ከወባ ነፃ የሆነች አፍሪካን ዕውን ለማድረግ የተቋቋመው የአፍሪካ መሪዎች የወባ መከላከል ጥምረት (አልማ) ኢትዮጵያን ጨምሮ ለስምንት አገሮች ላሳዩት ቁርጠኝነትና ላስመዘገቡት ውጤት የአልማን ሽልማት ሰጠ፡፡
በአፍሪካ ኅብረት 28ኛው የመሪዎች ጉባኤ አጋጣሚ ሽልማቱን የሰጠው ባጭሩ ‹‹አልማ›› የሚባለው ተቋም ዋና ጸሐፊ ጆይ ፑማፊ፣ ኢትዮጵያ የጤና ዘርፏን በማጎልበት የኅብረተሰቡን ጤንነት ለማሻሻል ያሳየችውን ቁርጠኝነት አወድሰዋል፡፡ በተለይ በወባ ወረርሽኝ ላይ ያከናወነችው ጠንካራ ተግባር የሚታይ ለውጥ ማምጣቷንም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡
አልማ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ከኢትዮጵያ ሌላ ቦትስዋና፣ ኬፕቨርዴ፣ ኮሞሮስ፣ ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ፣ ስዋዚላንድና ዑጋንዳ ተሸላሚ ሲሆኑ፣ ቻድ በተለይ ወባን በመከላከል ረገድ ያሳየችው ያመራርነት ሚና አሸልሟታል፡፡
ኢትዮጵያ በሽታውን ለመከላከል፣ የፀረ ወባ ተባይ ኬሚካል የመርጨት፣ አጎበርን በመጠቀምና በሽታውን በዘላቂነት ለማጥፋት ያደረገችው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑ የተወሳ ሲሆን፣ ባደረገችው ጠንካራ የጤና አጠባበቅ ከዓለም አቀፍ ፈንድ ይወጣ የነበረውን 129.8 ሚሊዮን ዶላር ማዳን መቻሏ ተጠቅሷል፡፡
የዓለም የጤና ድርጅት (ዓጤድ) መረጃ እንደሚያሳየው፣ ኢትዮጵያ በወባ በሽታ የሚያዙና በበሽታው የሚሞቱ ሰዎችን ቁጥር እ.ኤ.አ. ከ2010 እስከ 2015 ድረስ 40 በመቶ ቀንሳለች፡፡
በአፍሪካ በወባ በሽታ የሚሞቱት መጠን እ.ኤ.አ. ከ2000 ወዲህ 62 በመቶ ሲቀንስ፣ ከአምስት ዓመት በታች ያሉ ሕፃናት ሞት ደግሞ በ69 በመቶ ቀንሷል፡፡
እ.ኤ.አ. በ2009 የተመሠረተው አልማ፣ የቀድሞው የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ከሰተ ብርሃን አድማሱ በዋና ዳይሬክተርነት ከሚመሩት ከአዲሱ ሮል ባክ ማሌሪያ ተቋም ጋር በቅርበት የሚሠራ መሆኑ ታውቋል፡፡