Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየሰመራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት በቁጥጥር ሥር ውለው ምርምራ እየተደረገባቸው እንደሚገኙ ታወቀ

የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት በቁጥጥር ሥር ውለው ምርምራ እየተደረገባቸው እንደሚገኙ ታወቀ

ቀን:

– በቅርቡ የተከሰተው የግምጃ ቤት ቃጠሎ ለፕሬዚዳንቱ መታሰር ምክንያት መሆኑን ዪኒቨርሲቲው ይገልጻል

የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አቶ አደም ቦሪ ከሐሙስ ጥር 18 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ በአፋር ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኙ ታወቀ፡፡

ዩኒቨርሲቲውን ለስድስት ዓመታት ያህል መምራታቸው የተገለጸው አቶ አደም፣ ለእስር ያበቃቸው ጉዳይ ምን እንደሆነ ሪፖርተር በተለያየ መንገድ ለማጣራት ሙከራ ቢያደርግም፣ ከክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ዝርዝር መረጃውን ለማግኘት አልቻለም፡፡ የአፋር ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር አቶ መሐመድ አሎፍኪኤን አቶ አደም መታሰራቸውን ከማረጋገጥ በስተቀር ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ይሁንና አቶ አደምን ለእስር እንዳበቃቸው ከሚጠቀሱ ጉዳዮች መካከል ከሁለት ሳምንት በፊት በዩኒቨርሲቲው የተከሰተው የመጋዘን ቃጠሎ ስለመሆኑ እየተነገረ ነው፡፡ የሰመራ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ጉዳዮችና የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አቡበከር አሊ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ አቶ አደምን ለእስር እንዳበቃቸው ከክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የተገለጸውና ክስ እንዲመሠረትባቸው ምክንያት የሆነው፣ በቃጠሎው ምክንያት የተደረሰበትን የምርመራ ውጤት እንዲገለጽላቸው መጠየቃቸው ነው፡፡ የቃጠለው መንስዔ ሆን ተብሎ የተፈጸመ የወንጀል ተግባር እንደሆነ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን እንደሚያሚን ሲገለጽ፣ በአንፃሩ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የፎረንሲክ ምርምራ ክፍል ግን ከዚህ የተለየ ውጤት እንዳለው እንደሚገመት መላምቶች እየተደመጡ ነው፡፡ መላምቶቹን የጠቀሱት አቶ አቡበከር  የሚመሩት ተቋም ምርመራ እየተካሄደበት እንደመሆኑ መጠን ፕሬዚዳንቱ የምርመራ ውጤቱ ከምን እንደደረሰ የመጠየቅና የማወቅ መብት እንዳላቸው ተከራክረዋል፡፡  አቶ አቡበከር ይህን ቢሉም አቶ አደም ላይ  ተጨማሪ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ተጠይቆባቸው በእስር ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡

ከዩኒቨርሲቲው ግምጃ ቤት ቃጠሎ ጋር ይያያዛል ቢባልም ለአቶ አደም መታሰር እየተነገሩ ያሉት ምክንያቶች ግን ከዚህም የላቁ ናቸው፡፡ ከግንባታና ከግዥ ሒደቶች ጋር የተያያዙ የሙስና ወንጀሎች ለፕሬዚዳንቱ መታሰር ምክንያት እንደሆኑ ከክልሉ የሚወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ስለፕሬዚዳንቱ መታሰር ማብራሪያ እንዲሰጡ የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ቦርድ ሰብሳቢና የአርብቶ አደሮችና የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አወል ዋግሪስን ሪፖርተር አነጋግሮ፣ ስለጉዳዩ በማጣራት ላይ እንደሚገኙና የደረሰቡበትን ውጤት እንደሚያሳውቁ ገልጸዋል፡፡

በፕሬዚዳንቱ መታሰር ጉዳይ ላይ የትምህርት ሚኒስቴር ማብራሪያ እንዲሰጥበት በሚኒስቴሩ የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍን የሚመሩትና የሰመራ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ አባል የሆኑትን ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌን ሪፖርተር ለማነጋገርና ማብራሪያ ለማግኘት ሞክሮ አልተሳካለትም፡፡ በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የፎረንሲክ ምርመራ ዘርፍ ስለቃጠሎው ጉዳይ የደረሰበትን ውጤት ለማወቅ የተደረገው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ ይሁንና የአፋር ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ከፌዴራል ፖሊስ ጋር በመሆን ምርመራ ማካሄዳቸውን ከሰመራ ዩኒቨርሲቲ ለመረዳት ተችሏል፡፡

የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ከተመሠረተ ዘጠኝ ዓመታት ያስቆጠረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ሰባት ኮሌጆችና 34 የትምህርት ክፍሎችን አዋቅሮ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ የተቋሙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የቅበላ አቅሙ በመደበኛው የትምህርት መርሐ ግብር ከ4,000 በላይ፣ በማታው ክፍለ ጊዜ ከ1,000 በላይ፣ እንዲሁም በክረምት ወራት ከ1,500 በላይ ተማሪዎችን ለማስተናገድ የሚችልበት አቅም ላይ እንደሚገኝ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ሪፖርተር ለኅትመት ማክሰኞ ጥር 23 ቀን 2009 ዓ.ም. ምሽት እስከገባበት ድረስ አቶ አደም ከእስር አልተለቀቁም፡፡ 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...