Thursday, February 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልጌጥን በቤት

ጌጥን በቤት

ቀን:

አቶ የሺጥላ ክፍሌ በጥበቃ የሚሠራበት የግል መሥሪያ ቤት በራፍ አረፍ ብሎ፣ ወደ መሥሪያ ቤቱ የሚገቡና የሚወጡ ግለሰቦችን ይቆጣጠራል፡፡ ጎን ለጎን ጋዜጣና መጽሔት በአራት ማዕዘን ቅርፅ ይቆራርጣል፡፡ የቆራረጠውን ወረቀት በአንድ ጥግ አስቀምጦ ሲለካና ሲያስተካከል የተመለከቱ የመሥሪያ ቤቱ ሠራተኞች ምን እየሠራ እንደሆነ ይጠይቁታል፡፡ ‹‹ጌጣ ጌጥ እየሠራሁ ነው፤›› ሲላቸው እንዴት? በሚል ተገርመው ይመለከቱትና ወደ ሥራቸው ያመራሉ፡፡ ወረቀቶቹን ቀዶ ካስያዛቸው በኋላ እያድበለበለ በሙጫ ያጣብቃቸዋል፡፡ የመሥሪያ ቤቱ ሠራተኞችም እስኪ በስተመጨረሻ የሚሠራውን እናያለን በሚል ዓይነት ሲገቡ ሲወጡ በአትኩሮት ይመለከቱታል፡፡ 

ከጥቂት ቀናት በኋላ ከወረቀት የአንገትና የእጅ ጌጥ ሠርቶ አጠናቀቀ፡፡ ከጋዜጣና መጽሔት ቅዳጅ በተሠሩት ጌጦች የሚታዩት የተቆራረጡ ፊደሎችና ሥዕሎች ጌጦቹን ውበት አላብሰዋቸዋል፡፡ አንዳንዶቹ ጌጣ ጌጦች የተሠሩት ደግሞ ወረቀቶቹ ደማቅ ቀለም ተቀብተው ነው፡፡ ጌጣ ጌጦቹ ለሽያጭ ቀርበውም የመሥሪያ ቤቱ ሠራተኞች ይገዙ ጀመር፡፡ ሽያጩ ያበረታታው አቶ የሺጥላ ጆሮ ጌጥና የእጅ አምባር ወደ መሥራት ተሸጋገረ፡፡ ከጌጣ ጌጦቹ በተጨማሪ በፕላስቲክ መረብና በጨሌ የሚሠሩ ቦርሳዎችንም ጎን ለጎን ይሠራል፡፡

በእጅ ጌጣ ጌጥ መሥራት የተማረው ከባለቤቱ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ባለቤቱ በቆዳ፣ በጨሌ፣ በዶቃ፣ በወረቀትና በሌሎችም ቁሳቁሶች ጌጣ ጌጥ መሥራት ከጀመረች ዓመታት አስቆጥራለች፡፡ ለባለቤቷና ለልጆቿም ይህንን የፈጠራ ጥበብ አስተምራለች፡፡ የአንገት፣ የጆሮና የእጅ ጌጣ ጌጦች ሠርታ ፖስታ ቤት፣ ቸርችል ጎዳና፣ ፍል ውኃና ስታዲየም አካባቢ ትሸጣለች፡፡

እሱ እንደሚለው፣ የባለቤቱን የፈጠራ ሥራ መጋራት የጀመረው አንድም ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት ሲሆን፣ ጎን ለጎን እንደ አዕምሮ ማሳረፊያም ነው፡፡ ‹‹ቁጭ በምልበት ጊዜ ጌጣ ጌጥ ስሠራ የአዕምሮ እረፍት ይሰጠኛል፡፡ የገቢ ምንጭም ነው፤›› ይላል፡፡ ሥራውን ለማከናወን የሚያስፈልገውን ግብዓት ከመርካቶ ይገዛል፡፡ ጅማት ክር፣ የሀር ክር፣ መረብ፣ ዶቃ፣ ጨሌና ሌሎችም በብዛት ገዝቶ እሱ፣ ባለቤቱና ልጆቹ እየተጋገዙ ጌጣ ጌጥ ይሠራሉ፡፡

