Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

በሕግ አምላክትኩረት የተነፈገው የሕፃናት ከያኒያን መብት ጥበቃ

ትኩረት የተነፈገው የሕፃናት ከያኒያን መብት ጥበቃ

ቀን:

በውብሸት ሙላት

በበርካታ አገር አቀፍ ዝግጅቶች ላይ (የብሔረሰቦች ቀን፣ የመላው ኢትዮጵያ ጨዋታና ሌሎችም) ከረጅም ጊዜ ልምምድ በኋላ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሕፃናት ሲሳተፉ አስተውለናል፡፡ በቴሌቪዥን ድራማ፣ በፊልም፣ በሰርከስ፣ በ‹‹አይዶል ሾው››፣ በዳንስ ትርዒቶች ወዘተ ላይ ሕፃናት ይሳተፋሉ፡፡ በተለያዩ አማተር ክበቦችም ውስጥም እንዲሁ፡፡ በአንድ በኩል ሕጻናቱ በእንዲህ ዓይነት ኪነ ጥበባዊና ሥነ ጥበባዊ ክንዋኔዎች የመሳተፍ መብት ብቻ ሳይሆን ለሁለንተናዊ ዕድገታቸው በጎነቱን፣ ለኢንዱስትሪውም የሚኖረውን ፋይዳ ከግምት በማስገባት፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሕፃናቱ በአዕምሮና በአካል ካለመጎልመሳቸው የተነሳ ሊደርስባቸው ከሚችል ጥቃት ጥበቃ ያስፈልጋቸዋል፡፡ በመሆኑም ይህ ሁኔታ በኢትዮጵያ ሕግ ምን እንደሚመስል ቅኝት ይደረግበታል፡፡ በሌላ አገላለጽ ሕፃናትን ከተለያዩ የሥነ ልቦናና የአካል ጉዳት፣ የገንዘብ ብዝበዛ የሚጠበቁበት የሕግ ሥርዓት በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ምጥን ቅኝት ይደረጋል፡፡

ሕፃናት በቤተሰቦቻቸው፣ በትምህርት ቤት፣ በማኅበረሰቡና በሌሎች አካላትም ጥቃት ሊደርስባቸው ይችላል፡፡ ከጥቃት መታደግ በዋናነት የአሳዳጊዎች (የወላጆች) ድርሻ ቢሆንም ቅሉ ለቤተሰብ ብቻ ግን የሚተው አይደለም፡፡ የመንግሥትም ግዴታ ነው፡፡ ለነገሩ የአንድ አገር የውስጥ ጉዳይ ብቻ ከመሆን አልፎ የአኅጉራትና የዓለም አቀፍ ትኩረትም ከሆነ ዘመናት አስቆጥሯል፡፡ በመሆኑም በዓለም አቀፍ፣ በአኅጉር አቀፍና በአገር አቀፍ  ደረጃ ሕፃናትን የሚመለከቱ ሕግጋትና ተቋማት አሉ፡፡ 

- Advertisement -

ከኢትዮጵያ ሕገ መንግሥቱን፣ የቤተሰብ ሕጉን፣ የአሠሪና ሠራተኛና የሲቪል ሰርቪስ አዋጆቹን፤ ዓለም አቀፉንና የአፍሪካን የሕፃናት መብት ስምምነቶች ላይ በመመርኮዝ የሕፃናትን ጥቅም እንዲሁም ከቅጅና ተዛማጅ መብቶች አንፃር የሚኖራቸውን መብት እንዳስሳለን፡፡ በተጨማሪም የተወሰኑ አገሮች ሕግጋትን ለማነፃፀሪያነትና ለልምድ መቅሰሚያነት እንገለገልባቸዋለን፡፡ የሕፃናት ጥቅም ተቀዳሚነት (best interests of a child) መርህን መሠረት በማድረግ የሕፃናት ከያኒያን ጥበቃ ምን መምሰል እንዳለበት ብሎም የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ፣ የሴቶችና ሕፃናት፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ የወጣቶችና ስፖርት እንዲሁም የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴሮች አጽንኦት ሊሰጡባቸው የሚገቡ ነጥቦችን ይጠቆማሉ፡፡ ይህ ሁሉ ሚኒስቴር መዘርዘሩ የሥራቸውን ተያያዥነት ወይም ተደራራቢነት ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ከያኒነትን እንደ አንድ የሥራ ዘርፍ በማየት ሕፃናት እንዴት ሊሠማሩበት እንደሚችሉ ሥርዓት የማበጀት ኃላፊነት አለበት፡፡ የሴቶችና የሕፃናት ደግሞ ምንም እንኳን ስለሥራ ብዙም ባይመለከተውም የሕፃናት ሁኔታ በቀጥታ ስለሚመለከተው ነው፡፡ የሳይንስና ቴክኖሎጅም ከቅጅና ተዛማጅ መብት ጋር በተያያዘ እንዲሁ ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ ነው፡፡ ሌሎቹም እንዲሁ በተለያየ መልኩ የጉዳዩ ባለቤት ስለሚሆኑ ነው፡፡

የሕፃናት ከያኒያን ጥበቃ አስፈላጊነት

በዚህ ጽሑፍ ውስጥ አካለ መጠን ያልደረሰ ሕፃን ማለት ዕድሜው ከአሥራ ስምንት ዓመት በታች የሆነ ማለት ነው፡፡ በመሆኑም ሕፃንም ሆነ አካለ መጠን ያልደረሰ ማለት  ትርጉማቸው ተመሳሳይ ነው፡፡

በርካታ ሕፃናት ከያኒን በተለያዩ ምክንያቶች ሕፃንነታቸውን ተሰርቀዋል፡፡ በሌላ አገላለጽ በሕፃንነታቸው የወሲብ ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል፡፡ የመደፈር አደጋ ደርሶባቸዋል፡፡ ለአደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚነት ተጋልጠዋል፡፡ በወጣትነታቸው ራሳቸውን አጥፍተዋል፡፡ የችግሩን ግዝፈት በተመለከተ ሆሊውድን በምሳሌነት በመውሰድ ኮሬይ ፌልድማን የተባለ ከሕፃንነቱ ጀምሮ የፊልም ተዋናይ የሚታወቅ በቅርቡ ለኤቢሲ ኒውስ በሰጠው ቃለ ምልልስ ላይ እንዲህ በማለት ገልጾታል፡፡ ‹‹ቁጥር አንድ የሆሊውድ ችግር የነበረው፣ የሆነውና ሁልጊዜም የሚሆነው ከሕፃናት ጋር የሚደረግ ወሲብ (pedophilia) ነው፤›› አንድ ሌላ ተዋናይም ከልምዱ በመነሳት እንደተናገረው ‹‹ከሕፃናት ይልቅ በፊልም ውስጥ ለሚሳተፉ እንስሳት የተሻለ ጥበቃ እናደርጋለን፤›› ብሏል፡፡

ፊልምን እንደ አንድ ምሳሌ አነሳን እንጂ በሌሎች የጥበቡ ዘርፍም እንዲሁ ችግሮች አሉ፡፡ ዳንስን ብንወስድ ከላይ የተገለጹት ችግሮች እንደተጠበቁ ሆነው አንዳንድ የውዝዋዜው ዓይነቶች ወደ ወሲብ ቀስቃሽነት የመለወጥ አዝማሚያ ስለሚኖራቸው ሕፃናት ደግሞ በእንደነዚህ ዓይነት አድራጎቶች እንዳይሳተፉ ለማድረግ የሕግ ከለላ ያሻቸዋል፡፡

ሰርከስም ቢሆን ከዚሁ ተለይቶ መታየት የለበትም፡፡ በተለይ ደግሞ ለከፍተኛ አካላዊ አደጋ የተጋለጠ በመሆኑ፡፡

የኢንዱስትሪው ልዩ ባሕርያት

የሥነ ጥበብና የኪነ ጥበብ ኢንዱስትሪው ከሌሎች ሥራዎች ልዩ የሚያደርጉት ባሕርያት አሉት፡፡ ከጨቅላ ሕፃን ጀምሮ በዕድሜ የገፉ አዛውንት የሚሳተፉበትም ነው፡፡ አንድ አካለ መጠን ያልደረሰ ልጅ ውል ከተዋዋለ ውሉን በእርሱ ጠያቂነት ሊፈርስ ይችላል፡፡ ዕድሜው 18 ከሞላ በኋላ በተወሰኑ ዓመታት ውስጥ የማፍረስ መብትን የተለያዩ አገሮች ሕግጋት ዕውቅና ይሰጣሉ፡፡ ይህ ሁኔታ ለኢንዱስትሪው እጅግ ከፍተኛ ሥጋት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ የፊልም ኢንዱስትሪን ብንወስድ የሕፃናቱን መብትና ጥቅም ጠብቆ ብሎም ለምልመላ፣ ለሥልጠናና ለማቆያ ወጪ ካደረጉ በኋላ ሕፃናቱን ባሰኛቸው ጊዜ ያለምንም ተጠያቂነት ወይም የውል ኃላፊነት እንደማንኛውም ሥራ ሁሉ ውሉን ቀሪ የማድረግ መብት ከተሰጣቸው ኢንዱስትሪው ለከፍተኛ ኪሳራ መዳረጉ አይቀሬ ነው፡፡ ከገንዘብ በተጨማሪ ከፍተኛ ድካም ሙያውን በማሠልጠን ከተደከመባቸው በኋላ እንዳሻቸው ማቋረጥ ለኢንዱስትሪው ጉዳት አለው፡፡ የፊልም አዘጋጁም በመርሐ ግብሩ መሠረት ዕቅዱን ማሳካት አይችልም፡፡

የሙዚቃ ኢንዱስትሪውም ቢሆን የሙዚቃ አሳታሚዎች (ሪከርዲንግ ኩባንያዎች) ሕፃኑ ታዋቂ እስከሚሆን ድረስ በተለያዩ አጋጣሚዎች የማሠልጠን፣ ችሎታውን ማስተዋወቅና ለስኬታማነቱም የረጅም ጊዜ ፕሮጀክት ስለሚነድፉ ሕፃናቱ እንዳሻቸው ውሉን መሠረዝ ከቻሉ ለሙዚቃ አሳታሚዎች ራስ ምታት ነው፡፡ ውላቸውም በአብዛኛው የረጅም ጊዜ ነው፡፡ አንዳንድ አገሮች ሕፃናት ከእንዲህ መሰል ኢንዱስትሪዎች ጋር የሚያደርጓቸው ውሎች ላይ የጊዜ ጣራ አስቀምጠዋል፡፡ በእርግጥ የጊዜው ርዝመት የተለያየ ቢሆንም፡፡ ሦስትም፣ አራትም፣ ሰባት ዓመትም አለ፡፡ በመሆኑም የኢንዱስትሪውን ጥቅምና የሕፃናቱን መብት ማመጣጠን የግድ ይሆናል፡፡

ኢንዱስትሪው ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ከላይ ተመልክተናል፡፡ ሕፃናቱ ላይ ጉዳት የመድረሱን አጋጣሚዎችም እንዲሁ! በመሆኑም ሁለቱን ለማስማማት አገሮች የተለያዩ አማራጮችን ሥራ ላይ አውለዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ዋናው ከሕፃናት ጋር የሚደረጉ ውሎችን በፍርድ ቤት አስቀድሞ እንዲጸና ማድረግ ነው፡፡ ለዚህ ዓይነቱ አሠራር ፈር ቀዳጁ ‹‹የኩጋን ሕግ›› በመባል ይታወቃል፡፡ የኩጋን ሕግ ታሪክ እንዲህ ነው፡፡

ጃኪ ኩጋን የተወለደው እ.ኤ.አ. በ1914  ዓ.ም. ሲሆን በርካታ ድምፅ አልባ ፊልሞችና የቴሌቪዥን ድራማዎች ላይ ተሳትፏል፡፡ አባቱም ተዋናይ ነበር፡፡ በፊልም ላይ መሳተፍ የጀመረው በ1917 ዓ.ም. ገና የሦስት ዓመት እምቦቀቅላ እያለ ነው፡፡ በተለይም የቻርሊ ቻፕሊን “The Kid” በመባል የሚታወቀው ፊልም ላይ በ1921 ዓ.ም. በመሥራቱ ዝነኝነትን ያትርፍበት እንጂ ከቻርሊ ቻፕሊ ጋር መሥራት የጀመረው በ1919 ነው፡፡ ቻርሊ ቻፕሊ ጋር አብሮ ድክ ድክ ሲል የማያውቀው የለም ማለትም ይቻላል፡፡ በሕፃንነቱ በሠራባቸው ፊልሞች አማካይነት ወደ አራት ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ገንዘብ 18 ዓመት ሳይሞላው ተከፍሎታል፡፡

ምንም እንኳን 20 ዓመት እስከሚሞላው ድረስ ያገኘውን ገንዘብ ወላጅ አባቱ በተገቢው ሁኔታ እንዳስቀመጠለት ቢታወቅም፣ አባቱ ሲሞት ወላጅ እናቱና የእንጀራ አባቱ ያስተረፉለት 250,000 ዶላር ብቻ ነበር፡፡ ይሄንንም በ1938 ዓ.ም. በፍርድ ቤት ክስ በማቅረብ ያገኘው ነው፡፡ በአጠቃላይ ከጠበቃና ሌሎች ወጪዎች ተቀናንሰው በእጁ የገባው ግን 126,000 ዶላር ብቻ ነበር፡፡ ይህ ውሳኔ  ከተሰጠ በኋላ የብዙዎችን ቀልብ ስለሳበ ሕፃናት የሚያገኙት ገቢ ጥበቃ እንደሚያስፈልገው ታመነበት፡፡ በዚህ ምክንያት  የካፎርኒያ ግዛት በ1939 ዓ.ም. የኩጋን ሕግ የሚባል አወጣ፡፡ ዋና ይዘቱም ሕፃናት  በተለይም በከያኒያኒነት ከሚያገኙት ገቢ ውስጥ ቢያንስ የተወሰነው በዝግ የባንክ ሒሳብ እንዲቀመጥላቸው የሚያስገድድ ነው፡፡ በተጨማሪም የትምህርት ጊዜያቸውን፣ የሥራ ሰዓታቸውንና የዕረፍት ጊዜን ሥርዓት ያበጀ ሕግ ነው፡፡ ዓላማ ያደረገው ደግሞ ‹‹የሕፃናት ጥቅምን ተቀዳሚ›› ማድረግ የሚለውን መርሕ ማሳካት ነው፡፡ በእርግጥ ይህ የኩጋን ሕግ በተደጋጋሚ ተሻሽሏል፡፡ በተለይም “Home Alone” እና ሌሎች በርካታ ፊልሞች ላይ በመተወን የሚታወቀው ሕፃን፣ ማኮሌይ ከልኪን፣ አባትና እናቱ ላይ ክስ ካቀረበ በኋላ የካሊፎርኒያ ሕግ አውጪ ምክር ቤት ሕፃናት ከሚያገኙት ገቢ ላይ ቢያንስ 15 በመቶው በዝግ አካውንት በአደራ መልክ እንዲቀመጥ የሚያስገድድ ሕግ ወጥቷል፡፡

በአሜሪካ የፌደራሉ የአሠሪና ሠራተኛ ሕግ መሠረት አንድ ሕፃን 16 ዓመት ሳይሞላው መቀጠር ባይችልም፣ ፊልም፣ ትያትር፣ የሬዲዮና ቴሌቪዥን ክወናዎችን በተመለከተ ግን እያንዳንዱ ግዛት ሕግ ማውጣት ይችላል፡፡ በመሆኑም 32 ግዛቶች ከያኒ ሕፃናትን የሚመለከቱ ሕግጋት አውጥተዋል፡፡ የካሊፎርኒያን በአስረጅነት የምንጠቀመው በቀደምትነቱ፣ የሆሊውድ መገኛ በመሆኑ፣ የተሻለ ጥበቃ በማድረጉና በአስተማሪነቱ ነው፡፡

የገቢውንም ሁኔታ በተመለከተ አገሮች በፍርድ ቤትን ፈቃድ ይሁንታ ማግኘት አለበት በማለት የደነገጉ አሉ፡፡ አንዳንዶቹ ከወጪ ቀሪው ወይም ከተጣራ ክፍያው ላይ ሃምሳ በመቶ ብቻ መቀመጥ እንዳለበት የቤተሰብ ሕጎቻቸው ይደነግጋሉ፡፡ ገቢውም መቀመጥ ያለበት በዝግ የባንክ አካውንት ነው፡፡ በ18 ዓመቱ እንዲያንቀሳቅሰው ተደርጎ! ፍርድ ቤቱ የባንክ ቤቱን ስም፣ የሕፃኑን ስም፣ ወዘተ ይገልጻል፡፡ አሠሪው ወይም ከፋዩ በዚህ አካውንት ማስገባት አለበት፡፡ አንዳንድ አገሮች ደግሞ ፍርድ ቤቱ ተገቢ ነው ያለውን መጠን እንዲጠቀምበት የመወሰን ሥልጣንን በመስጠት ጥበቃ አድርገዋል፡፡

ሕግጋቱ ግን በዚህ የተገደቡ አይደሉም፡፡ የሥራ ላይ ጥንቃቄና ጤንነታቸውን የሚመለከቱ ጉዳዮችን፣ ፊልምና መሰል ሥራዎች ውስጥ ለመሳተፍ አስቀድሞ ፈቃድ ማግኘት፣ በተለይ ደግሞ ከትምህርት ጋር እንዴት እንደሚስማማ ከግምት መግባት አለበት፡፡

ይህ ፈቃድ ለሕፃኑ ወላጆችና ለቀጣሪውም ያስፈልጋል፡፡ በተለይ የቀጣሪው ሕፃንን ለመቅጠር ያለው ብቃት ተፈላጊ ነው፡፡ ፈቃዱ ለተወሰነ ጊዜ ወይም በቋሚነት ሊሠጥ ይችላል፡፡ የልምምድ ወቅት፣ ርዝመት የሥራ ሰዓትና የአመጋገብ ሁኔታ፣ የተለያዩ የመዋቢያና ማጌጫዎችን ከዕድሜ ጋር ማጣጣም፣ በሥራ ቦታው ሲጋራ ማጨስ፣ የሕፃኑ አጠቃላይ የጤና ሁኔታ፣ ለምሳሌ የአተነፋፈስ ሥርዓቱ ለውዝዋዜ/ለዳንስ ተፈላጊ ነው፡፡

ይህ ሁኔታ የፊልም ልምምድንና ቀረፃን እንዲሁም የቴአትር ትወና ሰዓትንም ይመለከታል፡፡ የወላጆቹም ይሁን የቀጣሪው ፈቃድ የሚታደስ መሆን አለበት፡፡ ሲታደስ የሕፃኑ አጠቃላይ የትምህርት ሁኔታ መሻሻል ወይም መቀነስ ግምት ውስጥ መግባት አለበት፡፡ የቀጣሪው የሕፃናት አያያዝም ታሪክም ለፈቃድ ዕድሳት አስፈላጊ ነው፡፡

ሕፃናትን በተለያዩ የዕድሜ ደረጃ፣ በቀን ውስጥ ለምን ያህል ሰዓት ሊሠሩ እንደሚችሉ ብሎም በመካከል ለምን ያህል ጊዜ ማረፍ እንዳለባቸውም የድንጋጌዎቹ አካል ናቸው፡፡  በቀጥታ ሥርጭት እንዲሁም በተከታታይ ቀረፃ ላይ መቆየት ያለባቸው ለምን ያህል ሰዓትና የተዋናይ ወይም የፊልም ተሳታፊ የመጨረሻ ትንሹ ዕድሜ የልምምድ ቦታ ምቹነት፣ የሱፐርቫይዘር ምደባና ቁጥጥር ሕግ በብዙ አገሮች አላቸው፡፡

ይህ ሁኔታ ሕፃናት ሞዴሊስቶች የሚያካትትባቸው አገሮች አሉ፡፡ ሞዴሊስት ቀጣሪዎች ፈቃድ የማግኘት ሁኔታ፣ ከተወሰነ ዕድሜ (ለምሳሌ ከ14) በታች የሆኑ ሞዴሊስቶችን በተመለከተ ኃላፊነት የሚጣልበት ወላጅ፣ ሞግዚት፣ ወይም ሌላ ሰው የሚመደብበት ሁኔታ፣ ቀጣሪዎች የሞዴሊንግ አሠልጣኝ (መምህር) እንዲኖራቸውና በመምህሩ አማካይነት ብቻ ትዕዛዝ ለሕፃኑ እንዲሰጥ ማስገደድን ይጨምራሉ፡፡ ምክንያቱም ደግሞ ሕፃናት የሚሳተፉባቸው በዋናነት በትምህርትና በሥልጠና መልክ መሆን ስላለበት ነው፡፡ ሞደል ለመሆንም ለሚፈለገው ሕፃንም በሞግዚቶቹ አማካይነት ፈቃድ መያዝ ይገባዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሁኔታ ስለ ሕፃናት ከያኒያን

በኢትዮጵያ ሕፃናት ከያኒያኒያን የሚመለከት ግልጽ ሕግ የለም፡፡ በመሆኑም የተለያዩ መርሆችንና ሕጎችን በመንተራስ ሁኔታውን በማብራራት ተጨማሪ ሕግ ማስፈለጉንና አሁን ያሉትን ለማብራራት ይሞከራል፡፡ ሕፃናት እንደማንኛውም ሰብዓዊ ፍጡር የሰብዓዊ መብት ባለቤቶች ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ማንኛውም ለአካለ መጠን ከደረሰ ሰው በተጨማሪ ደግሞ የተለያዩ መብቶች አሏቸው፡፡

የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 36 ላይም ይሄንኑ ተጨማሪ መብትና ጥበቃ አስቀምጧል፡፡ ከሕገ መንግሥቱ ለዚህ ጽሑፍ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ብቻ እንመለከታለን፡፡ ማንኛውም ሕፃን በሰውነቱ ሐሳቡን የመግለጽ መብት አለው፡፡ ሐሳቡን ደግሞ በሥነ ጥበብ መልክ መግለጹ የዚህ መብት ንዑስ ክፍል ነው፡፡ በአጠቃላይ ለሰብዓዊ ዕድገት በጎ ተፅዕኖ ይኖረዋል ተብሎ ይታሰባልም፡፡ መንግሥትም ለሥነ ጥበብና ለስፖርት እገዛ የማድረግ ግዴታ ስላለበት የዚሁ ድጋፍ ተጠቃሚ ከሚሆኑት የማኅበረሰብ ክፍሎች ውስጥ ሕፃናት ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡ አቅም በፈቀደ መጠንም ይሄንኑ መብት ዕውን ለማድረግ መንግሥት ገንዘብ በመመደብ ተግባራዊ ማድረግ አለበት፡፡ በአንቀጽ 36 ንዑስ ቁጥር 1 ፊደል ‹‹መ›› ላይ ‹‹ጉልበቱን ከሚበዘብዙ ልማዶች የመጠበቅ በትምህርቱ በጤንነቱና በደኅንነቱ ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ሥራዎች እንዲሠራ ያለመገደድ ወይም ከመሥራት የመጠበቅ፤›› መብት እንዳለው ተገልጿል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በዚሁ አንቀጽ ንዑስ ቁጥር 2 ላይ እንደተገለጸው በግል ድርጅቶች፣ በመንግሥት (ሕግ አውጪው፣ አስፈጻሚውና ተርጓሚው) ሕፃናትን የሚመለከቱ ውሳኔዎች በሚሰጡበት ጊዜ በቀዳሚነት ከግምት ውስጥ መግባት ያለበት የሕፃናት ጥቅም ወይም ደኅንነት ነው፡፡ ሕፃን ከያኒን የሚመለከት ውል ቢኖርና ውሉ በውልና ማስረጃ የሚፀድቅ ቢሆን አፅዳቂው መሥሪያ ቤት የሚደረገውን ውል ከተዋዋይ ወገኖች መብትና ግዴታ አንፃር እንዲሁም ውሉ በራሱ የሕፃኑን ተጠቃሚነትና ደኅንነት ያስቀደመ መሆኑን ማረጋገጥ አለበት እንደማለት ነው፡፡

ዓለም አቀፉ የሕፃናት መብት ስምምነትና አፍሪካ የሕፃናት መብቶችና ጥበቃ ቻርተርም ካስቀመጧቸው ጥበቃዎች ውስጥ ለዕድገታቸው እንክብካቤ ማግኘት፣ ትምህርትና የጤና እንክብካቤ ማግኘት፣ የራስን ባህል የመጠበቅ፣ ዕረፍት የማግኘት፣ የመዝናናትና የመጫወት እንዲሁም ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብቶች ከብዙዎቹ በጣት የሚቆጠሩት ናቸው፡፡ ይህ ማለት ግን ተገቢው ቁጥጥርና መመርያ አይሰጣቸውም ማለት አይደለም፡፡ ለመልካም አስተዳደጋቸው ወላጆቻቸው ወይም አሳዳጊዎቻቸው ተገቢውን ቁጥጥር ሊያደርጉና አመራር ሊሰጡ ይችላሉ፡፡

ከላይ በተጠቀሱት ስምምነቶችና የኢትዮጵያ የወንጀል ሕግም ጭምር ማንኛውም ሕፃን ከጉልበት ብዝበዛና ከጾታዊ ጥቃት የመጠበቅ መብት እንዳላቸው ይደነግጋሉ፡፡ አድራጎቱም የወንጀል ተጠያቂነትን ያስከትላል፡፡ ስለሆነም ሕፃናት ከያኒያንን ከእንዲህ ዓይነት ብዝበዛ ጥበቃ ለማድረግ የሚያስችል ሕግ መኖር አለበት ማለት ነው፡፡

የሕፃናትን ገቢ አስተዳደር በተመለከተ አግባብነት ያለው የቤተሰብ ሕጉ ነው፡፡ የሕፃናትን ንብረት የማስተዳደር ኃላፊነት ያለበት ሞግዚቱ ነው፡፡ ሞግዚት የሚባለው ወላጆች ወይም ሌላ ሰው ሊሆን ይችላል፡፡ ለአስተዳደጉ የሚያስፈልገውን ወጪ ከሕፃኑ ገቢ ላይ እንዲጠቀምበት ወጪ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ይህ እንግዲህ ሞግዚቶቹ ወላጆች ቢሆኑም ባይሆንም ልዩነት የለውም፡፡ ይሁን እንጂ ሞግዚቱ ከወላጆች ውጪ በሆነ ጊዜ ፍርድ ቤት ስለአስተዳደሩ መመርያ ሊሰጥ ይችላል፡፡ ስለንብረቱ አስተዳደርም ሪፖርት ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡ ይህ ወላጆችን አይመለከትም፡፡ በመሆኑም አንድ ሕፃን የሚያገኘውን ገቢ ወላጆቹ ለልጁ ጥቅም ያለገደብ ሊያውሉት ይችላሉ፡፡

የሕፃኑ ሀብት ከ500 ብር በላይ ከሆነ ሞግዚቱ አትራፊ በሆነ ተግባር ላይ ማዋል እንዳለበት ተደንግጓል፡፡ ይህ ገንዘብ በሞግዚቱ እጅ በገባ በሦስት ወራት ውስጥ ሥራ ላይ መዋል አለበት፡፡ አትራፊ ተግባር ላይ ካላዋለው ሞግዚቱ ከሕጋዊ ወለድ በተጨማሪ የጉዳት ካሳ ሊከፍል ይችላል፡፡ ከ14 ዓመት በላይ ለሆነ ልጅ ሞግዚት የሆነ ሰው ስለ ሕፃኑ የሚያደርጋቸውን ተግባራት እየተመካከረ መሆን አለበት፡፡ ከ14 ዓመት በታች ከሆነ ግን የሞግዚቱ ሥልጣን ነው፡፡ ዕድሜውንና የገንዘብ አቅሙን ከግምት በማስገባት እስከ 300 ብር የሚደርስ የዕለት ጉዳይ ሊያከናውን ይችላል፡፡ የገንዘቡ መጠን ከዚህ በላይ በሆነ የዕለት ጉዳይ አይደለም፡፡ እንዲሁም ለከያኒነት የሚደረጉ ውሎችን የዕለት ጉዳይ የሚያሰኛቸው ምክንያት የለም፡፡ በመሆኑም የሞግዚቱ ተሳትፎና ጣልቃ ገብነት አስፈላጊ ነው ማለት ነው፡፡

የቅጥር ሁኔታቸውን እንመለከት፡፡ ዓለም አቀፉ የሠራተኛ ድርጅትም ሕፃናት ሥራ የሚቀጠሩበትን ሁኔታ በዕድሜና በሥራው ዓይነት በመከፋፈል ደንብ አበጅቷል፡፡ አስቸጋሪ ሥራዎች ላይ መሳተፍ የሚችለው ከ18 ዓመት በላይ የሆነ ነው፡፡ አስቸጋሪ ያልሆኑና በሙሉ ቅጥረኛነት ደግሞ 15 ዓመት ሲሞላቸው ነው፡፡ ከትምህርት ጋር ሳይጋጩ ቀላል ሥራዎችን በተመለከተ 13 ዓመት ሲሞላቸው መቀጠር ይችላሉ፡፡ በኢትዮጵያ የሲቪል ሰርቪስና የአሠሪና ሠራተኛ አዋጆች መሠረት ደግሞ 14 ዓመት ያልሞላው ሕፃን ሊቀጠር አይችልም፡፡ የሥራውም ዓይነት ጤንነትን አደጋ ላይ የማይጥል መሆን አለበት፡፡ በመሆኑም ከዓለም አቀፉ የሠራተኛ ድርጅት ስምምነት ቁጥር 138 ካስቀመጠው ዝቅተኛ ዕድሜ የኢትዮጵያው የተሻለ ነው ማለት ይቻላል፡፡  

በመሆኑም በኢትዮጵያ ሕግ ስለሕፃናት ገቢ ሕግ ቢኖርም 14 ዓመት ያልሞላው ሕፃን ሥራ ሊቀጠር ስለሚችልበት ሁኔታ የሕግ መሠረት የለም፡፡ በመሆኑም የመዝናኛው ኢንዱስትሪ ከዚህ ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ጋር የሚያደርጉት ውል ሕጋዊነቱ አጠያያቂ ነው፡፡

በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የመዝናኛ ኢንዱስትሪው ውስጥ ስለሚሳተፉ ሕፃናት ተጨማሪ የሕግ ማዕቀፍ ያስፈልጋል፡፡ ተቀጥሮ እንዲሠራ ፈቃድ ማግኘት ጉዳይ፣ ውሎቹን በፍርድ ቤት የማስፀደቅ ሁኔታ፣ ከገቢው የተወሰነ መጠን ማስቀመጥ፣ ብሎም አትራፊ ኢንቨስትመንት ለምሳሌ አክሲዮን በመግዛት የሚቀመጥበትን ዝርዝር አሠራር ሕግ ማውጣት ሕፃናትን ከብዝበዛ መጠበቅ ነው፡፡ ከጉዳትም መታደግ ነው፡፡ ለኢንዱስትሪው ጤናማነትም ይበጃል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሕፃናት ያደረጓቸውን ውሎች ውድቅ የሚያደረግበትን ሁኔታ መገደብ ለኢንዱስትሪው መቀጠል ወሳኝ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሕፃናት ሲዋዋሉ በተደራዳሪዎች ወይም በሞግዚቶች/በወኪሎች ፊት እንዲሆን አስገዳጅ ሕግ ሊኖር ይገባል፡፡ ከያኒያን በአብዛኛው ጊዜ የሚኖራቸው የቅጅ መብት ሳይሆን ተዛማጅ መብት ነው፡፡ የተዛማጅ መብትን ምንነት ደግሞ እንኳንስ ሕፃናት ይቅርና በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎችም በአግባቡ አንጥረው ማወቃቸው አጠራጣሪ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ሕፃናቱ በክፍያም ሆነ በሌላ ሁኔታ ያገኟቸውን የዘፈን ግጥም፣ ዜማና ቅንብር በሌሎች ሰዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ በድጋሚ እንዳይከወኑባቸው አማካሪ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ይህ ሁኔታ የሚወሰነው በውል በመሆኑ!

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...