የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንደ ስትሮክ ላሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ዋነኛ መንስኤ እየሆነ መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት ባለፈው ሳምንት አሳሰበ፡፡ የድርጅቱ መረጃ እንደሚያመለክተው ይህ ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ አገሮች የሚታይ ችግር ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ 23 በመቶ የሚሆኑ ጎልማሶች፤ 81 በመቶ የሚሆኑ ተማሪዎች በቂ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አያደርጉም፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት እ.ኤ.አ. ከ2013 እስከ 2020 ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን የመከላከልና የመቆጣጠር አክሽን ፕላን ደግሞ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል ቀዳሚ ብሎ የሚያስቀምጠው ስትራቴጂ የሰዎችን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መጨመር ነው፡፡ ፕላኑ እንደሚያስቀምጠው የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በአሥር በመቶ መጨመር ከተቻለ እ.ኤ.አ. 2025 ላይ ለዘላቂ የልማት ግቦች ስኬት ትልቅ አስተዋጽኦ ይሆናል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት ለእያንዳንዱ የዕድሜ ክልል ይገባል የሚለውን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መጠን የሚያስቀምጥ ቢሆንም፣ ምንም ዓይነት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ካለማድረግ ማንኛውንም ማድረግ የተሻለ እንደሆነ ያመለክታል፡፡ ሰዎች ከትንንሽ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች ጀምረው ቀስ በቀስ እንቅስቃሴውን የዕለት ተዕለት ልምድ ቢያደርጉ እንዲህ እንዲህ እያሉ ጊዜውን፣ ድግግሞሹን አይነቱም እየጨመሩ እንዲሄዱ ይመክራል፡፡
ሰዎች የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በሚገባ ያደርጉ ዘንድ ማኅበረሰቦችና አገሮች በቂ የአካል ብቃት ማዘውተሪያ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት አስፈላጊውን ዕርምጃ እንዲወስዱ ይጠበቃል፡፡ ቢሆንም ግን እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በተለይም የከተማ መስፋፋትና የከተሜነት የአኗኗር ዘዬ ይበልጥ እየተስተዋለ ባለበት ሁኔታ ሰዎች በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ሊያደርጉ የሚችሉባቸው ዕድሎች እየጠበቡ እንደሆነ በተለያየ መንገድ ይስተዋላል፡፡ በቂ የስፖርት ማዘውተሪያዎችና የአረንጓዴ አፀዶች አለመኖር ችግር በተደጋጋሚ ይጠቀሳል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰዎችን ለሞት ከሚዳርጉ አሥር ነገሮች የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ አንዱ ነው፡፡ በቂ የአካል በቃት እንቅስቃሴ የሚያደርጉ፤ ቢያንስ በሳምንት ለ150 ደቂቃዎች መካከለኛ ሊባል የሚችል የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ከሚያደርጉ ለህልፈት የመዳረግ ዕድላቸው በ30 በመቶ የጨመረ ነው፡፡ መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ለልብ ችግር፣ ለስኳር፣ ለጡትና የአንጀት ካንሰርና ለመሳሰሉት የመጋለጥ ዕድልን ይቀንሳል፡፡ ለስትሮክ፣ ለደም ግፊትና ለድብርት የሚኖርን ተጋላጭነትም ይቀንሳል፡፡ የሰውነት ክብደትን ለመቆጣጠርም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ወሳኝ መሆኑ ይታወቃል፡፡