Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትየአገሪቱን የፀረ ሙስና ትግል ማጠናከር ወይስ ማዳከም?

የአገሪቱን የፀረ ሙስና ትግል ማጠናከር ወይስ ማዳከም?

ቀን:

በዋዳ ሙሉ

የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በአዋጅ ሲቋቋም ሦስት ዓላማዎችን ይዞ ነበር፡፡ የሥነ ምግባር ትምህርትና ሥልጠና በመስጠት ሙስናን የሚፀየፍ ኅብረተሰብ መፍጠር፣ በመንግሥት ተቋማት ሙስናንና ብልሹ አሠራርን በመከላከል ግልጽነትና ተጠያቂነትን ማስፈን፣ የሙስና ወንጀል ጥቆማዎችን በመቀበል፣ በመመርመር፣ በመክሰስና በማስቀጣት የተመዘበረ ሀብት ማስመለስ ዋናዎች ዓላማዎች ነበሩ፡፡ ነገር ግን በ1996 ዓ.ም. ተካሄደ በተባለ ጥናት መሠረት የፍትሕ ሥራዎችን በአንድ ቦታ ማደራጃት ለኅብረተሰቡ ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል በሚል እሳቤ፣ ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን፣ ከንግድ ውድድርና ከሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን ከፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የምርመራና የዓቃቤ ሕግ ሥራዎችን በመቀነስ የምርመራ ሥራን ለፌዴራል ፖሊስ፣ የዓቃቤ ሕግ ሥራን ደግሞ ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በአዋጅ ቁጥር 943/2008 እንዲሰጥ ተደረገ፡፡

የፍትሕ ሥራን ለዜጎች በአንድ መስኮት ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት መርህን ተከትሎ እንዲደራጅ መደረጉ በጣም  ደስ የሚል ቅዱስ ሐሳብ ቢሆንም፣ የሙስና ወንጀልን በዚህ አደረጃጀት ውስጥ እንዲካተት መደረጉ ግን ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንና በንግድ ውድድር ሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን የሚከናወኑ የምርመራ ሥራዎች ለሙስና የተጋለጡ ነበሩ፡፡ የምርመራ ሥራ እንዲሠራ የተፈቀደለት ፖሊስ በአገሪቱ ለሙስና ተጋላጭ ከሚባሉት ሴክተሮች ቁጥር አንድ መሆኑን ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል እ.ኤ.አ. በ2015 ያወጣው የባሮሜትር ሪፖርት፣ የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን በ2004 ዓ.ም. ኪሊማንጃሮ በሚባል ድርጅት እንዲሠራ ያደረገው ጥናት በግልጽ ያስረዳል፡፡ እንዲሁም እ.ኤ.አ. የ2016 የትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የአገሮችን የሙስና ተጋላጭነት ደረጃ ሲያስቀምጥ፣ በየአገሩ በቁጥር አንድ ለሙስና ተጋላጭ ካላቸው ሴክተሮች ውስጥ ፖሊስ ተጠቃሽ ነው፡፡ በፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን የየዓመቱ የምርመራና ዓቃቤ ሕግ ስታትስቲክስ መረጃ ሪፖርትም፣ በተከታተይ ዓመታት ለሙስና ተጋላጭ የሚያደርገው ፖሊስን ነው፡፡ በዚህና በሌሎች እውነታዎች ላይ የተመሠረተ መረጃ ባለበት ሁኔታ፣ የሙስና ወንጀል ምርመራ ሥራ ለፌዴራል ፖሊስ መሰጠቱ እንቆቅልሽ ሆኖብኛል፡፡

በየአገሩ ያለው የፀረ ሙስና ተቋም አደረጃጀት የተለያየ ነው፡፡ አንዳንድ አገሮች በተለይም በእስያ ሲንጋፖርና በአውስትራሊያ የፀረ ሙስና ተቋም፣ በአፍሪካ ደግሞ የቦስትዋናና የኡጋንዳ የፀረ ሙስና ተቋማት የማስተማር፣ የመከላከል፣ የምርመራና የዓቃቤ ሕግ ሥራ በማጣመር ያደራጁ ሲሆን፣ ኢትዮጵያም የእነሱን ፈለግ የተከተለ አደረጃጀት በመፍጠር የፀረ ሙስና ትግል ስታካሂድ ቆይታለች፡፡ ሁለተኛው አደረጃጀት የዓቃቤ ሕግ ሥራን ከፀረ ሙስና ተቋም ውጪ በሆነው የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሥር በማደራጃት ከፀረ ሙስና ተቋም ጋር በቅንጅት የሙስና ትግል ያካሂዳሉ፡፡  የሆንግ ኮንግንና የኬንያ የፀረ ሙስና ተቋማትን እንደ ምሳሌ መውሰድ ይቻላል፡፡  በአገሮቹ ሦስቱም የፀረ ሙስና ትግል ሥልቶች ተጣምረው ይከናወናሉ፡፡ የማስተማር፣ የመከላከልና የምርመራ ሥራዎች በጥምረት በማከናወን  ውጤታማ ከሆኑት የሆንግ ኮንግ የፀረ ሙስና ተቋም ተጠቃሽ ነው፡፡ ሦስተኛው የፀረ ሙስና ተቋም አደረጃጀት የፀረ ሙስና ትምህርት ማስተማርና በተቋማት የሙስና መከላከል ሥራዎች እንዲያከናወኑ የተቋቋሙት የፀረ ሙስና ተቋማት ናቸው፡፡

