– ኢትዮጵያ ከግብፅና ከደቡብ ሱዳን ጋር ያደረገችው ቆይታ
– ለኅብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር የተጠበቁት ዕጩ አለመመረጥ
– የሞሮኮ ከ33 ዓመታት በኋላ ወደ ኅብረቱ መመለስ
– ዶ/ር ድላሚኒ ዙማ ለደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንትነት መወዳደር
የአፍሪካ ኅብረት 28ኛው የመሪዎች ጉባዔ ከሰኞ ጥር 22 ቀን ጀምሮ ለሦስት ቀናት በአዲስ አበባ ሲከናወን፣ ከወትሮ ለየት ያሉ አዳዲስ ክስተቶች ታይተውበታል፡፡ ዋና ዋና ከተባሉት ክስተቶች መካከል ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ ለጉባዔው አዲስ አበባ ከተገኙት የግብፅ ፕሬዚዳንት አቡዱልፈታህ አልሲሲና ከደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ከወትሮው ለየት ባለ ሁኔታ መወያየታቸው አንዱ ነው፡፡ ለአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበርነት ይመረጣሉ ተብሎ ትልቅ ተስፋ የተጣለባቸው የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር አሚና መሐመድ ወድቀው፣ የቻድ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሙሳ ፋቂ መሐማት መመረጣቸው ሁለተኛው ክስተት ነው፡፡ ሦስተኛው ሞሮኮ እ.ኤ.አ. በ1984 ሯሳን ከቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት አግልላ ከቆየች ከ33 ዓመታት በኋላ መመለሷ ነው፡፡ አራተኛው ክስተት የኅብረቱን ኮሚሽን ሊቀመንበርነት የሚያስረክቡት ዶ/ር ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ተወዳዳሪ ይሆናሉ መባሉ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በተቀሰቀሰው ሕዝባዊ ቁጣ ሳቢያ በተከሰተው ቀውስ ከጀርባ የግብፅ ተቋማት እጅ እንዳለበት በመንግሥት ከተገለጸ በኋላ፣ በሁለቱ አገሮች መካከል የነበረው ግንኙነት የበለጠ ውጥረት ውስጥ ገብቶ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት የግብፅ መንግሥትን በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ መጠየቁ ለተፈጠረው ውጥረት በምክንያትነት ተወስቷል፡፡ በ28ኛው የኅብረቱ የመሪዎች ጉባዔ ላይ የተገኙት የግብፅ ፕሬዚዳንት ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ጋር የነበራቸው ቆይታ ፍሬያማ ነበር ተብሏል፡፡ በተለይ ሁለቱ መሪዎች በጎንዮሽ ባደረጉት ውይይት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መስማማታቸውን አስታውቀዋል፡፡ በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት በማጠናከር መተማመን መፍጠር እንደሚያስፈልግ፣ የአካባቢውን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የፀጥታ ትብብር በማጠናከር የሁለቱን አገሮች ወንድማማችነት የሚጎዳ ማንኛውንም ዓይነት ድርጊት መቆጣጠርና መገደብ፣ ታላቁ የህዳሴ ግድብን በተመለከተ የኢትዮጵያ፣ የሱዳንና የግብፅ የጋራ ቴክኒክ ኮሚቴ አማካይነት በትብብር የመሥራት አስፈላጊነት፣ በሁለቱ አገሮችና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ በመሪዎችና በተቋማት ደረጃ መረጃ በመለዋወጥ ተከታታይ ምክክሮች ማድረግ፣ የሕዝብ ለሕዝብ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱን የበለጠ ለማሳደግ፣ የመገናኛ ብዙኃንም ወሳኝ ሚና እንዲጫወቱ መደረግ እንዳለበት ስምምነት ላይ መድረሳቸው ታውቋል፡፡ ኢትዮጵያና ግብፅ ስትራቴጂካያዊ ግንኙነታቸውን የሚጎዱ ማናቸውንም ችግሮች በጋራ ለመከላከል መስማማታቸው ተገልጿል፡፡
