Sunday, March 26, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአራት አግሮ ፕሮሰሲንግ ፓርኮች ግንባታ በ1.5 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ሊጀመር ነው

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

–  የአገር ውስጥ ምግብና መጠጥ አምራቾች ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን እንዲተኩ ጥሪ ቀረበ

በአራት ክልሎች የተቀናጁ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ በ1.5 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ሊጀመር እንደሆነ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ምግብና ምግብ ነክ የሆኑ ምርቶችን የሚያቀነባብሩ ፋብሪካዎች የሚገነቡባቸው ሲሆን፣ ፓርኮቹ የሚገነቡት በአማራ ክልል ቡሬ፣ በምዕራብ ትግራይ ባከር፣ በኦሮሚያ ዝዋይ አካባቢ ቡልቡላ፣ በደቡብ ክልል ይርጋለም ከተማ ነው፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር መብራህቱ መለስ ማክሰኞ ጥር 23 ቀን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ የማስቀመጥ ሥነ ሥርዓት በቅርቡ ተካሂዶ ወደ ግንባታ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እያንዳንዳቸው በ250 ሔክታር ቦታ ላይ በፓይለት ፕሮጀክት ደረጃ ተጀምሮ ወደ 1,000 ሔክታር እንደሚሰፉ ዶ/ር መብራህቱ አስረድተዋል፡፡ ፓርኮቹን በባለቤትነት የሚገነቡት በየክልሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽኖች መቋቋማቸውን ገልጸዋል፡፡ የግንባታ ወጪው በመንግሥት፣ በአገር ውስጥና በውጭ ባንኮች በሚገኝ ብድር እንደሚሸፈን ተገልጿል፡፡

የፌዴራል መንግሥት ለአግሮ ፕሮሰሲንግ ፓርኮች ግንባታ 17 ቀጣናዎች መለየቱን፣ በፓይለት ፕሮጀክት ደረጃ የመጀመሪያዎቹ የአራቱ ፓርኮች ግንባታ በቅርቡ እንደሚጀመር ተገልጿል፡፡ የቀጣናዎቹ መረጣ የተካሄደው በዋናነት የጥሬ ዕቃዎች ምርት መገኛ መሠረት በማድረግ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ለአራቱም ፓይለት ፓርኮች በቅድሚያ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅትና ከዓለም የምግብ ድርጅት ጋር በመተባበር ዝርዝር የአዋጭነት ጥናት አካሂዷል፡፡ በዚህ መሠረት ዝርዝር የምህንድስና ዲዛይን ለማከናወን ከተመረጠው ማህንድራ ከተባለ የህንድ አማካሪ ድርጅት ጋር የተመድ የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ባለፈው ግንቦት ወር ውል ፈርሞ በአሁኑ ወቅት ረቂቅ ዲዛይኑ ተዘጋጅቶ ለምርመራ ቀርቧል፡፡

በፓርኮቹ የሚቋቋሙት መሠረተ ልማቶች የውስጥ ለውስጥ መንገዶች፣ የውኃ፣ የኤሌክትሪክ፣ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ዝርጋታዎች፣ የፈሳሽና የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ መስመሮች፣ ሞዴል የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያና ማምረቻ ሕንፃዎች፣ የማቀነባበሪያና ማምረቻ ድጋፍ ሰጪ መሣሪያዎችና መገልገያዎች መትከያ ሕንፃዎች፣ የጥሬ ዕቃዎችና የምርት መጋዘኖች ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የአንድ መስኮት አገልግሎት መስጫ፣ የአስተዳደር ቢሮ ሕንፃዎች፣ የባንክ፣ ኢንሹራንስ፣ የማሪታይም፣ የትራንዚት አገልግሎት ቢሮዎች፣ የሠራተኞችና የሥራ ኃላፊዎች መኖሪያ ቤቶች ሕንፃዎች፣ የሠራተኞች ማሠልጠኛ ማዕከል፣ የመዋዕለ ሕፃናትና ትምህርት ቤት፣ አረንጓዴ ቦታዎችን እንደሚያጠቃልል ዶ/ር መብራህቱ ገልጸው፣ የሠለጠነ የሰው ኃይል ወደ ክልሎች እንዲሳብ በተቻለ መጠን ሁሉም አገልግሎቶች የተሟሉበት ምቹ የሥራና መኖሪያ ቦታ እንደሚፈጠር ተናግረዋል፡፡ ከገጠር ወደ ከተማ ያለውን ፍልሰት ለመቀልበስ፣ ወደ ውጭ የሚደረገውን ስደት ለማስቀረት መንግሥት ሰፊ ሥራ እየሠራ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በፓርኮቹ እንደየአካባቢያቸው የግብርና ምርቶች ሁኔታ የጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎች፣ የዶሮና የከብት ሥጋ፣ የወተት፣ የማር፣ የአትክልትና ፍራፍሬ፣ የቡና ፋብሪካዎች እንደሚቋቋሙ ገልጸዋል፡፡

ለእያንዳንዱ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ወደ 50 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክና 6,000 ሜትር ኩብ ውኃ እንደሚያስፈልግ ተገምቷል፡፡ የፓርኮቹ ግንባታ ተጠናቆ በሙሉ አቅም ሲሠሩ ከቡሬ ፓርክ በዓመት 558,000 ቶን መጠን ያላቸው የተለያዩ ምርቶች እንደሚመረቱና 14 ቢሊዮን ብር ገቢ እንደሚገኝ፣ ከባከር ፓርክ 700,000 ቶን መጠን ያላቸው የተለያዩ ምርቶች እንደሚመረቱና 18 ቢሊዮን ብር ሽያጭ እንደሚገኝ፣ ከቡልቡላ ፓርክ 591,000 ቶን ምርትና 14 ቢሊዮን ብር ገቢ እንደሚገኝ፣ ከይርጋለም ፓርክ 233,000 ቶን ምርትና ስድስት ቢሊዮን ብር ሽያጭ እንደሚገኝ ተገምቷል፡፡ እያንዳንዱ ፓርክ 419,000 ቀጥተኛ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር፣ በተዘዋዋሪ ደግሞ ለ210,000 ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ታቅዷል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ባለሀብቶች መሬት፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ሌሎች መሠረተ ልማቶችና አገልግሎቶች ለማግኘት የሚያታክታቸውን ውጣ ውረድ በማስቀረት በፍጥነት ወደ ሥራ እንዲገቡና ሥራቸው ላይ ብቻ አተኩረው እንዲሠሩ እንደሚያስችል እንደሆነ የተናገሩት ዶ/ር መብራህቱ፣ ከዚህ በኋላ በተበታተነ ሁኔታ የኢንዱስትሪ ልማት እንደማይካሄድ አስረድተዋል፡፡ ‹‹በተበታተነ ሁኔታ የኢንዱስትሪ ልማት ማካሄድ የአገር ሀብት ማባከን ነው፡፡ መሬት ውድ ነው፡፡ መሠረተ ልማት በተለያዩ ቦታዎች ማሟላት ለመንግሥት አስቸጋሪ ነው፡፡ ባለሀብቱም ሁሉንም አገልግሎቶች በአንድ ቦታ ማግኘት ሲችል በተለያዩ ቦታዎች መንከራተት አላስፈላጊ የሀብትና ጊዜ ብክነት ያስከትላል፡፡ ስለዚህ የምናስተላልፈው መልዕክት ለማልማት ዕቅድ ያለው ወይም መንገድ ላይ ያለ ሁሉም ባለሀብት ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲገባ ነው፤›› ብለዋል፡፡

አክለውም መንግሥት በግብርናና በኢንዱስትሪ ዘርፎች መካከል ጋብቻ ለመፍጠር ጥረት ላይ መሆኑን፣ ሕንፃ ሠርቶ ማከራየት ወይም ሆቴል መገንባት ዘላቂ ልማት እንደማያመጣ፣ በቀጣይ ሀብት ለመፍጠርና ሰፊ የሥራ ዕድል የሚፈጥረው የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በመሆኑ ባለሀብቶች በዚህ ዘርፍ እንዲገቡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለሚገቡ ባለሀብቶች መንግሥት የባንክ አገልግሎትና ሌሎች ድጋፎች እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡

ከየካቲት ወር ጀምሮ ወደ አግሮ ፕሮሰሲንግ ፓርኮች ለሚገቡ ኩባንያዎች የሚያስፈልጉ መሥፈርቶች ተዘርዝረው በሚዲያ እንደሚገለጽ፣ አልሚዎች ከመስከረም 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ፓርኮቹ ይገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገልጿል፡፡

በተያያዘ ዜና ከውጭ የሚገቡ የምግብና የመጠጥ ምርቶችን የአገር ውስጥ አምራቾች በአገር ውስጥ ምርቶች እንዲተኩ ጥሪ ቀርቧል፡፡ የኢትዮጵያ ሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩትና የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመጠጥና የፋርማሲቲካልስ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመተባበር ጥር 23 ቀን 2009 ዓ.ም. በኢሊሊ ሆቴል ባዘጋጁት የምክክር መድረክ ላይ፣ ከውጭ ለሚገቡ ምግብ ነክ ምርቶች አገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እንደምታወጣ ተገልጿል፡፡ በአገር ውስጥ ሊመረቱ የሚችሉ የዶሮና የከብት ሥጋ፣ ወተት፣ ዓሳ፣ ጭማቂዎችን ሆቴሎች፣ ሱፐር ማርኬቶችና የኢትዮጵያ አየር መንገድ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከውጭ እንደሚገዙ ተገልጿል፡፡ ‹‹እንደ ደም ጠብታ የሚያስፈልገንን የውጭ ምንዛሪ ያላግባብ እያባከንን ነው፤›› ያሉት ዶ/ር መብራቱ፣ ‹‹የግብርና ምርት ጠፍቶ ሳይሆን እሴት ጨምሮ ማቀነባበር ስላቃተን ጥሬውን እንልካለን፡፡ አንዳንድ አገሮች የራሳችንን ምርት ጥሬውን ወስደው አቀነባብረው መልሰው ይሸጡልናል፤›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ምግብ ዝግጅት ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ አክሊሉ ሀብቱ፣ አየር መንገዱ በበረራ ወቅት ለሚቀርቡ ምግብና መጠጦች ዝግጅት የሚውሉ ጥሬ ዕቃዎችና ተያያዥ ምርቶች ግዥ በዓመት 100 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚያደርግ፣ ከዚህ ውስጥ 90 በመቶ ከውጭ ተገዝተው እንደሚገቡና የአገር ውስጥ ኩባንያዎች የሚያቀርቡት አሥር በመቶ ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ምግብ ዝግጅት ክፍል 600 ዓይነት ምርቶች ግዥ እንደሚፈጽም፣ ከእነዚህ ውስጥ 120 የሚሆኑት ምርቶች የአገር ውስጥ አምራቾች እንደሚያቀርቡ፣ 55 ያህል የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ከአየር መንገዱ ጋር አብረው እንደሚሠሩ አቶ አክሊሉ ተናግረዋል፡፡

ሐበሻ ቢራ፣ ፋሚሊ ወተት፣ ካስትል ዋይን፣ መቂ ባቱ አትክልትና ፍራፍሬ አምራቾች የኅብረት ሥራ ማኅበርና በሞጆ ከተማ የሚኘው ሉሜ አዳማ የዱቄት ፋብሪካ በአርአያነት ተጠቅሰዋል፡፡

አየር መንገዱ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ማር፣ ወተት፣ የተለያዩ ጭማቂዎች፣ የከብትና የዶሮ ሥጋ፣ ማር ማራታና ሌሎች በርካታ ምርቶች ከአገር ውስጥ አምራቾች መግዛት እንደሚፈልግ ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ተቀራርቦ መሥራት ፍላጎቱ እንደሆነ አቶ አክሊሉ ተናግረዋል፡፡ ‹‹የእኛ ፍላጎት ከምንፈልጋቸው ምርቶች 80 በመቶ ከአገር ውስጥ ኩባንያዎች መግዛት ነው፤›› ያሉት አቶ አክሊሉ፣ የምግብ ማቅረቢያና መመገቢያ ዕቃዎች (ማንኪያ፣ ሹካና ኩባያዎች) የፕላስቲክ ዕቃዎች በዓመት እስከ አንድ ሚሊዮን ዶላር ወጪ እየተደረገ ከውጭ እንደሚያስገባ፣ ነገር ግን እነዚህ ምርቶች በአገር ውስጥ ፕላስቲክ አምራቾች ሊመረቱ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹እኛ የምንፈልገው ጥራት፣ ብዛትና ቀጣይነት ያለው አቅርቦት ነው፡፡ ዛሬ አቅርቦ በሚቀጥለው ሳምንት አልችልም ማለት እኛ ዘንድ አይሠራም፡፡ በዋጋም ተወዳዳሪ መሆን ይኖርባችኋል፡፡ አስፈላጊውን ዝርዝር መረጃ በስልክም በአካልም መጥታችሁ ማግኘት ትችላላችሁ፤›› ብለዋል፡፡ የተለያዩ የምግብና የመጠጥ አምራቾች ከአየር መንገዱ ጋር አብሮ ለመሥራት ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸው አየር መንገዱ የሚፈልጋቸውን የምርት ዓይነቶች ዝርዝር፣ የጥራት ደረጃ መሥፈርቶች፣ የምርት ምርጫ መመዘኛዎቹን እንዲያሳውቃቸው ወይም መረጃዎቹን የሚያገኙበትን ሁኔታ እንዲያመቻችላቸው ጠይቀዋል፡፡

አምራቾቹ የመሬት፣ የፋይናንስና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግሮች እንዳሉባቸው ተናግረዋል፡፡ በጉምሩክ፣ በታክስ አሠራር፣ በጥራት ቁጥጥር ላቦራቶሪ አገልግሎቶች ላይ ችግር የገጠማቸውም ኩባንያዎች አቤቱታቸውን አቅርበዋል፡፡ የምርት ማሸጊያ ዕቃዎች እጥረትም እንዳለ ተገልጿል፡፡ የተዘረዘሩትን ችግሮች መንግሥት እንደሚመለከታቸውና መፍትሔ ለመስጠት እንደሚሞክር፣ የምክክር መድረኩ በቀጣይነትም እንደሚዘጋጅ ከመድረክ መሪዎቹ ተገልጿል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች