የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለልማት ሲባል በተነሱ ነገር ግን ለችግር የተዳረጉ አርሶ አደሮችን በድጋሚ ለማቋቋም በመሠረተው አዲስ ፕሮጀክት ጉዳይ ላይ፣ ከአርሶ አደሮች ጋር የመጀመሪያ ዙር ውይይት አካሄደ፡፡
ማክሰኞ ጥር 23 ቀን 2009 ዓ.ም. በአምስት ቦታዎች ላይ 2,000 ከሚጠጉ ተነሺ አርሶ አደሮች ጋር ውይይት በማድረግ 35 አባላት ያሉት ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ‹‹የተነሺ አርሶ አደሮች መልሶ ማቋቋሚያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት›› በሚባል ስያሜ አዲሱን ፕሮጀክት ካቋቋመ በኋላ በተከናወኑ ጉዳዮች ላይ ለአርሶ አደሮቹ ገለጻ ተደርጓል፡፡
ተነሺ አርሶ አደሮቹ በወቅቱ እንደገለጹት፣ በቂ ካሳና ምትክ ቦታ ሳይሰጣቸው ሲወርድ ሲዋረድ ከኖሩበትና ብቸኛ ሙያቸው ከሆነው ግብርና ሥራ እንዲራራቁ መደረጉ ለከፋ ችግር ዳርጓቸዋል፡፡
ተነሺ አርሶ አደሮቹ መንግሥት ዘግይቶም ቢሆን መልሶ ለማቋቋም ማቀዱ መልካም መሆኑን ገልጸው፣ ነገር ግን የተጀመረው ሥራ መና እንዳይቀር አሳስበዋል፡፡
አወያዮቹ መንግሥት በችግር ውስጥ ያሉትን ተነሺ አርሶ አደሮች በድጋሚ ለማቋቋም ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸውላቸዋል፡፡
በውይይቱ ወቅት ተነሺ አርሶ አደሮቹ ኮሚቴ እንዲመርጡ የተደረገ ሲሆን፣ ተነሺ አርሶ አደር ያሉባቸው አምስት ክፍላተ ከተሞች ሰባት፣ ሰባት ሰዎችን የኮሚቴ አባል አድርገው መርጠዋል፡፡
የተነሺ አርሶ አደሮች መልሶ ማቋቋሚያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አቡዱራዛቅ ያሲን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከአምስቱም ክፍላተ ከተሞች የተመረጡት 35 ሰዎች የራሳቸውን ስብሰባ አድርገው አምስት ሰዎችን ለቦርድ አባልነት ያቀርባሉ፡፡
እነዚህ በልማት ምክንያት ከቦታቸው የተነሱ አርሶ አደር የኮሚቴ አባላት፣ መቋቋም ያለባቸውን አርሶ አደሮች በመለየት ሒደት ትልቅ ሚና እንደሚኖራቸው አቶ አብዱራዛቅ ገልጸዋል፡፡
‹‹በአምስት ደረጃዎች ተከፍሎ አርሶ አደሮችን የማቋቋም ሥራ ይሠራል፡፡ ለአብነት ያህል በመጀመሪያ ምንም ገቢ የሌለው አነስተኛ ገቢ ያለውን በመለየት በአፋጣኝ ማቋቋም ያስፈልጋል፡፡ የተሻለ ገቢ ያለው ከሆነ ወደ ኢንቨስተር ደረጃ የማሳደግ ሥራ ይሠራል፤›› ሲሉ አቶ አብዱራዛቅ አስረድተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ የግንባታ ሥራ ከተጀመረበት ከ1990 ዓ.ም. ወዲህ ባሉ ዓመታት፣ በከተማው ዳርቻ አካባቢዎች የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮች ከኖሩበት ቀዬ ለልማት ተነስተዋል፡፡
አርሶ አደሮቹ በቂ ካሳና በቂ ምትክ ቦታ ካለማግኘታቸው በተጨማሪ፣ በመልካም አስተዳደር ችግሮች ደንብና መመርያ የሚፈቅዷቸውን አገልግሎት ማግኘት እንዳልቻሉ በተደጋጋሚ ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ከ18 ዓመት በላይ ለሆኑ ልጆች የመኖሪያ ቤት መገንቢያ ቦታ የሚፈቀድ ቢሆንም፣ በርካታ ወጣቶች ይህን አገልግሎት ማግኘት አለመቻላቸውን ይናገራሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ለችግር የተዳረጉ አርሶ አደሮችን በድጋሚ ለማቋቋም ዕቅድ አውጥቷል፡፡ ክፍላተ ከተሞቹ ቦሌ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ አቃቂ ቃሊቲ የካና ኮልፌ ቀራኒዮ ናቸው፡፡
አቶ አብዱራዛቅ እንዳሉት 2009 ዓ.ም. የዝግጅት ጊዜ ነው፡፡ ነገር ግን በተቻለ መጠን 20 ሺሕ አርሶ አደሮችን በድጋሚ ለማቋቋም የተለያዩ ሥራዎችን በመሥራት ላይ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