Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

ለዚህ ገጠመኝ መጻፍ ምክንያት የሆነው ረቡዕ ጥር 24 ቀን 2009 ዓ.ም. በሪፖርተር ጋዜጣ የወጣ ዜና ነው፡፡ ‹‹የአራት አግሮ ፕሮሰሲንግ ፓርኮች ግንባታ በ1.5 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ሊጀመር ነው›› የሚለው ዜና በውስጡ በርካታ አስገራሚ ጉዳዮችን ይዟል፡፡ እነዚህ አስገራሚ ጉዳዮች ትኩረቴን የሳቡት ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በምግብ ራሱን ችሎ ለሌሎች መትረፍ ሲገባው አሁንም የውጭ ዕርዳታ ይጠብቃል፡፡ ሸማቹ ሕዝብ በምግብ ዋጋ ንረት ሳቢያ ለከፍተኛ ችግር ተዳርጓል፡፡ ይህቺ ሳታጣ ያጣች አገር ውስጥ ተቀምጠን ጥሩ ምግብ እየናፈቀን የምንኖር ዜጎች እጅግ በጣም ብዙ ነን፡፡ የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችና ድርጅቶች ባለመኖራቸው ምክንያት ተመጣጣኝ ምግቦች ማግኘት ብርቅ ነው፡፡ አሉ የሚባሉት ጥቂት የምግብ አምራቾች ከውስን ሱፐር ማርኬቶች መደርደሪያ ማለፍ የማይችሉ ናቸው፡፡ በአንድ ጊዜ የአራት የአግሮ ፕሮሰሲንግ ፓርኮች ግንባታ ሊጀመር ነው ሲባል የራሴን ገጠመኝ ማውሳት ፈለግኩ፡፡

ከዓመታት በፊት ታንዛኒያ ዳሬሰላም ከተማ ለሁለት ሳምንታት የሚያቆየኝ ሥራ ነበረኝ፡፡ የህንድ ውቅያኖስ ዳርቻ ላይ የተመሠረተችው ዳሬሰላም ጎዳናዎች ላይ በስፋት የሚታዩ አነስተኛ የመመገቢያ ኪዮስኮች በርካሽ የሚያቀርቧቸው የዓሳ ምግቦች መቼም አይረሱኝም፡፡ በምሳ ሰዓት የዓሳ ጥብስ፣ ሾርባ፣ ጉላሽና የተለያዩ ምግቦች ከአትክልትና ከሩዝ ጋር እየበሉ በውኃ ወይም በለስላሳ መጠጦች ማወራረድ የተለመደ ነው፡፡ ምሽት ላይ በተለይ አፍሪካና በተባለው ጎዳና ኪሊማንጃሮ፣ ሳፋሪና ሴረንጌቲ የተባሉ ቢራዎችን እያጣጣሙ ጣት የሚያስቆረጥም የዶሮ ወይም የበግ ወይም የበሬ አሮስቶ፣ ወይም በተለያዩ አቀራረቦች የተዘጋጁ የሥጋ ምግቦችን ማጣጣም የዘወትር የዳሬሰላማውያንና የእንግዶች ተግባር ነው፡፡ ያውም ለማመን በሚያስቸግር ርካሽ ዋጋ፡፡ እ.ኤ.አ. በ2010 ይመስለኛል ዳሬሰላም ውስጥ አንድ ኪሎ ዓሳ ገበያ ውስጥ ግፋ ቢል በእኛ ከ25 ብር አይበልጥም ነበር፡፡ የበሬ ሥጋ ዋጋ ደግሞ 30 ብር አካባቢ ነበር፡፡ ለእኛ ግን ብርቅ ነው፡፡

በዓለማችን ካሉ ከተሞች በምርጥነቷ ከአንድ እስከ አሥር ባለው ደረጃ ውስጥ የምትገኘው ኬፕታውን ከተማ ውስጥ ለአሥር ቀናት ያህል ቆይታ ነበረኝ፡፡ የደቡብ አፍሪካ የመጨረሻው ደቡባዊ ጫፍ ላይ የምትገኘው ኬፕታውን በህንድ ውቅያኖስና በአትላንቲክ ውቅያኖስ ግራና ቀኝ የታቀፈች ስትሆን፣ በወይን ምርቷ በጣም ታዋቂ ናት፡፡ እኔን የገረመኝ ግን ከተማው መሀል ላይ የሚገኘው ‘ፒክ ኤንድ ፔይ’ ተብሎ የሚታወቀው ግዙፍ የመገበያያ ማዕከሏ ነው፡፡ ይህ ባለስድስት ፎቅ የሆነው ግዙፍ የግብይት ማዕከል በበርካታ ሸቀጦች የተሞላ ሲሆን፣ ከታች ምድር ቤት የሚጀምረው ሰፊው የምግብ አቅርቦት አዳራሽ ነው ይበልጥ የሚያስደምመው፡፡ ብዛት ካላቸው የአግሮ ፕሮሰሲንግ ፋብሪካዎች የሚቀርቡ የተለያዩ ዓይነት የዶሮ፣ የበግ፣ የበሬ፣ የአሳማ፣ የጥንቸል፣ ወዘተ ሥጋዎች ብዛት ያስደነግጣል፡፡ የዚያኑ ያህል ቅቤ፣ ወተት፣ ዓይብ፣ ቺዝ፣ እንቁላል፣ ወዘተ ብዛታቸውና ዓይነታቸው ያስደምማል፡፡ ዋጋን በተመለከተ አንድ ነገር ብቻ ልበል፡፡ አምስት ኪሎ ቅቤ የያዘ የታሸገ የፕላስቲክ መያዣ ላይ 150 ራንድ ተብሎ ተጽፏል፡፡ አንድ ራንድ በዚያን ጊዜ በእኛ 1.10 ብቻ ነበር፡፡ አስማት አይመስልም?

- Advertisement -

ከጎረቤት ኬንያ አንስቶ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳ፣ ሩዋንዳ፣ ሞዛምቢክ፣ ቦትስዋና፣ ደቡብ አፍሪካ… እያልን ስንጓዝ ዓሳ፣ ዶሮ፣ ሥጋ፣ ወተት፣ እንቁላል፣ ወዘተ ከእኛ አገር የድንች ዋጋ በታች እየተሸጡ ይበላሉ፡፡ በእነዚህ አገሮች በአማካይ የእኛ ደህና በሊታ የሚባሉ አምስት ሰዎች የማይደፍሩትን አንዱ በሚገባ ያጣጥመዋል፡፡ ለምን? ምግብ በአንፃራዊ ሁኔታ ርካሽ ስለሆነ ከልጅነት ጀምሮ በስፋት ተለምዷል፡፡ የእኔን አበላል እያዩ የሳቁብኝን የኬንያ ጓደኞቼን በፍፁም አልረሳቸውም፡፡ በሆዳቸው ‘አገሩ ምግብ ስለሌለ እንዴት መብላት ይችላል?’ የሚሉ ይመስለኝ ነበር፡፡ ልብ በሉ እንግዲህ፡፡ እኛ እጅግ በጣም ለም የሆነ ሰፊ መሬት፣ በአፍሪካ ከፍተኛ የሆነ ውኃ፣ ተስማሚ የሆኑ የተለያዩ የአየር ፀባዮች፣ ለሥራ ዝግጁ የሆኑ በርካታ ሚሊዮን ወጣቶችን ይዘን 5.6 ሚሊዮን ወገናችን አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ይለመንለታል፡፡ ከዚህ በላይ ምን የሚያሳፍርና አንገት የሚያስደፋ ነገር አለ? አንጀታችን የረባ ምግብ ሳያኝ የማይረባ ፖለቲካ ላይ ተጥደን የምንውለው ለምን እንደሆነ አይገባኝም፡፡ ‘ሆድ ሳይጠና ራስ ጉተና’ የተባለው ለዚህ ይሆን?

በሪፖርተር ጋዜጣ ዘገባ ላይ አየር መንገዱ ለበረራ መስተንግዶ ለሚቀርቡ ምግቦችና መጠጦች ዝግጅት ለሚውሉ ጥሬ ዕቃዎችና ተያያዥ ምርቶች ግዥ በዓመት 100 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ያደርጋል ተብሏል፡፡ አስገራሚው ጉዳይ ግን ለዚህ ግዥ ከሚወጣው 100 ሚሊዮን ዶላር 90 በመቶው ወደ ውጭ መኮብለሉ ነው፡፡ የአገር ውስጥ ድርሻ አሥር በመቶ ብቻ ነው፡፡ የበለጠ የሚገርመው አየር መንገዱ ከሚያከናውናቸው 600 ዓይነት ምርቶች ግዥ ከአገር ውስጥ 120 ያህሉን ሲገዛ አቅራቢዎች ደግሞ 55 ድርጅቶች ናቸው፡፡ አያሳዝንም? አትክልትና ፍራፍር፣ ማር፣ ወተት፣ የተለያዩ ዓይነት ጭማቂዎች፣ የከብትና የዶሮ ሥጋና ሌሎች የተለያዩ ምርቶች ከአገር ውስጥ ማቅረብ ባለመቻሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠር የውጭ ምንዛሪ ይባክናል፡፡ ይቅርታ ይደረግልኝና ብዙዎቹ የአገራችን የንግድ ሰዎች ‘ከአየር በአየር’ አስተሳሰብ ወጥተው ዓይናቸውን ቢገልጡ እኮ ይኼ ሁሉ ዶላር ለስንት ቁምነገር ይውል ነበር? ያሳዝናልም፣ ያሳፍራልም፡፡

የአግሮ ፕሮሰሲንግ ፋብሪካዎችና ማደራጃዎች በብዛት ቢኖሩ እኮ ምርት አይባክንም፡፡ የግብይት ሥርዓቱ ካለበት ኋላቀር አሠራር ወጥቶ ዘመናዊ ይሆን ነበር፡፡ ሰው ሠራሽ የዋጋ ግሽበቶች የሚፈጠሩት ገበያውን ጥቂቶች ስለሚቆጣጠሩት ስለሆነ የተበለሻሸው ገበያ ይስተካከላል፡፡ በዓል በመጣ ቁጥር 30 ሺሕ የእርድ ዶሮ አቅርበናል በሚሉ አላጋጭ ኢንቨስተር ተብዬዎች ምትክ በስፋት የሚያመርቱ ይፈጠራሉ፡፡ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የአልማዝ ያህል የሚቆጠሩት ሥጋ፣ ወተት፣ እንቁላል፣ ዓይብና የመሳሰሉት መሠረታዊ የምግብ ፍጆታዎች በጣም በተመጣጠነ ዋጋ ይቀርቡለታል፡፡ የሰው ልጅ በኑሮው ደስተኛ ሳይሆን ሕንፃ ቢገጠገጥ፣ መንገድ ቢገነባ፣ ውድ የሚባሉ መኪኖች በጎዳናው ላይ ቢርመሰመሱና ጥቂቶች ወዛቸው ግጥም ቢል ምንም አይፈይድም፡፡ መጀመሪያ ሕዝቡ የሚፈልገውን አግኝቶ በአገሩ ደስ ይበለው፡፡ (አበበ ሙላቱ፣ ከቄራ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...