የሁለቱ አገሮች መንግሥታት ውጥረት ውስጥ እንዳሉ በሚነገርበት በዚህ ወቅት፣ በዲፕሎማሲያዊ አቀራረብ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተነጋግረው መግባባት ላይ መድረሳቸው እንደ አዲስ ክስተት ታይቷል፡፡ በተለይ ደግሞ ሁለቱ መሪዎች በቋሚነት በተለያዩ ጊዜያት በሁለቱ አገሮች ጉብኝት ለማድረግ መስማማታቸው፣ ይህንንም ከወዲሁ ለመጀመር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በቅርቡ ግብፅን እንዲጎበኙ በፕሬዚዳንት አልሲሲ ተጋብዘዋል፡፡ በቅርቡ በሳዑዲ ዓረቢያ ከፍተኛ ባለሥልጣን የተመራ ልዑክ የታላቁን የህዳሴ ግድብ መጎብኘቱ በግብፅ መገናኛ ብዙኃን ከመጠን በላይ በመራገቡ፣ የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ከድጡ ወደ ማጡ ያደርገዋል ተብሎ መሠጋቱ አይዘነጋም፡፡ አሁን ከሁለቱ መሪዎች የተሰማው የመግባባት መግለጫ ግን ሥጋቱን ረገብ ያደረገው መስሏል፡፡
በኢትዮጵያና በደቡብ ሱዳን መካከል የነበረውን መልካም ግንኙነት ያበላሸዋል የተባለው ሰሞንኛ ክስተት፣ የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር በቅርቡ ወደ ካይሮ አቅንተው ፀረ ኢትዮጵያ ስምምነት አድርገው ተመልሰዋል የሚል ዜና መሰማቱ ነበር፡፡ ለኅብረቱ 28ኛ የመሪዎች ጉባዔ አዲስ አበባ የተገኙት ፕሬዚዳንት ኪር፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ጋር ከተወያዩ በኃላ የተናፈሰውን ወሬ አስተባብለዋል፡፡ ሁለቱን አገሮች በተመለከተ ማንኛውም ዓይነት ወሬ ቢናፈስ ተቀራርበው ለመነጋገር ምንም አያዳግታቸውም ካሉ በኋላ፣ ‹‹ግንኙነታችን ግን ተጠናክሮ ይቀጥላል፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹በመሠረተ ቢስ ወሬ ምክንያት ግንኙነታችን እንዲጎዳ አንፈልግም፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ፕሬዚዳንት ኪር ኢትዮጵያን በቅርቡ እንዲጎበኙ የጋበዙ ሲሆን፣ ፕሬዚዳንቱም ግብዣውን በደስታ መቀበላቸውን ገልጸዋል፡፡ በንግድና ኢንቨስትመንት በመሠረተ ልማት፣ በሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት መስማማታቸውን ሁለቱ መሪዎች ይፋ አድርገዋል፡፡
ደቡብ አፍሪካዊቷ ዶ/ር ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማን በአዲስ ተመራጭ ለመተካት በተካሄደው ምርጫ ያልተጠበቀ ውጤት ተገኝቷል፡፡ ለአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበርነት የተወዳደሩት ኬንያዊቷ ዶ/ር አሚና መሐመድ፣ ቦትስዋናዊቷ ፔሎኖሚ ቬንሰን ሞታይ፣ ቻዳዊው ሙሳ ፋቂ መሐማት፣ ኢኳቲሪያል ጊኒው አጋፒቶ ምባ ሞካይና ሴኔጋላዊው አብዱላዩ ባዚላይ ነበሩ፡፡ ከዕጩ ተወዳዳሪዎቹ መካከል ከፍተኛ ግምት የተሰጠው ለኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሚና መሐመድ ቢሆንም፣ ቻዳዊው ሙሳ ፋቂ መሐማት በድምፅ ብልጫ አሸንፈዋል፡፡ ዕጩዎችን ለመምረጥ ሰባት ዙር ምርጫ ተካሂዶ በመጨረሻው የቻድ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ላለፉት አራት ዓመታት የኅብረቱን ኮሚሽን በሊቀመንበርነት ከመሩት ዶ/ር ድላሚኒ ዙማ የኮሚሽን ሊቀመንበርነት ተረክበዋል፡፡ በዚህ ምርጫ የፈረንሣይኛ ተናጋሪ አገሮች ተፅዕኖ በማየሉ ምክንያት፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና በተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ከፍተኛ ልምድ የነበራቸው ኬንያዊቷ ዶ/ር አሚና ተሸንፈዋል፡፡ ለኬንያዊቷ መሸነፍ የተለያዩ ምክንያቶች ቢሰጡም፣ እሳቸውን ለማስመረጥ ከፍተኛ ጥረት ያደረጉት የኬንያ መንግሥት ባለሥልጣናት በሞሮኮና በሰሃራዊት ዓረብ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ መካከል መዋለላቸው መንስዔ መሆኑን ለጉዳይ ቅርበት ያላቸው ዲፕሎማቶች መናገራቸው ተሰምቷል፡፡ ከሁለቱ ባላንጣ ወገኖች ለአሚና ይገባ የነበረው ድምፅ ወደ ቻዱ ዕጩ ሳይሄድ እንዳልቀረ ተገምቷል፡፡