መርካቶ ከጌጣ ጌጥ ጀምሮ የቤት ውስጥ ቁሳቁሶችን በእጃቸው የማዘጋጀት ልምድ ያላቸው ሰዎች ተቀዳሚ መዳረሻ ነው፡፡ መርካቶ ውስጥ የማይሸጥ ነገር አለ ለማለት ይከብዳል፡፡ ጨሌ በኪሎ ከ500 እስከ 700 ብር ይሸጣል፡፡ የፕላስቲክና የመስታወት ጨሌዎች እንደየአስፈላጊነቱ መግዛትም ይቻላል፡፡ የተለያዩ ቀለም ያላቸው ክሮችና ሌሎችም ግብዓቶችም ይገኛሉ፡፡ አቶ የሺጥላ እነዚህን ግብዓቶች ገዝቶ የአንገት ሀብል እስከ 20 ብር፣ ቦርሳ እስከ 120 ብር ይሸጣል፡፡ ግብዓቶቹ ከሚሸጡበት ዋጋ አንፃር ሽያጩ አዋጭ እንዳልሆነም ይናገራል፡፡

‹‹በተለይም በበዓላት ወቅት በእጅ የሚሠራ ጌጣ ጌጥ የሚገዙ ሰዎች ቁጥር ይጨምራል፡፡ በትዕዛዝ የሚያሠሩም አሉ፡፡ ጫማና ኮፍያ ላይ ደማቅ ቀለም ጨሌ እንዲሰፋላቸው የሚጠይቁም ብዙ ናቸው፡፡ ሆኖም ለግብዓቶቹ የሚወጣው ወጪና መሸጫው መካከል ሰፊ ልዩነት አለ፤›› ይላል፡፡ ከሱ ገዝተው ሱቅ ውስጥ የሚሸጡ ሰዎች ከሚያገኙት ጥቅም አንፃርም የሱ ያነሰ ነው፡፡ በእጅ ለሚሠሩ ጌጣ ጌጦችና መገልገያዎች ቦታ የሚሰጡ ሰዎች ዕቃዎቹን አክብረው እንደሚገዙ ይገልጻል፡፡ አቅም ኖሮት ሰዎች በሚፈልጉት ቅርፅና መጠን ሰፋ ባለ ሁኔታ ጌጣ ጌጦቹን ለገበያ ቢያቀርብም ደስተኛ ነው፡፡ አቅሙ ጎልብቶ በሳጠራ የአበባ ማስቀመጫ፣ የሠርግ አበባ መበተኛ ዕቃና ሌላም ሠርቶ ለገበያ የማቅረብ ዕቅድ አለው፡፡ በወረቀት፣ በጨሌና በሽቦ እንደ ጌጥ የሚሆን ሰሃንና ሌሎችም መገልገያዎች መሥራትም ይፈልጋል፡፡

እንደ እሱ ሽያጭ ላይ አነጣጥረው በእጅ ጌጣ ጌጦች የሚሠሩ ግለሰቦች ያሉ ሲሆን፣ ቤታቸው የሚያዘጋጁትን ጌጣ ጌጥ ለራሳቸው መዋቢያ የሚያውሉት አሉ፡፡ የፈጠራ ችሎታ ያላቸው ሰዎች ከወዳደቁ ቁሳቁሶችና ግብአት በመግዛትም ይሠራሉ፡፡ በተለይም በትርፍ ጊዜያቸው በቤታቸው እነዚህን ጌጣ ጌጦች የሚያዘጋጁ ሰዎች እንደ መዝናኛ የሚወስዱበትም ጊዜ አለ፡፡ አንዳንዶች ከጠጠር ጀምሮ ፕላስቲክ፣ ብረታ ብረት፣ እንጨትንና ሌሎም ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ቁሳቁሶችን በመጠቀም አስገራሚ ጌጣ ጌጥ ይሠራሉ፡፡ መርፌ ቁልፍ፣ ሹካና ማንኪያ፣ ብይ፣ መርፌ፣ ጥጥና ሸክላ የሚጠቀሙ ይጠቀሳሉ፡፡ እንዲህ ዓይነት ሰዎች የሚገኙት አልፎ አልፎ ሲሆን፣ ብዙዎች ጌጣ ጌጥ ሲበጠስባቸው የመጠገን ወይም በሚፈልጉት መጠን የማስተካከል ልማዱ አላቸው፡፡