የእነዚህ ተቋማት ሚናቸው በተለይም በማስተማርና በመከላከል ረገድ የፀረ ሙስና ትግል አድማሳቸውን በማስፋት የተለያዩ ተግባራት የሚያከናወኑ ሲሆን፣ የሙስና ወንጀል ምርመራ ሥራ በልዩ ሁኔታ በተደራጀ ተቋም ተጠሪነቱን ለአገሪቱ መሪ ጭምር በማድረግ የፀረ ሙስና ትግል ሥራዎችን ያከናውናሉ፡፡ የዓቃቤ ሕግ ሥራ በእነዚህ አገሮችም በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሥር ነው፡፡ የአሜሪካ፣ የደቡብ አፍሪካና የአልጄሪያ የፀረ ሙስና ተቋማት አደረጃጀት ለዚህ በምሳሌነት ይወሰዳል፡፡ አራተኛውና የመጨረሻው ደግሞ የማስተማር፣ የመከላከልና የመመርመር ሥራዎች ከሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ጋር በማደራጀት የፀረ ሙስና ትግል የሚያካሂዱ አገሮች ናቸው፡፡ በእነዚህ አገሮችም የዓቃቤ ሕግ ሥራ በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ይከናወናል፡፡ ለዚህ በአፍሪካ ሩዋንዳ ተጠቃሽ ነች፡፡

ወደ እኛ አገር ስንመለስ የዓቃቤ ሕግ ሥራ በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሥር መደረጉ በጣም ትክክል ነው፡፡ ምክንያቱም በዓለም ላይ የተባበሩት የፀረ ሙስና ኮንቬሽን  ፈራሚ የሆኑ 178 አገሮች ከላይ ከተገለጹት አንድ አደረጃጀት በመፍጠር የፀረ ሙስና ትግል የሚያካሂዱ ሲሆኑ፣ አብዛኛዎቹ ተቋማት ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግና የፀረ ሙስና ተቋማትን ለይተው በማደረጃታቸው የኢትዮጵያም የአብዛኛዎቹን አገሮች ተሞክሮ መከተሏ ተገቢ ነው፡፡

ከላይ እንደተገለጸው በየትኛውም አገር የሙስና ወንጀል ምርመራ ሥራዎች በፖሊስ ሥር እንዲሆን አልተደረገም፡፡ ፖሊስ በሁሉም አገሮች ውስጥ ለሙስና ተጋላጭ መሆኑን በተለያዩ ምሁራን በተለያየ ጊዜ የተካሄዱ ጥናቶች ይህን ያጠናክራሉ፡፡ ይህ የሚሆነው በየአገሮቹ ፖሊስ የሚሰጠው አገልግሎት በጣም ብዙና ከፍተኛ ከመሆኑም በላይ፣ ብዙ የፖሊስ አባላትን እስከ ታች ድረስ ስለሚያስተዳደር፣ እንዲሁም አባላት ሥራቸው ደግሞ ከኅብረተሰብ ጋር  ዕለት ተዕለት ስለሚያገናኛቸው የሙስና ተጋላጭነታቸው በጣም ከፍተኛ የመሆን ዕድል ስላለው ነው፡፡ በየደረጃው ያሉትን ሁሉንም አባላቱን የሥራ እንቅስቃሴ ለመከታተልና ለመቆጣጠር አዳጋች የሚሆንበት አጋጣሚ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡

የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን በአዋጅ ከተቋቋመ 15 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ኮሚሽኑ በቆይታ ወቅት በኅብረተሰቡ የተለያዩ ስሞች ሲሰጡት ነበር፡፡ ‹የኢሕአዴግ የፖለቲካ ፓርቲ ተላለኪ ነው፣ ውቅያኖስን ትቶ ኩሬ ላይ ይንቦጨራቃል፣ አሞራውን ትቶ ወፎችን ያሳድዳል፣ ለኮሚሽኑ ለራሱ ሌላ ኮሚሽን ማቋቋም ያስፈልጋል፣. . .› ሌሎችም ስሞች ሲሰጡት ነበር፡፡ እኔም ከተጠቀሱት የተወሰኑትን በመጠኑ እጋራለሁ፡፡ ነገር ግን የተባለው ሁሉም ልክ ነው ለማለት ያስቸግራል፡፡ ኮሚሽኑ በቆይታው ትልልቅ የመንግሥት ሹማምንትን ለሕግ ፊት አቅርቧል፣ አስቀጥቷል፡፡ ብዛት ያለው ሀብትና ንብረት ከሙስና ወንጀል ተጠርጣሪዎች ማስመለሱን በየጊዜው ከሚያቀርባቸው ሪፖርቶች ማየት ይቻላል፡፡ በኅብረተሰቡ ዘንድ ገነው የወጡት የመመርመርና የመክሰስ ሥራዎች ብቻ ስለሆኑ ያስተማራቸውና የተከላከላቸው የሙስና ተጋለጭነት ሥራዎች በኅብረተሰቡ ዘንድ እምብዛም አይታወቁም፡፡

ማንም ሰው ስለኮሚሽኑ ቢጠየቅ  ሙስና የሚሠሩትን ያስራል፣ ይከሳል የሚለውን ይረዳል እንጂ ሌሎች ሥራዎች መኖራቸውን በትክክል አይረዳም፡፡ በተለይ ሚዲያዎች መዘገብ የሚፈልጉት የምርመራና የዓቃቤ ሕግ ሥራ ብቻ መሆኑን በጣም ጠንቅቄ አውቃለሁ፡፡ ሌሎች የኮሚሽኑን ሥራዎች መስማትም አይፈልጉም፡፡ ቢሰሙም ለመዘገብ  ፈቃደኛ አይሆኑም፡፡ ለዚህ ደግም ምክንያት የሚሰጡት ሰሚ ወይም አድማጭ ማግኘት አንችልም ነው ምላሹ፡፡ በዚህ ዙሪያ የመንግሥትም ሆነ የግል ሚዲያዎች (ከሪፖርተር ጋዜጣ በስተቀር) ተመሳሳይ አቋም አላቸው፡፡ በሙስና ወንጀል የሚለውን ዜና ካገኙ በፊት ገጻቸው ላይ ያወጡታል፡፡ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች በተመሳሳይ የምርመራና የክስ ሥራ እንጂ ሌሎች ዘግበው እንኳን ዘገባውን በሚዲያቸው አያሳዩም፡፡ ይህ እውነት ነው፡፡ አሁን አሁን ግን ቴሌቪዥን ጣቢያ ሁለት የሙስና መከላከል ጥናት ሥራዎች ሊዚያውም ከሁለት ዓመት በፊት የተካሄዱትን የሙስና መከላከል ጥናቶችን በመጠቀም፣ የኢንቨስቲጌቲቭ ጆርናሊዝም ሥራ መሥራቱ ጥሩ ጅማሮ ነው፡፡ የጀመረውን ከቀጠለበት የበፊቱን ጥፋት አርሟል ወይም ክሷል ማለት ነው፡፡

ይኼም በመሆኑ በአዋጅ 943/2008 የምርመራና ዓቃቤ ሕግ ሥራ ከኮሚሽኑ ከወጣ በኋላ ኮሚሽኑ ፈርሷል የሚል አስተሳሰብ እንዲያድር፣ መንግሥት በአንድ በኩል የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና  የእሱ መገለጫ የሆነውን ሙስና በጽናት እታገላለሁ ባለበት አንደበት፣ የፀረ ሙስና ኮሚሽንን ማዳከሙ ሁለት ተቀራኒ ነገሮች እንደሆኑ በስፋት በኅብረተሰቡ ይነገራል፡፡ እውነት ነው ለእኔም ብዥታን ፈጥሯል፡፡ ኮሚሽኑ ያደራጃቸው የፀረ ሙስና ጥምረት አካላት መድረክ ሲዘጋጅ ይህ አጀንዳ ቀዳሚ ጥያቄ ነው፡፡ የኮሚሽኑ ሠራተኞችም ይህን ጥያቄ በተደጋጋሚ ይጠይቃሉ፡፡ ቀጣይ ዕጣ ፈንታው ላይ ጥርጣሬ ያደረባቸው ከ100 በላይ ሠራተኞች ኮሚሽኑን ለቀው ሄደዋል፡፡ በብሔራዊ በተለይ አዲስ አበባ ዞን የተሃድሶ መድረክ ላይ ይህ ጥያቄ በተደጋገሚ ይነሳ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ በተደጋጋሚ ሲነሳ የነበረው ጥያቄ ደግሞ የዓቃቤ ሕግ ሥራ ለምን ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሄደ  ሳይሆን፣ ለምን የሙስና ወንጀል ምርመራ ለፌዴራል ፖሊስ ተሰጠ? የሚል ነበር፡፡

