ሰላም! ሰላም! ‹ከአሜሪካና ከሞት የሚቀር የለም› ብሎ ነገር ውኃ ሊበላው ነው አሉ ስል፣ “ውኃ ምን አደረገህ? ትራምፕ ሊበሉት ነው አትልም?” ያሉኝ ባሻዬ ናቸው። ደግሞ ብለን ብለን ሰውዬውን የምሳሌያዊ አነጋገር ማስታወሻ እናድርጋቸው? ጉድ እኮ ነው እናንተ። መቼስ አገርን መውደድ፣ አገርን በሙሉ ሐሳብና ኃይል ማገልገልን የመሰለ ነገር ያለ አይመስለኝም። ግን ግርም የሚለኝ በ21ኛው ክፍለ ዘመን አገር አጥሮ፣ አስሮ፣ አሳስሮ በማስቀመጥ አገሬን ላገለግል ነው የሚሉ ትራምፕ ነክ ነፍሶች መኖራቸው ነው። ያውም በአሜሪካ ምድር! ይልቅ አሁን እሱን እንተወውና ወዲህ እንጫወት። ወዲህ ወደ እኛው አገር ምን መጥቷል መሰላችሁ? የትራምፕ ልዩ የፀጉር ቁርጥ። እውነቴን እኮ ነው። ጥሎብን እኛ ደግሞ ቁርጥና ቆረጣ እንወድ የለ? በቀደም ማንጠግቦሽ፣ ‹‹ኧረ ይኼን ፂምና ፀጉር ከርከም ከርከም አስደርገው. . .›› ብላ ብትቆጣኝ ቃሏን ሰምቼ ወደ ፀጉር ቤት ገሰገስኩ። የሚስታችውን ቃል ከመስማት በሰይፍ መቀላት የሚመርጡ ሰዎች እየበዙ መምጣታቸውን ታዝቢያለሁ። ትራምፕን ይጣልባቸው እንጂ ሌላ ምንም ማለት የምችል አይመስለኝም።
የምር ግን አሁን አቶ ትራምፕ ደርሰው ብድግ ብለው ‹ወደ አሜሪካ ለመግባት ቪዛ ማግኘት የሚቻለው እያንዳንዱ ባል በተለይ (የአፍሪካ ባሎችን ይመለከታል) ለሚስቱ በሚያሳየው አክብሮትና እንክብካቤ ነጥብ አጠራቅሞ ሲያበቃ ነው› ቢሉ አስባችሁታል? ለምን ይሆን ግን ዳንሱ፣ ጭፈራውና ዝላዩ ሁሉ ስፖንሰር ሲደረግ እነ መከባበር፣ መዋደድና መደማመጥ የሚረሱት? ለነገሩ እግረ መንገዴን ካነሳሁት አይቀር ነው ያጫወትኳችሁ። ታዲያ ፀጉር ቆራጩ ምን ቢለኝ ጥሩ ነው፣ ‹‹ጋሽ አንበርብር አዲስ ቁርጥ ጀምረናል፡፡ ለምን አይሞክሩትም?›› እኔ ደግሞ በስተርጅና ፋሽን እያልኩ፣ ‹‹እኮ ምን ይባላል?›› ስለው ‹‹ትራምፒዝም!›› አይለኝ መሰላችሁ። በአስተሳሰባቸው ስንገሸገሽ ደግሞ በፀጉራቸው ሊያጠምቁን መጡ? ምኞት አይከለከልም ነዋ ጨዋታው!
መቼም ስለምኞት አንስቼላችሁ እንዲሁ ማለፍ ይከብደኛል። ያው በእኛ ጊዜ “ማሙሽ ወደፊት ምን መሆን ትፈልጋለህ?” በማለት አቅፎ የማይጠይቀን አልነበረም። የአሁኖቹ እንኳን ‘ስማርት’ ናቸው። ያውስ እንኳን ሰው ስልኩ ‘ስማርት’ በሆነበት ጊዜ? ምን ነካችሁ። አንዱ ለምሳሌ፣ “ስታድግ ምን መሆን ትፈልጋለህ?” ስለው ኮራ ጀነን ብሎ፣ “አሜሪካዊ!” ብሎኛል። “እንዴ! አሜሪካዊ መሆን እኮ መክሊትን ማግኘት ማለት አይደለም፤” ብለው በሆዴ ‘ትራምፕ ያልሰሙት ጉድ እያልኩ፣ “የለም አትዮጵያዊነት ነዋ፤” ብሎ የወጣልኝ ሞኝ አድርጎኝ አረፈው። የዘንድሮን ነገር እንዲሁ በሆድ ይፍጀው ካላለፍነው አቃጥሎ ሊጨርሰን ነው። ስለቀደመው ምንም ያለማወቅ የልጅነት ጊዜ እንቀጥል።
እና እንደነገርኳችሁ በየሄድንበት ሰው ሆነን ተፈጥረን ሰው አድርገው ላይሠሩን ሙያተኛና የሆዳችን ባሪያ ሆነን ለምንቀረው፣ “ወደፊት ምን መሆን ነው የምትፈልጉት?” ስንባል የምንመልሳቸው መለሶች ከምናችንም ጋር የማይዛመዱ ነበሩ። አንድ ወዳጄ፣ ‹‹እግዜር ይችን አገር ፈጣሪ እንደሚወዳት ያወቅኩት እንደ ምኞታችን ስላላደረገን ነው፤›› አለኝ። “እንዴት?” ስለው፣ “እስኪ አስበው ከግማሽ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ እኮ ክፉና ደግ ሳይለው እንደቀባጠረው ቢሆን የሽቦ ‘ቦይንግ’ አብራሪና ራሱን በራሱ መርፌ ወጊ ሆኖ ቀርቶ ነበር። ‘ፓይለት፣ ዶክተር’ ካልን መመለሻ ነበረን እንዴ?” ሲል ፈገግ አሰኝቶኛል። አክሎ፣ “ለነገሩ ምንም ማድረግ አትችልም። ቤትህ ለመጣ እንግዳ ከሁለቱ ውጪ እሆናለሁ ብለህ ወይ ፓይለት ወይ ሐኪም ካላልክ ማታ ‘ማንን ልታሰድብ ነው?’ ተብለህ በቀኝና በግራ የሚወርድብህ የኩርኩም መድፍ አይጣል ነው፤” ቢለኝ የአንድ አብሮ አደጋችን ገጠመኝ ትዝ አለኝ። ማደግ የሚሉት መዓት መጥቶ በትዝታ እንለቅ ግን?
ጓደኛችን ምን አደረገ መሰላችሁ? የእናቱ የቅርብ ዘመድ ከውጭ ይመጣል። ጉብላሊት የወደቀ ‘ዩፎ’ እንደምናይ እንግዳውን ከበን ባህር የተሻገረ ዘመድ ባለው ጓደኛችን ቀንተን ተኮልኩለናል። የልጅነት ቁጭታችን ይሆን ‘ኢሚግሬሽኑን’ የሚያጨናንቀው? አይታወቅም እኮ! ኋላ እንግዳው በልቶ ጠጥቶ ከቤት ሲሸኝ ጓደኛችንን ከመሀል ነጥሎ ጠርቶት፣ “ማስቲካ ከመስጠቴ በፊት ወደፊት ምን መሆን እንደምትፈልግ ንገረኝ?” አለው። ከእኛ ከእኩዮቹ ጋር ተቧድኖ ሌባና ፖሊስ እንደ መጫወት መስሎት ሲቅለበለብ “ፖሊስ!” አለ። እናት አጠሩ። “ምን? አንተ! እኔ ብቻዬን እየተንገላታሁ የማሳድግህ ተምረህ ‘ፖሊስ’ እንድትሆን ነው?” ሲሉት እንግዳው ፊት ስለቆመ ብቻ በቁጣ የተቀየረለት ኩርኩም ማታ በተኛበት እንዳይመጣ አጉል ብልጥ ሊሆን “እሺ ሌባ!” ብሎ እንግዳውንም እናቱንም በሳቅ ገደላቸው። ሳይገባን አብረን ሳቅን። አይ ልጅነት!