ቢታንያ ኤፍሬም ቤት ውስጥ ጌጣ ጌጥ ማዘጋጀት የጀመረችው የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለች ነበር፡፡ እናቷ ከቅርብ ጓደኞቻቸው ጋር የከፈቱት የልብስ ስፌት ሱቅ ደጋግማ መሄዷ ለፈጠራው ሥራ እንዳነሳሳት ትገልጻለች፡፡ ከትምህርት ቤት ስትወጣ፣ ቅዳሜና እሑድ ወደ ሱቁ እየሄደች ልብስ ዲዛይን ሲደረግ፣ ጨርቅ ሲቀደድና ሲሰፋ ትመለከታለች፡፡ ልብስ በማይሰፋበት ወቅት ደግሞ የእጅ ሥራ ይሠራል፡፡ የሶፋ ልብስና አልጋ ልብስ፣ ዳንቴል አንዳንዴም ሹራብና ካልሲ ሲዘጋጅም ታያለች፡፡ ‹‹የሚሠሩባቸው ክሮች፣ ቀለማትና ቁልፎች ይማርኩኝ ነበር፤ በየጊዜው ሁለትና ሦስት ቁልፍ ከሱቅ እወስድም ነበር፤›› ትላለች፡፡ የምትወስዳቸውን ቁልፎች ተጠቅማ ጌጣ ጌጥ የመሥራት ፍላጎት ቢኖራትም፣ እንዴት ማዘጋጀት እንደምትችል እስከሚገለጽላት ጊዜ ወስዶባታል፡፡

እሷ እንደምትለው፣ ቁልፎችን እየገጣጠሙ በክር መስፋት ጀመረች፡፡ ከዚያም ሸቦ ላይ ቁልፍ በመሰካት ጆሮ ጌጥ መሥራትና ቁልፎችን ጨርቅ ላይ በመስፋት የእጅ ጌጥ ማዘጋጀትን ራሷን በራሷ አስተማረች፡፡ ደማቅ ቀለም ያላቸው ቁልፎችን በጥቁር ክር አስገብታ የእግር ጌጥም ትሠራ ጀመር፡፡ ረዘም ያለ ጊዜ ወስዳ ጌጣ ጌጥ ስለምትሠራ በመጠኑ ከዕድሜ እኩዮቿ የተገለለችበት ወቅት እንደነበር ታስታውሳለች፡፡ ‹‹የጥናት ጊዜን ይሻማል›› በሚል ታላቅ እህቷና እናቷ ጌጣ ጌጥ መሥራት እንድታቆም ያስገድዷትም ነበር፡፡ አሥራ ሁለተኛ ክፍል ስትደርስ የቤተሰብ ቁጣና የትምህርት ጫናም ተደራርቦ ጌጣ ጌጥ መሥራት ማቋረጧን ትገልጻለች፡፡

ከማትሪክ ፈተና በኋላ ግን ሙሉ ጊዜዋን ለጌጣ ጌጥ ሥራ ሰጠች፡፡ በዚህ ወቅት እናቷና እህቷ ጌጣ ጌጥ ለመሥራት የሚያስፈልጋትን ግብዓቶች ከማሟላት ሌላ አማራጭ እንዳልነበራቸውም ትናገራለች፡፡ አሁን በመንግሥት መሥሪያ ቤት ተቀጥራ የምትሠራው ቢታንያ፣ በወቅቱ ከቁልፍ አልፋ ማንኛውንም ነገር ወደ ጌጣ ጌጥ የመለወጥ ፍላጎቷ እንዳደገ ትናገራለች፡፡ ‹‹ቤት ውስጥና መንገድ ላይም የማየውን ነገር በሙሉ ወደ ጌጥ መለወጥን ማሰብ ጀመርኩ፤›› ትላለች፡፡ የእስኪርቢቶ ክዳን፣ ወረቀት፣ ጨሌ፣ የልብስ መለያ (ብራንድ) ቅዳጅና የቆዳ ቀበቶን ጨምሮ ለጌጥ መሥሪያ ያልተጠቀመችበት ነገር አለ ለማለት ይከብዳል፡፡

‹‹ዩኒቨርሲቲ ከገባሁ በኋላ ጌጣ ጌጦችን ለሰዎች በስጦታ መልክ መስጠት፣ ቤቴ መጥተው የሠራሁትን እንዲያዩ ማድረግ ጀመርኩ፤›› ትላለች፡፡ በዚህ ሁኔታ ጌጣ ጌጦች እንግዛሽ? የሚል ጥያቄ ይቀርብላት ጀመር፡፡ ለስሜቷ ብላ የምትሠራውን ጌጣ ጌጥ በነፃ መስጠት ቢያስደስታትም ቀስ በቀስ ግን ወደ ሽያጩ ገባች፡፡ የሰዎችን መጠሪያ ስም የመጀመርያ ፊደል የያዘ የእጅና የአንገት ጌጥ እየሠራች መሸጥንም ተያያዘችው፡፡ የአንገት ጌጥ እስከ 80 ብር፣ የእጅና የእግር ጌጥ እስከ 50 ብርና የጆሮ ጌጥ እስከ 30 ብር ትሸጥ ነበር፡፡ በየጊዜው አዳዲስ ፈጠራዎችን ለማግኘት ድረ ገጽ መጎብኘት እንደጀመረችም ትናገራለች፡፡

ቢታንያ ‹‹ጌጣ ጌጥ መሥራት እንደ ሜዲቴሽን [ተመስጦ] ነው፤›› ትላለች፡፡ ስትጨነቅ ወይም ስትበሳጭ ጌጣ ጌጥ መሥራት ያረጋጋታል፡፡ ክር መርፌ ውስጥ ለማስገባት ወይም ብረት በፒንሳ ለመቁረጥ የሚጠይቀው ዝግታ ሐሳብን እንደሚያስረሳትም ትገልጻለች፡፡ ሥራ ከያዘች በኋላም ጌጣ ጌጦቿን መሸጥ ቀጥላበታለች፡፡ ራሱን የቻለ ቢዝነስ እንዲሆን እንደምትፈልግም ትናገራለች፡፡ አሁንም የምትሸጥበት ዋጋ ከ100 ብር እንደማይበልጥና ለሷ ከገንዘቡ ይልቅ ፈጠራዋ ቦታ ማግኘቱ እንደሚያስደስታትም ታክላለች፡፡

ደስታ ደጀኔ በበኩሏ ተፈጥሯዊ ነገሮችን ወደ ጌጣ ጌጥ መለወጥ ትመርጣለች፡፡ ‹‹ሁልጊዜ መሬት እያየሁ እሄዳለሁ፡፡ የወደቀ ቅጠል ወይም ፍራፍሬ ለቃቅሜ ጌጥ እሠራባቸዋለሁ፤›› ትላለች፡፡ ከባህር ዛፍ ፍሬ ያዘጋጀቻቸው ቀለበቶችና ከአንፀባራቂ ድንጋይ የተሠሩት የእጅ ጌጣ ጌጦች ይጠቀሳሉ፡፡ ተፈጥሯዊ ግብዓቶችን ወደ ጌጥነት ለመለወጥ እንደ ማያያዣ የምትመርጠው ደግሞ የወዳደቁ የኤሌክትሪክ ገመዶች፣ አግራፍና ማንኛውም ዓይነት ብረት ነው፡፡

‹‹ቁሳቁሶች ለአንድ አገልግሎት ታስበው ከተሠሩ በኋላ ያን አገልግሎት ሰጥተው ሊጣሉ ወይም ጥቅም ላይ ሳይውሉ ሊቀሩም ይችላሉ፡፡ እነዚህን በድጋሚ ግልጋሎት ላይ ማዋል ደስ ይለኛል፤›› ትላለች፡፡ ደስታ ጌጣ ጌጦች ስትሠራ የምትጠቀምባቸውን ግብዓቶች ዳግም ሕይወት እየዘራችባቸው እንደሆነ ታምናለች፡፡ ኦሪጂናልነታቸውን እንዳያጡ ስለምትፈልግም አትቆራርጣቸውም፡፡ ቀለምም አይቀቡም፡፡

ተፈጥሮ ሲባል ብዙውን ጊዜ ትኩረት የሚሰጠው በሕይወት ላሉ ዛፎች ወይም ዛፍ ላይ ለሚገኙ ፍሬዎች እንደሆነ ትገልጻለች፡፡ በሷ ዕይታ ግን መሬት ላይ የረገፉ ቅጠሎችና ፍራ ፍሬዎችም አንድ የተፈጥሮ ገጽታ ናቸው፡፡ ይህን ሐሳቧን ይረዳሉ ብላ ለምታስባቸው ሰዎችም ጌጣ ጌጦቹን ትሰጣለች፡፡ እሷ እንደምትለው፣ ከመደበኛ ሥራዋ ጎን ለጎን ጌጣ ጌጦቿን የምትሸጥበት ሱቅ መክፈት ብትፈልግም፣ ጌጣ ጌጦቹ ለገበያ ብቁ ናቸው ብላ አታስብም፡፡ ለዚህ እንደ ምክንያት የምትጠቅሰው ደግሞ ጌጣ ጌጥን በጥራት ለመሥራት የሚያስችሉ መሣሪያዎች በቀላሉ አለመገኘታቸውን ነው፡፡ ጌጣ ጌጥ በሚፈለገው ጥልቀት ለመሥራት የምትፈልጋቸውን መሣሪያዎች ማሟላት የምትችልበት የገንዘብ አቅም ሲኖራት ወደ ቢዝነስ እንደምትለውጠውም ትገልጻለች፡፡

በማሽን የተሠሩ ጌጣ ጌጦች ሲበላሹባቸው የመጠገን፣ አንድ ጌጥ ላይ ሌላ ግብዓት የመጨመር ወይም የመቀነስ ዝንባሌ ያላቸው ብዙዎች ናቸው፡፡ ለአንዳንዶቹ ቦታ የሚሰጠው የፈጠራ ውጤት ሲሆን፣ ለሌሎች እንደ ጊዜ ማሳለፊያም ነው፡፡ ከቤት ውስጥ ሥራ ወደ ቢዝነስ የማሳደግ ፍላጎት ያላቸው ግለሰቦች በተለያየ መንገድ ሥራዎቻቸውን ሲያስተዋውቁም ይታያል፡፡ በቫይበርና በፌስቡክ ጌጣ ጌጦቻቸውን የሚያስተዋውቁ አስተውለናል፡፡

 ከነዚህ አንዷ የስጦታ ቅርጫት (ጊፍት ባስኬት) የሠራች ወጣት ናት፡፡ ለልደት፣ ለሠርግ፣ ለምርቃት፣ ለበዓላትና ለሌሎችም ሁነቶች የሚሆኑ የስጦታ ቅርጫቶች አዘጋጅታ በቫይበር እያስተዋወቀች ነበር፡፡ መግዛት የሚፈልጉ ሰዎች በቅርጫቶቹ ውስጥ እንዲካተቱላቸው የሚፈልጓቸውን ቁሳቁሶች ያሳውቋትና ታዘጋጃለች፡፡ ወይን፣ ቡናና ሌላም ነገር በቅርጫት ውስጥ እንዲካተትላቸው ገዥዎች ይጠይቃሉ፡፡ እሷም ቅርጫቱ የተፈለገበትን ሁነት የሚወክል ቅርፅ ታስይዘዋለች፡፡ ለምሳሌ ለምርቃት ሲሆን፣ ትምህርት ማጠናቀቅን በሚያመላክቱ ፎቶግራፎችና ቅርጾች ቅርጫቱን ታሳምራለች፡፡ ለልደት በዓል ያዘጋጀችው ቅርጫት የገና አከባበርን በሚያመላክቱ ሃይማኖታዊ ምስሎችና በመብራት ያጌጠ ነበር፡፡

አዲስ አበባ ውስጥ እየተዘወተሩ የመጡት የንግድ ዐውደ ርዕዮችም ቤት ውስጥ የሚዘጋጁ የፈጠራ ውጤቶች ማሳያ እየሆኑ ነው፡፡ በጋዜጣ የተሠራ ቦርሳና ከቃጫ ገመድ የተዘጋጀ ጫማ በቅርቡ ከታዩት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ ከጌጣ ጌጦች ባለፈ የቤት ውስጥ መገልገያዎችን በእጅ የሚሠሩም አሉ፡፡ በእጅ ከሽቦ የተሠራ የአበባ ማስቀመጫና በእምነበረድ ፍርካሽ የተጌጠ መስታወት እንደምሳሌ ይጠቀሳሉ፡፡ በብዛት በዲዛይን፣ በአርክቴክቸርና በሥነ ጥበብ ሙያ ውስጥ ያሉ ግለሰቦች አልባሳት፣ ጌጣ ጌጥና የቤት መገልገያም ራሳቸው የማዘጋጀት ዝንባሌ አላቸው፡፡

ስንሻው ተገኘ (ስሙ ተቀይሯል) የአንገትና የእጅ ጌጥ ከእንጨት መሥራት የጀመረው በቅርቡ ነው፡፡ ጌጣ ጌጥ ማዘጋጀት ከመጀመሩ በፊትም፣ በእጅ መሠራት የሚችሉ ነገሮችና ቤት ውስጥ የመሥራት ሐሳብ ያስደስተው እንደነበር ይናገራል፡፡ ‹‹ድሮ መብራት በየሠፈሩ በተራ በሚጠፋበት ጊዜ እኔና አባቴ ቤት የምናበራውን ሻማ አቅልጠን ሲደርቅ የጧፍ ክር ከተን ሌላ ሻማ ለመሥራት እንሞክር ነበር፤›› ይላል፡፡ እናቱ ቤት ውስጥ የልብስ ስፌት መኪና ስላላቸው ልብስ ሲሰፉም ያግዝ ነበር፡፡ ከነዚህ በመነሳት የራሱን የፈጠራ ውጤት የማዘጋጀት ፍላጎት እንዳደረበትም ያወሳል፡፡

‹‹ከማንኛውም ዓይነት ቁሳቁስ እንጨት ይማርከኛል፤›› የሚለው ስንሻው መጠነኛ መጋዝ፣ ቫርኒሽና ሌሎችም አስፈላጊ ነገሮችን አሟልቶ ጌጣ ጌጥ መሥራት ሲጀምር ብዙ ጓደኞቹ እንዳልተቀበሉት ያስታውሳል፡፡ ወንበር፣ ጠረጴዛ ወይም የመጽሐፍ መደርደሪያን የመሰሉ ግዙፍ ነገሮች መሥራት እንደሚገባው የነገሩትም ነበሩ፡፡ በእሱ እምነት የሰዎችን ውበት ማጉላት ቅድሚያ ይሰጠዋል፡፡ አርክቴክቸር መማር እንደሚፈልግ የሚናገረው ስንሻው፣ ከተወሰነ ዓመት በኋላ ከጌጣ ጌጥ በተጨማሪ የቤት ውስጥ ቁሳቁስም መሥራት ይፈልጋል፡፡

አሁን በመስቀል፣ ከክዋክብትና ሌሎችም ቅርጾች ጌጣ ጌጦች ይሠራል፡፡  እንደሚሠራው የጌጥ ዓይነት ከአንድ እስከ ሦስት ሳምንት ይወስድበታል፡፡ ቢያንስ እንጨት ሳይቆርጥ ወይም የጌጣ ጌጥ ዲዛይን ሳይሥል የዋለባቸው ቀናት በጣት እንደሚቆጠሩ ገልጾ፣ ‹‹እንደ ሱስ ነው፤›› ይላል፡፡ ፈጠራ ደስ ስለሚለው ይሥራ እንጂ እንደ ቢዝነስ እንደማያየው ይናገራል፡፡ በሙዚቃ ኮንሰርቶች፣ በምግብና መጠጥ ፌስቲቫሎችና ባዛሮች ላይ ከተለያየ ቁሳቁስ የተሠሩ ጌጣ ጌጦች ሲሸጡ ሲያይ ቢያስደስተውም፣ ‹‹ለምቀርባቸው ሰዎች ከመስጠት ባለፈ መሸጥ አልፈልግም፤›› ይላል፡፡

በእጅ የተሠሩ ጌጣ ጌጦች የሚሸጡባቸው በርካታ ድረ ገጾች ማግኘት ይቻላል፡፡ ጌጣ ጌቹን ለመሥራት ከሚወስደው ጊዜና ጉልበት አንፃርም ዋጋቸው ይወደዳል፡፡  ቤት ውስጥ እንዴት ጌጣ ጌጥ መሥራት እንደሚቻል በጽሑፍና በቪዲዮ የሚያስተምሩ ድረ ገጾችም አሉ፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ጥቁር የመልበስ ውዝግብና የእምነት ነፃነት በኢትዮጵያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ኅዳር ወር ላይ በፓርላማ...

የኢንሹራንስ ዘርፉን የሚቆጠጠር ገለልተኛ ተቋም ለመመሥረት እንቅስቃሴ ተጀመረ

ከ70 በላይ አዳዲስ የፋይናንስ ተቋማት ዘርፉን ሊቀላቀሉ ነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ...

እስቲ አንገፋፋ!

እነሆ መንገድ። ጊዜና ሥፍራ ተጋግዘው በውስንነት ይዘውናል። መፍጠን ያቃተው...