የምርመራ ሥራ ለፌዴራል ፖሊስ የተሰጠው የፍትሕ አካላትን አሠራር ቀልጣፋ ለማድረግ መርህ አይመስለኝም፡፡ ኮሚሽኑ ከተለያዩ ኅብረተሰብ አካላት የተለያዩ ዓይነት ዕይታዎች አሉት፡፡ የመጀመሪያው በሙስና ወንጀል የተከሰሱ ቤተሰቦችና ጓደኞቻቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች በምንም ተዓምር ኮሚሽኑ ጥሩ ይሠራል የሚሉ አይደሉም፡፡ ስም ለማጥፋት ሲፈልጉ መርማሪዎች ጉቦ ይጠይቃሉ ይላሉ፡፡ ለሚሰጡት ስም ግን ማንም ሰው ማስረጃ ማቅረብ አይችልም፡፡ ሁለተኛው የመንግሥትና የገዥው ፓርቲ ተላለኪ ነው የሚሉ ሰዎች ናቸው፡፡ እነዚህ መንግሥት እሰር ያለውን ያስራል፡፡ ፍታ ያለውን ይፈታል እያሉ ያወራሉ፣ ያስወራሉ፡፡ ሦስተኛው ኮሚሽኑን ራሱ ሌባ የሚሉ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ሙሰኞች ላይ አፋጣኝ ዕርምጃ ካልተወሰደ ኮሚሽኑ ራሱ ሙስና ይሠራል ብለው ያስወራሉ፡፡ ብዙውን ጊዜ ጥቆማ የሚያቀርቡ ሰዎች ለአገር ተቆርቋሪ ሆነው ሳይሆን፣ የራሳቸው ዓላማም ስላለቸው ባቀረቡት የሙስና ወንጀል ጥቆማ መሠረት ሁሉም ሰው እንዲታሰርና ተሰረቀ የተባለው ንብረት በአንድ ሌሊት ተመላሽ እንዲሆን የሚፈልጉ ናቸው፡፡ አራተኛው ሙስና የፈጸሙና የመፈጸም ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ሲሆኑ፣ እነዚህ ደግሞ የኮሚሽኑን አለመኖር በጣም ስለሚፈልጉ ያለ የሌለ ኃይላቸውን ተጠቅመው ኮሚሽን ለማዳከም ይሠራሉ፡፡ ይህ አካል በጣም ጉልበት ያለውና የመንግሥትን እጅ እስከ መጠምዛዝ የሚደርስ ነው፡፡

ሌሎች በኮሚሽኑ ሥራ ላይ እርካታ ያላቸው ናቸው፣ እነዚህ ሰዎች ኮሚሽኑ የሙስና ወንጀሎችን በማስቀጣቱ አንጀታቸው የራሰ ናቸው፡፡ የተቀሩት ግን ስለኮሚሽኑ ምንም የማያውቁ ናቸው፡፡ ኮሚሽኑ በዚህ ዙሪያ ችግር የለበትም የሚል አቋም የለኝም፡፡ አለበት፡፡ የመጀመርያው ከሰው ኃይል የማስፈጸምና የመፈጸም አቅም የሚያያዝ ሲሆን፣ የሙስና ወንጀል መከላከልና የመዋጋት ሥራ ላይ በቂ ዕውቀትና ክህሎት ስለሌላቸው የተፈለገውን ያህል ሥራ አልተሠራም፡፡ በተለያዩ ተቋማት በተለያየ ሙያ ሲሠሩ ቆይተው ወደ ኮሚሽኑ የተቀላቀሉ ስለሆነ፣ የሙስና ወንጀል መከላከልና መዋጋት ሥራ እስከሚለምዱ ጊዜ ይወስድባቸዋል፡፡ ከለመዱም በኋላ ኮሚሽኑን ለቀው ስለሚሄዱ ተተኪ ተቀጥሮ እስኪለምድ ጊዜ ይወስዳል፡፡ የሙስና ወንጀል ክትትል የኢንተለጀንስና የፍሪላንስ ባለመኖሩ ኮሚሽኑ የምመራ ሥራ ሲያከናውን የነበረው በጥቆማ ብቻ ላይ የተመሠረተ ሥራ በመሥራቱ፣ በአብዛኛው በጥቃቅን ሙስና ወንጀሎች ምርመራ ላይ እንዲያተኩር አድርጎታል፡፡ ወይም እንዲንገዳገድ አድርጎታል፡፡ ሦስተኛው ድክመት የራሱ ሚዲያ አለመኖር ነው፡፡ የሙስና ወንጀል በመከላከልና በመዋጋት ሥራ ላይ ውጤታማ የሆኑ አገሮች ሚዲያዎችን በስፋት በመጠቀም ወደ ኅብረተሰቡ በመቅረብ በመሥራታቸው ነው፡፡ በፀረ ሙስና ትግል የሚዲያ ሚና በጣም የላቀ ነው፡፡

ሚዲያ ለፀረ ሙስና ትግል ከፍተኛ ኃይል ቢሆንም፣ ኮሚሽኑ አንዳንድ ስፖርቶችንና ጭውውቶችን በግዥ ከማስተላለፍ ውጪ ሚዲያን በተገቢው መንገድ በመጠቀም የፀረ ሙስና ትግሉን አላካሄደም፡፡ አራተኛው ችግር በሠራተኞች ላይ የሚደረግ ክትትልና ቁጥጥር ደካማ መሆን ነው፡፡ የኮሚሽኑ መርማሪዎች በመንግሥት የበላይ ኃላፊዎች ጭምር ይደራደራሉ ሲባሉ ይደመጣል፡፡ ይህን የሚሉት ግን መረጃ ማቅረብ አይችሉም፡፡ እኔ እስከማውቀው ድረስ የተጠረጠሩ 13 ሠራተኞች ማስረጃ ባይገኝባቸውም ከኮሚሽኑ ያለምንም ቅድሚያ ሁኔታ እንዲሰናበቱ ተደርጓል፡፡ በመርማሪዎች ላይ ማንም ሰው መረጃ በማቅረብ ማስረዳት ባይችልም፣ በየመድረኩ እንዲህ ዓይነት አስተያየት በመስጠት ላይ በመሆኑ መንግሥት ልዩ ሥልት በመጠቀም ማጣራትና ዕርምጃ መውሰድ ይገባ ነበር፡፡ የአመራር ድክመት ካለም መዳሰስ ነበረበት፡፡

ከላይ የተገለጹት ዝርዝር ጉዳዮችን በመንተራስ መንግሥት አሁንም የሙስና ወንጀል ምርመራ ሥራን በተመለከተ ሊያስብ ይገባል፡፡ ምክንያቱም በሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎሜሽን ዕቅድ ሰነድ ላይ የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና የእሱ መገለጫ የሆነው ሙስናን መታገል የሞት ሽረት ጉዳይ ባለበት አንደበት፣ የፀረ ሙስና ትግሉን የበለጠ በማጠናከርና የኅብረተሰቡን የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት የኅብረተሰቡን አመኔታ ሊፈጥር ይገባል፡፡ ለዚህም የሙስና ወንጀል ምርመራ ሥራን ለሥነ ምግባርና ለፀረ ሙስና ኮሚሽን በመመለስና የኮሚሽኑን የሰው ኃይል የመፈጸምና የማስፈጸም አቅም በማጎልበት የክትትልና የቁጥጥር ሥራን በማጠናከር ውጤታማ መሆን ይኖርበታል፡፡ ወይም ሌላ የተጠናከረ ራሱን የቻለ የሙስና ወንጀል ምርመራ ተቋም ለብቻው በማደራጃት፣ ተጠሪነቱን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ማድረግ የሚለውም መታየት አለበት፡፡ ካልሆነ ግን አሁን በተዋቀረው አደረጃጀት የሙስና ወንጀልን የመከላከልና የመዋጋት ሥራ ውጤታማ ይሆናል ማለት ራስን ማሞኘት ይሆናል፣ የታቀደውን የኅብረተሰብ አመኔታ ለማግኘት ያስቸግራል የሚል አስተያየት አለኝ፡፡ አንዳንዴ ወደታችኛው ኅብረተሰብ ወርዶ የሚባለውን መስማት ለመንግሥት ሥራ አመራር ውጤታማነትና አመኔታ  ከፍተኛ ጠቃሜታ አለው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...