Friday, June 2, 2023

የኤርትራ ፕሬዚዳንት በኢትዮጵያ ፌዴራል ሥርዓት ላይ ያሰሙት የከረረ ጥላቻ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አዲሱ የአውሮፓውያን ዓመት ምክንያት በማድረግ በቅርቡ ሰፊ ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡፡

በዚህ ለሦስት ጋዜጠኞች በተሰጠው ከሦስት ሰዓት በላይ የፈጀ ቃለ ምልልስ፣ በኤርትራ ውስጥ ስላለው ወቅታዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁኔታ፣ በአካባቢያዊ የፀጥታና የፖለቲካ ሁኔታ፣ እንዲሁም ኢትዮጵያን በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

የአውሮፓውያን አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር ሰፊ ቃለ ምልልስ በመስጠት የሚታወቁት አቶ ኢሳያስ፣ አዲሱ ዓመት በገባበት የመጀመሪያው ጥር ወር መጠናቀቂያ ላይ የሰጡት ቃለ ምልልስ፣ በኤርትራ ቴሌቪዥን የተላለፈ ሲሆን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ረዘም ያለ ጊዜ የፈጀ ነበር፡፡

ሦስቱ ጋዜጠኞች እየተፈራረቁና ‹‹ፈራ ተባ›› እያሉ ላቀረቡባቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ፣ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ የሚያነሷቸውን በአፍሪካ ቀንድ ቀውስ ተጠያቂ በኢትዮጵያ ያለው ‹‹የወያኔ ሥርዓት›› ነው እና የአሜሪካ ድጋፍ ስላለው አስተዋጽኦ አንስተዋል፡፡ በዚሁ ቃለ ምልልሳቸው ደጋግመው ሁለቱ አገሮች ኤርትራን ፀጥ ለማድረግ ያገኙት ‹‹አዲሱ ሥልት›› የሰብዓዊ መብት ጉዳይ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

በአገር ውስጥ ስላለው ወቅታዊ የሕዝብ ኑሮና የሥራ ዕጦት፣ እንዲሁም የመኖሪያ ቤት ችግር በተመለከተ በሰፊው ተናግረው፣ ከምርታማነት ጋር በተያያዘ ለቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡት ምላሽ ግን ቀልብ የሚስብ ነበር፡፡ ‹‹ምርታማነት ምን ማለት ነው?›› ቆጣ ቆጣ እንደ ማለት እያሉ ፕሬዚዳንቱ ቀጠሉ፡፡ ‹‹በየሻይ ቤቱና በየመናፈሻው ተጎልቶ እየዋሉ ስለምርታማነት ማውራት ይቻላልን?›› በማለት ይጠይቃሉ፡፡

በአብዛኛው ንግግራቸው ወጣቶች ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ ወደ በኋላም ወጣቱ በተለይ የኢትዮጵያ መንግሥትና የአሜሪካ ፕሮፓጋንዳ ሰለባ ሆኖ አገሩን እየለቀቀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ኤርትራን ወጣት አልባ ለማድረግ ሆን ተብሎ የቀረፀው ስትራቴጂ መሆኑን በመግለጽ፡፡ ባለፈው ዓመት በተለይ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የወጣው ሰፊ ሪፖርት በኤርትራ ውስጥ ከመቼም ጊዜ በበለጠ ኢሰብዓዊ የሆነ የዜጎች አያያዝ፣ አፈናና ጭቆና እየተፈጸመ እንደሆነ መግለጹ ይታወሳል፡፡

ይህንን ጉዳይ በወፍ በረር ጠቀስ አድርገው ያለፉት ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግሥትና ግብረ አበሮች የሚሏቸው የአሜሪካና የአውሮፓ መንግሥታት በጋራ ኤርትራን ፀጥ ለማስደረግ የሚጠቀሙበት ‘የሰብዓዊ መብት’ ሥልት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በአዲሱ የአውሮፓውያን ዓመት ዋዜማ፣ ለዓለም መሪዎች በሙሉ እንዲያውቁት በማለት ባስተላለፉት መልዕክት፣ በኢትዮጵያ በጉልበት ተይዟል የሚሉትን የባድመ ግዛት መልሰው እንዲያገኙ እንዲተባበሯቸው ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡ በዚህ ቃለ ምልልስም ደግመውታል፡፡

ንግግራቸው በአብዛኛው የሚያዝ የሚጨበጥ ነጥብ የሌለው ቢመስልም፣ ባለፈው ዓመት በኢትዮጵያ ስለተከሰተው የፖለቲካ ሁከትና እሱን ተከትሎ ስለታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በየመን አካባቢ እየተጠናከረ ያለው ዓረባዊ ኃይል ቅንጅት ድጋፍ በከፍተኛ በራስ መተማመን እንዲያወሩ የረዳቸው ይመስላል፡፡ ‹‹ስለድንበር የተነሳው ዋናው ጉዳያችን ሆኖ አይደለም፡፡ በአጠቃላይ በቀጣናው ለፈጠሩት ቀውስ መገለጫ ስለሆነ አብሮ የሚነሳ ስለሆነ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ኤርትራን ሰይጣናዊ ለማድረግ ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያ መንግሥት ብዙ መሥራቱንም ተናግረዋል፡፡ መንግሥታቸው በመስኖ ግብርና፣ እንዲሁም በቱሪዝም ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ያለፈው ዓመት ቀውስ ተከትሎ፣ የዩኒቨርሲቲ መምህራንና ተማሪዎች እንዲሁም የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በማነጋገር የ25 ዓመታት ጉዞውን መገምገሙና ቀጣይ ዕቅድ መያዙ ይታወሳል፡፡

በተመሳሳይ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ መንግሥታቸው የ25 ዓመታት ድክመቶችና ጥንካሬዎች፣ እንዲሁም ቀጣይ ሥራ የሚያሳይ ፍኖተ ካርታ (ሮድ ማፕ) መዘርጋቱን ተናግረዋል፡፡

ፍኖተ ካርታው ቀይ ባህርን አሰብን ጨምሮ የተለያዩ የአገሪቱ እሴቶችን፣ ደኅንነትንና አጠቃቀምን ይጨምራል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ኤርትራን ሰይጣናዊ አድርጎ ለመሳል የፈጸማቸው ሥራዎች በዚሁ ዓመት መክሸፋቸውን ፈገግታ በተሞላው አኳኋን ነበር የተናገሩት፡፡

በቅርቡ ለሦስተኛ ጊዜ የተራዘመው በተመድ የተጣለባቸውን ማዕቀብ በአግባቡ እንደተቋቋሙትና ይልቁንም የአካባቢው ሰላምና መረጋጋት ጉዳይ እንደሚያሳስባቸው ተናግረዋል፡፡ ‹‹የድንበር ጉዳይ ለብቻው ተነጥሎ የሚታይ አይደለም፤›› በማለትም ‹‹የወያኔ ሥርዓት›› ሰለባ ሆኗል ስላሉት የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ስለሶማሊያ ሕዝብ ስቃይ፣ እንዲሁም ሱዳን በሁለት በመከፈሏ የተነሳ እየተከሰተ ስላለው ዕልቂትና መበታተን አንስተዋል፡፡ የእነዚህ ሁሉ ችግሮች መነሻ ምዕራባዊያንና ግብረ አበሯ ኢትዮጵያ የሚከተሉት የከፋፍለህ ግዛ ስትራቴጂ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

‹‹እነሱ የሚከተሉት ስትራቴጂ የሰው አዕምሮንም ለማደንዘዝ ያለመ ነው፡፡ አንዳንድ አዳዲስ አመራሮች ሲመጡም የድንበር ጉዳዩን ላያውቁት ይችላሉ፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

ስለአንቀጽ 39

ኤርትራ ነፃ የወጣችው ለኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት መሠረት በሆነው፣ ‹‹ራስን በራስ የመወሰን መብት›› መሠረት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የኤርትራን ነፃነት በቀጥታ ከዚህ አንቀጽ ጋር ማገናኘት የግድ አስፈላጊ ባይሆንም፣ ኤርትራ በይፋ ከኢትዮጵያ የተገነጠለች ግን ከዚሁ አንቀጽ 39 በመነጨ አስተሳሰብ ነበር፡፡ አቶ ኢሳያስ በአጠቃላይ በምሥራቅ አፍሪካ ምዕራባዊያን አንዱን ጠላት ሌላውን ወዳጅ አድርገው እንደ ሞግዚት በመጠቀማቸው በቀጣናው ቀውስ እንደተፈጠረ ገልጸዋል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥም ተግባራዊ የሆነው ይኼው አካሄድ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በ1986 እና 1987 ዓ.ም. ‹‹ፌዴራላዊ›› አስተሳሰብ እንድትተው ለምነው እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ‹‹አልሰማችም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ከላይ ስታየው የሚያብለጨልጭ የተኳኳለና የተዋበ ነገር ነው፣ ይዘቱ ግን ሌላ ነው፡፡ ኢትዮጵያን የሚበታትን ነው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡ በተለይ አንቀጽ 39 በተመለከተ ከኢሕአዴግ መሪዎች ጋር ብዙ እንዳወሩበትና እሳቸው ራሳቸው ይኼ ነገር አይጠቅምም የሚል ምክር መስጠታቸውን ገልጸዋል፡፡

ይህንን ምክር ወደ ጎን በማለት፣ ‹‹ኢትዮጵያን መግዛት የሚቻለው በዚህ መንገድ ብቻ ነው›› በሚል እሳቤ ባለፉት 25 ዓመታት ብዙ በታሪክ የሚመዘገብ ጥፋት በአገሪቱ እንደደረሰ ይናገራሉ፡፡ አቶ ኢሳያስ ይህንን ይበሉ እንጂ፣ ‹‹ለኢትዮጵያ የመቶ ዓመት የቤት ሥራ ሰጥቻለሁ፤›› ሲሉ እንደተናገሩ ከዓመታት በፊት ብዙ የተባለበት እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ይህ የእሳቸው መካሪነት ግን አዲስ ክስተት ሳይሆን አይቀርም፡፡

በመቀጠልም ባለፈው ዓመት ‹‹ፈነዳ›› ያሉት ችግር የዚሁ የተከመረ ችግር ውጤት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ዛሬም ድረስ ‹‹ኤርትራ ገባችበት፣ ግብፅ አለችበት ይላሉ፤›› በማለት የሚናገሩት ፕሬዚዳንቱ፣ ‹‹ፌዴራላዊ›› በመባል የሚታወቀው ሥርዓት ‹‹ውስጣዊ ይዘቱ›› ይኼው ነው ይላሉ፡፡ ውጤቱም በመጨረሻ መበታተን እንደሆነ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡ ‹‹የሚያሳዝነው የዚህ ሥርዓት ቀውስ አደጋ ዋና ሰለባ እየሆነ ያለው ምስኪኑ የትግራይ ሕዝብ ነው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

ጥቂቶች በተቆጣጠሩት ሥልጣንና ኢኮኖሚ፣ የትግራይ ሕዝብ በአገሪቱ በጠላትነት እንዲታይ ምክንያት ሆኗል በማለትም አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ በመንግሥት ተመዝግቧል ተብሎ የሚነገረው የኢኮኖሚ ዕድገትም የውሸት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሥርዓት፣ የለየለት ሙሰኛና የሌብነት እንደሆነም አመልክተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ ለተነሳው ሁከት መፍትሔ ያስገኛል ወይ የሚል ጥያቄም ቀርቦላቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ለተፈጠረው ችግር መፍትሔ እንደማይሆንና የችግሩ ምንጭ ራሱ ሥርዓቱ ባለፉት የሥልጣን ዘመናት የወለደው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በኢትዮጵያ የፌዴራል ሥርዓት አወቃቀር ላይ እንዲህ የከረረ ጥላቻ ሊያሰሙ የመጀመሪያቸው ይመስላል፡፡

ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ሊቢያና ግብፅ በመሳሰሉ አገሮች ስላለው የፖለቲካና የደኅንነት ክፍተቶችም ተናግረዋል፡፡ የመን ውስጥ ስላለው ችግርም አክለዋል፡፡ በአካባቢው የተፈጠረው መተባበርም፣ እያንዳንዱ ለአካባቢው ሰላም አስተዋጽኦ ለማበርከት ያለመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ‹‹በተለይ ሳዑዲ ዓረቢያና ግብፅ በቀጣናው ሊጫወቱት የሚገባ አዎንታዊ ሚና ከፍ ያለ እንዲሆን ያደርጋል፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -