Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየሚኒስትሮች ምክር ቤት የፀረ ዶፒንግ ሕጉን ሊያፀድቅ ነው

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የፀረ ዶፒንግ ሕጉን ሊያፀድቅ ነው

ቀን:

–   አይኦሲ ‹‹ንፁህ አትሌቶችን እንጠብቅ›› የሚል አዲስ ዘመቻ ጀመረ

 በአገር ደረጃ በቅርቡ የተቋቋመው ብሔራዊ የፀረ ዶፒንግ ጽሕፈት ቤት ሕግ በየካቲት ወር ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ እንደሚፀድቅ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ በሌላ በኩል ኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ ‹‹ንፁህ አትሌቶችን እንጠብቅ›› የሚል አዲስ የመከላከል ዘመቻ መጀመሩ አስታውቋል፡፡

      በለንደን ኦሊምፒክ 3,000 ሜትር መሰናክል የነሐስ ሜዳሊያ ያገኘችው ሶፊያ አሰፋ፣ ሜዳሊያዋ ወደ ብር ከፍ ማለቱ በተበሰረበት ሥነ ሥርዓት የታደሙት የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋዬ ይገዙ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ የተቋቋመው ብሔራዊ የፀረ ዶፒንግ ጽሕፈት ቤት ሕግ በዚህ ወር ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ ይፀድቃል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ እየታየ ያለው አበረታች ቅመሞችን በመጠቀም በተለያዩ ውድድሮች ያላግባብ ውጤት የማስመዝገብ ችግር የኢትዮጵያም ሥጋት እየሆነ መምጣቱ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

እንደ ሚኒስትር ዴኤታው፣ ሚኒስቴሩ ከአገር አቀፍ ማኅበራት ጋር በመቀናጀት በመላ አገሪቱ በየእርከኑ ሰፊ የሆነ የፀረ ዶፒንግ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ያለው ጅምር ተጠናክሮ እንዲቀጥል የአገሪቱ ጽኑ እምነት ነው፡፡ ይህንኑ የሚያጠናክረው ሕግ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ እንዲፀድቅ ሲደረግም ኢትዮጵያ ለጉዳዩ የሰጠችው ትኩረት ምን ያህል ጠንካራ እንደሆነ ማሳያ መሆኑን ጭምር ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ ተስፋዬ አገላለጽ፣ በትክክለኛው መንገድ የሚመዘገብ ውጤት ዘመን የማይሽረውና የምንጊዜም ድል ሆኖ እየተዘከረ ይኖራል፡፡ ከዚህ ውጪ በአትሌቶችና በሌሎች አካላት (ማናጀሮች፣ አሠልጣኞችና ሐኪሞች) ፍላጎት መነሻ በአበረታች ቅመሞች ድጋፍ የሚመዘገብ ውጤት አትሌቱን፣ ስፖርቱንና በአጠቃላይ አገርና ሕዝብ የሚያዋርድ ተግባር መሆኑን መረዳት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡

ዓለም አቀፍ የፀረ ዶፒንግ ኤጀንሲ (ዋዳ)፣ ኢትዮጵያ የዚህ ችግር ሰለባ ከሆኑ አምስት አገሮች አንዷ መሆኗን ይፋ ካደረገ ውሎ አድሯል፡፡ ከዚህ አኳያ እየተደረገ ያለው ቁጥጥርና ክትትል እንዴት እየሄደ ነው? ለሚለው የሪፖርተር ጥያቄ ሚኒስትር ዴኤታው፣ ዋዳ ኢትዮጵያን ከአምስቱ ተጠርጣሪ አገሮች አንዷ አድርጎ የወሰደበት ዋናው ምክንያት፣ አገሪቱ ችግሩን ለመከላከል እያደረገች ካለው አገራዊ ንቅናቄ፣ ተቋማዊ አደረጃጀትና ካላት የሰው ኃይል ሥምሪት ሁኔታ በመነሳት እንጂ አትሌቶቿ ያን ያህል የችግሩ ተጠቂ ሆነው እንዳልሆነ ነው ያስረዱት፡፡

ሥጋቱ እንዳለ እርግጥ ነው ሲሉ ያከሉት አቶ ተስፋዬ፣ ለዚህም ዋዳ ከሪዮ ኦሊምፒክ ዝግጅት ቀደም ብሎ ለኢትዮጵያ ያስተላለፈው መመርያ ነበር፡፡ መንግሥት በአገር አቀፍ ደረጃ ብሔራዊ የፀረ ዶፒንግ ጽሕፈት ቤት ለማቋቋም የቻለው ያንን መነሻ አድርጎ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ዋዳ በሚሰጠው አቅጣጫና መመርያ መሠረት የአትሌቶች ደምና ሸንት ናሙናዎች በሚፈለገው መጠንና ደረጃ ወደ ተመረጠው ቦታ ለምርመራ እየተላከና ውጤቱም እየመጣ አስፈላጊው ዕርምጃ እየተወሰደ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡ ይህ የኢትዮጵያ እንቅስቃሴና ጅምር በዓለም አቀፍ ተቋም እየተገመገመ ይሁንታን እያገኘ መምጣቱም በአቶ ተስፋዬ ተገልጿል፡፡

በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እነዚህ አበረታች ቅመሞችና መድኃኒቶች ወደ ኢትዮጵያ በገፍ እንደሚገቡ፣ ለዚህ ደግሞ በማናጀር፣ በአሠልጣኝና በሐኪም ስም ወደ አገሪቱ የሚገቡ ሰዎች ላይ የሚደረገው ቁጥጥርና ክትትል የላላ መሆኑ እንደሆነ የሚናገሩ አሉ፡፡ የተደረጉ የዳሰሳ ጥናቶችም በዚህ የላላ ቁጥጥርና ክትትል ክፍተት በመጠቀም አትሌቶች በሚያዘወትሩባቸው የልምምድ ሥፍራዎች ሳይቀር ሻንጣ ሙሉ አበረታች መድኃኒቶችና ቅመሞች ሳይቀር በገሃድ የሚታዩበት ሁኔታ መኖሩ ተረጋግጧል፡፡ ሚኒስትር ዴኤታው ለዚህ፣ መግቢያና መውጫ ድንበሮችን በሚመለከት መሥሪያ ቤታቸው ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው አካል ጋር ተነጋግሮ አስፈላጊውን ቁጥጥርና ክትትል እንደሚያደረግና እስካሁንም እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዋናነት ግን በዙሪያው የሚንቀሳቀሱ አትሌቶች፣ ማናጀሮች (የውጭም የአገር ውስጥም) አሠልጣኞችና ለሌሎችም አካላት ግንዛቤ ማስጨበጥ የቅድሚያ ሥራ መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡

‹‹በአንድ ውድድርና ለአንድ ሰው ክብር ተብሎ ሕዝብና አገርን ብሎም ስፖርቱን ሊጎዳ ከሚችል ርካሽ ነገር መቆጠብ ለድርድር ሊቀርብ የሚገባ ጉዳይ አይደለም፤›› በማለት ጠንከር ያለ አስተያየት የሰጡት አቶ ተስፋዬ፣ ይህን የስፖርቱ ባለድርሻ አካለት ሊወስዱትና ሊማሩበት እንደሚገባ ነው ያስረዱት፡፡

በሌላ በኩል የኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ (አይኦሲ)፣ ‹‹ንፁህ አትሌቶችን እንጠብቅ›› የሚል አዲስ የመከላከል ዘመቻ መጀመሩ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ይፋ አድርጓል፡፡

እንደ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ከሆነ፣ አይኦሲ በጃፓን ቶኪዮ ይዘጋጃል ተብሎ በሚጠበቀው የ2020 ኦሊምፒክ ድረስ ተቋሙ 40 ነጥቦች ላይ ትኩረት አድርጎ ይሠራል፡፡ ከነዚህ ነጥቦች ውስጥ በድርጊቱ ወንጀለኞችን ከማሳደድ ይልቅ ‹‹ንፁህ አትሌቶችን እንጠብቅ፤›› ለሚለው መርሁ 20 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በመመደብ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ ይፋ አድርጓል፡፡

ተቋሙ ተፈጥሯዊ ባልሆነ መንገድ የተከለከሉ ቅመሞችን ተጠቅመው ውጤት የሚያስመዘግቡ አትሌቶችን ሜዳሊያ በማስመለስ፣ ክብሩንና ሜዳሊያውን ለንፁህ አትሌቶች በመስጠት ዕርምጃ መውሰድ ከጀመረ ዓመታት ተቆጥሯል፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት በለንደን በተከናወነው 30ኛው ኦሊምፒያድ 3,000 ሜትር መሰናክል ሩሲያን ወክላ የተወዳደረችው ዮሊያ ካራፖቫ ያስመዘገበችው ውጤት ተፈጥሯዊ ባልሆነ መንገድ ‹‹ስትሪዮድ ትሪናቦል›› የተሰኘ ንጥረ ነገር ተጠቅማ መሆኑን በማጋለጥ ክብሩንና ሜዳሊያውን ለተከታዮቿ አትሌቶች በቅደም ተከል አስረክቧል፡፡

ከ2020 አዲስ የመከላከል ስትራቴጂክ ዕቅድ ጋር ተያይዞ የወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ አይኦሲ በቤጂንግ 2008 እና በለንደን 2012 ኦሊምፒኮች በተለያየ የውድድር ዘርፍ በርካታ አትሌቶች ላይ የደምና የሽንት ናሙና ወስዶ መርምሯል፡፡

በወቅቱ በነበረው የምርመራ ቴክኖሎጂ ሳይገኝ የቀረው የሩሲያዊቷ የምርመራ ውጤት፣ አይኦሲ እንደገና ሩሲያዊቷን ጨምሮ የ1,000 አትሌቶች የደምና ሽንት ምርመራ አድርጎ የ98 አትሌቶች ውጤት ፖዘቲቭ ሆኖ መገኘቱን ገልጿል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...