Saturday, May 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየተመድ ዋና ጸሐፊ ዓለም ኢትዮጵያን ከድርቅ አደጋ እንዲታደግ ጥሪ አቀረቡ

የተመድ ዋና ጸሐፊ ዓለም ኢትዮጵያን ከድርቅ አደጋ እንዲታደግ ጥሪ አቀረቡ

ቀን:

‹‹የምናባክነው ጊዜ ሊኖር አይገባም›› የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች አስተባባሪ

አዲሱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ኢትዮጵያ የተጋረጠባትን ድርቅ እንድትቋቋም በጋራ እንዲቆም ጥሪ አቀረቡ፡፡ ለአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ አዲስ አበባ የመጡት ጉተሬዝ ከተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ስቴፈን ኦሪን ጋር በሰጡት መግለጫ፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለኢትዮጵያ አጋር መሆኑን የሚያሳይበት ወሳኝ ጊዜ ነው ብለዋል፡፡

‹‹ይኼ ወቅት ዓለም ለኢትዮጵያ አንድነቱን የሚያሳይበት ነው፡፡ እዚህ ላይ ግልጽ መሆን ያለበት ለኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት አጋርነትን ማሳየት የለጋሽነት ጉዳይ አይደለም፡፡ ይልቁንም ፍትሐዊነትና የራስ ፍላጎትን ማሳያ ሊሆን ይገባዋል፤›› ያሉት ዋና ጸሐፊው፣ በኢትዮጵያ አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው 5.6 ሚሊዮን ዜጎች በፍጥነት ሊደረስላቸው ይገባል ብለዋል፡፡

- Advertisement -

የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ድንበራቸውን ክፍት አድርገው በአፍሪካ አንደኛ ስደተኞችን አስተናጋጅ መሆናቸው የለጋስነታቸውን መጠን ያሳያል ያሉት ጉተሬዝ፣ ለአሥር ዓመታት የተመድ የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽነር ሆነው መሥራታቸው ይህንን ከፍተኛ የሆነ ለጋስነት እንዳሳያቸው ተናግረዋል፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው ከፍተኛ የሆነ የፀጥታ ችግር ባለበት ሁኔታ ውስጥ ነው ብለው፣ ዓለም ለስደተኞች ድንበሩን በዘጋበት ጊዜ መሆኑ ደግሞ ሊታወስ ይገባል ሲሉ አስረድተዋል፡፡ የአሁኑ አዲሱ ድርቅ ከአየር ንብረት መለዋወጥ ጋር የተያያዘና ተከታታይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአካባቢው ‹‹የመረጋጋት ምሰሶ›› ናት ያሉት ዋና ጸሐፊው፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድርቁ ለተጨማሪ አለመረጋጋት፣ ማኅበራዊ ሁከት ወይም ለግጭት ማባባሻ እንዲሆን መፍቀድ የለበትም ብለዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስደተኞችን ለመቀበል ፍላጎት በሌለበት በዚህ ጊዜ በድርቁ ምክንያት የዜጎች መፈናቀል እንዳይፈጠር ፈጣን ምላሽ መገኘት አለበት ሲሉ አክለዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሽብር ሥጋት መንሠራፋቱ ብዙ አገሮችን እያስፈራ ስለሆነ፣ የኢትዮጵያ መንግሥትን በማገዝ የድርቁ ተፅዕኖ መቀነስ አለበት ብለዋል፡፡ ምክንያቱን ሲያስረዱ ዜጎች በድርቁ ጉዳት ሳቢያ ለስደት እንዳይዳረጉ መደረግ አለበት ብለዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ጋር በሚፈጠር የትግል አንድነት አብሮ መሥራት የሚያስፈልገው አሁን ያለውን የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎት ከማሟላት ብቻ ሳይሆን፣ በልማት መስክ የሚታየውን ከፍተኛ ተግዳሮት ለመቀልበስ በሚደረገው ጥረት ለመተባበርና ዘላቂ ልማትን በማረጋገጥ ዓለም እየተጋፈጠ ያለውን ሰላምና ፀጥታ አስተማማኝ ከማድረግ አንፃር ነው በማለት ጉተሬዝ አስረድተዋል፡፡

የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ስቴፈን ኦሪን በበኩላቸው፣ ለሦስት ቀናት በደቡባዊ ምሥራቅ የአገሪቱ ክልሎች ባደረጉት ጉብኝት የአሁኑ ድርቅ በሰዎች ሕይወት ላይ የደቀነውን አደጋ ተናግረዋል፡፡ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በዋርዴር ዞን ድርቁ ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጥሯል ያሉት ኦሪን፣ ከመዘግየት በፊት በፍጥነት ዕርምጃ መወሰድ አለበት ብለዋል፡፡ እ.ኤ.አ. ለ2017 በወጣው የሰብዓዊ ዕርዳታ ሰነድ መሠረት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ 5.6 ሚሊዮን የድርቅ ተጎጂ ወገኖችን ለመታደግ 948 ሚሊዮን ዶላር ዕርዳታ ማድረግ እንዳለበት አስረድተዋል፡፡

‹‹የምናባክነው ጊዜ ሊኖር አይገባም፡፡ እንስሳት እየሞቱ ነው፡፡ አርብቶ አደሮችና አርሶ አደሮች ከእንስሳት ውኃና ግጦሽ ፍለጋ ከቀዬአቸው ርቀው እየሄዱ ነው፡፡ ሕፃናት በተለይም ሴቶች ከትምህርት ቤት እየቀሩ ወላጆቻቸውን በሥራ እያገዙ ነው፡፡ ዕርዳታ በጊዜው ካልደረሰ ረሃብና የተመጣጠነ ምግብ ዕጦት በቅርቡ እየጨመሩ ይሄዳሉ፡፡ በዚህም ሴቶች ከጤና ጋር በተያያዘ ችግር ሊገጥማቸው ይችላል፤›› በማለት ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

የተመድ ዋና ጸሐፊ ጉተሬዝ፣ ‹‹የአሁኑ የድርቅ ቀውስ የገጠመው የኢትዮጵያ መንግሥት ስላልተዘጋጀበት ሳይሆን፣ የድርቁ ስፋት ከአገሪቱ አቅም በላይ በመሆኑ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በቋሚነት ድርቅን የሚቋቋም ፖሊሲ ሥራ ላይ በማዋል ተፅዕኖዎችን መቋቋም የቻለች አገር ናት፡፡ አሁን ግን ያጋጠመው የአየር ንብረት ለውጥ የፈጠረውና በአካባቢው በተደጋጋሚ ጊዜ በመከሰቱ ነው፤›› በማለት፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለዚህች አገር አጋርነት በአንድነት ሊቆም ይገባዋል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡  

በሌላ በኩል መንግሥት በአገሪቱ የተወሰኑ አካባቢዎች የተከሰተው ድርቅ በሰው ሕይወትና በእንስሳት ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ርብርብ እያደረግኩ ነው ብሏል፡፡ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ለ5.6 ሚሊዮን ዜጎች አስቸኳይ ዕርዳታ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፣ መንግሥት ችግሩን ለመቅረፍ የአንድ ቢሊዮን ብር በጀት ማፅደቁን አስታውቀዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...