Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉከተገልጋይ ጋር ቀጥተኛ ግንኙት ያላቸው የመንግሥት ተቋማት በሚታደስ የኮንትራት ቅጥር ሠራተኞች አገልግሎት...

ከተገልጋይ ጋር ቀጥተኛ ግንኙት ያላቸው የመንግሥት ተቋማት በሚታደስ የኮንትራት ቅጥር ሠራተኞች አገልግሎት እንዲሰጡ ቢደረግስ?

ቀን:

በዓለሙ ሳሙኤል

መንግሥታችን የመልካም አስተዳደር ችግር ኅብረተሰቡን እያማረሩ እንደሆነና ለዚህ መንስዔው ደግሞ የመንግሥት አገልግሎት የሚሰጡ አመራርና ሠራተኞች በኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብ ችግሮች እየተለከፉ፣ የመንግሥት አገልግሎት ሟጓተታቸው መሆኑን በግልጽ አስቀምጧል፡፡ ዕውን የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብ ችግር ብቻውን ለመልካም አስተዳደር ችግር እያደረገ ነው ያለው? የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብ ችግር የችግሮቹን ትልቅ ቦታ ቢይዝም፣ ሌሎች ቀላል የማይባሉ ችግሮችም በስፋት መንስዔ ናቸው፡፡ የችግሮቹ መንስዔ የመንግሥት አመራርና ሠራተኞችና የኅብረተሰብ አካል የሆኑ ሰዎች ናቸው፡፡

የአመራርና የሠራተኞች የሥራ ላይ ብቃትና ክህሎት ማነስ የመጀመሪያው  መንስዔ ነው፡፡ ለመንግሥት አገልግሎት ተሹመው አገልግሎት የሚሰጡትን አመራርና ሠራተኞችን በቅድሚያ እንያቸው፡፡ ከእነዚህ ሰዎች የድርጅት አባል የሆኑ በብዛት አሉ፡፡ አባል በመሆናቸው ለድርጅቱ ታማኝ ናቸው፣ የድርጅቱን መዋጮ በወቅቱ ይከፍላሉ፡፡ የድርጅቱን የተለያዩ ድርሳናት ገዝተው ያነባሉ፡፡ አያመልጣቸውም፡፡ በድርጅት ጉዳይ ላይ እየተሰበሰቡ ይወያየሉ፣ ይገምግማሉ፣ አስተያየት ይሰጣሉ፣ ይቀበላሉ፡፡

ከእነዚህ ሰዎች ውስጥ በዕውቀትና በክህሎት ላይ የተመሠረተ የሥራ እንቅስቃሴ የሚያደርጉና የዓላማ ፅናት ያለቸውና የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብ ችግር የሌለባቸው ንፁህ ዜጋ የሆኑ አባላት ስላሉ፣ ይህ አስተያየት እነሱን አይመለከትም፡፡  ቁጥራቸው አነስተኛ ያልሆኑ ግን የለብ ለብ ዕውቀት ያላቸው፣ የጠለቀ ዕውቀት የሌለቸው፣ በተሰማሩበት የሥራ መስክ ምን ታቅዶ ምን እንደሚከናወን፣ የሥራ ውጤት ምን እንደሆነ በትክክል የማያውቁ  አባላት ናቸው፡፡ በድርጅት ውስጥ ጠብ የሚል ነገር ፍለጋ የገቡና የዓላማ ፅናት የሌላቸው ናቸው፡፡

እነዚህ ሰዎች በተሰማሩበት የሥራ መስክ ዕውቀትና ክህሎት ስሌላቸው የወር ደመወዝ ከመጠበቅ ውጪ፣ ለዜጎች የተሰማሩበትን የመንግሥት አገልግሎት በተፈለገው ልክ መስጠት የማይችሉ ናቸው፡፡ በሰሙት ልክ ብቻ የማስተገባት አቅም ያላቸው ናቸው፡፡ የመናገር አቅም ይኖራቸዋል፡፡ በዕውቀትና ክህሎት ላይ የመሠረተ አገልግሎት መስጠት ስለማይችሉ ኅብረተሰቡን በጣም ያጉላሉ፡፡ የለውጥ መሣሪዎችን አያውቁም፣ ለማወቅም ፍላጎት የሌላቸው ናቸው፡፡ ሥልጠና ተሰጥቶአቸው አይገባቸውም፡፡ በለውጥ ትግበራ ላይ አቃቂር ለማውጣት በጣም አቅም ያላቸው ናቸው፡፡ ደመወዝ ስለሚከፈላቸው ብቻ መሥሪያ ቤት ውስጥ ይውላሉ፡፡ በዜጎች ቻርተር ላይ የሚያስቀምጡትን ስታንዳርድ እንዴት እንደሚላክ ዕውቀትና ክህሎት የላቸውም፡፡ እንዲኖራቸውም አይፈልጉም፡፡ በጉዳዮች ላይ ውሳኔ መስጠት ለመስጠት ይፈራሉ፡፡ ጊዜ ለመውሰድ ቀጠሮ በመስጠት ተገልጋዮች ያመላልሳሉ፡፡

ከእነዚህ ጋር ተመሳሳይ አቋም ያላቸው ነገር ግን የድርጅት አባል ያልሆኑ በብዛት በመንግሥት ተቋማት ውስጥ ይሠራሉ፡፡ በመንግሥት ተቋም ውስጥ ለምን እንደሚሠሩ፣ በተቋሙ ውስጥ የእነሱ ሚና መሆን እንዳለበት ዕውቀቱም ክህሎቱም የሌላቸው፣ ለሥራ ብለው ብቻ ከቤት የሚወጡ፣ በዕውቀትና በክህሎት ላይ ተመሥርተው ምንም ዓይነት ውጤታማ ሥራ የማያከናወኑ፣ በየወሩ ደመወዝ የሚጠብቁ፣ መንግሥትን በማማት ሲመሽ ቤታቸው የሚገቡ ቁጥራቸው ቀላል ያልሆነ  ሠራተኞች በብዛት አሉ፡፡

ዕውቀትና ክህሎት ካለቸው አመራርና ሠራተኞች ውስጥ የክፋት መንፈስ የተጠናወተቸውን በሌላ ረድፍ እንያቸው እስቲ፡፡ እነዚህ የመናገር፣ በውሸት የማሳመን፣ ለሥራ በቂ ዕውቀትና ክህሎት ያላቸው ናቸው፡፡ ከደመወዛቸው በተጨማሪ ገቢ እንዴትም ማግኘት ይፈልጋሉ፡፡ ለዚህም የግል የገቢ ማግኛ ዕቅድ አውጥተው ይንቀሰቀሳሉ፡፡ አቅም ስላለቸው የተሠማሩበትን የመንግሥት የሥራ መስክ ያወሳስቡታል፡፡ ለተገልጋይ የተዛባ መረጃ ይሰጣሉ፡፡ በተንኮልና በውሸት የተካኑ ናቸው፡፡ አገልግሎት ለማግኘት የሚመጡ ተገልጋዮች ጉቦ እንዲሰጥዋቸው የተመቻቸ ሁኔታ ይፈጥራሉ፡፡

 የገባው (አራዳው) ተገልጋይ ጉቦ ሰጥቶ አገልግሎት ሲያገኝ፣ ያልገባው ተገልጋይ ደግሞ በደላላ አማካይነት አዕምሮው ተዋክቦ ጉቦ ከፍሎ አገልግሎት ያገኛል፡፡ እነዚህ ሰዎች በሰጥቶ መቀበል መርህ ለሚንቀሳቀሱ ተገልጋዮች ንቁህ አዕምሮ ያላቸው ናቸው፡፡ የመንግሥት ሀብትና ንብረት በሕገወጥ መንገድ ይጠቀማሉ፣ ሌሎችም እንዲጠቀሙ ያደርጋሉ፡፡ ተጨማሪ ገቢ ስለሚፈልጉ ከመንግሥት በጀት ላይ የግል ድርሻቸውን ለማግኘት የተለያዩ ዘዴዎችን ይነድፋሉ፡፡ የማይሳካለቸውን ትተው የሚሳካውን ሥልት በመጠቀምና ግዥዎች በማወሳሰብ ጥቅም ያገኛሉ፡፡ ለዚሀ ማሳያ የዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል የመድኃኒት ግዥና አስተዳደር ላይ የቀረበውን የኢብኮ ዘገባ ከዩቲዩብ ማየት በቂ ነው፡፡

ሀብታም ለመሆን የሚፈልጉ ተገልጋዮች እነዚህን ሰዎች በስፋት ይጠቀማሉ፡፡ በአቋራጭ ሀብታም የሆኑና የበለጠ ሀብት ለማግኘት ሲሉ የእነዚህን ሰዎች እጅ ጠምዝዘው ጭምር የሚፈልጉትን ጥቅም ያገኛሉ፡፡ በተለይም ልማታዊ ያልሆኑ ባለሀብቶች የመንግሥት አመራሮችና ሠራተኞችን በጥቅም በማንባርከክ የመንግሥትን ጠንካራ ሕግ ለመሻር ተግተው ይሠራሉ፡፡ ለእነሱ የማጭበርበር ፍላጎት የሚያመች ሕግ እንዲወጣ ከጀርባ ሆነው በትጋት ይሠራሉ፡፡ አሳሪ የሆኑ ሕጎችን ያስቀይራሉ፡፡ በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄው ሰነድ ውስጥ ይህን የሚያመለክትና የሚያጠናክር ሐሳብ ያነበብኩ ይመስለኛል፡፡

ሌላው መልካም አስተዳደር ለማስፈን እንቅፋት የሚሆነው የአመራርና የሠራተኞች የኪራይ ሰብሳቢነት የአስተሳሰብ ችግር ነው፡፡ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት ችግር ያለባቸው አመራሮችና ሠራተኞች ሥራ የሚሠሩት ለራሳቸው ገቢ ፍለጋ መሆኑን እያወቁ ሁሌም መንግሥትን ያማርራሉ፡፡ ጧት ሥራ ሲገቡ ተገደው እንዲገቡ እንደተደረጉ ያስባሉ፡፡ ሁሌም ይህ መንግሥት ለምን ደመወዝ አይጨምርም የሚል መፈክር ያሰማሉ፡፡ በእርግጥ ከፍተኛ የኑሮ ውድነት በተለይም በከተሞች ውስጥ መኖሩ ይታወቃል፡፡ የቤት ኪራይ ውድ ነው፣ አከራዮች በየጊዜ የኪራይ ዋጋ ይጨምራሉ፡፡

መንግሥት ሠራተኞች የትራንስፖርት አገልግሎት በነፃ እንዲያገኙ ቢያደርግም ጧት መነሳትን ስለማይፈልጉ ሥራ አርፍደው ሥራ ይገባሉ፡፡ በመሆኑም ለትራንስፖርት ወጪ ይጋለጣሉ፣ በራሳቸው ጥፋት መንግሥትን ያማርራሉ፡፡ ስህታተቸውን ስለማይረዱ ሁሌም ከአፋቸው የሚወጣው ይህ መንግሥት ለምን ደመወዝ አይጨምር የሚል ነው፡፡ የተሰጣቸውን ነፃ የትራንስፖርት አገልግሎት በመርሳት መንግሥት ለምን የትራንስፖርት ችግር አይፈታም እያሉ ያመርራሉ፡፡ የተሠማሩበትን ሥራ በቅልጥፍና ለመሥራትና ውጤታማ ለመሆን አያስቡም፡፡ ሁሌም እከሌ የሚባል መሥሪያ ቤት ብዙ ደመወዝ ይከፍላል፣ ለእኛ ግን አይጨመርም፣ መንግሥት የሀብት ክፍፍል ላይ ያዳላል ይላሉ፡፡ የቅልጥፍናና የፈጠራ አመለካከት ከእሱ በጣም የራቀ ነው፡፡

በእርግጥ የፈጠራና የኢንትርፕራነር ተሰጥኦ ያለቸው አመራሮችና ሠራተኞች ከፍተኛ ደመወዝ ወደሚከፈልበት ይሄዳሉ፡፡ ወይም የግል ሥራ የመፍጠር አቅም ስላለቸው በመንግሥት ተቋም ውስጥ እምብዛም ተቀጥረው አይሠሩም፡፡ እንግዲህ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት መገለጫው የሚመጣው እዚህ ላይ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ያሉት ግን ያልሠሩትን ማግኘት ይፈልጋሉ፣ ይመኛሉ፡፡ በተሰማሩበት የሥራ መስክ ምንም ተጨማሪ ነገር ሳይሠሩና ውጤት ሳያስመዘግቡ ተጨማሪ ጥቅም ብቻ ይፈልጋሉ፡፡ በመካከላቸው ጠንካራ ሠራተኛና አመራር ካለ የት ልትደርስ ነው ይላሉ፣ ያሸማቅቃሉ፣ ይፈታተናሉ፣ በሥራው ውጤታማነት ላይ አቃቂር ያወጣሉ፡፡

የትርፍ ሰዓት ሥራ በመሥራት እንኳን ገቢያቸውን ለማሳደግ ፍላጎት የላቸውም፡፡ ለተከፈላቸው በቂ አገልግሎት ሳይሰጡ መንግሥት የደመወዝ ጭማሪ እንዲፈቅድ ያልማሉ፡፡ ሥራ አርፍደው ስለሚመጡ ተገልጋይ ይጉላላል፡፡ ሁሌም የኑሮ ውድነትን እያሰቡ ስለሚሠሩ ወይም አገልግሎት ስለሚሰጡ ሥራን ከልባቸው አይሠሩም፡፡ ግማሽ ሐሰባቸው በቤት ኪራይ ውድነት፣ በልጅ ትምህርት ቤት ክፍያ መጠን ማደግ፣ በቤት ውስጥ ቀለብ ማነስ፣ በትራንስፖርት ችግር ላይ ስለሆነ ለተገልጋዩ ብዙ አያስቡም፣ ደንታም አይሰጡም፡፡ ለተገልጋዮች ተደጋጋሚ ቀጠሮ ይሰጣሉ፡፡ በስብሰባ ላይ መቀመጥንና ጊዜ አሳልፈው መሄድን ይመርጣሉ፣ ሻይ ባይጠጡ እንኳን ሻይ ቤት ወይም መዝናኛ ክበብ ውስጥ መቀመጥን ያዘውትራሉ፡፡ ላይብረሪ ጋዜጣ በማንበብ ጊዜ ያሳልፋሉ፡፡

ከላይ የተገለጹት የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰቦች እያደጉ ስለሚመጡ፣ ተመሳሰይ አስተሳሰብ ካለቸው የሥራ ባልደረቦች ጋር ሲገናኙ የመንግሥትን የልማት እንቅስቃሴ ያንቋሽሻሉ፣ መንግሥትን ያማሉ፡፡ ከሌሎች ሥርዓቶች ጋር እያነፃፀሩ የበፊቱ የተሻለ ነው ይላሉ፡፡ ለምሳሌ የደርግ ወይም የንጉሡ ዘመን እያሉ ያወራሉ፣ ያስወራሉ፡፡ የእከሌ መንግሥት በነበረበት ወቅት ጥሩ ጥቅም አገኝ ነበር አሁን አጣሁ ይላሉ፡፡ አንዱን ብሔር ከሌላው ያስበልጣሉ፡፡ መንግሥት የሚሠራቸው የልማት ሥራዎች ለእሱ አይዋጥላቸውም፡፡ ለእነሱ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ምናቸውም አይደለም፡፡ መንግሥት ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስለመሆኑ ምን ማረጋገጫ አለው ይላሉ፡፡ በመንግሥት ተቋማት እየተተገበረ ያሉ የለውጥ መሣሪያዎች በአግባቡ አልተተገበረም ይላሉ፡፡ በተቋም ውስጥ ለውጥን የሚመሩ ሰዎች አቅም የሌላቸው ናቸው የሚል ወሬ ይነዛሉ፡፡ ግን አማራጭ የለውጥ ትግበራ ሐሳብ ለማቅረብ አቅም የላቸውም፡፡ በከተማ ውስጥ የሕንፃዎች መብዛት የእኔን ሕይወት አይቀይርም እያሉ ያማርራሉ፡፡ መንግሥት ቤታቸው ድረስ ደመወዝ እንዲልክላቸው ይፈልጋሉ፡፡

በተቀራኒ ደግሞ አቅም እያላቸው መንግሥትን የሚያሙት የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብ የሚያራምዱ ሠራተኞችና አመራሮች ተጨማሪ ገቢ ሊያገኙ የሚችልበት መስክ ያስሳሉ፣ ዕቅድ ያወጣሉ፣ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ተግባራዊ ያደርጋሉ፡፡ በዚህም የመንግሥት ንብረት ይዘርፋሉ፡፡ ጥቅም ለማግኘት ሲል አድሎአዊ ሥራዎችን ይሠራሉ፡፡ የማጭበርበር ሥራዎችን ያከናውናሉ፡፡ በተለይም የሚሰጠው አገልግሎት ከተገልጋይ መስተንግዶ ጋር የተያየዘ ከሆነ ጥቅም የሚያገኙባቸውን ሥራዎች አሳደው ይሠራሉ፡፡ እነዚህን በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ ሥራ አይለውጣቸውም፡፡ መንግሥትና ሕዝብን እያቃቀሩ ይኖራሉ፡፡ የመንግሥት መሥሪያ ቤትን በጡረታ ወይም በሞት ካልሆነ በስተቀር አይለቁም፡፡ በዲስፕሊን ተጣርቶ እንዳይበራሩ ሥራቸው በሥውር ነው፡፡ ካልተነቃባቸው ጥቃቅንና ከፍተኛ ሙስናዎችን ይሠራሉ፡፡ ሌቦች ስለሆኑ የመንግሥትን አገልግሎት ማጥላላት፣ ጥላሸት መቀበትና ውሸት ማስወራት ይወዳሉ፡፡ ሰው አቅሙን በማሳደግ ውጤታማ ሥራ ሲሠራ አይዋጥላቸውም፡፡

መንግሥት ይህን በመረዳት በተቋማት የጥልቅ ተሃድሶ እንዲካሄድ አቅጣጫ ሰጥቷል፡፡ የጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ ፕሮግራም መኖሩ በጣም ጥሩ ጅማሮ ነው ሚል አስተያየት አለኝ፡፡ ቢያንስ በተለይም ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች ያሉባቸው ሠራተኞች እንደተነቀባቸው እንዲያወቁት ያደርጋል፡፡ ሌሎች ታታሪና ሥነ ምግባር ያላቸው ሠራተኞች በሆዳቸው ይዞውት የነበረውን ችግርና ቂም በአደባባይ ለመጋለጥ ዕድል አግኝተዋል፡፡ ይህም ሆኖ ግን ችግር ያለባቸው አመራሮችና ሠራተኞች ከሌሎች የሚነሱ ችግሮችን ላለመቀበል በጣም ሲንፈረፈሩ ነበር፡፡

 እኔ ችግር አለብኝ ልታረም የሚል ሰው አለመኖር የሰዎች ባህሪ ቢሆንም፣ አንዳንድ የቀናነት ባህሪ የሚስተዋልባቸው በጣም ጥቂት ሰዎች ጥፋት ባይኖርብኝም ውስንነት አለብኝ ማለታቸው ለእኔ በቂ ነው፡፡ አብዛኛዎቹ ችግሩን ውጫዊ ያደርጉታል፡፡ ወይም ወደ ሌላ አካል እጃቸውን ይቀስራሉ፡፡ ሆኖም ግን የተሃድሶ ፕሮግራም እንደ አሁኑ ለዓመታት ቆይቶ መምጣት የለበትም፡፡ የአንድ ጊዜ ሥራም ሊሆን አይገባም፡፡ በበጀት ዓመት በየስድስት ወራት ሊካሄድ ይገባል፡፡ የመንግሥት ተቋማት ተከታታይነት ያለው የአመለካከት ለውጥ የሚያመጡ ሥልጠናዎችን እንዲሰጡ፣ በመንግሥት በኩል ግልጽ አቅጣጫ ሊቀመጥና ሊተገበር ይገባል፡፡

በአሁኑ ተሃድሶ ቢያንስ ውስንነት አለብኝ ያሉት ቦታቸውን ለሌለ ኃላፊና ሠራተኛ በመልቀቅ ሌላ ሥራ እንዲሠሩ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ መንግሥትም ለዚህ ግልጽ አቅጣጫ ማስቀመጥ አለበት፡፡ አቅም ያላቸውና ታታሪ የሆኑ አመራርና ሠራተኞች ተለይተው እንደገና ምደባ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡ በተለይም ከተገልጋይ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ባለቸውና በተለይም በጣም ትኩረት የሚሰጥባቸው ቦታዎች በየጊዜው ዕድሳት በሚደረግ የኮንትራት ቅጥር ሠራተኞች መያዝ ይኖርባቸዋል፡፡ የኮንትራት ቅጥሩ የዓመት፣ የሁለት ዓመትና ከዚያ በላይ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለሆነም መንግሥት የመልካም አስተዳደር ችግሮች የሚስተዋልባቸው፣ በተለይም የዕለት ተዕለት አገልግሎት መስጫና ከፍተኛ የሀብት እንቅስቃሴ የሚደረግባቸው የሥራ ቦታዎች ላይ፣ በጊዜ ገደብ ዕድሳት በሚደረግበት የኮንትራት ቅጥር ሠራተኞችና ኃላፊዎች አገልግሎት እንዲሰጥ ቢደረግ አሁን እየታየ ያለው የመልካም አስተዳደር ችግር ሊቀረፍ ይችላል፡፡

ዳታኛ የሆነና ችግር ላለበት አመራርና ሠራተኛ የኮንትራት ቅጥር ዕድሳት ላለማድረግ በጣም ዕገዛ ያደርጋል፡፡ ስለሆነም የኮንትራት ቅጥር አመራርና ሠራተኛ ሥራውን ተጠንቅቆ እንዲሠራ፣ የመንግሥት አገልግሎትን በጥንቃቄ እንዲሰጥ አስገዳጅ ሁኔታ ይፈጥራል የሚል አስተያየት አለኝ፡፡ ከዕድሳት ጋር ሠራተኛው ራሱን እንዲያየው ሊያደርግ ስለሚችል፣ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ቢያስብበት መልካም ነው የሚል አስተያየት አለኝ፡፡ አፍሪካን ጨምሮ በብዙ አገሮች ይህ ተግባራዊ እንደሚደረግ አውቃለሁ፡፡ መንግሥት በሚገባ ያስብበት፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡      

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...