የ56 ዓመቱ ሙሳ ፋቂ መሐማት በመጨረሻው ዙር 39 ድምፅ በማግኘት 54 አገሮች አባል የሆኑበትን የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበርነት ጨብጠዋል፡፡ ዶ/ር ድላሚኒ ዙማ ደግሞ አዲስ አበባን ከለቀቁ በኋላ በቀጣዩ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንትነት ምርጫ በመወዳደር የቀድሞ ባለቤታቸውን ጃኮብ ዙማ መንበር ለመቆናጠጥ እንዳሰቡ ተሰምቷል፡፡ ዶ/ር ድላሚኒ ዙማ በደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ ውስጥ ተሰሚነት ካላቸው ፖለቲከኞች መካከል በዋነኝነት የሚጠቀሱ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ነበሩ፡፡ የኅብረቱን ኮሚሽን ሊቀመንበርነት ካስረከቡ በኋላ በኢትዮጵያ ለነበራቸው ቆይታ ለኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ከፍተኛ ምሥጋና አቅርበዋል፡፡ በተለይ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ለኅብረቱ ጉባዔዎቹ መሳካት ላደረጓቸው ትብብሮች አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡
የዘንድሮው የመሪዎች ጉባዔ ሌላው ክስተት የሞሮኮ ጉዳይ ነው፡፡ ሞሮኮ ከ33 ዓመታት ቆይታ በኋላ ወደ አፍሪካ ኅብረት ለመመለስ ባደረገችው እንቅስቃሴ መጠነኛ እንቅፋት ቢገጥማትም በድል ተወጥታዋለች፡፡ ወደ ኅብረቱ አባልነት ለመመለስ በሞሮኮ ጥያቄ ያቀረበችው በሐምሌ 2008 ዓ.ም. በሩዋንዳ ኪጋሊ ተካሂዶ በነበረው የመሪዎች ጉባዔ ነው፡፡ በአዲስ አበባው የአሁኑ የመሪዎች ጉባዔ ሰኞ ጥር 22 ቀን 2009 ዓ.ም. ጥያቄውን የመረመረው በከፍተኛ ክርክር ታጅቦ ነበር፡፡ በተለይ ደቡብ አፍሪካና አልጄሪያ በሞሮኮ ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ ያሰሙባት ሲሆን፣ ከ53 አገሮች የ39 አገሮችን ድጋፍ አግኝታ ወደ አባልነቷ ተመልሳለች፡፡ አሥር አገሮች ድምፅ እንዳልሰጧት ታውቋል፡፡
ሞሮኮ እ.ኤ.አ. በ1984 በአዲስ አበባ በተካሄደው የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ውሳኔ አኩርፋ ነበር አባልነቷን የተወችው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የራሷ ግዛት እንደሆነች ለምታስባት ሰሃራዊት ዴሞክራቲክ ዓረብ ሪፐብሊክን የወቅቱ የአፍሪካ ድርጅት በአባልነት መቀበሉ ነበር፡፡ በዚህ ሳቢያ ለ33 ዓመታት ከመድረኩ የጠፋቸው ሞሮኮ ከዚህ ጉባዔ በፊት ባደረገችው ቅስቀሳና የማግባባት ዲፕሎማሲ ሥራ ፍላጎቷን አሳክታለች፡፡ በተለይ ባለፈው አንድ ዓመት ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች በንጉሧ መሐመድ ስድስተኛ የተደረጉ ጉብኝቶችና የኢንቨስትመንት ስምምነቶች የዚህ ጥረት ማሳያ ናቸው ተብሏል፡፡ ሞሮኮ ወደ አፍሪካ ኅብረት በመመለስ ተፅዕኖ ፈጣሪ አገር ለመሆን ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላት በስፋት ይነገራል፡፡
የአፍሪካ ኅብረት 28ኛው የመሪዎች ጉባዔ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውይይት ያደረገ ሲሆን፣ በተለይ ተሰናባቹ የኅብረቱ ሊቀመንበር የቻድ ፕሬዚዳንት ኢድሪስ ዴቢ ከአሁን በኋላ በአፍሪካ የሚደረጉ ምርጫዎች ለዜጎች ሥጋት መፍጠር አይኖርባቸውም ብለዋል፡፡ አዲሱ ተመራጭ ሊቀመንበር የጊኒ ፕሬዚዳንት አልፋ ኮንዴ ደግሞ የኅብረቱን ተደማጭነት ለመጨመርና ድምፁን ለማስተጋባት ጥረት እንደሚያደርጉ በንግግራቸው ገልጸው፣ አፍሪካ በአንድ ድምፅ መናገር እንጂ መከፋፈል እንደሌለባት ኮንዴ አሳስበዋል፡፡ በአባል አገሮች መካከል ትብብር እንዲጠናከር፣ ለ700 ሚሊዮን አፍሪካዊያን የኢነርጂ ልማት እንደሚያስፈልግና በወጣቱ ላይ ኢንቨስት ሊደረግ ይገባል ብለዋል፡፡
በዘንድሮው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ በክብር እንግድነት ከተገኙት መካከል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒ ጉተሬዝና የፍልስጤም ፕሬዚዳንት መሐመድ አባስ ተጠቃሽ ናቸው፡፡