Tuesday, December 5, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበፋይናንስ ፍሰት መስተጓጎል የኮንዶሚንየም ቤቶች ግንባታ ችግር እንደገጠመው ተጠቆመ

በፋይናንስ ፍሰት መስተጓጎል የኮንዶሚንየም ቤቶች ግንባታ ችግር እንደገጠመው ተጠቆመ

ቀን:

የመኖሪያ ቤቶችን ችግር ለመፍታት በአዲስ አበባ ከተማ የተጀመሩ የ20/80 እና የ40/60 ቤቶች ግንባታ፣ በፋይናንስ ፍሰት በኩል መስተጓጎል በመፈጠሩ የቤቶቹ ግንባታ ችግር እንደገጠመው ተጠቆመ፡፡

የቤቶች ግንባታ ዋነኛ ተዋናይ የሆኑት በሺሕ የሚቆጠሩ ኮንትራክተሮች፣ አማካሪዎች፣ ጥቃቅንና አነስተኛ ልማት ድርጅቶች፣ የግንባታ ዕቃ አቅራቢዎችና የትራንስፖርት ባለንብረቶች ለሠሩት ሥራ ክፍያ በወቅቱ እየተከፈላቸው ባለመሆኑ ችግር ውስጥ እንደሚገኙና ሥራቸውንም ማከናወን የማይችሉበት ደረጃ ላይ እየደረሱ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር በበኩሉ በ20/80ም ሆነ በ40/60 ቤቶች ግንባታ ዝቅተኛ የሥራ አፈጻጸም እንደተመዘገበ አምኖ፣ የችግሩ መንስዔ በፋይናንስ (ክፍያ) አፈጻጸም ላይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዲስ አሠራር በመጀመሩ መሆኑን ገልጿል፡፡ ሚኒስቴሩ አዲሱ አሠራር ወደ መስመር እስኪገባ ድረስ የተፈጠረ የሥራ መጓተት ነው ብሏል፡፡

በተያዘው በበጀት ዓመት መጀመሪያ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሚገነባቸው ቤቶች  የሚውል የቦንድ ብድርና የውጭ ምንዛሪ ፍላጎት ተሰልቷል፡፡ በሥሌቱ መሠረት አጠቃላይ ፍላጎቱ 31.03 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከዚህ ከሚያስፈልገው ገንዘብ ውስጥ 15 ቢሊዮን ብር የቦንድ ብድር ፈቅዷል፡፡

ከዚህ ውስጥ 8.5 ቢሊዮን ብር ለአዲስ አበባ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት (20/80)፣ 6.5 ቢሊዮን ብር ደግሞ ለአዲስ አበባ ቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ (40/60) ተደልድሏል፡፡

ነገር ግን የክፍያ አፈጻጸም ላይ ለውጥ ተደርጓል፡፡ የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት እንደሚጠቁመው ሀብትን በተገቢው መንገድ ሥራ ላይ ማዋል በሚለው መርህ መሠረት፣ ክፍያዎች በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል እንዲፈጸሙ ተደርጓል፡፡ ባንኩ በቅርብ ክትትልና ቁጥጥር ተግባራዊ እንዲያደርግ በመወሰኑ ምክንያት የክፍያ አፈጻጸም ሒደቱ የተጠበቀውን ያህል ቀልጣፋ ሊሆን አለመቻሉ ተገልጿል፡፡

‹‹ባለፉት ስድስት ወራት የቦንድ ብድር አጠቃቀም በአጠቃላይ ከ2.5 ቢሊዮን ብር በላይ ከፍ ሊል አልቻለም፡፡ ይኸውም ለ20/80 ቤቶች ፕሮግራም 1.4 ቢሊዮን ብር፣ ለ40/60 ቤቶች ፕሮግራም 1.05 ቢሊዮን ብር ብቻ ወጪ ተደርጓል፤›› ሲል የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሪፖርት ያስረዳል፡፡፡

ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር ክፍያ የጠየቀ የቤቶች ግንባታ ተዋናይ፣ ከአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ቼክና ክፍያው እንዲፈጸም የሚገልጽ ደብዳቤ ይሰጠዋል፡፡ ይህንን ይዞ ወደ ባንክ ሲሄድ ክፍያው ይፈጸም ነበር፡፡

አሁን ባለው አሠራር የግንባታ ተዋናዩ ክፍያ እንዲከፈለው ለፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ደረሰኝ ይቆርጣል፡፡ የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ክፍያ እንዲፈጽም ለባንኩ ይገልጻል፡፡ ባንኩ ክፍያ ይፈጽማል፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ባንኩ ክፍያ እየፈጸመ ባለመሆኑ ድርጅቶቹ ለሠራተኞቻቸው ደመወዝ መክፈል እንኳ እያቃታቸው መምጣቱን እየገለጹ ነው፡፡

ይህ ችግር አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኙ 18 የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቶችን ያጨናነቀ መሆኑም ተመልክቷል፡፡

በ2006 ዓ.ም. የተጀመሩ 20,931 የ40/60 ቤቶች ግንባታ በስምንት ሳይቶች እየተካሄደ ነው፡፡ በግማሽ ዓመቱ ግንባታውን 9.7 በመቶ ለማከናወን ቢታቀድም፣ ውጤቱ ግን 4.8 በመቶ ብቻ ነው፡፡ በ2007/2008 ዓ.ም. የተጀመሩ የ17,005 ቤቶች ግንባታ በአራት ሳይቶች እየተካሄደ ነው፡፡ በግማሽ ዓመቱ በአማካይ 14.2 በመቶ ለማከናወን ቢታቀድም ውጤቱ ግን 7.9 በመቶ ብቻ ነው፡፡

በ40/60 የቁጠባ ቤቶች ፕሮግራም ከተጀመሩት መካከል 1,292 ቤቶች (972 መኖርያ፣ 320 የንግድ ቤቶች) ግንባታቸው በአብዛኛው ተጠናቋል፡፡

‹‹ቤቶቹ ስለሚተላለፉበት ሁኔታ የተለያዩ መድረኮች በማዘጋጀት ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እየተደረገ ሲሆን፣ የሚተላለፉበት ዋጋና ሌሎች ተያያዥ ውሳኔ የሚሹ ጉዳዮች ተለይተው ለውሳኔ ሰጪ አካላት ተላልፏል፤›› ሲል የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሪፖርት ያመለክታል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ በስፋት ሲካሄዱ የቆዩ የቤቶች ግንባታዎች ተቀዛቅዘዋል፡፡ አንዳንድ ቦታ ላይ ጭራሽ የቆሙ ግንባታዎችን ማየት የተለመደ ክስተት ሆኗል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...