ዛጐል ደረቅ፣ ጠንካራ የባሕር ተሳቦ ልብስ ትልቅና ትንሽ፤ ሕብሩ ነጭና አርንጓዴ የሆነ ይለዋል፤ አምስት አሠርታት ያስቆጠረው የአለቃ ደስታ ተክለወልድ አዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት፡፡ ዛጐል ለልዩ ልዩ ተግባራት አገልግሎት የሚሰጠው ለሰው ልጅ ብቻ አይደለም፡፡ የባሕር ፍጥረታትም ተጠቃሚም ናቸው፡፡ እንደ ጄደብሊው ድረ ገጽ አገላለጽ፣ ሞለስክ በመባል ከሚታወቁት የባሕር ፍጥረታት አብዛኞቹ ሰውነታቸውን የሚሸፍኑበት ዛጐል አላቸው፤ ይህ ዛጐል በባሕሩ ወለል አካባቢ ያለውን ከፍተኛ ጫና ተቋቁመው እንዲኖሩ ያስችላቸዋል። መሐንዲሶች፣ ዛጐሎች እነዚህን ፍጥረታት ምን ያህል ከአደጋ እንደሚከላከሉላቸው ሲመለከቱ፣ ተሳፋሪዎችን ወይም ነዋሪዎችን ከማንኛውም አደጋ ሊጋርዱ የሚችሉ ተሽከርካሪዎችንና ሕንፃዎችን ለመሥራት በማሰብ የዛጐሎችን ቅርፅ እና አሠራር ማጥናት ጀምረዋል። የድረ ገጹ ንቁ መጽሔት እንዳብራራው፣ መሐንዲሶች ባይቫልቭ (ለሁለት የሚከፈሉ) እና ስፓይራል (ጥምዝምዝ ቅርጽ ያላቸው) በሚባሉት ሁለት የዛጐል ዓይነቶች ላይ ጥናት አካሂደዋል።
ባይቫልቭ የሚባሉት የዛጐል ዓይነቶች በውጭ በኩል ሸንተረሮች አሏቸው፤ እነዚህ ሸንተረሮች በዛጐል ላይ የሚያርፈው ጫና ወደ መገጣጠሚያውና ወደ ጠርዙ እንዲሄድ ያደርጋሉ። ስፓይራል የሚባሉት የዛጐል ዓይነቶች ደግሞ ጎበጥ ያለ ቅርፅ አላቸው፤ ይህም በዛጐሉ ላይ የሚያርፈው ጫና፣ ወደ ዛጎሉ ጫፍና ጫፍ እንዲሄድ ያደርጋል። ሁለቱም የዛጐል ዓይነቶች ያላቸው ቅርፅ፣ የሚደርስባቸው ጫና ጠንካራ ወደሆነው ክፍል እንዲሄድ ለማድረግ የሚያስችል ነው፤ ይህም አደጋ በሚመጣበት ጊዜ በዛጐሉ ውስጥ ባለው ፍጥረት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት በጣም ይቀንሰዋል።