ኢትዮጵያ በተለያዩ አራት የዱር እንስሳት ጥበቃ ቦታዎች ፓርኮች ላይ ልዩ ልዩ የልማት ሥራዎችን ለማከናወን እንዲያስችላት ለቀረጸችው የሰባት ዓመት ፕሮጀክት 7.3 ሚሊዮን ዶላር በዓለም ባንክ ቡድን መጽደቁን የኢትዮጵያ የዱር እንስሳትና ልማት ባለሥልጣን (ኢዱልጥባ) አስታወቀ፡፡
የባለሥልጣኑን የግማሽ የበጀት ዓመት ዋና ዋና ተግባራት ክንውን አስመልክቶ ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ዳውድ ሙሜ እንደገለጹት፣ የዓለም ባንክ ይህንኑ ገንዘብ ሊያጸድቀው የቻለው ፕሮጀክቱ በተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) ግሎባል ዋይልድ ላይፍ ፕሮግራም ቀርቦ ተቀባይነት ካገኘ በኋላ ነው፡፡
ለፕሮጀክቱ በተገኘው ገንዘብ በባቢሌ፣ ቃፍታ ሽራሮ፣ ጉራይሌና ያንጉዳረማ የተባሉት የዱር እንስሳት የጥበቃ ቦታዎችን መልሶ የማበልጸግ፣ እንዲሁም በዱር እንስሳትና ውጤቶቻቸው ላይ የሚፈጸመውን ሕገወጥ ንግድ የመቆጣጠርና በተጠቀሱት ተግባራት ላይ የየአካባቢው ማኅበረሰብ እንዲሳተፉ የማድረግ ሥራ ይከናወንበታል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በዚህ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ሕገወጥ አደን ሙሉ ለሙሉ በቁጥጥር ሥር ሲውል፣ የሕገወጥ ዝውውርና የንግድ እንቅስቃሴ ደግሞ የመቀነስ አዝማሚያ ማሳየቱን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
በጥበቃ ክልል ውስጥ ሲፈጸም የነበረው አደን ሙሉ ለሙሉ በቁጥጥር ሥር ሊውል የቻለው በጥበቃው ላይ የተሰማሩ ታጣቂ እስካውቶች በየአቅራቢያቸው ካሉት የማዘዣ ጣቢያዎች (ኮማንድ ፖስት) ጋር ተቀናጅተው በመንቀሳቀሳቸው ነው፡፡ ከጥበቃ ክልል ውጭ የሚካሄደው የዱር እንስሳትና ውጤቶቻቸው ሕገወጥ ዝውውር ወይም ንግድ ቀንሶ ሊታይ የበቃው ኤርፖርቶችን ጨምሮ በአራቱም ማዕዘን በሚገኙ 11 መግቢያና መውጪያ በሮች ላይ ለተመደቡ የፖሊስና የመከላከያ ሠራዊት አባላት፣ ለገቢዎችና ጉምሩክ ሠራተኞች፣ ለመረጃና ደኅንነት ባለሙያዎች በጥበቃው ዙሪያ ያተኮረ ሥልጠና ስለተሰጣቸው ነው፡፡
ከዚህም ሌላ የግንዛቤ ማስጨበጫ በራሪዎችና መጻሕፍት በየቦታው ተደራሽ መደረጉ የዱር እንስሳትን በተመለከተ ባለሥልጣኑ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ተፈራርሞ በሞባይል ስልክ አጭር መልዕክት እንዲተላለፍ፣ እንዲሁም በእንግሊዝኛ፣ በአማርኛ፣ በኦሮምኛና በትግርኛ ፖስተሮችና መጽሔቶች ታትመው በየአካባቢው እንዲሰራጩ መደረጉ ለሕገወጥ ዝውውሩ መቀነስ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡
በየዓመቱ ከ300 በላይ የሚሆኑ የአቦሸማኔ ግልገሎች ከምሥራቅ ኢትዮጵያ በሕገወጥ መንገድ ወደ የመንና መካከለኛው ምሥራቅ አገሮች እንደሚጓጓዙ በጥናት መረጋገጡን ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመው፣ በዚህ ዙሪያ የሚደረገው ቁጥጥርና ክትትል እየተጠናከረ በመምጣቱ የተነሳ በተጠቀሰው በጀት ዓመት ከፍ ብሎ ወደተጠቆሙት አገሮች በሕገወጥ መንገድ ሊጓጓዙ የተዘጋጁ ስድስት የአቦሸማኔ ግልገሎች ቶጎጫሊ ውስጥ መያዛቸውን አስረድተዋል፡፡