ምን እየተባባልን ነበር? አዎ! አንድ ነገር አስባችሁ ስትሮጡ ያላሰባችሁት ነገር በዚህም በዚያም መሰናክል ሆኖ ከተፍ ይላል። ይኼው ቢቢሲና አልጄዚራ እንደሚያሳዩን ባህሩን ተሻግረው አውሮፕላኑ በሰላም አርፎም በያዙት ፓስፖርት ምክንያት ወደ አገራችን መግባት አትችሉም ሲባል ልብና ተስፋ እኩል ክስክስ ሲሉ እያየን ነው። ኧረ ዘንድሮ የማናየው የለም። ያልታመመው ይታመማል። ማርገዟን ሳትሰሙ ጠግባ መስሏችሁ ሆዶ ገፍቶ ያያችኋት ቆንጆ፣ መንታ ዱብ ዱብ አድርጋ ፌስቡክ ላይ መለጠፏን አንዱ ወሬ አነፍናፊ ሳትጠይቁት ይነገራችኋል። እንኳን ለሞት የሚያደርስ ደዌ ሊያውቀው ሲያስነጥሰው አይታችሁ ‘ይማርህ!’ ብላችሁት የማታውቁት ወዳጅ ‘አረፈ!’ ይባልና ድንኳን ተከላ ላይ በካስማ ቸካይነት እንድትተባበሩ ትጠራላችሁ። ብቻ ምን አለፋችሁ ባሰባችሁት አትዋሉ ከተባላችሁ ለቀማሪው ቀመሩ ‘ሲምፕል’ ነው። (እንግሊዝኛዬ እንዴት ነው? እየተሻሻለ ነው?) ደስታንም ሐዘንንም በጋራ የመካፈል እንቁ ባህላችን ቀንደኛ ደጋፊ ብሆንም (ምነው ቀንደኛ ደጋፊ ስል ተሸማቀቃችሁብኝ?) ባህል እኮ ተቃዋሚ ፓርቲ አይደለም ሥራ ሲያስፈታኝ አልወድም።
ስለዚህ ያሉብኝን ማኅበራዊ ግዴታዎች እየሸዋወድኩ አንድ ቪላ ላከራይ ብዙ ዋተትኩ። የዋተትኩት ተከራይ አጥቶ ወይ ጠፍቶ እንዳይመስላችሁ። እኮ እንዴት ተብሎ? ይልቅ ወገኔ እንኳን ቪላ ኮንዶሚኒየም ቤትም ተከራይቶ መኖር እንዴት እንዳጎበጠው ስለማውቅ፣ ከሐበሻ ተከራይ ይልቅ የውጭ ዜጋ ልፈልግ ብዬ ነው። በለስ ቀንቶኝ አንድ ቻይና አገኘሁ። ቤቱን ልየው ብሎኝ ወስጄ ሳሳየው ታዲያ፣ “ጥሩ ነው! ይበቃል! ይሆናል!” ሳይል ዝም ብሎ በሌባ ጣቱ ሐሳባዊ መስመር እያሰመረ ይቆጥራል። “ቤቱ ሙሉውን ነው የሚከራየው በካሬ አይደለም፤” አልኩት በአስተርጓሚ። እሱም፣ “አውቃለሁ መኝታ ክፍሎቹን ሳይጨምር ሳሎኑ ስንት ፍራሽ ይወጣዋል የሚለውን እየቆጠርኩ ነው፤” አለኝ። ‘የምን ፍራሽ?’ ብዬ አልጠየቅኩም። ብቻ ቆጥሮ ሲጨርስ የሸሪኮቹን ብዛት ለማወቅ “ስንት?” አልኩት። “ሳታጠጋጋው 30!” አይለኝ መሰላችሁ? ትራምፕ እኮ ወደው አይደለም ስትሉ ሰማሁ ልበል?!
በሉ እንሰነባበት። ‘ኮሚሽን’ በተቀበልኩ አመሻሽ ባሻዬ ደወሉልኝ። የማርያም አራስ ሊጠይቁ ያለ እኔ አልሆንላቸው ብሎ ነበር የደወሉልኝ። ተያይዘን አራስ ጥየቃ። ሳያት የት እንደማውቃት ጠፋኝ እንጂ መልኳ አዲስ አልሆነብኝም። ባሻዬን ጠጋ ብዬ፣ “መቼ አገባች? አልሰማሁም ማግባቷን፤” አልኳቸው። ባሻዬ ደንግጠው፣ “ኧረ እባክህ ስለፈጠረህ ዝም በል። እኔ የወለደ እንጠይቅ አልኩህ እንጂ ላገባና ላላገባ እንመስክር ብዬ አመጣሁህ?” ብለው ሲቆጡኝ ነገሩ ገባኝ። የገባኝ መስዬ ባሻዬን ለመካስ፣ “እንዴት ነበር ታዲያ ምጡ? ጠናብሽ?” ብዬ መጠየቅ። አፌ አያርፍም እኮ አንዳንዴ። “ማማጥ ድሮ ቀረ። ዕድሜ ለቀዶ ጥገና፤” አለችኛ። ባሻዬን ቀና ብዬ አላየሁም። ግድ ካልሆነ ባሻዬ በምንም ተዓምር በቀዶ ጥገና መገላገልን አይደግፉም። ስንንቀለቀል መስማት የማይፈልጉትን ስላሰማኋቸው እንደሚቆጡኝ ገብቶኛል። ምኔ ሞኝ ነው ታዲያ? አውቄ ስልክ ተደወለለኝ አልኩና ‘ማርያም ጭንሽን ታሙቀው’ ብዬ ላጥ። ወዲያው ለልጃቸው ደወልኩለት።
የተለመደችዋ ግሮሰሪ እንድንገናኝ ተነጋገርን። ስንገናኝ የሆነውን ለልጃቸው ነገርኩት። እንደ ወትሮው በአባቱ ወግ አጥባቂነት ዘና እያለ ያጫውተኛል ስል ኮስተር ብሎ፣ “በቃ አምጦ መውለድ ተረት ሊሆን ተቃረበ ማለት ነው?” አለኝ። “አቤት?” ስለው ባሻዬ የመጡ መስሎኝ ክው ብዬ፣ “አሳሳቢ የሆነ እክል ሊገጠም እስካልቻለ ድረስ ሰው ለምን አምጦ መውለድ እንደሚፈራ አልገባኝም። በምጥ የሚወለድ ልጅ፣ የሚገኝ ፍሬ እኮ ጤናማነቱ ጥንካሬው ሌላ ነው። እህ በአቋራጭ የመክበር፣ በአቋራጭ የመደለብ፣ በአቋራጭ የመንገሥ የዘመኑ አካሄድ ስንቱን ጤናማ ተፈጥሯዊ በረከት አበላሸው መሰለህ? ሕመም ፈርተን፣ ላብ ተፀይፈን፣ ሥራ ንቀን፣ ጎንበስ ማለት ጠልተን፣ በአጠቃላይ ምጥ ገሸሽ ብለን ያዋጣናል? ማቋራረጥና ዝላይ ዋጋ እንዳያስከፍሉን ፍራ፤” እያለ ሲያስፈራራኝ አመሸሁ። እንደ አገርም እንደ ግለሰብም ምነው ባሰብንበት መዋልና ማደር አቃተን አያሰኝም? መልካም ሰንበት!