Saturday, April 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለውጭ ገበያ ይቀርባል የተባለውን ያህል ቡና አልቀረበም

ተዛማጅ ፅሁፎች

– አንዱ ምክንያት በላኪዎች ላይ የተወሰደው ዕርምጃ ነው ተብሏል

ከቡና፣ ቅመማ ቅመምና ከሻይ ቅጠል ምርቶች በግማሽ በጀት ዓመት ይገኛል ተብሎ የታቀደውን ያህል አለመቅረቡ ታወቀ፡፡ ለዚህም በቅርቡ በቡና ላኪዎች ላይ የተወሰደው ዕርምጃ ዋናውን ድርሻ እንደሚይዝ ተጠቁሟል፡፡ ከቡናና ሻይ ባለሥልጣን የተገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው፣ በ2009 በጀት ዓመት የመጀመርያዎቹ ስድስት ወራት 107,271 ቶን ቡና፣ ቅመማ ቅመምና የሻይ ቅጠል ምርቶችን ለውጭ ገበያ አቅርቦ 401.1 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ የተገኘው ግን 321.2 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡

ከሦስቱም ምርቶች ከታቀደው ውስጥ መላክ የተቻለው 89,574 ቶን በመሆኑ፣ በዕቅዱና በክንውኑ መካከል ከ27 ሺሕ ቶን በላይ ልዩነት ታይቷል፡፡

በተለይ በግማሽ በጀት ዓመቱ ለውጭ ገበያ የቀረበው የቡና መጠን ካለፈው ዓመት በተመሳሳይ ወቅት ከተላከው ያነሰ ሲሆን፣ በምርት ዘመኑ ግን የአገሪቱ የቡና ምርት በ26 በመቶ ጨምሯል፡፡

እንደ ባለሥልጣኑ መረጃ በግማሽ በጀት ዓመቱ 98,561 ቶን ቡና ለውጭ ገበያ ይቀርባል ተብሎ ማቅረብ የተቻለው 85,425 ቶን ነው፡፡ ከገቢ አንፃርም ቡና ያስገኛል ተብሎ ታሳቢ የተደረገው 385 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን፣ የተገኘው 315.7 ሚሊዮን ዶላር በመሆኑ ገቢው ከዕቅዱ ወደ 19 በመቶ ሊያንስ ችሏል፡፡

በ2008 ግማሽ የበጀት ዓመት ግን ለውጭ ገበያ የቀረበው ቡና 87,785 ቶን ሲሆን፣ ይኼም በ2009 በጀት ዓመት ግማሽ በጀት ዓመት ከተላከው ጋር ሲነፃፀር በ2,332 ቶን ወይም የ2.7 በመቶ የቀነሰ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሆኖም ከገቢ አንፃር የተገኘው የውጭ ምንዛሪ የዘንድሮው ግማሽ ዓመት በ2.8 በመቶ ብልጫ አሳይቷል፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ ባለፉት ጥቂት ወራት የዓለም አቀፍ የቡና ዋጋ በመሻሻሉ ነው፡፡

ቡና የዕቅዱን ያህል ለውጭ ገበያ ላለመቅረቡ የተለያዩ ምክንያቶች መኖራቸውን ባለሥልጣኑ ገልጿል፡፡ ባለፉት ዓመታት በሕገወጥ መንገድ የኤክስፖርት ቡና ምርት ከገበያ ገዝተው መላክ ባልቻሉ ላኪዎች ላይ ሕጋዊ ዕርምጃ ከመወሰዱ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የባለሥልጣኑ የስድስት ወራት ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ በምርት ገበያው ያላቸውን ወንበር በመጠቀም ምርት የገዙላቸው አንዳንድ የምርት ገበያው አገናኝ አባላት በሆኑ ላኪዎች ላይ የተወሰደው የዕግድ ዕርምጃ የራሱን አሉታዊ ተፅዕኖ ፈጥሯል፡፡

የዓለም የቡና ገበያ ዋጋ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው የተሻለ እንደሆነ የሚጠቁመው የባለሥልጣኑ ሪፖርት፣ ቡና ላኪዎች በበጀት ዓመቱ ሦስት ወራት  (ከሐምሌ እስከ መስከረም) ቀደም ብሎ የዓለም ቡና ዋጋ ዝቅተኛ በነበረበት ወቅት ላይ ኮንትራት በመፈጸማቸው ከአገር ውስጥ ዋጋ ጋር መናበብና በግዥ መሟላት አለመቻሉ ለአፈጻጸሙ መቀነስ ምክንያት ሆኖ ቀርቧል፡፡

ባለፈው ዓመት በተከሰተው የኤልኒኖ የአየር ጠባይ ምክንያት በአንዳንድ አካባቢዎች በጥራት ላይ አሉታዊ የሆነ ተፅዕኖ በማሳደሩ፣ የተወሰኑ ላኪዎች የገቡትን ኮንትራት ለማሟላት በቂ ጥረት ያለማድረግ፣ የውጭ ቡና ገዥ ኩባንያዎች አዲሱን ምርት የመጠበቅ አዝማሚያ ማሳየታቸውም ተጨማሪ ምክንያት ሆኖ ቀርቧል፡፡

በተለይ የሻይ ቅጠልና የቅምማ ቅመም ምርቶች አቅርቦት ከተጠበቀው ውጤት በታች ተመዝግቦበታል፡፡

በሪፖርቱ እንደተገለጸው፣ በመጀመሪያው ግማሽ ዓመት ለውጭ ገበያ ይቀርባል ተብሎ የታቀደው 7,192 ቶን ቅመማ ቅመም ምርት ቢሆንም፣ የተላከው 3,200 ቶን ብቻ ነው፡፡ ይኽም የዕቅዱን 44 በመቶ ብቻ ማሳካት የተቻለ መሆኑን  ያሳያል፡፡ በገቢም ረገድ ከቅመማ ቅመም ምርቶች የወጪ ንግድ ይገኛል የተባለው ገቢ ከግማሽ በላይ እንዲቀንስ አድርጎታል፡፡ የታቀደውን ያህል ቅመማ ቅመም ቢላክ ኖሮ 13.5 ሚሊዮን ዶላር የሚገኝ ቢሆንም፣ በስድስት ወራት መገኘት የቻለው ግን 5.7 ሚሊዮን ዶላር ወይም የዕቅዱ 42.5 በመቶው ብቻ ነው፡፡

በተመሳሳይ የሻይ ቅጠል ምርት የወጪ ንግድም በዕቅዱና በክንውኑ መካከል ልዩነት ታይቶበታል፡፡ በባለሥልጣኑ መረጃ መሠረት በመጀመሪያው ግማሽ በጀት ዓመት  1,517 ቶን ሻይ ቅጠል ለውጭ ገበያ አቅርቦ 2.7 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ቢታቀድም፣ ለውጭ ገበያ ማቅረብ የተቻለው 948 ቶን ብቻ ነው፡፡ የተገኘው ገቢም 1.7 ሚሊዮን ብር ብቻ በመሆኑ የገቢ አፈጻጸሙ 64 በመቶ ሊሆን ችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች