Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ይድረስ ለሪፖርተርየሥራ ውጤት ምዘናውን ያላለፈው ብሔራዊ ባንክ

የሥራ ውጤት ምዘናውን ያላለፈው ብሔራዊ ባንክ

ቀን:

ሪፖርተር ጋዜጣ ሙያዊ ብቃቱንና ድርጅታዊ ጥንካሬውን የአንድ ወገን ያውም የመንግሥትን ሐሳብና አመለካከት አብዝቶ ለማጉላት መጠቀሙን አቃወማለሁ፡፡

 እሑድ ጥር 14 ቀን 2009 ዓ.ም. በታተመው ሪፖርተር ጋዜጣ የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ የሰጡት ቃለ ምልልስ ወጥቶ ነበር፡፡ በዚህ ቃለ ምልልስ ላይ በማተኮር ዋናዎቹ ነጥቦቼ ላይ ብቻ አተኩራለሁ፡፡ በመጀመሪያ፣ የባንኮች ቁጥር ገና በወጉ ሃያ እንኳ ሳይደርስ፣ መዋሃድ አለባቸው የሚባለው ነገር አሁን ያሉት ባለአክሲዮኖች ዘርፉን በሞኖፖል እንደተቆጣጠሩት ለማስቀጠልና እስካሁን ካካበቱት የበለጠ ትርፍ እንዲያጋብሱ ለማድረግ ካልሆነ በስተቀር፣ እንደ እኔ ሐሳብ ለአገሪቱ የሚጠቅመው በባንክ ሥራ ዘርፍ ውስጥ ያለውን ውድድርና የነፃ ገበያ አሠራር ማጠናከር ነው፡፡ ገዥው ራሳቸው እንዳሉት፣ በናይጄሪያ ውህደት የተጀመረው የባንኮች ቁጥር ዘጠና አካባቢ ከደረሰ በኋላ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የግል ባንኮች ቁጥር ግን ገና ሃያ አልሞላም፡፡

አቶ ተክለወልድ ኢኮኖሚው ከአሥር በመቶ በላይ አድጓል ብለዋል፡፡  ኢኮኖሚው በዚህ መጠን አደገ ሲሉ ግን ያደገው ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት ነው ወይስ የነፍስ ወከፍ ምርት ወይም የነፍስ ወከፍ ፍጆታ ነው? የጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አካል የሆነው ጠቅላላ ኢንቨስትመንትስ በምን ያህል አድጓል? ይህ የኢኮኖሚ ዕድገት በሕዝቡ የኑሮ መሻሻል ልክ ነው የተንፀባረቀው? ዕድገቱ ወደ ሰፊው ሕዝብ ተዳርሷል ወይስ የጥቂት ሰዎች ኢኮኖሚያዊ ብልፅግና ማሳያ ሆኖ ቀርቷል?

- Advertisement -

ለመሆኑ በዚህ ‹‹ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት›› ሒደት ውስጥ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ የሚመሩት ብሔራዊ ባንክ ሚናው ምን ነበር? እንደሚታወቀው በዓለም ዙሪያ የማዕከላዊ ባንክ በእኛ አገር አጠራር የብሔራዊ ባንክ የሥራ ውጤት የሚመዘንባቸው ሦስት ዓበይት መስፈርቶች አሉ፡፡ እነዚህም የዋጋ ንረትን መቆጣጠር፣ የአገር ውስጥ ገንዘብ (የብር) የውጭ ምንዛሪ ተመን የተረጋጋ እንዲሆን ማድረግና የባንክና በአጠቃላይም የፋይናንስ ዘርፉን ጤናማነት ማረጋገጥ ናቸው፡፡ እንደሚታወቀው ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት የገበያ ዋጋ ሰላሳ እጥፍ ጨምሯል፡፡

የብር የውጭ ምንዛሪ ተመን ያሽቆለቆለው በዘጠና ሁለት በመቶ ነው፡፡ በሌላ በኩል ባለፉት ዓመታት ይፋዊ በሆነ መንገድ ከሥሮ የተዘጋ ባንክ ባይኖርም (እርግጥ ኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ከስሯል እየተባለ ይወራ ነበር)፣ በባንክ አሠራር ረገድ ብዙ ጉድለቶች ታይተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለመንግሥት ያለገደብ ያበድራል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደግሞ በትዕዛዝ ያበድራል፡፡ ዕዳ ይሰርዛል፡፡ እናም፣ ከላይ በተጠቀሱት ሦስት ዓበይት መስፈርቶች መሠረት፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሚያገኘው የሥራ ውጤት መመዘኛ ማርክ በዝቅተኛነቱ የሚገለጽ ነው፡፡

የዋጋ ንረትን መቆጣጠር ብዙም አልተሳካለትም፡፡ በያመቱ የሚታየው የዋጋ ለውጥ ከፍተኛ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ የብር የውጭ ምንዛሪ ተመንን ማረጋጋት ላይ በቁጥጥር ስልሆነ እንጂ ኢኮኖሚው የመግዛት አቅሙን ዝቅተኛነት እያጋለጠበት በመሆኑ የብሔራዊ ባንኩን ውጤት ዝቅተኛ ያደርግበታል፡፡ የፋይናንስ ዘርፍ ጤናማነትም ቢሆን የሚያኩራራ አይደለም፡፡                                    

አቶ ተክለወልድ የባንክ ቅርንጫፎች ከ680 ወደ 3,900 አድገዋል፤ ከፍተኛ የቁጠባ ገንዘብ ማሰባሰብም ተችሏል ብለዋል፡፡ ከምርት ዕድገት ጋር ባልተጣጣመ መንገድ፣ ገንዘብ ኢኮኖሚው ውስጥ ለሚረጨው ጥሬ ገንዘብ ምንጮቹ ብሔራዊ ባንክ እንዲሁም በመንግሥት ትዕዛዝ ጭምር በገፍ የሚያበድረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ናቸው፡፡ በተለይ እነዚህ ሁለት ባንኮች ኢኮኖሚው ውስጥ በሚያንቀሳቅሱት ገንዘብ ምክንያት የዋጋ ንረት እየጨመረ በመምጣቱ፣ የኢትዮጵያ ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት በጊዜው ዋጋ ከነበረበት 60 ቢሊዮን ብር ገደማ፣ በአሁኑ ጊዜ ከ1.5 ትሪሊዮን ብር በላይ መድረሱ ተገልጿል፡፡ በግልጽ ለማስቀመጥ ያደገው ምርት ሳይሆን፣ የዋጋ ንረት ነው፡፡

አቶ ተክለወልድ እንዳሉት ባንኮች ከሚያበድሩት ገንዘብ ሃያ ሰባት በመቶ እየቀነሱ ቦንድ እንዲገዙ የተገደዱት ለዓባይ ግድብ መዋጮ ሳይሆን፣ ለኢንዱስትሪ ልማት ነው ማለታቸው በየትኛው የመንግሥት ፖሊሲ ላይ ተመሥርተው እንደሆነ ሊገባኝ አልቻለም፡፡ ሁሉም ሰው እንደሚያውቀው፣ የሃያ ሰባት በመቶ የግዴታ የቦንድ ግዥ ለዓባይ ግድብ መሆኑ ይፋዊ በሆነ መንገድ የተገለጸ መረጃ ነው፡፡ ይህ የግዴታ ቦንድ ግዥ በባንኮች ላይ ምንም ጉዳት አላደረሰም ማለታቸው አስገራሚ ነው፡፡ አክለውም ይህ አዲስ ነገር አይደለም፣ እንዲያውም በህንድ 40 በመቶ ነው ብለዋል፡፡ ይህን መረጃ ለማረጋጥ ሞክሬ አልቻልኩም፡፡

የባንክ ባለአክሲዮኖች እስከ አርባ በመቶ የትርፍ ክፍፍል ድርሻ እንደሚያገኙ ገልጸዋል፡፡ ይህ እውነት ነው፡፡ ግን ለምን እንዲህ ሆነ? ከተባለ የባንኩን ዘርፍ ጥቂት ባንኮች በከፊል ሞኖፖል ስለተቆጣጠሩት ነው፡፡ አቶ ተክለወልድ ይህም ሆኖ፣ የባንኮች ቁጥር በውህደት መቀነስ አለበት ባይ ናቸው፡፡ ይህ ግን ትርፉን ከ40 በመቶ ወደ 60 እና 70 በመቶ ለማሳደግ ካልሆነ በቀር ለውህደት ጊዜው ገና ነው፡፡  

አቶ ተክለወልድ ባንኮች ለገንዘብ አስቀማጮች አምስት በመቶ ወለድ እየከፈሉ፣ ያንኑ ገንዘብ በ17 በመቶ በማበደር፣ ወጪያቸውን ሸፍነው ከአሥራ አንድ በመቶ በላይ ትርፍ እንደሚያገኙ ገልጸዋል፡፡ ይህም እውነት ነው፡፡ የዋጋ ንረት ከፍተኛ በሆነበትና የባንኮች ትርፍም ከፍተኛ በሆነበት ዓውድ፣ በተቀማጭ ገንዘብ ላይ የሚከፈለውን ወለድ ከአምስት በመቶ በላይ ፈቀቅ ሳይል እንዲቆይ ያደረጉት ለምንድን ነው? እንዲያውም፣ የዓለም የገንዘብ ድርጅት የሚሉት በተቀማጭ ገንዘብ ላይ የሚከፈለው ወለድ ከዋጋ ንረት በላይ መሆን አለበት ነው፡፡ ተበዳሪዎች እንኳንና 17 በመቶ ሰላሳ በመቶም ወለድ ቢጠየቁ መክፈል እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡ ምክንያቱም ለምሳሌ በሌተር ኦፍ ክሬዲት ከውጭ የሚያስመጧቸውን ዕቃዎች በመቶ ፐርሰንት ትርፍ መሸጥ ይችላሉ፡፡ ብሔራዊ ባንክ ዋጋን ለመቆጣጠር የሚያስችል የገንዘብ ፖሊሲ የለውም፡፡

አቶ ተክለወልድ በአገሪቱ ለደረሰው የውጭ ምንዛሪ እጥረት በዋናነት ተጠያቂ መሆናቸውን የተገነዘቡት አልመሰለኝም፡፡ ትክክለኛ የገንዘብ ፖሊሲ ቢኖራቸው ኑሮ፣ የፖሊሲው አንዱ ወሳኝ ሁኔታ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ይሆን ነበር፡፡ እሳቸው የሚመሩት ብሔራዊ ባንክና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኢኮኖሚው ውስጥ በብድር መልክ የሚረጩት ጥሬ ገንዘብና የባንክ ሒሳብ ገንዘብ፣ በብርና በዶላር መካከል ያለውን የመጠን ዝምድና ያዛባዋል፡፡ ብዙ ብር ጥቂት ዶላሮችን ያሳድዳል፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ይፈጠራል፡፡ የብር የውጭ ምንዛሪ ተመን ያሽቆለቁላል፡፡ በማክሮ ኢኮኖሚ ደረጃ የሆነው ይህ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ተጠያቂዎቹ የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክና የፕላን ኮሚሽን ናቸው፡፡ እርግጥ ከሁሉም በላይ ተጠያቂው እነዚህን ሁሉ ሥራዎች አስተባብረውና አቀናጅተው መምራት የሚጠበቅባቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ መሆናቸው አያጠያይቅም፡፡ ቻው፡፡

(ተክለብርሃን ገብረሚካኤል፣ ከአዲስ አበባ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...