጥጥር ሥር እንዲውሉ የተደረጉ ከ2,200 በላይ ዜጎች የተሃድሶ ሥልጠና ወስደው ሙሉ ለሙሉ መለቀቃቸውን አመልክተዋል፡፡

መንግሥት ከገባው ቃልና ሕዝቡ በትዕግሥት ከሚጠብቀው ለውጥ አንፃር መንግሥት ራሱን የመፈተሽ ዕርምጃ እየወሰደ እንደሆነ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ፣ ከፌዴራል መንግሥት እስከ ክልል ድረስ መንግሥትን መልሶ የማዋቀር ሥራ መሠራቱን፣ እንዲሁም ገዥው ፓርቲ ውስጥ ጥልቅ ተሃድሶና ግምገማ እየተካሄደ እንደሆነ ጠቅሰው መንግሥት የገባውን ቃል እየተገበረ ነው ብለዋል፡፡  በቀጣይነትም በሙስናና በሌብነት የተጠረጠሩ አመራሮች ተጠያቂ የሚሆኑበት ሁኔታ እንደሚኖር ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡ በቀጥታ ከሕዝብ ጋር የሚደረገው ግምገማም በፐብሊክ   ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴር በኩል እየተካሄደ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በተለያዩ ደረጃዎች የተዋቀረው የኮማንድ ፖስት ሕግን ለማስከበር ዕርምጃ በሚወስድበት ወቅት ቅሬታ ያለው ከታች እስከ ላይ እስከ ሴክሬታሬያቱ ድረስ አቤቱታ የማቅረብ መብት እንዳለውም አክለዋል፡፡ እስካሁን የቀረቡ ቅሬታዎችም አስቸኳይ ምላሽ ማግኘታቸውን ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳን ጋር ያላት ግንኙነት እንደሻከረ ተደርጎ የተወራው ሆን ተብሎ የተፈበረከ ወሬ መሆኑን ገልጸው፣ በአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪርና ከግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ ጋር በአንዳንድ ወሳኝ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን አስታውሰዋል፡፡ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከመቅጽበት አምባሳደርን ማባረርና ግንኙነትን በክስተት ማቋረጥን እንደማይፈቅድና መርህን የተከተለ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ የጽንፈኛ ሚዲያዎችና ፖለቲከኞች የኅብረቱ ስብሰባ በአዲስ አበባ እንዳይካሄድ ከፍተኛ ፕሮፓጋንዳ በመንዛት መሪዎችንም ጭምር ጥርጣሬ ውስጥ ከተው እንደነበር ዶ/ር ነገሪ አስረድተዋል፡፡

እንደ ሚኒስትሩ እምነት፣ የኅብረቱ ስብሰባ ያለምንም የፀጥታ እንከን የተከናወነ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ትርፍ ያገኘችበት እንደነበርም ገልጸዋል፡፡ የሞሮኮ ወደ ኅብረቱ ተመልሶ መቀላቀልም የኢትዮጵያ አቋም እንደነበር ተናግረዋል፡፡

አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እየተከተሉ ካለው ፖሊሲ አንዱ ስለሆነው ሰነድ አልባ ስደተኞችን የማባረር ዕርምጃ በተመለከተም ጥያቄ ተነስቶላቸው ነበር፡፡  አሜሪካ የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን በአጋጣሚ ሰነድ አልባ መሆናቸውንና መንግሥትን የሚያጥላሉ ቢሆኑም፣ የመባረር ዕድል የሚገጥማቸው ከሆነ መንግሥት ምንም ይሁኑ ምን እጁን ዘርግቶ ይቀበላቸዋል ብለዋል፡፡

‹‹ኢትዮጵያ እንኳን ለዜጎቿ የሌሎች አገሮች ዜጎችንም፣ ተቀብላ ታስተናግዳለች›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ በተለያዩ ምክንያቶች በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጥላቻና የማጥላላት ዘመቻ ሲከፍቱ የኖሩትን ጭምር መንግሥት ተቀብሎ፣ በአገራቸው ገብተው ኢንቨስት እንዲያደርጉና በሰላም እንዲኖሩ ይተባበራቸዋል ብለዋል፡፡ ከሕገወጥ መንገድና ከፅንፈኝነት ወጥተው ከሕጋዊ ተቃዋሚዎች ጋር ሆነው የመሥራት መብት እንዳላቸውም ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ግሪን ካርድ ለማግኘት መንግሥትን የሚያጥላሉት ከልባቸው አይደለም››  በማለት፤ የአሜሪካ መንግሥት የሚያባርራቸው ከሆነ የኢትዮጵያ መንግሥት ዜጎቹን በጠላትነት የሚፈርጅበት ምክንያት አይኖርም ብለዋል፡፡

ቀደም ሲል በአይኤምኤፍና የዓለም ባንክ በመሳሰሉ የዓለም የገንዘብ ተቋማት ኢትዮጵያ የብርን የምንዛሪ ዋጋ እንድትቀንስ ጥያቄ ቢቀርብም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ይኼንን ማድረግ በሕዝቡ ላይ የሚያስከትለው የኑሮ ውድነትና ተያያዥ ችግሮች ምክንያት ጥያቄውን እንዳልተቀበለው ተናግረዋል፡፡

ይኬንን ከማድረግ ይልቅ መንግሥት ቡናን ጨምሮ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች ላይ እንቅፋት የሆኑ ነገሮችን መፈተሽና ሕገወጥ ድርጊት በሚፈጽሙ ላይ ዕርምጃ መውሰድ፣ እንዲሁም ከውጭ የሚገቡ ዕቃዎችን ለመቀነስና በአገር ውስጥ የሚመረቱበትን አቅጣጫ እየተከለተ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

 

 

            

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -